Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአራት እንደ አርባ - የፖለቲካው እንጦሮንጦስ

አራት እንደ አርባ – የፖለቲካው እንጦሮንጦስ

ቀን:

በበላይ አበራ

የአገራችን ፖለቲካ አስገራሚ ሽግግር እያደረገ ነው፡፡ ከልክ ባለፈ ተስፋ ተጀምሮ ዕልም ባለ ምሬት እየተተካ ነው፡፡ ከመደበኛው ሕዝብ እስከ ምሁሩና ዳያስፖራው ድረስ ተመሳሳይ የስሜት ንደት መስተዋል ጀምሯል፡፡ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ተመሳሳይ የተስፋ መቁረጥ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

ለምሳሌ ዳያስፖራው ከጥልቅ ድጋፍ ወደ ጥልቅ ተቋውሞ እየተሸጋገረ ነው፡፡ የብልፅግና ባለሥልጣናትን ፎቶ የታጀቡ የድጋፍ ሠልፎች በተለያዩየ የውጭ አገሮች ከማካሄድና ለልማታዊ ሥራዎች፣ ለተቸገሩና ለተፈናቀሉ ዜጎች መዋጮ ከማዋጣት ምሬት የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎችን ወደ ማሳየት እየተቀየረ ነው፡፡ ወደ አገር ተመልሶ በንግድ ሥራዎች ላይ ለመሠማራት ከመንቀሳቀስ፣ ወደ ወረቀት አሳድሶ ተመልሶ ውጭ አገር መሰደድ መታየት ጀምሯል፡፡

- Advertisement -

በምሁራን በኩል ደግሞ ብልፅግናን የሚደግፉ ተግባራትን ከማከናወን ይልቅ፣ ተቃውሞ የሚያስነሱ ሥራዎች ላይ መሳተፍ እየተለመደ ነው፡፡ ለብልፅግና የሚበጁ ሐሳቦችን ከማቅረብ ወደ ችግሮችን አስታኮ መቃወም እየታየ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ተሳታፊ ከመሆን ተቺ መሆን የተሻለ አማራጭ ሆኗል፡፡

ፖለቲከኞችም በተመሳሰይ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተለየ ሐሳብ ላላቸው ፖለቲከኞች ክፍት ምኅዳር ከመክፈት ወደ አሳዶ ማሰርና ማሰቃየት ተተክቷል፡፡ በአገራችን የሠለጠነ አካሄድ የሚመራ ፖለቲከኛ እምብዛም አለ ተብሎ ባይታሰብም፣ ያሉት ፖለቲከኞች አሁን ያለውን መንግሥት ከማበረታታት ወደ አጥብቆ መቃወም ተቀይረዋል፡፡ በሐሳብ በጣም የሚለያዩ ኃይሎች ሳይቀሩ በተቃውሞ መደገፍ ጀምረዋል፡፡ መካከለኛ ፖለቲከኛ የነበሩ ኃይሎችም ወደ ጥግ ሄደው መቃወም ጀምረዋል፡፡ ከእዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታት የሠሩዋቸውን ጥፋቶች የወቅቱ መንግሥት ላይ መለጠፍ ተጧጡፏል፡፡

መደበኛው ሕዝብ በየመኖሪያ ቤትና ንግድ ሥፍራዎች የብልፅግና ባለሥልጣናት ፎቶ ከመለጠፍ፣ ወደ ፎቶዎች መቅደድና ሰብስቦ ማቃጠል ዞሯል፡፡ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት በምርጫ ከተሳተፈው ሕዝብ የማይተናነስ ሕዝብ፣ የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ እየሆነ ባለው ፖለቲካ ደስተኛ አለመሆኑን አሳይቷል፡፡ ሕዝቡ መንግሥታዊ ሚዲያዎችን ከማዳመጥና ከመመልከት መንግሥትን የሚቃወሙ ሚዲያዎችን መከታተል ጀምሯል፡፡ ሕዝብ በሚሰበስብባቸው ቦታዎች ብልፅግናን የሚቃወሙ ሐሳቦችን አንስቶ መከራከር ከተለመደ ሰነባብቷል፡፡ የብልፅግና ባለሥልጣናትን ስም እየጠሩ መሳለቅና በሚከሰቱ ጥፋቶች ተጠያቂ አድርጎ መበየን ተለምዷል፡፡ ከእዚህ አልፎም ከዚህ ቀደም በሕዝብ የሚጠሉ ግፈኛ መሪዎችን ሲያመሠግን ይስተዋላል፡፡

ነጋዴውም በብልፅግና ደስተኛ አለመሆኑን እያሳየ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የተፈጠሩ አብዛኞቹ ባለሀብቶች በሕወሓት ድጋፍ ያደጉ መሆናቸው ቢታመንም፣ ከእዚህ ውጪ የሆኑትም ቢሆን ለብልፅግና ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ሰው ሠራሽ የምርት እጥረት በመፍጠር ሕዝቡ በኑሮ ውድነት ብልፅግና ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ እየጣሩ ነው፡፡ ብልፅግናን ለሚታገሉ ታጣቂ ቡድኖች የገንዘብና ቁሳዊ ድጋፍ በህቡዕ እያደረጉ ነው፡፡

ሚድያውም ለብልፅግና ያለውን ተቃውሞ እያሳየ ነው፡፡ ብልፅግናን አጥብቀው የሚተቹ ልሂቃንን ለሚዲያ ውይይት መጋበዝና ማቅረብ መደበኛ ሥራቸው ሆኗል፡፡ ብልፅግናን ከልክ ባለፈ የሚተቹ ሚዲያዎች የተመልካቾች ቁጥር ጨምሮላቸዋል፡፡ ከዚህ አልፎም ብልፅግናን ዘርጥጠው የሚተቹ ሚዲያዎች የዩቲዩብ ገንዘብ በገፍ ተቀባይ ሆነዋል፡፡ እንደ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራምና ዩቲዩብ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ብልፅግናን በሚቃወሙ ፕሮግራሞች ተጥለቅልቀዋል፡፡ በተከታታዮችም ተንበሽብሸዋል፡፡ ደጋፊ የሚመስሉ ሚዲያዎች ግን በተከታይ ዕጦት ጥም እየተሰቃዩ ነው፡፡ የሚዲያው ሽግግር በብርሃን ፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡

ከመካከለኛ ፖለቲከኞች ይልቅ የታጠቁ ቡድኖች ተበራክተዋል፡፡ ከሐሳብ ይልቅ ጠመንጃ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ማስፈጸሚያ መሣሪያ እየሆነ ነው፡፡ መሀል አገር ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች እየከሱ በዱር የታጠቁ ቡድኖች እየወፈሩ ነው፡፡ የታጠቁ ቡድኖች እንደ በረሮ በየቦታው እየተፈለፈሉ ነው፡፡ ከምርጫ ይልቅ ጡንቻ ገዥ ነው የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች በርክተዋል፡፡

ሌላው ደግሞ የብልፅግና ባለሥልጣናት አዎንታዊ ሐሳብ የሚያቀርቡ ምሁራንን ከማዳመጥ ይልቅ ቦታ አለመስጠት እየታየ ነው፡፡ ምንም እንኳን አገር ከተለያዩ ምሁራን በሚወጣጡ ሐሳቦች ብትገነባም፣ የብልፅግና ባለሥልጣናት ማንንም አልሰማም እያሉ ነው፡፡ አልሰሜም ሆነዋል፡፡ ተለምነው የማያዳምጡ በመሆናቸው ምሁራኑ እነሱን የሚያዳምጥ ሌላ መንግሥት እንዲመጣ መማፀን ጀምረዋል፡፡ ምሁራኑ አዲስ የመንግሥት ለውጥ መምጣት እንዳለበት እየተማመኑ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ ለማብራራት ያነሳኋቸው ሐሳቦች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በብልፅግና ላይ ያላቸውን እሮሮ እንዲያነሱና ያለፉት አራት ዓመታት ልክ እንደ አርባ ዓመታት እንዲመስሉ እያደረጉ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ያለፉት አራት ዓመታት የምጥ ዓመታትና እጅግ የረዘሙ የሚመስሉ ጊዜያት ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ የብልፅግና ባለሥልጣናት እንደ ሕዝቡ ሁኔታው ያንገበገባቸው አይመስሉም፡፡

አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በብልፅግና ሙሉ  በሙሉ የተፈጠሩ ናቸው ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የአገራችን ችግሮች ለባለፉት 150 ዓመታት ሳይፈቱ ከመንግሥት ወደ መንግሥት ሲንከባለሉ የተሸጋገሩ መሆናቸውን ብዙዎች ይረዳሉ፡፡ በባለፉት 30 ዓመታት ደግሞ እንደ ተባባሱ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ልዩነት ሰባኪውና ዘራፊው ሕወሓት አሁንም ከሚከሰቱ ችግሮች ጀርባ መሽጎ፣ ብልፅግና በሕዝቡ ሲጠላ ባለው የጦር መሣሪያና አደረጃጀት ተጠቅሞ ወደ ሥልጣን ለመመለስ እንደሚሞክር ይታመናል፡፡ ሕዝቡ ሕወሓትን አጥብቆ በመቃወሙ ከብልፅግና ጋር አብሮ ታግሎ እንዳሽቀነጠረው ማብራሪያ አያስፈልገውም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥልጣን ላይ ላለው ለመንግሥት ያለውን ድጋፍ በተለያዩ መንገዶች አሳይቶ ነበር፡፡ ለመከላከያ ገንዘብ፣ ሠንጋ፣ ብሉኮ፣ ዳቦ ቆሎና የተለያዩ ምግቦችን በስጦታ መልክ አቅርቦ ነበር፡፡ ልጆቹንም ወደ ውትድርና ልኮ ነበር፡፡ የድጋፍ ሠልፎችን በተደጋጋሚ አካሂዶ ነበር፡፡ ዳያስፖራውም በዲፕሎማሲው በኩል አጥብቆ ታግሎ ነበር፡፡ ከትዊተር ዘመቻ እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ደጃፍ የማያባራ ተቃውሞ በማድረግ የውጭ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ተረባርቦ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በምላሹ ተመሳሳይ ውጤት ባያገኝም ሕዝቡ የቻለውን ጥረት አድርጎ ነበር፡፡

በአገራችን የግጭቶች መበራከት ብዙ ዜጎችን እያሠጋ ነው፡፡ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የጎሳ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቦታ ቦታ መስፋፋታቸው በአገር ህልውና ላይ ደንቃራ ሆኗል፡፡ አንዳንዶች ብሔራዊ መግባባት ቢደረግ ችግሩ ይፈታል ብለው ያስባሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ መንግሥት ጠንካራና አስተማሪ ዕርምጃ ቢወሰድ ይረጋጋል ይላሉ፡፡ ሌሎች ግን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እስካሉ ድረስ ግጭቶች አይበርዱም ይላሉ፡፡ በዓለም ላይ ሰላማዊ የሚባሉ አገሮች ዜጎቻቸውን ወደ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያሸጋገሩ ናቸው፡፡ በጣም ደሃ ሳይሆን በጣም ሀብታም ያልሆነ መሠረታዊ ፍላጎቱ የተሟላለት ሕዝብ በመፍጠራቸው ከቀውሶች ለማምለጥ ችለዋል፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ ኖርዌይና ዴንማርክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንዚህ አገሮች አነስተኛ የሚባል የፀጥታ ሠራዊት ሲኖራቸው ነገር ግን የተረጋጉና ሰላማዊ አገሮች ናቸው፡፡

የአገራችን ሁኔታ ቻይና በ1970ዎች መጀመርያ አካባቢ ከነበረችበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ቻይና አደገኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ሲፈታተናት በወቅቱ የነበሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ መሆኑን በመረዳታቸው፣ የአንድ ሕፃን ፖሊሲ ቀርፀው ትግበራው ከኮሙዩኒስት ፓርቲው አመራሮች ተጀመረ። የውልደትና የሞት ምጣኔው ከከፍተኛ ወደ ዝቀተኛ ሲለወጥ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ዜጎች ቁጥር ከ25 በመቶ በታች ሲሆን፣ ከ15 እስከ 64 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች መጠን ከፍ ስለሚል ጥገኛ የሆኑትን ቁጥር ቀንሶ አምራች የሆነውን ክፍል መጨመሩ የኢኮኖሚ አብዮት እንዲመጣ አስችሏል። በዕድሜ ስብጥር ከሚመጡ ለውጦች ጋር የሚዛመዱ ፖሊሲዎችንና መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማሟላት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን አግኝተዋል።

የአገራችን ችግሮች ከፖለቲካዊ ችግሮች የዘለሉ ናቸው፡፡ መንግሥት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለሁለት አሥርት ዓመታት በሁለት አኃዝ እያደገ የውልደት ምጣኔ 4.1 ነው ቢልም፣ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፡፡ አንድ አገር ያላት የኢኮኖሚ ዕድገት የኑሮ ሁኔታን የሚያሻሽለው የውልደት ምጣኔ ከ2.6 በታች ሆኖ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ዜጎች መጠን ከ25 በመቶ በታችና የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አኃዝ ሲሆን ነው፡፡

እንግዲህ አገራችን በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ አገራችን አሁን ካለችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ ደግሞ መንግሥት ቆራጥ መሆን አለበት፡፡ ሕወሓት በጦላይ ወንዝ ወያኔነትን ያጠመቀቻቸው ጎምቱ ፖለቲከኞችን ማፅዳት፣ ምግባረ መልካም ምሁራንን መተካት፣ በመንግሥትና በድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች አማካይነት ለወጣቶች በተለያዩ የሙያ መስኮች አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት በተለያዩ ሥራዎች ማሠማራት፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በማከናወን የውልደት ምጣኔውን ከ2.6 በታች ማውረድ፣ በርካታ ወጣቶችን የሚቀጥሩ ትልልቅ ፋብሪካዎችን መክፈትና የምግብ ምርትን ማሳደግና ነጋዴዎች በእርሻ ሥራ እንዲሠማሩ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል belayab2020@gmail.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...