Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማሸግ እስከ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ መዳኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወደ ውጭ የሚላኩ ቡናና የቅባት እህሎችን በአገር ውስጥ በማሸግ በዓመት እስከ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ ማዳን መቻሉን፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ።

ወደ ውጭ የሚላኩ የቡና፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከዚህ ቀደም በብትን ይላኩ እንደነበርና አሳሽጎ ለመላክ ወጪ ያስፈልግ እንደነበር፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የኩል ቼይን ሎጂስቲክስ አስተባባሪ አቶ ኤርጋና ቡቼ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከዚህ በፊት ላኪዎች ይጠየቁ የነበረውን በኮንቴይነር 112 ዶላር ወጪ በአገር ውስጥ በማሸግ ማስቀረት እንደተቻለ ጠቁመው፣ በዓመት ከሚላከው እስከ 70,000 ኮንቴይነር ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህል ከፈተኛ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

ምርቶቹ ከዚህ በፊት በጂቡቲ በሚታሸጉበት ወቅት በብትን የሚላክ በመሆኑ በመንገድ ላይ ስርቆት ያጋጥም እንደነበር፣ ይህም በሻጮችና በደንበኞቻቸው መካከል አለመተማመንን ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸዋል። በተሽከርካሪ ሲደረግ የነበረው ማጓጓዝም በአገር ውስጥ ሲታሸግ በባቡር እንዲጓጓዝ በመደረጉ እስከ 40 በመቶ ወጪ ይቀንሳል ያሉት አቶ ኤርጋና፣ ጂቡቲ ከደረሱ በኋላም ኮንቴይነር ለማግኘት ለብዙ ቀናት በመጠበቃቸው የሚጠየቁትን ተጨማሪ ክፍያ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

ከቡና ምርት ላኪዎች ውስጥ 98 በመቶ የሚሆኑት በዚሁ መንገድ እየተገለገሉ መሆኑን ገልጸው፣ በሌሎች ምርቶችም ይህ አሠራር ሊሰፋ ይገባል ብለዋል። ጥራጥሬ ወደ ውጭ ከሚልኩ ነጋዴዎች መካከል ደግሞ 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በአገር ውስጥ አሽጎ በመላክ እየተገለገሉ እንደሆነ፣ በቀጣይ ደግሞ ለማሻሻል እየሠሩ መሆናቸውንና ነጋዴዎችም ወደ እዚህ ሥርዓት መግባት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ በአሁኑ ወቅት ቡና በብትን መላክ የቀረ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለቡናው ጥራት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል። በአገር ውስጥ በመታሸጉና በባቡር በመጓጓዙም የደኅንነት ሥጋት እንዳይኖርና ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስም አክለዋል።

የኦሮሚያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ የኋላሸት በበኩላቸው፣ ቡናን በአገር ውስጥ አሽጎ መላክ ጥቅም ቢኖረውም፣ በላኪዎች ፍላጎት ብቻ የሚወሰን አይደለም ብለዋል። ወጪን ከመቆጠብ አንፃርም ሆነ ለሌሎች የጥራት ችግሮች በአገር ውስጥ መታሸጉ የተሻለ ቢሆንም፣ ተቀባዮች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት የት ይታሸግ የሚለው መወሰን እንዳለበት ገልጸዋል። ለዚህም ቡና ላኪዎች፣ የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ሁሉም ባለድርሻዎች በመነጋገር ሊወስኑት እንደሚገባና ካለው ውድድር አኳያ የተቀባዮችን ፍላጎት ያማከለ መሆን አለበት ሲሉ አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች