Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሰውነት ክቡር ማንነት

ሰውነት ክቡር ማንነት

ቀን:

በፍሬሰላም አባተ

በአገራችን የተለመደ አባባል አለ፡፡ ሰው በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው የሚል፡፡ ለዚህ መነሻ ሊሆን የሚችል የተለያዩ የሃይማኖት አስተምህሮዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ለዚህ ጽሑፍ እንደ ዋና መነሻ በምንጠቀምበት በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ይህንን ሐሳብ በሚገባ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡

የምንኖርበትን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር የመምጣት ሒደት በሚተርከው ኦሪት ዘፍጥረት በተባለው የመጽሐፉ የመጀመርያ ክፍል ላይ፣ እግዚአብሔር ሰውን ለመፍጠሩ የወሰነበትን ሁኔታ ያስቀምጥልናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፣ የባህር ዓሳዎችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዙ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው›› ዘፍ 1፡2627፡፡

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሰው ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ተለይቶ በፈጣሪ የልብ ትኩረት ይልቁንም ሴትም ሆነ ወንድ ሳይለይ በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረ ታላቅ ፍጥረት ነው፡፡ ይህም ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የከበረ ዋጋ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ይህ ዕሳቤ ነው እንግዲህ ለሰብዓዊ መብትና ሥነ ምግባር ዕሳቤዎች መሠረት ሆኖ በብዛት ጥቅም ላይ ሲውል የሚገኘው፡፡

እኛ የሰው ልጆች በፈጣሪ ሐምሳል የተፈጠርን ታላቅ ፍጥረቶች ነን፡፡ የክብራችን፣ የልዕልናችንና ዋጋችንም ከዚህ ተፈጥሯችን የሚመነጭ ነው፡፡ ሰውነታችን እነዚህ መሠረታዊ መገለጫዎቻችንም ላይለያዩ የሚተሳሰሩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡

እነዚህ መሠረታዊ የሰውነት መገለጫዎች የሚመነጩት መብቶቻችንም እንደ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን ስለሚቀበል ወይም ስለማይቀበል፣ ነጭ ወይም ጥቁር ስለሆንን፣ ከአሜሪካ ወይም ከኢትዮጵያ ስለሆንን የምናገኛቸው ወይም የምናጣቸው ሳይሆን፣ በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠርን ክቡር ፍጥረት በመሆናችን የተቀበልነው ክቡር ማንነት ነው፡፡

ይሁንና በታሪክ አጋጣሚ ይህ መሠረታዊ እውነት ሁልጊዜ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አናገኘውም፡፡ የዓለምን ታሪክ ስናጠና በተለያዩ የታሪክ አንጓዎች የተለያዩ ባህሎች የሰውነት መብት (ሰብዓዊ መብት) ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የሚገባ አድርገው ሲያስተምሩና ሲኖሩት ቆይተዋል፡፡ ሰብዓዊ መብት የቆዳ ቀለማቸው ነጭ ለሆነ ብቻ፣ ለመሬት ከበርቴዎች ብቻ፣ ለወንዶች ብቻ፣ ወዘተ.፡፡ ለምሳሌ የዴሞክራሲ መነሻ በምትባለው ጥንታዊቷ ግሪክ የሰውነት መብቶች ለሴቶችና ለሕፃናት የተነፈጉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ሴቶችና ሕፃናት በሕዝብ ቆጠራ እንኳን የማይቆጠሩ በመሠረታዊነት ከንብረት የተለየ ዋጋ የማይሰጣቸው ነበሩ፡፡

አንዳንድ የዘርፉ አጥኚዎች እንደሚያነሱት አብዛኞቹ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሐሳቦችን ከክርስትና አስተምህሮ በተለይም ከታላቁ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) አስተምህሮ መሠረት ያደረጉ ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠረው የሚለው ሐሳብ ፀረ ባሪያ አሳዳሪ (አቦሊሽኒስት) ተከራካሪዎች የባሪያ ፍንገላ ሥርዓትን ለማስቀረት ተጠቅመውበታል፡፡ ሴቶች በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል የሚለው ሐሳብ የሴቶች መብት ተሟጓቾች ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ፣ የሴቶች የመምረጥ መብትን የመሳሰሉ የፆታ ክርክሮቻቸውን ለማስረዳት እንደ ዋነኛ መሣሪያ ተጠቅመውበታል፡፡

ሕፃናት በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል የሚለው ዕሳቤም እንዲሁ የሕፃናት መብት ተሟጓቾችን በተለይም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተሟጓቾች ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ ይልቁንም ለፀረ ውርጃ ተከራካሪዎች (ፕሮ ላይፍ አድቮኬት) ደግሞ ይህ መብት እስከ ማህፀን የሚዘልቅ ሲሆን፣ ማንኛውም ፅንስ የሰው ልጅ ነው፣ የሰው ልጅ ደግሞ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ በሕይወት የመኖር መብትና ነፃነት አለው ለሚለው ክርክራቸው እንደ ዋና እርሾ ተጠቅመውበታል፡፡

ፍትሕ ለሁሉም

ሁሉም ሰው በማይገሰስና የማይነፈግ የሰውነት መብት አለው ካልን፣ እነዚህን መብቶች ደግሞ በሕግ መጠበቅ ያለባቸው መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ይሁንና የዓለም ታሪክ የሚያሳየን በተለያዩ ጊዜያት ሕጎች የሰዎችን መብት ማስጠበቅ ሲገባቸው ሲነፍጉ፣ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ሊጠብቁት የሚገባውን መብት ችላ ሲሉ በተቃራኒው ለሌሎች መጠቀሚያ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

ታዋቂው አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች ማርቲ ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የመናገር ነፃነቱን ተጠቅሞ ስለተጨቆኑት ኅብረተሰብ ክፍሎች መብት በመናገሩ፣ አላባማ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ታስሮ ነበር፡፡ ኪንግ እስራቱ ያላግባብ  መሆኑን ቢረዳም እስሬ ያላግባብ ነው ልፈታ ይገባል የሚለውን ትግሉን ያቀረበው በሺዎች ለሚቆጠሩ የእሱ ተከታይ ደጋፊዎች ሳይሆን፣ ብዙዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መብታቸውን ጠይቀው የተነፈጉበትን ሕግ ነው፡፡ በወቅቱ ኪንግ እንዲህ ብሎ ጥፎ ነበር፡፡ ‹‹አንድ ሰው ሕጉ ፍትሐዊ ወይም ኢፍትሐዊ መሆኑን እንዴት መለየት ይችላል?›› ብሎ ይጠይቅና፣ ‹‹ፍትሐዊ ሕግ ሰው ሠራሽ ሕግ ሆኖ ከሞራል ሕጎች ወይም ከፈጣሪ ሕጎች ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡ ኢፍትሐዊ ሕጎች ደግሞ ከተፈጥሮ ወይም ከፈጣሪ ሕጎች ጋር የማይጣጣሙ የሰው ሕጎች ናቸው፤›› ይልና፣ ‹‹ማንኛውም የሰውን የተፈጥሮ ልዕልና የሚያጎላ ሕግ ፍትሐዊ ሕግ ነው በተቃራኒው የሰውን የተፈጥሮ ልዕልና ዝቅ የሚያደርግና የሚያዋርድ ሕግ ኢፍትሐዊ ሕግ ነው፤›› ይላል፡፡ ስለሆነም ጭቆና የሰውን ልጅ ነፍስ ሊቀበለው በማይችልና ከሰው ነፃ ተፈጥሮ ተቃራኒ የሆነ ተግባር በመሆኑ ኢፍትሐዊ ነው በማለት ክርክሩን አቅርቧል፡፡ እዚህ ላይ ታዋቂ የመብት ተሟጋችና የሃይማኖት መሪ የሆነው ኪንግ በእሱ ዘመን የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተጋፈጠው በጊዜው በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት (ኮመን ኮንሰንሰስ) ኖሮ ሳይሆን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተንፀባረቀው የእግዚአብሔር ባህሪና ስላለው ተፈጥሮ በተጻፈው እውነት ላይ መሠረቱን አድርጎ ነው፡፡

አንዳንድ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተቀመጡ መርሆዎች ጋር እያነፃፀርን ብንመለከታቸው፣ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀጽ አራት ማንኛውም ሰው ቀለምን፣ ዘርን፣ ፆታንና የመሳሰሉ ነጥቦችን ከግምት ሳያስገባ እኩል ነው በማለት የሚደነግግ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በአንቀጽ ሁለት በዚህ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ሁሉም መብቶች ያለ ምንም ልዩነት ለሁሉም ሰው የተሰጡ መሆናቸውን ያሳያል፡፡

ይህንኑ ሐሳብ ታላቁ መጽሐፍ በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ በግልጽ ያስቀመጣቸው ሲሆን፣ በገላትያ 3፡28 ላይ ‹‹አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፣ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡ በተመሳሳይ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ምዕራፍ 3፡11 ላይ የግሪክ ሰው፣ የአይሁዳዊ፣ የተገረዘ፣ ያልተገረዘም፣ አረማዊ፣ እስኩቴስም፣ ባሪያም፣ ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፣ በሁሉ ነው፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡

ይህ የመጽሐፍ ክፍል በተጻፈበት ዘመን በሰዎች መካከል በተለያዩ መነሻዎች ልዩነት ማድረግ የተለመደ ሲሆን፣ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መመልከት እንደሚቻለው አይሁድ በሆኑና ባልሆኑ መካከል፣ በወንዶችና ሴቶች መካከል፣ በተገረዙና ባልተገረዙ መካከል፣ ባርያና ጨዋ በሚል ደረጃዎች የተለያዩ ልዩነቶች ይደረጉ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡

አንድ ብዙዎች የሚያነሱት ቀላል ምሳሌ ለማንሳት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡16-24 ባለው ክፍል ላይ የተጻፈውን ስንመለከት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ዕለት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ሰዓቱ በመምሸቱ፣ እንዲሁም የነበሩበት ቦታ ምድረ በዳ በመሆኑ በዚያ ሥፍራ ትምህርቱን ሲሰማ ለነበረው ሕዝብ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሳ ባርኮ በማቅረብ በሥፍራው የነበረው ሕዝብ ሁሉ ጠግቦ እስኪያስተርፍ ድረስ እንዲበላ ያደረገበትን ተዓምር የሚተርክ ሲሆን፣ በዚህ ምዕራፍ ቁጥር 21 ላይ ቦበታው ተገኝተው ከተዓምራቱ የተሳተፉ ሰዎችን ቁጥር ሲያስቀምጥ፣ ‹‹ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር፤›› ይላል፡፡ እዚህ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚያስቀምጡት በቦታው የነበረው ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው ሥርዓት ሴቶችና ሕፃናት እንደ ሕዝብ ስለማይቆጠሩ የሰው ቁጥር አምስት ሺሕ ብቻ ተደርጎ ተጽፏል፡፡

ይህን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ በተለያዩ ክፍሎች ላይ በሰዎች መካከል በነበረው ሥርዓት ይደረግ ስለነበረው ልዩነት የሚያሳዩ ክፍሎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህንን ሥርዓት ነው እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያና በቆላስያስ መልዕክቱ የክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁሉ፣ በሰው መካከል የሚደረግ ልዩነት በክርስቶስ ቀሪ እንደተደረገ የሚያስተምረን፡፡

እንግዲህ እነዚህና ሌሎች ምሳሌዎችን አንድ በአንድ እያነሳን ስንመለከት፣ በአማኙ ዘንድ ለሰው ተፈጥሮ የሚበጀው የሕይወት ሥርዓትና ሕግ የከተበበት መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን በምድር ላይ ካሉ ነገሮችም ሆነ ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የተለየና የከበረ አድርጎ ፈጣሪ ያበጀው ስለሆነ፣ የላቁትም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚሉት እግዚአብሔር ሊኖሩ የሚገባቸውን ፍጥረታት ሁሉ ሠርቶ ከፈጸመ በኋላ የሰውን ልጅ በመጨረሻ መፍጠሩ በምድር የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ለሰው አገልግሎትና ዓላማ የተፈጠሩ ስለመሆናቸው፣ ነገር ግን የሰው ሥርዓት ቁስ፣ መሬት ወይም ሌላ ግዑዛዊ የሆነ የገንዘብ ዋጋ ያለው ነገር ወይም ክብር የሚሰጠው ምድራዊ ሥርዓት ወይም አሠራር ከክብሩ የሰው ልጅ የላቀ ሥፍራ ተሰጥቶት መታየቱን ይተቻሉ፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር አምለክ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ የወደደው ክብሩ የሰው ልጅ እንደ ተራ ነገር ከግዑዛን ተርታ ዋጋው መቀመጡን አብዝተው ይኮንናሉ፡፡

እዚህ ላይ ቆም እንበልና ወደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ አምስት እንመለስ፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ በግልጥ እንደተቀመጠው በወንጀል ተጠርጣሪው ወይም በሌላ ምክንያት የተያዙ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ የመያዝ መብት እንዳላቸው፣ ይልቁንም ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት ወይም አያያዝ ሊደረግባቸው እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የወጡ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የበላይ ሕግ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተያዙ ሰዎች መብት በሚለው ክፍል ላይ በአንቀጽ 19 የተያዙ ሰዎች የተከሰሱበት ዝርዝር በሕግ ፊት በሚገባቸው ቋንቋ እንዲደርሳቸው በተከሰሱበት ጉዳይ ያለመናገር መብት እንዳላቸው፣ በተገቢው ጊዜ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸው፣ በዋስ የመፈታት፣ በራሳቸው ላይ ያለመመስከር መብት እንዳላቸው በጉልህ ያሳያል፡፡

በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀት 16፣ 17 እና 18 ደግሞ ማንኛውም ሰው የአካል ደኅንነቱ መጠበቅ እንዳለበት፣ በሕግ በተደነገገው አግባብ ካልሆነ በቀር ነፃነቱን ሊያጣ እንደማይገባ፣ እንዲሁም በምንም ምክንያት ኢሰብዓዊ አያያዝ እንዳይፈጸምበት የመጠበቅ መብት እንዳለው ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ዓለም አቀፍና አገራዊ የሕግ ማዕቅፍ እንግዲህ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ፣ በኃጥያቱና በበደሉ ሞት ሲገባው አምላክ የሆነው ክርስቶስ የሞተለትን ክቡሩን የሰው ልጅ ለመጠበቅ የተደነገጉ ናቸው፡፡ 

በዚህች አጭር መጣጥፍ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ሕጎች ተዘርዝረው የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የመዘርዘር ዓላማ የለኝም፡፡ ይልቁንም በክርስትና እምነት አስተምህሮ ዋነኛ መነሻ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ዓይነተኛ ማሳያዎችንና በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ሰነዶች፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጡ ሰብዓዊ መብት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በማነፃፀር ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ተሞክሯል፡፡

የሐሳቡ ዋና ማጠንጠኛም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎች የተዋደቁለት፣ የሞቱለትና አሁንም እየታገልንለት ነው የሚሉት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ መነሻው ፈጣሪ ነው፡፡ ይህም ፈጣሪ የሰው ልጅን በራሱ አምሳል ሠራው ውብና ድንቅ አድርጎ ፈጠረው የሰውን ተክለ ተፈጥሮ በጥልቀት ላጠና ሰው የፈጣሪን ድንቅ ሥራ የሚያይበት መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሰው ልጅ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥለት ድረስ እንዲሁ የወደደ ፍጥረት ነው፡፡ የሰው ልጅ በደም ቤዛ የተገዛ ታላቅ ፍጥረት ነው፡፡ እንግዲህ ፈጣሪ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ እንዲህ ያከበረው ዕፁብ ድንቅ ፍጥረት ነው፡፡

እንግዲህ በዘመናችን (ሥራ በዚህ ወቅት ብቻ ለማለት አይደለም) ከእንስሳት ባልተለየ መንገድ በባርነት ሲሸጥ፣ ሲነገድበት፣ ሲታረድ፣ ሲደፈር፣ ብዙ ቃላት ተዘርዝሮ ሊያልቅ የማይችል ግፎች አንዱ የሰው ልጅ በሌላው ላይ ሲፈትም ይስተዋላል፡፡ የሰው ልጅ ስለገንዘብ፣ ስለቁስ፣ ስለድንበርና መሬት ያለው የገዘፈ ግምት ክብር ለሆነው የሰው ልጅ ከሚሰጠው ትርጉም ጋር በእጅጉ የማይመጣጠን ሲሆን ይታያል፡፡ እነዚህን ግዑዛን አካላት ከሰውነት አግዝፎ የመመልከቱ ጉዳይ እጅግ የተለመደ ሆኗል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ አማኝ በሆነበት አገራችንም በሩቅ የምንሰማቸው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ግፎችና በደሎች ባልተለመደ ሁኔታ ተበራክተው ማስተዋል ከጀመርን ሰነባበትን፡፡ እኛም እንዲህ እንላለን ልደቱ ስለሰው ነው፣ ጥምቀቱም እንደዚያው፣ ስቅለቱም ስለሰው፣ ትንሳዔውም ጭምር፡፡ እርገቱም ለሰው ልጅ ነው፣ ዳግም ምቱም እንደዚያው፡፡ ክርስቶስ ስለፍቅር ወንድማማችነትና ይቅርታ ወደ ምድር መጣ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 18 እንደሚል፣ ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ የሰማዩ አባቴ ያደርግባቸዋል፡፡ ክርስቶስ ስለፍቅር ሞተ ጥላቻን በመስቀሉ ሰቀለ፡፡ ማንም እግዚአብሔርን ወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፡፡ ያየውን ወንድሙን  የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔር እንዴት ሊወድ ይችላል? ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ?

የሕግ ፍልስፍና (Jurisprudence) አጥኚዎች በዚህ ላይ የተለየ ዕሳቤና አረዳድ አላቸው፡፡ በተለይም (Utilitarian) እየተባለ የሚጠራውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን በተለይ ከላይ ካስቀመጥናቸው መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ዕሳቤዎች ጋር የማይጣጣሙ ሐሳቦችን ያነሳሉ፡፡ እንደ እዚህ ምሁራን አተያይ ስለአብዛኛው ማኅበረሰብ ደኅንነትና መልካም ይዞታ ሲባል የጥቂቶችን መብት መንፈግ ተገቢ ነው የሚል አተያይ አላቸው፡፡

ለምሳሌ በሕግ ማንም ሰው በህግ ጥላ ሥር እያለ ከየትኛውም ኢሰብዓዊ አያያዝ (ድብደባ፣ ቶርቸር) የመጠበቅ መብት እንዳለው በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዲሁ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 23 ላይ በሸንጎ በቀረበበት ወቅት፣ ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ወታደሮች ጳውሎስን እንዲመቱት ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስ በምላሹ፣ ‹‹አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፣ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን አለው?›› በማለት ሲመልስ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ ያለ ሕግ የሚደረግን ድብደባ ሲቃወም በግልጽ እንመለከታለን፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ (Utilitarianism) አስተሳሰብ አራማጅ  ሊቃውንት በዚህ ሐሳብ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለመስማማት ይቸገራሉ፡፡ ለዚህም ተደጋግሞ የሚያነሱት አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ፣ በከተማው ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ጅምላ ጨራሽ ቦምቦችን እንዳጠመደ የተጠረጠረ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቢውል፣ ሕጋዊና ቴክኒካዊ በሆነ የምርመራ ዘዴዎች ሁሉ ይህንን ቦታ እንዲጠቁም ጥረት ተደርጎ፣ ግለሰቡ ተሳስታችኋል የማውቀው ነገር የለም በማለት ሸምጥጦ ቢክድ የግለሰቡ ሰብዓዊ መብት እንዳይነካ ከመተው ይልቅ የእሱን መብት በማስጠበቅ ዋጋ የተቀበሩ ቦምቦች ፈንድተው የብዙዎችን ሕይወት ሊያሳጡ ከመቻላቸው አንፃር፣ ስለብዙኃኑ መብት ግለሰብ ቶርቸር ተደርጎም ቢሆን ቦምቦቹ የተጠመዱበት ቦታ ሊያሳይ ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡ መነሻቸውም የአንዱ መብት ከብዙኃኑ መብት ሊበልጥ አይችልም የሚል ነው፡፡

በእኔ አተያይ በሁሉም መንገድ ሳየው ተግባራችንም ሆነ ሕጎቻችን ክቡሩን የሰው ልጅ ማዕከል ያደረጉ ሲሆኑ፤ ከፈጣሪም ሆነ ከተፈጥሮ መዋቅር ተስማምተው መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳለው፣ ‹‹ማንኛውም የሰውን የተፈጥሮ ልዕልና  ከፍ የሚያደርግና የሚያጎላ ሕግ ሁሉ ፍትሐዊ ሕግ ነው በተቃራኒው የሰውን የተፈጥሮ ልዕልና ዝቅ የሚያደርግና የሚያዋርድ ሕግና ተግባር ሁሉ ኢ ፍትሐዊ ነው፤›› ሰውነት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ክብር ማንነት የሰው ልጅ ክቡር ሰው መሆን ክቡር፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...