የመረጃና ደኅንነት ሥራ በኢትዮጵያ ታሪካዊ አጀማመሩ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ በወቅቱ በነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር ‹‹የፀጥታ ጠቅላይ መምሪያ›› በተለይም የአርበኞችን ተቃውሞ መከላከል፣ ጣልያኖች በዘረጉት የክልሎች የከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት በተፈጠሩ የክልላዊ አስተዳደሮች ሊነሱ የሚችሉ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠርና ከጣልያን ወረራ በኋላ የነበረውን አለመረጋጋት መቆጣጠር ዋነኛው ተግባሩ እንደነበር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በርካታ ለውጦች እየተደረጉበት ከቆየ በኋላ የደርግ መንግሥት በ1966 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የነበረውን የንጉሡን ዘመን የመረጃና የደኅንነት ተቋም በማፍረስ፣ የራሱን በደርግ ጽሕፈት ቤት ‹‹የመረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ›› በሚል ተቋቁሞ በወቅቱ የነበረውን የሶማሊያ ሁኔታ መከታተልና ፀረ አብዮተኞችና የኢምፔርያሊስቶች ቅጥረኛ የሚባሉ ኃይሎችን መከታተልና ሌሎችንም ኃላፊነት ተሰጥቶት ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ይጠቀሳል፡፡
የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የሽግግሩ መንግሥት የነበረውን የደርግ የመረጃ ተቋም አደረጃጀት በአዋጅ እንዲፈርስ ካደረገ በኋላ፣ በ1987 ዓ.ም. ተቋሙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ስያሜውም ‹‹የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን›› በሚል በአዋጅ ቁጥር 6/1987 እንደገና በማቋቋም፣ በአገር ውስጥና በውጪ የአገር የሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ ሥራ መሥራት፣ የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ፖሊሲ ማዘጋጀትና ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ፣ በአገር ነፃነትና ኢኮኖሚ የሚጠነሰሱ ሴራዎችን መከታተል፣ ማጣራትና ለሚመለከተው ማሳወቅና ሌሎች ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በነሐሴ 2004 ዓ.ም. ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ሥልጣን የተረከቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በተቆናጠጡ ማግስት፣ ይኼው የስለላ ተቋም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት በሚል በ2005 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 804/2005 እንደገና ተቋቋመ፡፡
በተሻሻለው በዚህ አዋጅ መሠረት ተግባሩ የመረጃና ደኅንነት ተልዕኮዎችን መፈጸም ሲሆን፣ በመረጃ ረገድ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የመከታታል እንዲሁም በየአካባቢው የሚነሱ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መረጃ በማሰባሰብና ጥልቅ ትንታኔ በማድረግ ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ ተሰጥቶታል፡፡ በተለይም ደግሞ ከሽብርተኘነት፣ ከአክራሪነትና ፅንፈኝነት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የሥጋት አዝማሚያዎችን አስቀድሞ በመገመት የመከላከል ሥራዎችንም እንደሚሠራ ተብራርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ በበርካቶች ዘንድ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ዋነኛ መሣሪያ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
የዓለም አቀፍ የደኅንነት ተቋማት ልምድና ተቋማዊ ቁመና በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት አደጉ የሚባሉ አገሮች፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት ተቋማት ራሳቸውን ችለው ከፖለቲካ ሥርዓት ገለልተኛ በሆነ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ የደኅንነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የፖለቲካ ቁንጮውን በሚዘውሩ መሪዎች ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ አሁኑ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት ድረ ገጽ ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ተቋሙ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሣሪያ ሆኗል የሚሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ እንደሚነሱበት፣ ሚስጢራዊነትን ተገን በማድረግ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ይፋ ሊሆኑ የሚገባቸው መረጃዎች አለመገለጻቸው የተቋሙን የግልጸኝነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ያትታል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጄንሲ አዋጅ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ዘመን አገሪቱን ሲያስተዳድሩ በነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም የሥልጣን ዘመን በ2005 ዓ.ም. ከተሻሻለ ወዲህ፣ ሳይሻሻል የቆየ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ተቀዳጅተው በአዲስ ያቋቋሙት የብልፅግና ፓርቲ በግንቦት 2013 ዓ.ም. በአብላጫ ድምፅ ማሸነፉን ተከትሎ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአገር ላይ የሚቃጡ ‹‹የሥነ ልቦና›› ጦርነቶችን ለመመከት፣ በበላይነት እንዲመራና እንዲያስተባብር የሚፈቅድና ተሻሽሎ የቀረበ አዋጅ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ወደ ፓርላማው መምራቱ ይታወሳል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በ2011 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ፣ ለዘመናት በመሪዎች ቁጥጥር ሥር የነበረውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጨምሮ በርካታ ከፀጥታ ጋር የተገኙ ወደ አሥር የሚደርሱ ተቋማት በዚሁ አዋጅ እንደ አዲስ ለተቋቋመና ለፓርላማው ተጠሪ በነበረው የሰላም ሚኒስቴር ሥር ተካተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በመስከረም 2014 ዓ.ም. የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን እንደገና ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ፣ የብሔራዊ ደኅንነቱን ተቋምና በሰላም ሚኒስትር ሥር የነበሩ ተቋማትን ጨምሮ በድምሩ 20 የሚሆኑ ቁልፍ የሚባሉ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
አዲስ ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ ሥራ ላይ ያለው አዋጅ ተግባርና ኃላፊነት ውስጥ የሌሉ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ቀርቧል፡፡ ለአብነትም አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የሌለውና አዲሱ ረቂቅ ላይ ተጨማሪ ሆኖ የገባው ረቅቂ አንቀጽ፣ በአገር ላይ የሚቃጡ ‹‹የሥነ ልቦና›› ጦርነቶችን የመመከት ሒደት በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት፣ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋቶችንና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓትን በኃላፊነት የመምራት፣ የሚመለከታቸውን አካላት በበላይነት የማስተባበር ኃላፊነት ለአገልግሎት ተቋሙ መስጠቱ ነው፡፡
በውይይት ላይ ባለው ይህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረበው የሥነ ልቦና ጦርነቶችን የመመከት ሒደት በበላይነት የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት ያለ ግልጽ ማብራሪያ የተቀመጠና ለትርጉም የተጋለጠ ነው፡፡
‹‹የሥነ ልቦና ጦርነት›› የሚለው ሐረግ ጥሬ ቃል ትርጉም በዘርፉ ምሁራን ሲተነተን በኤሌክትሮኒክና ኅትመቶች አማካይነት የቴክኖሎጂ ዕድገቶችን መሠረት አድርገው የሚሠራጩ መረጃዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ የሥነ ልቦና ጦርነት ለዘመናት ዓለም ላይ በተካሄዱ የጦር ሜዳ ውጊያዎች ላይ እንደ አንድ የጦር መሣሪያ ውሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከተሰየመው ሕወሓት ጋር ሲያካሂደው በነበረው ጦረነትና አሁንም በቀጠለው የፕሮፓጋንዳ ሥርጭት አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ለጦርነቱ ያበረከቱት አሉታዊ ሚናና፣ ኢትዮጵያን ከምዕራባውያኑ ኃያላን አገሮች ጋር ለገባችበት ዕሰጣ ገባ እንደ ዋነኛ ምክንያት በመንግሥት በኩል ሲነሳ ይስተዋላል፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ተዘጋጅቶ ፓርላማው እንዲያፀድቀው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ በአገር ላይ የሚቃጡ የሥነ ልቦና ጦርነቶችን የመመከት ሒደት በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት መስጠት፣ ተቋሙ በሚዲያ ተቋማት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው የተቆጣጣሪነትና የመረጃ ነፃነት ላይ ሊያስከትለው ስለሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ሥጋት እንዳላቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሚዲያ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደ አዲስ የገባውና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ የተሰጠውን ተቋም የማደራጃት ኃላፊነት፣ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 11 ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥልጣንና ተግባሩን ለመወጣት የሚያስችሉትን ድርጅቶች የማቋቋምና የመቆጣጠር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመረጃና የደኅንነት ትንተና ውጤቶች የፍሰትና የሥርጭት ሥርዓት የማደራጀትና በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ይሰጠዋል፡፡
በተመሳሳይ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 18 ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋምን በበላይነት የሚመሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተር እንደሚሾሙለት በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ ረቂቅ ውስጥ ማንኛውም የአገልግሎቱ ሠራተኛ፣ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ደርጅት አባል መሆን፣ ወይም በቅስቀሳ ወይም መሰል ድርጊቶች ላይ መሳተፍ እንደማይችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡት ኃላፊዎች በሚመሩት ተቋም የሠራተኞች ከፖለቲካ ነፃ መሆን የአገልግሎቱ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው የሚያነሱም አልጠፉም፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደ አዲስ የገባው ሌላኛው ክፍል የአገልግሎቱ ሠራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በሥራው አጋጣሚ ወይም በሥራ ሥምሪቱ ያወቃቸውንና ያገኛቸውን ማናቸውም መረጃዎች፣ ሰነዶች ወይም ሪከርድ የተደረገ መረጃን ወይም የመረጃ ምንጭ ያለ አገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዕውቅና መግለጽ አግባብነት ባላቸው ሕጎች የሚያስጠይቅ መሆኑ ነው፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ሚስጢራዊነትን ተገን በማድረግ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ይፋ ሊሆኑ የሚገባቸው መረጃዎች አለመገለጻቸው የተቋሙን የግልፀኝነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ቢገለጽም፣ ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የአገልግሎቱ ሠራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በሥራው አጋጣሚ ወይም በሥራ ሥምሪቱ ያወቃቸውንና ያገናኛቸውን ማናቸውም መረጃዎች፣ ሰነዶች ወይም ሪከርድ የተደረገ መረጃን ወይም የመረጃ ምንጭ ያለ አገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዕውቅና መግለጽ አግባብነት ባላቸው ሕጎች የሚያስጠይቅ መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል፡፡
ሌላኛውና በረቂቁ አንቀጽ 27 ላይ በአስገዳጅት የመጣው ሐሳብ ማንኛውም ሰው ከአገልግሎቱ የተሰተጠውን መረጃ መጠቀምና ሥራ ላይ ማዋል አለበት የሚለው ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባላያሙያዎች እንደሚሉት ከዚህ አንቀጽ መረዳት የሚቻለው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከአገልግሎቱ የተሰጣቸውን መረጃ አየር ላይ የማዋል ግዴታ እንደሚጥል ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መመህር የሆኑት ስሜነህ ኪሮስ (ዶ/ር) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አዋጅ በ2005 ዓ.ም. ሲቋቋም ከባህሪው አኳያ ተቋሙ ትንሽ ለየት ያለ አደረጃጀት ያለው በመሆኑ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነበር፣ በተለይም ኢሕአዴግ የነበረውን የመንግሥትነት ባህሪ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ አግራሞት ባይፈጥርም፣ አሁን ላይ በተለይም መንግሥት ለውጥ እያካሄደ መሆኑን በሚናገርበት ጊዜ ይህን የማቋቋሚያ አዋጅ አሻሽላለሁ ብሎ ሲነሳ፣ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ማብራሪያ ነው ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ማብራሪያ ነው ብሎ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ የሚያሳየው አጠቃላይ የአገሪቱን የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ያለበትን መሠረታዊ ድክመት ተከትሎ የተዘጋጀ መሆኑንና ችግሩ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አዋጆች ላይ ማሻሻያም ሆነ ለውጥ እንዲደረግ ጥያቄ ሲቀርብ ተገቢ የሆነ ጥናት ተካሂዶበት እንደማይሻሻል ማሳያ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በረቀቅ አዋጁ ‹‹በአገር ላይ የሚቃጡ የሥነ ልቦና ጦርነቶች የመመከት ሚና በበላይነት መምራት›› በሚል በአዲስ የተጨመረው ንዑስ አንቀጽ ትርጉም በግልጽ እንዳልተብራራ የገለጹት የሕግ ምሁሩ፣ ይህ የሥነ ልቦና ጦርነት ምንድነው ሲባል ዋነኛ ጉዳዩ ወሬ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን ይህ የደኅንነት ተቋም የተሰጠው ሥልጣን በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ለሚከሰቱ ሥጋቶች በመሆኑና የሥነ ልቦና ጦርነት ሲባል ወሬ ነው ከተባለ ይህ ወሬ ደግም በአገር ውስጥ ባሉ ማኅበራዊ ሚዲያና መደበኛ ሚዲያ ተቋማት ወይም በግለሰቦች ሊሠራጭ የሚችል ጉዳይ ስለመሆኑ ስሜነህ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በዚህ ትርጓሜ ለዚህ ተቋም አገር ላይ የሚቃጡ የሥነ ልቦና ጦርነቶች የመመከት ኃላፊነት ከተሰጠው፣ የእነዚህ የሥነ ልቦና ጦርነቶች ከውስጥም ሆነ ከውጭ በወሬ በመረጃ መልክ ሲሰነዘሩ ለመመከት የተሰጠው ኃላፊነት ነው ማለት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 ላይ የብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎችና ሥጋቶች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር በሚል የተቀመጠውን ሐሳብ አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ተቋሙ እዚህ ላይ በምን መልኩ ነው ግንዛቤ የሚፈጥረው የሚለውን ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሚዲያ መጠቀሙ አይቀርም፤ ነገር ግን ምን ዓይነት መረጃዎችን ነው ግንዛቤ የሚያስጨብጠው ለሚለው፣ ምናልባት ለወደፊት የሚታይ ቢሆንም እስካሁን የነበረው የመንግሥት እንቅስቃሴ ግን አስደሳች እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በረቂቁ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ማንኛውም ሰው ከአገልግሎቱ የተሰጠውን መረጃ መጠቀምና ሥራ ላይ ማዋል አለበት በሚል የቀረበው አንቀጽ ተቋሙ መረጃ ይሰበስባል ከዚያ ይሄንኑን መረጃ ተጠቀሙበት ብሎ ለፈለገው አካል ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ዋነኛ የተቋሙ ዓላማ መረጃዎችን ተንትኖ ሥጋቶችን ለይቶ ዕርምጃ መውሰድ ለሚችል ተቋም መስጠት ነበር፡፡ አሁን ግን የመጣው አንቀጽ መረጃን ለማንኛውም ሰው ይሰጣል ያ ሰው ይህን መረጃ የመጠቀም ግዴታ ያስቀምጥበታል፡፡
ለምሳሌ ባንኮች ወይም የሚዲያ ተቋማት ይኼ መረጃ አለና በዚህ ዓይነት መልኩ ሥሩ ወይም አስተላልፉ ሊል ይችላል፡፡ አሠራሩ ምን ዓይነት ይሆናል የሚለውን ወደፊት የምናየው ሆኖ ከላይ ከተገለጸው አንቀጽ 7 ጋር ስናስተያየው በተለይም ግንዛቤ ለመፍጠር ይሠራል ከተባለ ለሚዲያዎች ይህንን መረጃ አሠራጩ ብሎ መስጠት ይችላል ማለት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ያንን መረጃ ያላሠራጨ ደግሞ የሚከተለው ቅጣት ሊኖር እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ አንቀጽ 7 እና አንቀጽ 21 ላይ የተቀመጡትን ሐሳቦች ስመለከት የሚመጣልኝ ሐሳብ የመናገር ነፃነትና የሚዲያ ነፃነትን የሚመለከት ጉዳይ ነው ያሉት የሕግ ምሁሩ፣ በዚህ አካሄድ ሁኔታው አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን ቆርሶ ተቋም ሲያደራጅ አንድ ተቋም መሰጠት ያለበት ተመጣጣኝ የሆነ ሥልጣን በመሆኑ፣ የዚህ ተመጣጣኝ ሥልጣን መመዘኛዎቹ ደግሞ አዋጁ ላይ የተቀመጡት ኃላፊነትና ተግባራት በመሆናቸው፣ የረቂቅ አዋጁን ውይይት በአንክሮ ሊሄዱበት እንደሚገባ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመሆኑም ይህ ለተቋሙ የሚሰጠው ሥልጣን በዜጎች መብት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖና ተቋሙ በሚሠራው ሥራ የሚያመጣው ደኅንነት ተመጣጣኝ መሆኑን ፓርላማው በረቂቁ ላይ በሚወያይበት ጊዜ አመዛዝኖ ይወስናል ብዬ አስባለሁ ብለዋል፡፡
ሌላው ጉዳይ አደረጃጀትን በተመለከተ ለውጥ እየተካሄደ ከሆነ ይህ ተቋም ተጠሪነቱ መሆን የነበረበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆን አልነበረበትም ያሉት ስሜነህ (ዶ.ር)፣ ለዚህ ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ ተቋሙ የተሰጠው ሥልጣን ሰፊ እና የሚሠራቸው ሥራዎች ብዙ በመሆናቸው የተጠያቂነት ሥርዓቱን ለማጠናከር ለፓርላማው ተጠሪ በማድረግ ነገር ግን በተዋረድ ሪፖርት አቀራረቡ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊደረግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ደኅንነትን በተመለከተ አቅጣጫም ሆነ ፖሊሲ የሚወጣው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም በአስፈጻማው አካል ቁንጮ በመሆኑ ሪፖርት አቀራረቡንና ተጠሪነቱን በዚህ መልኩ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በ2005 ዓ.ም. አዋጁ ሲወጣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ መሆኑን እንረዳለን፤ ነገር ግን አሁን ለውጥ እየተደረገ ነው ከተባለ ደግሞ ወደ ዚህኛው የተሻለ መንገድ መምጣት እንደሚገባ የሕግ ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 ላይ አገልግሎቱ ሥልጣንና ተግባሩን ለመወጣት የሚያስችሉትን ‹‹ድርጅቶች የማቋቋምና የመቆጣጠር›› በሚል የተጨመረው ንዑስ አንቀጽን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ይህ የደኅንነት ተቋም ራሱ ድርጅት ሆኖ ሳለ ሌላ ድርጅት ማቋቋም ሲባል የሚቋቋመው ድርጅት የሕግ ሰውነት ምን ይመስላል? እንዴት ዓይነት ተጠያቂነት ይከተለዋል የሚለው ነገር ትንሽ አሳሳቢ እንደሚሆንም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በዋኝነት ይህ የደኅንነት ተቋም የሥራው ባህሪ ሀኖ የሚሠራው ሥራ በዜጎች መሠረታዊ መብት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስለሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሪፎርም ከተባለ ይህ ተቋም እስካሁን በነበረበት ዘመን የዜጎችን መብት የሚያከብር ስለነበር፣ አሁን የሚደረጉ ለውጦች የዜጎችን መብት ማክበር ላይ የተመሠረቱ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ዓምደ ገብርኤል አድማሱ የተባሉ ምሁር ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ማሻሻል የተፈለገበት ምክንያት፣ የብሔራዊ ‹መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ተቋም ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበትና የመጃ ማፈትለክ እያጋጠሙት መሆኑን በተለይም ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ተቋሙን በጠንካራ አቋም ላይ እንዲቆም ማድረግ እንዳልተቻለና ብዙ ክፍተቶች እንዳለበት መግቢያው ላይ ያለው መንደርደሪያ ያመለክታል ብለዋል፡፡
አቶ አምደ ገብርኤል የሥነ ልቦና ጦርነት መመከትና በበላይነት የመምራት ሲባል፣ ሥነ ልቦና የሚለው ቃል ትርጉም በግልጽ ትርጓሜ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በተለይም የሥነ ልቦና ጦርነትን በበላይነት መምራት ሲባል የሚዲያ ሆነ ሌሎች ተቋማትን ሊመራ የሚችልበት የሕግ አግባብ አይኖረውም ብለዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚዲያ ተቋማት በሚዲያ ሕጉ ይመራሉ እንጂ በዚህኛው ሕግ ሊመራ አይችልም፡፡ ምናልባት እንኳ የዚህ ዓይነት ሚዲያን በበላይነት የመምራት ዝንባሌ ቢከሰት እንኳ፣ የሚዲያ ተቋማት ሊያቀርቡት የሚገባው ምክንያት የምንመራው በሚዲያ ሕጉ ነው የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ የደኅንነትን ተቋም የሚያስተዳድር አዋጅ የሚዲያ ተቋምን ሊያስተዳድር ስለማይችል እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 21 ላይ ማንኛውም ሰው ከአገልግሎቱ የተሰጠውን መረጃ መጠቀምና ሥራ ላይ ማዋል አለበት በሚል ተሻሽሎ የቀረበው አዲስ አንቀጽ ‹‹ማንኛውም›› ማለት የተቋሙን ሠራተኞች እንጂ ሁሉንም ዜጋ በዚህ መልኩ ሊያስገድድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ኢ-ሕገመንግሥታዊ ስለሚሆን ብለዋል፡፡
ከለውጥ በፊት የነበረው የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም የዜጎች ሰብዓዊ መብትን ሲጥስ መቆየቱን፣ ነገር ግን ለአገሪቱ ሥጋት የሆኑ በፍጥነት ማግኘት ይችል እንደበርና ለሕዝብ ያደርስ የነበረ መሆኑን የገለጹት አቶ አምደገብርዔል፣ ከለውጥ በኋላ ይህ ተቋም ምናልባት በመገንባት ሒደት ላይ ስለነበር ጠንካራ ሥራ ሠርቷል ለማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡