Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

[ክቡር ሚኒስትሩ ከዴሞክራሲ ሥርፀት ዳይሬክተሩ ጋር በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው]

 • እሺ ውይይቱን ከየት እንጀምር? 
 • ዴሞክራሲን ለመትከል ተግዳሮት ከሆኑብን ጉዳዮች ብንጀምር መልካም ይመስለኛል ክቡር ሚኒስትር።
 • ጥሩ። 
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲን ለማስረፅ ከጀመርናቸው እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት መሆኑ ይታወቃል። 
 • ከታወቀ ለምን ትደግመዋለህ? 
 • ለመንደርደሪያ ያህል ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከመንደርደር በቀጥታ ጉዳዩን ማንሳት አይሻልም? 
 • ጥሩ ክቡር ሚኒስትር። ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ባስቀመጠነው አቅጣጫ መሠረት አቅርበናቸዋል ብቻ ሳይሆን መቀራረባችንን የሚመጥን ስያሜ እንዲያገኙ አድርገናል። 
 • የምን ስያሜ?
 • ተቃዋሚ የሚለውን ስያሜ በመቀየር ተፎካካሪ ብለናቸዋል። 
 • አሁንም መንደርደሪያ ላይ ነህ?
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን ወደ ጉዳዩ አትገባም?
 • ወደ እሱ እየመጣሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ 
 • እሺ ተፎካካሪ ብለን ሰየምናቸው። ምን አገኘን? 
 • ተፎካካሪ ብለን በመሰየም ብቻ አላቆምንም። የካቢኔ አባል ጭምር እንዲሆኑም አድርገናል።
 • ጤና የለውም እንዴ ሰውዬው! ምን ልትነግረኝ ነው የፈለግከው? 
 • ክቡር ሚኒስትር መሠረቱን ያነሳሁት ቀጥዬ ለማቅርበው ዋና ጉዳይ ጠቀሜታ ስላለው ነው።
 • እሺ ቀጥል። 
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በገለጽኩት መንገድ መሠረቱን በማስያዛችን አሁን ላይ ውጤቱን ማየት ጀምረናል።
 • ምንድን ነው መታየት የጀመረው ውጤት? 
 • ክቡር ሚኒስትር የእኛን ካድሬዎች ጣልቃ እንዲገቡ ሳናደርግ መናቆር ጀምረዋል።
 • ያስቀመጥነው ግብ መናቆር ነው ወይስ መቆም እንዳይችሉ ማድረግ? ይህንን ነው ውጤት የምትለው!
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን የታየው ጅማሮ ነው። ያስቀመጥነው ግብ ላይ በፍጥነት መድረሳቸው አይቀርም። 
 • ያስቀመጥነው ግብ ላይ በፍጥነት መድረስ ካልቻልን ዴሞክራሲን ማፅናት ፈጽሞ አንችልም። 
 • ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር።
 • እሱን ንገረኝ አላልኩም። 
 • ግቡን በፍጥነት ማሳካት የምንችልበትን ስትራቴጂ ቀርፀን እየተንቀሳቀስን ነው ክቡር ሚኒስትር።
 • ምን ለማድረግ ነው ያሰባችሁት?
 • የበለጠ ማቅረብ! 
 • ጥሩ። ከእኛ ጋር በቅርበት የማይሠሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል? 
 • እርማት ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን እርማት?
 • እነሱን ተፎካካሪ ፓርቲ ብለን አንጠራቸውም።
 • እና?
 • ተቃዋሚ ነው የምንላቸው። እነሱም እንደተቃዋሚ ነው የሚንቀሳቀሱት።
 • ይሁን እሺ። የእነሱን ጉዳይ እንዴት እየተከታተላችሁ ነው? ለምሳሌ በቅርቡ ለሚዲያ ቃለመጠይቅ የሰጡ እንዳሉ ሰምቻለሁ። 
 • አሁን የተቸገርነው በሚዲያዎች ነው። 
 • ለምን … እንዴት?
 • አብዛኞቹን አስገብተናቸዋል ስንል….ከሥር ይፈላሉ!
 • በቅርቡ ቃለመጠይቅ የሰጡት ተቃዋሚ ላይ የሚደረገው ክትትል እንዴት ነው? 
 • ክትትሉን አጠናክረን ቀጥለናል ክቡር ሚኒስትር። ከሰሞኑ የሰጡት ቃለመጠይቅም በጎ የሚባል ነው። 
 • አገሪቱ ገደል አፋፍ ላይ የቆመ አቶብስ እንደምትመሰል መግለጻቸው ነው በጎ የሚባለው? 
 • ዋናው ነገር …
 • እሺ። የፊት ጎማቸው ገደሉ ውስጥ ገብቶ በኋላ ጎማቸው ብቻ ነው የተንጠለጠሉት ማለታቸው ነው በጎ ነገር? 
 • አውቶብሱን ተጋግዘን ማውጣት አለብን ብለዋል እኮ ክቡር ሚኒስትር? 
 • እሱስ ቢሆን? በራሳቸው መውጣት አይችሉም ማለታቸው አይደለም? 
 • ዋናው ነገር …
 • ምንድን ነው ዋናው ነገር … ዋናው ነገር የምትለው? ምን ዋና ነገር አለው!
 • ሹፌሩ አውቶብሱ ውስጥ አለ ብለዋል። 
 • እርግጠኛ ነህ እንደዚያ ብለዋል? 
 • ሹፌሩ ከአውቶብስ ውስጥ እንዳለ አውቶውብሱን ተጋግዘን እናውጣ ነው ያሉት!
 • እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ነው።
 • እንደዚያ ነው ያሉት። በዚህ ከቀጠሉ ትንሽ አይተን ስያሜያቸው ቢቀየር ጥሩ ነው።
 • ስያሜያቸው ምን ሊባል?
 • አጋር፡፡ 
 • በአንድ ጊዜ አጋር?
 • እና ምን ይሻላል? 
 • በተፎካካሪ ይቆዩ።

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንዲሳተፉ ከተለዩ ባለሀብቶች መካከል እንዱ ጋ ስልክ ደውለው በንቅናቄው ላይ እንዲሳተፉ ግብዣቸውን እያቀረቡ ነው]

መቼም ኢትዮጵያ ታምርት በሚል የተጀመረውን አገር አቀፍ ንቅናቄ ሳትሰማ አትቀርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ልክ ነው፣ ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር። አሁን ደግሞ ንቅናቄውን ለማጠናከር ኢትዮጵያ ታምርት የሚል የታላቁ...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ሥራቸውን አጠናቀው ከውጭ አገር የመጣ ወንድማቸውን ለመጠየቅ ያረፈበት ገስት ሀውስ ሲደርሱ ወንድማቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ፕሮግራም በመገረም እየተከታተለ አገኙት]

ውይ መጣህ እንዴ? እስኪ አረፍ በል፡፡ ምንድነው እንዲህ ያስደነቀህ? ተደንቄ ሳይሆን ግራ ግብት ብሎኝ ነው። ምኑ ነው ግራ ያጋባህ? የድልድይ ማስመረቅና የድልድይ ማፍረስ ነገር ነዋ። አልገባኝም? አለቃችሁ ድልድይ ሲያስመርቁ የተናገሩትን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በዓሉን በመኖሪያ ቤታቸው እያከበሩ ነው። ባለቤታቸውም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦ ባርከው እንዲቆርሱ ለሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

በል ዳቦውን ባርክና ቁረስልንና በዓሉን እናክብር? ጥሩ ወዲህ አምጪው... አዎ! በል መርቅ... ከዓመት ዓመት ያድርሰን... ኧረ በሥርዓት መርቅ ተው? ከዓመት ዓመት ያድርሰን አልኩኝ እኮ ...አልሰማሽም? ከዓመት ዓመት መድረሱ ብቻ ምን...