Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትስዊች በዘጠኝ ወራት በኤትኤም ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ አንቀሳቀሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

R2304 Business

Keywords፡- ቢዝነስ፣፣ ፖዝ ማሽን

Beza

 

በዳዊት ታዬ

የሁሉንም ባንኮች ኤትኤሞች በማስተሳሰር በአንድ ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤትኤሞች መጠቀም በሚያስችለው አሠራር ተጠቃሚዎች ቁጥር፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንና በዘጠኝ ወራት ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳስ መቻሉ ተጠቆመ፡፡

ይህንን አገልግሎት በማዕከል የሚያሳልጠው ኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር በ2014 የሒሳብ ዓመት ዘጠኝ ወሮች ብቻ በኤትኤም የተንቀሳቀሰው ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡

የኢትስዊች የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም እንደሚያመለክተው፣ የአንዱ ባንክ ደንበኛ በሌላኛው ባንክ የኤትኤም ማሽኖችን በመጠቀም ከ27.7 ሚሊዮን በላይ ግብይት ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡

በ2013 የሒሳብ ዓመት ደንበኛ ከሆኑበት ባንክ ውጭ ባሉ ኤትኤሞች የተደረገው ግብይት 16.3 ሚሊዮን ሲሆን፣ ማንቀሳቀስ የተቻለው የገንዘብ መጠን 18.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡ ይህም በሁለቱ ዓመታት በተመሳሳይ ወቅቶች የተፈጸመው የግብይት መጠን ከአሥራ አንድ ሚሊዮን በላይ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ደግሞ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አሳይቷል፡፡

በዘንድሮው የኢትስዊች አፈጻጸም ከኤትኤሙ በላይ የክፍያ መፈጸሚያ መሣሪያ (ፖዝ) ተጠቅመው ግብይት የፈጸሙ ተጠቃሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምሩ መቻላቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡

አኃዛዊ መረጃው ደንበኛ ባልሆኑበት ባንክ የግብይት መፈጸሚያ መሣሪያ (ፖዝ) በመጠቀም የተፈጸመው የግብይት መጠን 829 ሺሕ 662 ሲሆን በዚህ የግብይት መንቀሳቀስ የቻለው የገንዘብ መጠን ደግሞ 7.6 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

ዓምና በመሳሳይ ወቅት በፖዝ የተፈጸመው የግብይት መጠን 6,403 ብቻ እንደነበር የሚያመለክተው ይኸው መረጃ በወቅቱም በዚህ ግብይት ተንቀሳቅሶ የነበረው የገንዘብ መጠን 67.6 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በዘንድሮው ግን በዘጠኝ ወራት ከ7.6 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የተንቀሳቀሰ መሆኑ ዕድገቱ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡

ኢትስዊች በሚያሳልጠው በሌላ አገልግሎቱም በተመሳሳይ ለውጥ የታየበት ውጤት መመዝገቡ ታውቋል፡፡ ይህም የአንድ ባንክ ደንበኛ በሌላው ባንክ የሞባይል ባንክ መተግበሪያ በመጠቀም ከባንክ ወደ ባንክ ከ553.3 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዘዋወር የተቻለ ሲሆን፣ ይህ የገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ403 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ በዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት ያሳየው የባንክ ደንበኞች በዚህ አገልግሎት የመጠቀም ልምዳቸው እያደገ በመምጣቱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በኢትስዊች በኩል ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በካርድ ባንኪንግና በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች የሚጠቀሙ የባንክ ደንበኞች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡

በዚህ አገልግሎት ዕድገት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደገለጹት ለዕድገቱ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቅሱት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በሰፊው መሠራታቸውና በየባንኩ የሚሰጡ የካርድ አገልግሎቶች እየሰፉ መምጣታቸውን ባንኮች በየዓመቱ ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት የኤትኤም ካርዶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም የኤትኤም ማሽኖች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡

በየትኛውም ባንክ ካርድ በየትኛውም ባንክ ኤትኤም መጠቀም ከጊዜ ቁጠባ አንፃር ያላው ጠቀሜታ በተገልጋዮች ዘንድ እየታመነበት መምጣቱም አሁን እየታየ ላለው ለውጥ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች