ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከፍተኛ የሚባል የውጭ ምንዛሪ ከምታወጣባቸው ምርቶች መካከል ነዳጅ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ለነዳጅ ግዥ የሚወጣው ወጪ ከፍና ዝቅ እያለ ቢቆይም አሁን ላይ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ የምታውለው ወጪ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ሆኗል፡፡
ከፍና ዝቅ እያለ የመጣው የነዳጅ መግዣ በ2011 በጀት ዓመት 2.6 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2013 በጀት ዓመት ደግሞ 1.94 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደገለጸው ደግሞ፣ በ2014 በጀት ዓመት ብቻ የአገሪቱ የነዳጅ ግዥ ወጪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህ ወጪ እስካሁን ለነዳጅ ግዥ የወጣ ከፍተኛ የሚባል ወጪ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ያለው ወጪ ደግሞ እጅግ የበዛ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ በዓመት ለነዳጅ ግዥ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ በዓመት ከምታገኘው የወጪ ንግድ ገቢዋ ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ፣ አገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በሙሉ ለነዳጅ ግዥ ታውላለች እየተባለ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን ይህ አባባልም እንደሚለወጥ ይጠበቃል፡፡ ይህ አባባል ሁለት ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን፣ አንደኛው የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ከነዳጅ መግዣ አያልፍም የሚለውን ለማመልከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆኑንና የወጪ ንግዳችን ደግሞ ዝቅተኛ ነው የሚለውን ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ መጠን ከወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ አንፃር ተቀራራቢ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ የወጪ ንግድ ገቢው ለነዳጅ ግዥ ብቻ ነው የሚለው አባባል ተደጋግሞ ቢነገርም፣ አንድም ጊዜ ዓመታዊ የነዳጅ ግዥ ወጪዋ ከወጪ ንግድ ገቢው በልጦ አያውቅም፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በየዓመቱ እንደሚያደርገው ለ2015 በጀት ዓመት የሚያስፈልገውን ነዳጅ ለመግዛት ባወጣው ጨረታ አሸናፊ ከሆነው ቪቶል ከተባለው የባህሪን ኩባንያ ጋር ስምምነት ባደረገበት ወቅት የታየው የዋጋ ለውጥ ግን አሳሳቢ ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መረጃ ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት ወደ 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ያስፈልጋታል፡፡ ከዚህ የነዳጅ ፍላጎት ውስጥ ለዓመቱ ከሚያስፈልገው ነጭ ናፍጣ ግማሽ ያህሉን 1,600 ሜትሪክ ቶንና 860 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቤንዚን በዚሁ ቪቶል ኩባንያ በኩል የሚቀርብ ነው፡፡ ለዚህ አቅርቦት ኢትዮጵያ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡ ይህ ወጪ በ2014 ዓ.ም. ለዓመት ለሚያስፈልጋት ነዳጅ ያወጣችውን ያህል በ2015 ዓ.ም. ለግማሽ ፍጆታዋ የምትውለው መሆኑን ያሳያል፡፡
በባህሪኑ ኩባንያ ከሚገባው ነዳጅ ሌላ ቀሪውን የ2015 የነዳጅ ፍላጎት ቀጥታ የሚሞላው በጨረታ በሚደረግ ግዥ ነው፡፡ ቀሪውን ነዳጅ ወደ አገር ለማስገባትም ተጨማሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ በ2015 በጀት ዓመት ለሚያስፈልጋት ጠቅላላ ነዳጅ ግዥ ልታወጣ የምትችለው 5.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ በ2015 በጀት ዓመት ለነዳጅ ታወጣለች ተብሎ የተገመተው ጠቅላላ ወጪ፣ ከ2014 በጀት ዓመት ከወጣው ወጪ አንፃር ከታየም በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ለዚህም ነው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ለነዳጅ ግዥ ብቻ የሚውል ነው የሚለውን ትርክት በእጅጉ ይለውጣል ተብሎ የሚጠበቀው፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ካልጨመረ ከዚህ በኋላ የወጪ ንግድ ገቢ ለነዳጅ ግዥ እንኳን የማይበቃ ይሆናል ወደሚል መደምደሚያ የሚወስደው፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ለመጀመርያ ጊዜ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የተገኘበት በ2012 እና በ2013 በጀት ዓመት መሆኑ ይታወቃል፡፡
አቶ ታደሰም የሚያሳስበን እሱ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን የ2015 በጀት ዓመት ወጪያችን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ እጅግ እየጨመረ በመሄዱ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ግዥ እንድታውል እያስገደዳት ነው ብለዋል፡፡ 2015 በጀት ዓመት የነዳጅ ግዥ ወጪ እንዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ላይ የወጣው የዓለም ነዳጅ ዋጋ ብቻ በመጨመሩ አይደለም፡፡ የነዳጅ የማጓጓዣና ለተያያዥ አገልግሎቶች እየተጠየቀ ያለው ወጪ እስከዛሬ ባልታየ ሁኔታ ከፍ ብሎ መገኘቱ ጭምር ነው፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ ኢትዮጵያ ነዳጅን በሁለት መንገድ ታስገባለች፡፡ አንደኛው መንግሥት ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በሚፈጸም ግዥ መሠረት ከኩዌት በቀጥታ ግዥ የሚፈጸም ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዓለም ገበያ በሚደረግ ጨረታ የሚገዛ ነው፡፡ አቶ ታደሰ እንደገለጹት ከኩዌት መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በዓመት ከሚያስፈልገው የነጭ ናፍጣ 50 በመቶ የሚሆነውንና 100 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ነው፡፡ ቀሪውን 50 በመቶ ናፍጣና መቶ በመቶ የሚሆነውን ቤንዚን በጨረታ ከዓለም ገበያ የሚገዛ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአንድ ዓመት የሚሆነውን ነዳጅ ግዥ ቀድሞ ለመግዛት ባወጣው ጨረታ፣ ኩባንያው አሸናፊ የሆነው ቪቶን ከሌሎች ሁለት ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ የተሻለ ፕሪሚየም በማቅረቡ የተመረጠ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በተመሳሳይ በ2004 ዓ.ም. የሚያስፈልገውን ነዳጅ አቅርቦ የነበረ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ነዳጅ ሲያቀርብ የነበረው ‹‹ትራፊ ጉራ›› የተባለው የስዊዝ ኩባንያ ሲሆን፣ በዘንድሮው ጨረታ ተሳታፊ አልሆነም፡፡ በ2015 የሚቀርበው ነዳጅ መጠን ከ2014 አንፃር ሲታይ ናፍጣ የተወሰነ ጭማሪ ሲታይበት፣ ቤንዚን በ21 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የነዳጅ ግዥ ወጪዋ እንዲህ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ብቻ አይደለም፡፡ አጠቃላይ ከነዳጅ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች በሙሉ ዋጋ በመጨመራቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ገለጻም ነዳጅን ለማቅረብ ስምምነት የማያደርጉ ኩባንያዎችም የሚጠይቁት ፕሪሚየም ከፍ ብሏል፡፡ በተለይ የመርከብ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅና በኢንዱስትሪው ያልተጠበቀ ዋጋ እንዲጠየቅበት እያደረገ ነው፡፡
በተለይ የፕሪሚየሙ ዋጋ በጣም ነው የጨመረው፡፡ ይህም የመርከብ ዋጋ በጣም ከፍ በማለቱና እጥረት በመፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአውሮፓ አገሮች ነዳጅ የሚያስመጡት ከሩሲያ ነበር፡፡ አሁን እየቀረ በመምጣቱ ራቅ ካለ ቦታ ማምጣት መጀመራቸው የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን የምልልስ ጊዜ በማራዘም እጥረት ተፈጥሯል፡፡
ሌላው የሎጅስቲክሱን ወጪ ያናረው ሥጋት ነው፡፡ አንድ ኩባንያ ነዳጅ አቀርባለሁ ብሎ ከተዋዋለ በኋላ እንደ ቀድሞ ከፈለገበት አገር መግዛት ስለማይችል ይህ ሥጋት ለዋጋው መጨመር ሌላ ምክንያት መሆኑን አቶ ታደሰ አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የነዳጅ ወጪዋ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱና ኢኮኖሚያዊ ጫናው የበለጠ ይገለጻል ተብሎ የሚታመነው ሌላው ማሳያ ደግሞ ከብር የመግዛት አቅም አንፃር እየታየ ያለው ከፍተኛ ልዩነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተከታታይ ዓመታት ሪፖርቶች እንደሚሳዩት፣ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዥ የሚወጣው ወጪ በብር ሲመነዘር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት እየታየበት መሆኑን ነው፡፡ የአገሪቱ የነዳጅ ወጪ በቀነሱባቸው ዓመታት እንኳን ከብር አንፃር ሲመነዘር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ ከዚሁ የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም፣ ከዛሬ 16 ዓመታት በፊት በ1998 ዓ.ም. ለነዳጅ የወጣው 7.4 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ግን ይህ ወጪ 28.2 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ የነዳጅ ግዥ በ2009 ዓ.ም. ወደ 40.9 ቢሊዮን ብር፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 61 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡
የዓለም የነዳጅ ዋጋ በቀነሰበት በ2013 ዓ.ም. ለውጭ ምንዛሪ ለግዥው የወጣው ወጪ ከቀደመው ዓመት የሚያንስ ቢሆንም፣ በብር ሲተመን ግን ዓመታዊ ወጪው 72 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ ችሏል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት የነዳጅ ግዥ ከወቅታዊ የብር የምንዛሪ አማካይ ዋጋ አንፃር ሲታይ ደግሞ ዘንድሮ ለነዳጅ ግዥ የወጣው ወጪ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
በዚህ ሥሌት በቀጣይ ዓመት ለነዳጅ ግዥ የሚወጣው ወጪ ታሪካዊ የሚያደርገው በነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ልክ የብር የመግዛት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በተደከመበት ወቅት በመሆኑ የነዳጅ ግዥው በብር አንፃር ሲመነዘር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡