Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየዜጎች የጋራ የልብ ትርታ የሆነው አገራዊ ፕሮጀክት!

የዜጎች የጋራ የልብ ትርታ የሆነው አገራዊ ፕሮጀክት!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ኢትዮጵያ በየትውልዱ ካከናወነቻቸው ድንቅ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ አሁን ላለው ትውልድም ይነስም ይብዛም በልበ ሙሉነት ኮርቶ ከሚነገርላቸው የዜግነት አሻራዎች በቀዳሚነቱ ይጠቀሳል፡፡ በእዚህ ሁሉ ልዩነት፣ ንትርክና ትርምስ ውስጥም ቢሆን ሁሉም ዜጋ ዓይኑን የማይነቅልበት ፕሮጀክት መሆኑ ጥርጥር የለውም፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን ዓለምም እንደሚያውቀው ይህ በቀጣናው ብቻ ሳይሆን በአኅጉራችንም ተጠቃሽ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ፣ በአገራችን ሉዓላዊ ግዛት ምዕራባዊ ጫፍ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ መገንባት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በመሪ ደረጃም ቢሆን ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሥራውን መርተውታል፡፡ ያም ሆኖ በየትኛውም ጊዜና አመራር፣ ሌላው ቀርቶ በየትኛውም ወቅታዊ ፈተና ሳይናወጥ ወደ ኃይል ማመንጫ ቀዳሚ ምዕራፍ መድረስ ችሏል፡፡

- Advertisement -

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ትልቁእንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ አሥር ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ መሆኑ የተለየ የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን፣ አገራችን በከፍተኛ ሕዝባዊ ቁርጠኝነት በራስ አቅም ልትገነባው ቆርጣ የተነሳችበት ብቻ ሳይሆን የምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ ሳይለየው የዘለቀ በመሆኑ የተለየና ዓይን ገላጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ወደፊትም ለበረታ ትውልድ የዕድገት መስፈንጠሪያ መሰላል መሆኑ አይቀርም፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያና ሕዝቧቿ ከራሳቸው በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት ይዘው የቆዩትን የቁጭትና የማይደፈር አድርጎ የመቁጠር አዙሪት የቀየረ ፕሮጀክት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የግብፅና የሱዳን ብቸኛ ኢፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ዕሳቤ በመቀየር መላውን የተፋሰሱ አገሮች በሀብታቸው የመጠቀም ተነሳሽነት የፈጠረ ነው፡፡

አገራችን ይህን ፈር ቀዳጅ ዕርምጃ በመውሰዷ ግን የገጠማት ፈተናና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይ ነባሩ ጥቅማቸው የተነካ የመሰላቸውን የግብፅና የሱዳን ፖለቲከኞች በተለያየ መንገድ እንቅፋት ሲደቅኑ  ቆይተዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተባባሪ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚና ተፋላሚዎችን በመደገፍ፣ በማደርጀትና በማስታጠቅ፣ ብሎም በፕሮፓጋንዳ እስከ ማገዝ የደረሰ ጥቃት እስከ ማድረስ የዘለቀ ተፅዕኖዎቸን እያደረጉ መሆናቸውም የሚታወቅ ነው፡፡

ታላቁ ፕሮጀክት ገና ከመነሻው በዋናነት ለኃይል ማመንጫ ሥራ የሚውል መሆኑ ተረጋግጦ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የውኃ ፍሰቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን በሚጎዳበት ደረጃ የውኃ መጠኑ እንደማይቀንስ በጥናትም የተረጋገጠም ሀቅ ነበር፡፡ ይህን ተፈጥሯዊና ሳይንሳዊ ዕሳቤ ለመቀበል የማትፈልገው የግብፅ ፖለቲከኞችና አጋሮቻቸው ግን እውነትና ፍትሕን በመካድ ነው የቆዩት፡፡

በአገራችን የተጀመረው በዓባይ ውኃ በፍትሐዊነት የመጠቀም ተግባርም የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን፣ የውኃ ሀብታቸው ያለ ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ እያዩ ምንም ማድረግ ልቻሉ ሕዝቦችን በመፍራት ከሴራ ድርጊት ሳይወጡ ቆይተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፈው ዓመት አገራችን ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ዕውን ካደረገች በኋላ ኃይል የማመንጨት ሙከራ በማድረጓ የተፈጠረ የውኃ ፍሰት መቀነስ ባይኖርም፣ ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎቻቸው ከማጥላላት አጀንዳቸው ሲወጡ አልታዩም፡፡ ብዙኃኑ የግብፅ ሕዝብም መንግሥቱ የአገራቸውን ጥቅም አሳልፎ እንደሰጠ ነው እየገመተ ያለው፡፡

በመሠረቱ የሱዳንና የግብፅ የተዶናቆሩ ፖለቲከኞች የእኛ ወይም የእነሱ አታካራ መፍጠርቸው ባይቆምም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ አንስቶ የአገራችንን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብንም ይበልጥ የሚያስተሳስርና የሚጠቅም ፕሮጀክት ነበር። ለአካባቢው አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ መሆኑና የቀጣናውን ሥነ ምኅዳር ለማስተካከል ያለውን ዘላቂ ፋይዳ እንኳን አቆይተን፣ ለሁለቱ አገሮች ከደለል የፀዳና ተመጣጣኝ የውኃ ፍሰት እንደሚያቀርብ መካድ እንደ ተራ ጭፍንነት የሚቆጠር ድርጊት ነው (አንዳንድ ትልልቅ የግብፅ የውኃ ተመራማሪዎች ሳይቀሩ ይህን ሀቅ ሲክዱ መመልከት ግን እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው)፡፡

ለነገሩ ኢትዮጵያዊያን ከእነ ጉድለታቸውም ቢሆን ያልዘነጉት ፕሮጀክታቸው ሆኗልና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዳር እንደሚደርስ የማያጠራጥር ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች የተጀመረው ዜጎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የልማት ድርጅቶች ግድቡን ለማፋጠን የሚረዳ የሀብት ማሰባሰብና ቦንድ ግዥ መርሐ ግብርን አጠናክረው መጀመራቸው መታየት ያለበትም ከእዚሁ እውነታ አኳያ ነው፡፡ ለነገሩ ሕዝቡ በፋይናንስ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በሞራልና በአንድነት ተባብሮ ከዳር እንደ ሚያደርሰው ጥርጥር የለውም፣ መንግሥት ፀጥታና ደኅንነቱን አጠናክሮ እስከሄደበት ድረስ፡፡

ይህ በመጨረሻዎቹ ምዕራፎች የግንባታ ሒደት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት አልፎ አልፎ የሚደቀኑበትን የፀጥታ ችግሮችና ፈተናዎች ተባብሮ የመመከቱ ጉዳይም ቸል ሊባል የማይገባው ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት ጉባና አካባቢው፣ እንዲሁም በምዕራብ ኢትዮጵያ ቀጣና እየገጠመ ያለው የውስጥና የውጭ ኃይሎች የማተራመስ ሙከራ ከምንጩ እንዲደርቅ የተባበረ ሥራ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው ሊባል የሚችለውም በሞራል፣ በፋይናንስ፣ በጉልበትና ዕውቀት በመሳተፋችን ብቻ ሳይሆን ሰላምና ደኅንነቱንም መጠበቅ ሲቻል ነው፡፡ በእርግጥ በመላው አገሪቱም ቢሆን የሰከነ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የተረጋጋ ሰላምና ዘላቂነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዕውን ማድረግ ካልቻለ ጉባ ብቻውን ሰላም ሊያገኝ አይችልም፡፡ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየአካባቢው በመተሳሰብና በአገር ፍቅር ስሜት በየተሰማራበት እየተንቀሳቀሰ፣ ትውልዳዊ የታሪክ አሻራውን ማጠናቀቅና አገሩን ለማፅናት መትጋት ነው ያለበት፡፡

ምንም እንኳን የአገራችን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ጎረቤት አገሮች በተለይ ግብፅና ሱዳን ከፕሮጀክቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ በመሆናቸው በፋይናንስ ሊደግፉት የሚገባ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለውጭ ተፅዕኖ ተጋላጭ ያልሆነው በራሳችን አቅም ብቻ እየተገነባ በመሆኑ ነው። እንኳንስ የሀብት ምንጩ ከውጭ ሆኖ ይቅርና ሲቪል ኮንትራቱን የወሰደው የጣልያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ለቆ እንዲወጣ ጫና እስከ ማድረስ የሚገዳደሩ ባላንጣዎች አሉበት፡፡

ነገር ግን ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ብዙ ዓመታት የቆየ በመሆኑና ኢትዮጵያውያን በደንብ ስለሚያውቅ ጫናውን ተቋቁሞ አብሮን ተሠለፈ እንጂ፣ ሌላ ኩባንያ ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር እንደነበር ለመገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ አገራችን የፕሮጀክቱን የአደጋ ተጋላጭነት የቀነሰችባቸው የመሬት፣ የመልከዓ ምድር አመቺነት፣ የግንባታ የፋይናንስ ምንጭና የመሳሰሉት ብቻ ሳይሆኑ አስተማማኝ የግንባታ ኮንትራክተሮችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በየጊዜው እያጠናከሩ በመሄድም ነው፡፡ ይህም ተጠናክሮ ከፍፃሜ ሊደርስ ይገባል፡፡

 በኢትዮጵያዊያን ላብ፣ ገንዘብ፣ ደምና አጥንት ጭምር የሚገነባው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከራሳችን አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ቱሩፋት ይኖረዋል ሲባል ለፕሮፓጋንዳ  አይደለም፡፡ ይልቁንም ተያያዥና ተመጋጋቢ በሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በቴክኖሎጂና ምርምር በዳበሩ ዕውቀቶችና ክህሎቶች የተሞላ የለውጥና የዕድገት ማዕከል በመሆኑም ነው፡፡

አሁን በምንገኝበት ሁኔታ የቀጣናው ሰላምና ደኅንነት መደነቃቀፉ ያሳደረው ጫና መኖሩ እንጂ፣ በአካባቢው ያሉ ከተሞችን የሚያስመነድግ የቱሪስት ማዕከል፣ መማሪያና መመራመሪያ የውኃ አካል፣ የዓሳ ሀብት ማመንጫ (በቅርቡ በተያዘው ውኃ ላይ የዓሳ ልማት ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ልብ ይሏል) መሆኑ በተግባር የሚታይ ነው፡፡ አንድ አገር ቀጣይ ዕድገትን የሚያረጋግጠው ደግሞ፣ እንዲህ የተፈጥሮ ሀብትን አስተማማኝ በሆነ የቴክኖሎጂ አቅም አጠቃቀም ለፍሬ ማብቃት ሲችል ነው፡፡

ለተስፋና ለተሻለ አገር ግንባታ ለመፅናት ግን ጠላት ካዘጋጀልን ወጥመድ ወጥቶ መደማመጥና መስከን ሲቻል ነው፡፡ በተለይ  በየአካባቢው የነገሡና የተሳከሩ የዘር ወይም የእምነት ፖለቲከኞች የዘነጉት ወሳኝ ጉዳይ፣ ባልተረጋጋችና ወደ ትርምስ በምታመራ አገር ውስጥ እንኳን ታላቁን ህልም ማሳካት ይቅርና በሰላም ወጥቶ መግባት የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ ደሃና ማንም የሚፈነጭባት አገር ከሆነች እንደሚመኙት የተበጣጠሱ አውራጃዎችስ ቢፈጠሩ ማን ሊጠቀም ነው? ተያይዞ ከመስጠም ውጪ፡፡

እናም በወቅታዊ የፖለቲካ እሰጥ አገባ አለመስከን አገርን ማተራመሱና ማወናበዱ አደብ ሊገዛ ግድ ይለዋል፡፡ መንግሥትም ቢሆን አገር ሳትረጋጋ፣ ሕዝብን ከመጨነቅ፣ ከመሸበር፣ ከመፈናቀልና ከሞት ሳይከላከል ምኑን አገር እየመራሁ ነው ለማለት ይቻለዋል? እናም የኢትዮጵያውያን የእምነት፣ የብሔርና የአመለካከት ብዝኃነት እንደ አሉታዊ መገለጫ በመቁጠር እርስ በርስ ለማባላትና በውጤቱም የተዳከመች አገርን በስም ብቻ ለማስቀረት፣ በውስጥና በውጭ የዶለቱ ኃይሎችን መታገል ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ሕዝቡንም ከጎኑ በማሠለፍ ከአዙሪቱ መውጣትና የህዳሴው ግድብን የመሰሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ ሊታገል ይገባል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አሁን ከግንባታ ጋር ተያያዥ የሚሆኑ ፈተናዎችን በአብዛኛው ያለፈ ለመሆኑ ቦታው ላይ ተገኝተው የተመለከቱ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው። ከጊዜና ከሀብት ጫና ጋር ተያይዞ ጥያቄ መነሳቱም ቢሆን በደሃ አገር ውስጥ እንዲህ ያሉ ግዙፍ ሥራዎች ሲከወኑ የሚያጋጥም ፈተና ነው፡፡ አሁንም ዋናው መፍትሔ ሳይሰለቹና ሳይዘናጉ ጅምሩን ከዳር ለማድረስ መትጋት፣ መሥራትና መምራት ላይ ማተኮር ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በጋራ በዓለማችን ረጅም በተባለው የዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ከመወሰናችንና ግንባታው ከመጀመሩ በፊት፣ ከፍተኛ ቁጭት እንደነበረን ይታወሳል። እኛ በዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የነበረን ቁጭት ተወግዶ ግንባታውን በመጀመር የግንባታው ሒደት መፋጠኑ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ አገር በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ የመቆማችን፣ ለወደፊትም ይህንን መንገድ የመከተላችን ዋነኛ ማሳያ እንደ ሆነም ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ነው። ለዚህም ነው ፕሮጀክቱ የጋራ፣ ለጋራ፣ በጋራ የሚከናወንና እንደ ልብ ትርታችን የሚታይ ወሳኝ የልማት ሥራ ነው ለማለት የሚያስደፍረው፡፡

ለነገሩ በተለያዩ ወቅታዊ ጫናዎችና ፈተናዎች እየተናጠብን እንጂ፣ አብዛኛው የአገራችን ሕዝቦች ዓይንና ጆሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ ከከተመ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚገኝበት ደረጃ አበረታች መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እሸት ማቅመስ የጀመረበት መሆኑ ተስፋ የሚያጭር ነው፡፡ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ብቻ ሳይሆኑ፣ መላው ሕዝብም (በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ ዳያስፖራው) እንደ ጀመረው ዘርፈ ብዙ ተሳትፎውን በማጠናከር ከፍፃሜው ለማድረስና ሥራውን ለማጠናቀቅ ይበልጥ መነሳት አለበት፡፡ ትግሉ በሁሉም መስኮች መሆኑንም አለመዘንጋት ያስፈልጋል፡፡

ይህ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ፍፃሜው ሩቅ ላይሆን የሚችለውም ሆነ፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ አካባቢው የሚኖረው ገጽታና ማራኪነት ከወዲሁ ተስፋ ሰጭ ሆኖ የሚታየው አገራችን ሰላም፣ የተረጋጋችና አንድነቷ የተጠበቀ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እንደ ስፋቱ፣ የወሰደው ጊዜና ሀብት በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ ሀብት የሚያመነጭ፣ ባለሀብት የሚፈጥርና አገር የሚገነባ መሆን የሚችለውም ዋናዎቹን አገራዊ ግቦች የሚያሳካ ትወልድ እየበረታ ሲሄድ ብቻ ነው። እናም ተነጥሎ የሚታይ ነገር ሊኖር አይችልም፡፡

በአጠቃላይ የእኛ ትውልድ የትልቅ የኃይል ምንጭ፣ የግዙፍ ሐይቅና ለመጭዎቹ ትውልዶች ፋይዳ ያለው አገራዊ ሀብት ባለቤት ለመሆኑ ለአፍታም መዘናጋት የለበትም፣ አይገባም፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ እኮ ከፍታው 145 ሜትር፣ የጎኑ ርዝመት 1.8 ኪሎ ሜትር የሚደርስ፣ የሚያከማቸው የውኃ መጠንም የጣና ሐይቅን ሁለት እጥፍ ሊሆን የሚችል ነው።

ግድቡ ሲጠናቀቅ 1,680 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር የውኃ መጠን ይኖረዋል የሚለው እውነታ እኮ መሬት ላይ መታየት ጀምሯል። ከግድቡ ወደኋላ ሜዳ ማስፈር አልፎ በርቀት የሚታዩት አነስተኛ ተራራ ማስፈሪያዎች ጭምር ወደ 246 ኪሎ ሜትር በሚሞላ ሐይቅ ተሞልተው ደሴት እንደሚፈጥሩ በዓይነ ህሊናችን ማለም ጀምረናል። በገቢርም እየታየ ነው፡፡ በግድቡ ምክንያት የሚፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት የሚመረትበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለአካባቢው ሥነ ምኅዳር ጠቀሜታ ያላቸው ሌሎች በየብስና በውኃ ነዋሪ የሆኑ እንስሳት፣ ዕፅዋትና አዕዋፍ መኖሪያ እንደሚሆንስ ማን ሊክደው ይችላል? እናም ትልቅ ሆነን ትልቅ ህልምና ፕሮጀክቶች ይዘን በመጥበብና በመነጣጠቅ ከመበዛን መውጣት የሁላችንም ዓላማ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን በከንቱ ትውልድነት ከመወቀስ የሚድን ማንም የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል nwodaj@yahoo.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...