Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ሊቋቋም ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ብድርና ሌሎች ተዛማጅ የባንክ አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ባንክ ሊቋቋም ነው፡፡

ከአገር ውስጥና ከውጭ የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባንክ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ ለመመሥረት የበቃው ባንክ ‹‹ፕሮግረስ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ታውቋል፡፡

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለዓላማቸው መሳካት ገቢ ለማግኘት፣ በማንኛውም ሕጋዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ አግባብነት ባላቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ሕጎች መሠረት የመሳተፍ መብት አላቸው የሚለው ድንጋጌ ባንኩን ለመመሥረት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ አባል አቶ መስፍን ነመራ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ በዝቷል›› ቢባልም እውነታው እንደዚያ እንዳልሆነ፣ ኬንያ ለ50 ሚሊዮን ሕዝብ 49 ያህል ባንኮች እንዳላት አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ወስጥ የሚገኙ ባንኮች አካሄዳቸው ተመሳሳይ ነው፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ ይህም ከደሃው ኅብረተሰብ የቁጠባ ገንዘብ በመስብሰብ ለሀብታም የማበደር አካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኘው ባንክ እንደ ማንኛውም ባንክ ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉ የሚጠበቅና በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚደረግበት ቢሆንም፣ ትርፍን መሰብሰብ ዋነኛው ዓላማው እንዳልሆነ፣ በተቻለ መጠን ገንዘቡ ለተሰበሰበበት አካባቢ ተመልሶ በብድር  ተሰጥቶ የሚሠራበት መሆኑን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ፕሮግረስ ባንክ የልማት ባንክ ዓይነት ሚና የሚጫወት እንደሆነ ያስረዱት አቶ መስፍን፣ እንደ መደበኛ ባንኮች ወለድን መሠረት በማድረግ የሚቀርብ አሠራርን የሚከተል ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ለማኅበረሰቡ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ የማኅበረሰብ ክፍሎችንና ማኅበራትንም ለመደገፍ የሚውል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ባንኩ ስለሚሰጣቸው አገልግሎት ለሚዲያ አካላት ማክሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በዘሃብ ሆቴል መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ በዕለቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ተገኝተዋል፡፡

‹‹መንግሥት የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፤›› በማለት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከመንግሥት ጎን ለጎን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም አካታችና ተራማጅ በሆነው የኢኮኖሚ ሪፎርም የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚጠበቅ አስታውቀው፣ የፕሮግረስ ባንክ ምሥረታም ትብብር ካለ መሳካት የማይቻል ነገር እንደማይኖር ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡

አቶ ጂማ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ማነቆ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አለማደግና አለመስፋፋት አንዱ ነው፡፡ የተቋቋሙት ባንኮችና ሌሎች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ትልቁ ችግራቸው የፋይናንስ አቅማቸው አነስተኛ መሆኑና በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተጠቁ መሆናቸውን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ችግር በመቅረፍ ሒደት ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚደግፍ በዓይነቱ የተለየ ባንክ ለማቋቋም የተደረገውን እንቅስቃሴ ትልቅ ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዋና ዳይሬክተሩ እንደተመላከተው፣ ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 አሳሪ ካስባሉት ጉዳዮች ውስጥ አገር በቀል ድርጅቶች ከውጭ ምንጭ ገንዘብ በማምጣት እንዳይሠሩ ገደብ መጣሉ፣ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ሀብት እንዳይሰባሰብም በርካታ ማነቆዎችን አኑሮ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ድርጅቶች እንዲፈርሱና በዚህ ወቅት የሚገኙትም የፋይናንስ አቅማቸው እንዲዳከም አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር ብለዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መሠረት ያደረገ ባንክ መቋቋሙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይበልጥ እንዲነቃቁና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ጂማ፣ ከውጭ ዕርዳታ በተወሰነ ደረጃ እንዲላቀቁና የራሳቸውን ሐሳብ መፈጸም እንዲችሉ የሚያግዛቸው እንደሚሆን ይታመናል ብለዋል፡፡

በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ከመሳተፍ አንስቶ፣ የንግድ ኩባንያና እንዲያቋቁሙና ሕዝባዊ መዋጮዎችን በመሰብሰብ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ በግልጽ መፈቀዱ ተነግሯል፡፡

የፕሮግረስ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከበደ ቀጄላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመደበኛነት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ባንኮች ጠቀሙ የሚባለው ጥቂት ግለሰቦችን ነው፡፡ ፕሮግረስ ባንክ ግለሰብን ሳይሆን አደረጃጀትን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ የሚከተል እንደሆነ ተገልጾ ለአብነትም ዕድሮችን፣ ዕቁቦችን፣ የመምህራን፣ የሴት፣ የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች ከባንኩ አክሲዮን ገዝተው የሚገኘውን ብድርና ሌሎች ጥቅሞች ለራሳቸው ተግባራት ማዋልን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አቶ ቀጄላ አስታውቀዋል፡፡ በአጭሩ ባንኩ አደረጃጀትን የሚከተል ነው ሲባል ተበዳሪዎች ተደራጅተው ባገኙት ገንዘብ ሀብት እንዲያመነጩ፣ ያንንም መልሰው ኢንቨስትመንት ላይ እንዲውሉ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኩ የሚያበድረው ብድር ለቡድን ለተደራጁ ማኅበራት የሚደርስ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር በኅብረተሰቡ የማኅበራዊ አኗኗር ውስጥ ጉልህ ድርሻ ካላቸው የዕድር አደረጃጀቶች ጋር ቅርበት በመፍጠር ይሠራል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማሳደጉ ይታወሳል፡፡ ይህም አዲስ የሚመሠረቱ ባንኮችን ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይ የቆዩትን ባንኮች ተፈላጊውን ካፒታል እንዲያሟሉ ሲባል ውህደት ውስጥ የሚከታቸው እንደሆነ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ፕሮግረስ የሚፈለገውን ካፒታል ያሟላል ወይ? የሚለውን ለመመለስ በምሥረታ ላይ የሚገኘው ባንክ አደራጆች መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መሆናቸውን  የአደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች