Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

አራተኛ ቀኑን የያዘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ

ትኩስ ፅሁፎች

አንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ በሐዋሳ እየተከናወነ ይገኛል። አራተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ኦሊምፒክ ጨዋታ አትሌቲክስና እግር ኳስን ጨምሮ የኦሊምፒክና ከኦሊምፒክ ውጪ የሆኑ ስፖርቶች በተለያዩ በከተማዋ ቦታዎች እየተከናወነ ይገኛል። ከትግራይ ክልል በስተቀር አዲሱን የደቡብ ምዕራብ ክልል ጨምሮ፣ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተለያዩ ስፖርቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከሦስት ዓመት በፊት ቢሾፍቱ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ እንዲጀመር በጠቅላላ ጉባኤ ያፀደቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ሳያከናውን ቆይቷል። ዘንድሮ በግብፅ አስተናጋጅነት የሚሰናዳውን የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ግቡ ያደረገው የመጀመሪያው ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ሐዋሳ ላይ ከትሟል። ላይ ተሳታፊ ለመሆን፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሻምፒዮኖችን እንዲሁም የትምህርት ቤት ውድድሮች አሰናድተው የነበረ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ ከተካፈሉ ታዳጊዎች መርጠው በኦሊምፒክ ጨዋታው ማሳተፍ ችለዋል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሀሚድ አሺም እንዲሁም የኬንያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፖል ቴርጋት በተገኙበት ግንቦት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የኦሊምፒክ ችቦ በመለኮስ በይፋ ጀምሯል።

የአማራ ክልል በአትሌቲክስ ካለማሳተፉ በስተቀር፣ ክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮች ከሁለት የስፖርት ዓይነቶች በላይ በመያዝ በጨዋታው ላይ እየተካፈሉ ይገኛሉ። የኦሊምፒክ ጨዋታው ለማሰናዳት ለሚመለከታቸው ፌዴሬሽኖች ማሳወቁን የገለጸው ኮሚቴው፣ ለዚህ ይረዳው ዘንድ ኮሚቴ አዋቅሮ አውራ ደንብ አውጥቶ ዝግጅት ሲያደርግ መሰንበቱን አቶ ዳዊት አስፋው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ለሪፖርተር አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት በተቀመጠው አውራ ደንብ የክልል ባለሙያዎች ተጋብዘው በዝግጅቱ ዙሪያ ለቀናት ተመካክረውና ተወያይተው ዕቅዱን ለክልል አመራሮች ስለማቅረባቸው አቶ ዳዊት ያስረዳሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ጨዋታው ከመከናወኑ አስቀድሞ የሁሉም ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጎ፣ ሐሳብ ከተሰጠበት በኋላ ጨዋታው መጀመሩን ተገልጿል። በዚህም ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞችን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ የነበረ ሲሆን፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በበኩሉ፣ በክልል የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ዳኞችን ሌሎች ኮሚቴዎችን አካተው ውድድሮችን መምራት እንደሚችሉ አስቀምጠዋል።

የኦሊምፒክ ጨዋታውን መሰናዳት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ ጨዋታው ከፌዴሬሽኑ ዕውቅና ውጪ መከናወኑ የገለጸ ሲሆን፣ የአትሌቲክስ ውድድሩን እንደማይመራ አስታውቋል። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሌላኛው የኦሊምፒክ ጨዋታውን እግር ኳስ ጨዋታ ለመምራት ያልተገኘ ፌዴሬሽን ነው።

እንደ ዋና ጸሐፊው አስተያየት ከሆነ፣ ለሁሉም ፌዴሬሽኖች ስለ ጨዋታው ቀድሞ ማሳወቁን አስታውሶ፣ ከሁለቱ የፌዴሬሽኖች በስተቀር ከሌሎቹ ጋር በመሆን ጨዋታውን ከትብብር እያሰናዳ መሆኑ እየታወቀ ሁለቱ መሳተፍ አለመፈለጋቸው ግልጽ አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

ምንም እንኳ በደንቡ ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው ከአንድ ክልል በላይ ወይም ከተማ አስተዳደር በላይ የሚሳተፉበት ስፖርታዊ ውድድር በሚዘጋጅበት ጊዜ ኃላፊነት የሚወስዱት ፌዴሬሽኖች ናቸው የሚል መከራከሪያ ቢቀርብም፣ በውይይት የሚፈቱ ነገሮችን መፍታት ሲቻል ለጨዋታው ሲዘጋጁ የነበሩ ታዳጊዎችን ከውድድር ማስቀረት ተገቢ እንዳልሆነ የሚከራከሩ አሉ።

በኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት በዝግጅት ላይ ያለ የውድድር መንፈስን ማወክ ተገቢ እንዳልሆነ ያመለከቱት ዋና ጸሐፊው፣ ከፍተኛ ውጪ ወጥቶባቸው ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉትን ተወዳዳሪዎች ድካም መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።

‹‹በኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካካል ስለ ነበረ ቁርሾ አሁን እያነሳን የምንወቃቀስበት ምክንያት የለም። ይኼ በውድድሩ ለመሳተፍ ጉጉት አድሮባቸው ለመጡ ታዳጊዎች አይበጅም። ይልቅ ከሁሉም ጋር በጋራ ሆነን መሥራት ነው የምንፈልገው፤›› በማለት አቶ ዳዊት ለሪፖርተር አስረድተዋል።

አንደኛው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጨዋታ በግብፅ ከሚሰናዳው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ባሻገር፣ በቀጣይ ለሴኔጋል ዳካሩ የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክና የአፍሪካ ጨዋታ እንዲሁም በዞናል ሻምፒዮናዎች ላይ ተካፋይ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ከወዲሁ ለመምረጥ ዕድል እንዳለው ተገልጿል።

ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታን በየሁለት ዓመት ለማድረግ መወሰኑንም አስታውቋል።

በመጀመርያው ኢትዮጵያ ወጣቶች የኦሊምፒክ ጨዋታ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 6,000 ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚከናወነው ጨዋታው፣ የኦሊምፒክ ስፖርት በሆኑና ባልሆኑ ስፖርቶች እየተካሄደ ሲሆን፣ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተሸፍኗል። ለዚህም ኦሊምፒክ ኮሚቴው 134 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡ ታውቋል፡፡

በጨዋታው ላይ ለሚካፈሉት ተወዳዳሪዎች ብሔራዊ ፀረ- አበረታች ቅመሞች
ጽሕፈት ቤት ምርመራ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ የዕድሜ ማጭበርበር እንዳይኖር የሚከታተል የሕክምና ግብረ ኃይልም ተሰማርቷል።

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች