Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነጋዴዎችና ከ50 በላይ ከንቲባዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ተዘጋጀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከተለያዩ ከተሞች ከ50 በላይ ከንቲባዎችና ነጋዴዎች የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ፣ በመጪው ረቡዕ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ሊካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ለሪፖርተር እንደተናሩት፣ ከዚህ ቀደም የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ የምክክር ኮንፍረንስ ተካሂዶ ያውቃል፡፡ በመጪው ረቡዕ የሚካሄደው መድረክ ለሁለተኛው ጊዜ የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ውቤ እንዳስረዱት፣ የኮንፈረንሱ አጠቃላይ ዓላማ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ግንኙነት በመፍጠር የቢዝነስ ልማትን በየደረጃው የተሻለ ማድረግ ነው፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ ችግር እንደ ከተሞቹ የሚለያይ ቢሆንም፣ በመድረኩ ተሳታፊ የሚሆኑት ከንቲባዎች በከተሞቻቸው ያለውን ችግር በመለየት ስለሚያከናውኗቸው ጉዳዮች እንዲያስቡ ዕድል ያመቻቻል ተብሏል፡፡

ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊው እንደተናገሩት፣ በምክክሩ በጅማ ከተማ ምን ዓይነት የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ግንኙነት አለ? ባህር ዳርም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ላይስ? የሚለውን የከተሞቹ ከንቲባዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ ግንዛቤ የሚያገኙበት ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በምክክር መድረኩ የንግድ ማኅበረሰቡን ሊያግዙ የሚችሉ፣ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማምጣት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫና ምክክር ከማድረግ ባለፈ፣ መንግሥት ያወጣውን የግልና የመንግሥት አጋርነት አዋጅ መሠረት ተደርጎ እንዴት በየደረጃው ቢሠራ ይሻላል የሚለው የሚታይበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከፍተኛ የፓርኪንግ ችግር እንዳለ የተናገሩት አቶ ውቤ፣ የግሉ ዘርፍ በፕሮጀክት ስምምነት እንዴት በዚህ ዘርፍ ሊገባ ይችላል የሚለው ጉዳይ እንደሚነሱ አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በመንግሥት ብቻ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን ከግሉ ዘርፍ ጋር በማጣመር መሥራት እንደሚቻል የገለጹት አቶ ውቤ፣ ይህንን ለማድረግ ይህ ዓይነቱ የውይይት መድረክ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በመጪው ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ይከፈታል ተብሏል፡፡

 ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ኢግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትና በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ምርቶችና አገልግሎቶቻቸውን የሚያቀርቡበትና የአቻ ለአቻ የንግድ መድረክና የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡

በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ በኤሊያና ሆቴል በተሰጠ የጋዜጣዊ መግለጫ የተገኙት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የገበያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ዓለማየሁ፣ ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ የሚሆኑበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ከውጭ የሚመጡ የንግድ አካላት የሚሳተፉበት ስለሆነ ልምድ ለመለዋወጥና ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ፣ እንዲሁም ከ50 በላይ ከንቲባዎች የሚሳተፉበት የግሉ ዘርፍና ከንቲባዎች ምክክር የሚካሄዱበት መድረክ ይሆናል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች