Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትፕሪሚየር ሊጉ በባህር ዳር ፍጻሜውን ያደርጋል

ፕሪሚየር ሊጉ በባህር ዳር ፍጻሜውን ያደርጋል

ቀን:

አዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት አማካሪ ድርጅት ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

በሐዋሳ ከተማ የውድድር ዓመቱን መርሐ ግብር የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ በባህር ዳር ስታዲየም የሚያከናውነውን መርሐ ግብር ቅዳሜ ይጀምራል፡፡ ለፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚደርስ ሲነገርለት የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን ተከትሎ አማካሪ ድርጅቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑ ታውቋል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ በባህር ዳር ፍጻሜውን ያደርጋል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በውድድር ዓመቱ ሽንፈትን ያላስተናገደው የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ 14 ጊዜ ከፍ በማድረግ ተፎካካሪ ያልተገኘለት አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሊጉ በአክሲዮን ማኅበር ከተደራጀ በኋላ የመጀመሪያውን ዋንጫ ማንሳት ይችል ዘንድ ከወዲሁ ነገሮች የተመቻቹለት ይመስላል፡፡

- Advertisement -

በሊጉ በጠንካራ ተፎካካሪነታቸው የሚታወቁት ያምናው አሸናፊ ፋሲል ከነማን ጨምሮ ኢትዮጵያ ቡናና ሌሎችም ክለቦች፣ ዘንድሮ እያሳዩት ያለው ብቃት ወጥነት የጎደለው መሆኑ ዋንጫውን ከወዲሁ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አሳልፈው ለመስጠታቸው ማሳያ ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አልጠፉም፡፡

የዘጠኝ ሳምንት ጨዋታውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ በድሬዳዋ ስታዲየም ስድስትና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተመሳሳይ የስድስት ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡ ቀሪውን የጨዋታ መርሐ ግብር ደግሞ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ከቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚያከናውን ሊጉን በባለቤትነት የሚያወዳድረው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስታውቋል፡፡

የዘንድሮ ውድድር ክለቦች የተጨዋቾችን ወርኃዊ ክፍያ ባለመክፈል፣ እንዲሁም ከውጤት ጋር በተገናኘ አሠልጣኝ በማሰናበትና በመቅጠር ብዙውን ጊዜያቸውን ያሳለፉበት ዓመት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ብዙዎቹ ክለቦች አሠልጣኝ ባሰናበቱ ማግሥት ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴና ውጤት ሲያስመዘግቡ የታዩ ክለቦችም ነበሩ፡፡

የቡድኑን ዋና አሠልጣኝ ካሰናበተ በኋላ

ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ክብረ ወሰኑን እንዳስቀጠለ የሚገኘው የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ 47 ነጥብ ሲያስመዘግብ፣ ፋሲል ከተማ በ37 ነጥብ ይከተለዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ፋሲል ከተማም ከውጤት ጋር በተገናኘ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደን ማሰናበቱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ዋና አሠልጣኙን በከባድ ማስጠንቀቂያ ያስቀጠለው ሲዳማ ቡና፣ ወላይታ ድቻና ሐዋሳ ከተማ በጎል ልዩነት ተበላልጠው በ34 ነጥብ ሦስተኛ፣ አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ፣ ሀድያ ሆሳዕና በ29 ነጥብ፣ ወልቂጤ ከተማ በ28 ነጥብ ስድስተኛና ሰባተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት ከመሆኑ ባሻገር ኳስ ተቆጣጥሮ እንደሚጫወት የሚነገርለት ኢትዮጵያ ቡና፣ በውድድር ዓመቱ ውጤት ካልቀናቸው ክለቦች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ይሁንና ለቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጊዜ በመስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ ከተማና አርባ ምንጭ ከተማ 26 ነጥብ ይዘው በጎል ክፍያ ተበላልጠው በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ስምተኛ፣ ዘጠነኛና አሥረኛ ተቀምጠው ይከታተላሉ፡፡

‹‹የጣና ሞገድ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ባህር ዳር ከተማ፣ ውጤት ከራቃቸው ክለቦች አንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እንደ ሲዳማ ቡናው ገብረ መድኅን ኃይሌ ሁሉ ተመሳሳይ ዕጣ የተሰጣቸው መሆኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ባህር ዳር ከተማ በ25 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በቅርቡ የቀድሞ መጠሪያው ‹‹መቻል›› ተብሎ እንደሚቀጥል የሚጠበቀው መከላከያና የዋና አሠልጣኝ ለውጥ ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ፣ በተመሳሳይ 21 ነጥብ ይዞ በወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገው አሠልጣኝ ኡስማኤል አቡበክርን አሰናብቶ በአዲስ አሠልጣኝ ቢቀጥልም፣ በውጤት ደረጃ ግን ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡

ጅማ አባ ጅፋርና ሰበታ ከተማ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉ የአሠልጣኝ ለውጥ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይሁንና ሁለቱም ክለቦች ምንም ዓይነት የደረጃ ለውጥ ሳያደርጉ በ16 እና በ13 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ግርጌ ላይ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ውጤታቸውን ተከትሎ ዋና አሠልጣኞቻቸውን ከማሰናበታቸው ባሻገር፣ የተጨዋቾቻውን ወርኃዊ ክፍያ ባለመክፈል ወቀሳ ከሚቀርብባቸው መካከል ቀዳሚዎቹ ስለመሆናቸው ጭምር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ ፕሪሚየር ሊጉ ከሚቀረው ጨዋታና ቡድኖቹ ካላቸው የነጥብ ተቀራራቢነት አኳያ፣ ሒሳቡ ሲሰላ ብዙዎቹ ከወራጅ ቀጣና ሥጋት ውጪ አይደሉም፡፡

በሌላ በኩል በዕድሳት ላይ የሚገኘውና ለፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚደርስ ሲነገርለት የቆየው፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ጉዳይ በመጓተቱ አሁንም በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የግንባታው አማካሪ ድርጅት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከግንባታ ጥራትና ስታንዳርድ ጋር ተያይዞ ዕገዳ ከጣለባቸው ስታድየሞች መካከል የአዲስ አበባ ስታዲየም አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዕገዳውን ተከትሎ በወቅቱ በስፖርት ኮሚሽን አማካይነት ስታዲየሙ ዕድሳት እንዲደረግለት በተደረሰው ውሳኔ መሠረት፣ ዕድሳቱን ከሚያከናውነው ተቋራጨ ጋር ውል ተገብቶ ዕድሳቱ መጀመሩም አይዘነጋም፡፡ ዕድሳቱ በዚህ ዓመት ተጠናቆ የፕሪሚየር ሊጉን የመጨረሻ ውድድር የሚያስተናግድ እንደሚሆን ጭምር ተነግሮ ነበር፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ግንባታውን እየተከታተለ የሚገኘው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ሚያዝያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ለግንባታው አማካሪ ድርጅት ማለትም ‹‹ዮሐንስ ዓባይ አማካሪ ድርጅት›› የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ምክንያቱን አስመልክቶ ሲያብራራ፣ ድርጅቱ እንደ አማካሪነቱ መሥራት ያለበትን ቀድሞ ባለመሥራቱ፣ ግንባታውን የሚከታተሉ ባለሙያዎችን ባለመመደቡ፣ የተመደቡም ቢሆን ቦታው ላይ የማይገኙ ከመሆኑ ባሻገር፣ የፕሮጀክቱ አንገብጋቢነት በተደጋጋሚ እየተነገረው በተቃራኒው ሥራዎችን በማጓተትና በጊዜ እንዳይጠናቀቁ በማድረግ ችግር በመፍጠሩ ነው ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...