የአማራ ክልል መንግሥት ‹‹ሕግ ማስከበር›› ባለው ሰሞነኛ ዘመቻ 4,500 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት በሕገወጥነትና በሥርዓተ አልበኝነት በፈረጃቸው ኃይሎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ቀደም ብሎ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ የክልሉ መንግሥት ጠንካራ መግለጫ ደግሞ በክልሉ ሰፊ የእስራት ዘመቻ ሊከሰት እንደሚችል ጠቋሚ ነው ያሉ ወገኖች፣ በራሳቸው መንገድ ሊከተል ይችላል ስላሉት ሁኔታ ለማስተንተን ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን የእስር ዘመቻው ከአራት ሺሕ እንዳለፈ የገለጸው የክልሉ መንግሥትም፣ ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በዕርምጃው እንደሚገፋበት ነው ያስታወቀው፡፡
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ‹‹የሕግ የበላይነት የማስከበር ተግባሩ ዋና ዓላማ ክልሉ ከወንጀለኞች የፀዳ እንዲሆን፣ አንድነቱ የተጠበቀ ሕዝብ እንዲኖርና ሊመጣ ከሚችል የጠላት ጥቃት ራሱን እንዲከላከል ማስቻል ነው፤›› ይላሉ፡፡
ይህን መሰሉ የአማራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስተያየት የማያሳምናቸው ወገኖች ግን በርካታ ናቸው፡፡ አማራ ክልል ከውጭ ከሦስተኛ ወገን ሊቃጣ የሚችል የጥቃት ሥጋት ኖሮበት ሳይሆን፣ ክልሉን የሚመራው አማራ ብልፅግና ፓርቲ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ስም የሚቀናቀኑት ኃይሎችን ለማጥፋት የፈጠረው ሴራ ነው ሲሉ አንዳንዶች ይተቻሉ፡፡ በሌላ በኩልም እንደ ፋኖ ያሉ ኃይሎችን ለማፈራረስና ኃይል ለመበተን የተወጠነ ዘመቻ ነው ብለው ጉዳዩን የሚበይኑት አሉ፡፡
ከዚህ አለፍ ሲልም የሕግ ማስከበሩ ሰሞነኛ ዘመቻ ራሱ የአማራ ክልልን ለማዳከም ታስቦ በፌዴራል መንግሥቱ የተወጠነ ሴራ ነው ሲሉ የሚገምቱ ወገኖችም አሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በአማራ ክልል ላይ ያተኮረውን እንደ ፋኖ ያሉ የታጠቁ ኃይሎችን ለማፈራረስ ያቀደው፣ በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲን የበላይነት ለማጠናከር ነው የሚሉ ሙግቶችም ይሰማሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህንና ሌሎች ግምቶችን በተመለከተ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጡት ምላሽ ፍፁም የተለየ ነው፡፡
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ ያነጣጠረ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡ ዘመቻው በብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት መመርያ መሠረት መጀመሩን ያመለከተው የመከላከያ መግለጫ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ዘመቻው መጀመሩን ነው ያመለከተው፡፡
በኦሮሚያና አጎራባች ክልሎች እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ የሽብር ቡድኖችን የመደምሰስ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ደግሞ እንደ አልሸባብ በመሳሰሉ ኃይሎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ዘመቻው የታጠቁ ኃይሎችን ከማደን በተጨማሪም በሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በገንዘብ ዝውውር፣ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን በማምከንና የሕዝቡን አካባቢያዊ ፀጥታ በማረጋገጥም እየተካሄደ ነው በማለት የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ በሰፊው አትቷል፡፡
ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱም ሆን የክልል መስተዳድሮች የሚያወጧቸው የሕግ ማስከበሩን ዘመቻ የተመለከቱ ተከታታይ መግለጫዎች ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱባቸው ነው፡፡
የሕግ ማስከበር ሥራ መደበኛ የመንግሥት ሥራ እንጂ በዘመቻ የሚረጋገጥ ነገር አይደለም የሚሉ ወገኖች፣ የሰሞኑን ዘመቻ ስኬት ይጠራጠሩታል፡፡ በሌላም በኩል ዘመቻው በግብታዊ ዕርምጃዎች የሚካሄድ ነው በማለት፣ ንፁኃንና በሕግ ጥሰት ውስጥ የሌሉ ወገኖች ተጎጂ እንዳይሆኑ የሚሠጉ ወገኖችም አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዕርምጃው በራሱ ሕግን በማስከበር ስም ለሕገወጥ ዓላማ ሊውል ይችላል በሚል ጥርጣሬ የሚመለከቱት ወገኖችም አሉ፡፡
ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ የሕግ ባለሙያዎችም ቢሆኑ እነዚህን ሥጋቶች የሚያጠናክሩ ሐሳቦችን ያንሸራሸሩ ሲሆን፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በጥንቃቄ መታየትና መያዝ ያለበት ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
የሕግ ባለሙያ አቶ አበባው አበበ በኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ረገድ ፈታኝ የሆነው፣ ‹‹በሕግ የመግዛት ወይስ በሕግ የመገዛት›› (Rule of Law or Rule by Law) ነው ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው ሁለቱ ነገሮች መሠረታዊ የሆነ ሰፊና የማይታረቅ ልዩነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከሆነ ጉዳዩ ሁሉም ሰው በሕግ ጥላ ሥር እኩል ነው ማለት ነው፡፡ ሕጉ ለሁሉም እኩል የሚሠራ ሲሆን፣ ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል አመልካች ነው፡፡ ነገር ግን የሚደረገው በሕግ የመግዛት (Rule by Law) ከሆነ ግን አስፈጻሚ አካላት ወይም መንግሥት ሕግን በመጠቀም የዜጎችን መብቶች ደፍጥጠው የሚገዙበት ሥርዓት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከተፈተሸ በሕግ ስም የመግዛት ሁኔታ ያጋደለበት ነው፤›› ሲሉ አቶ አበባው ሐሳባቸውን ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲጣስ የሚጋብዝ ነው የሚል ሥጋት የሚያነሱ አሉ፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በርካታ ዓለም አቀፍና አገር በቀል የሲቪክ ማኅበራት ይህንኑ ሥጋት ሲያንፀባርቁ ይታያል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ሌሎች ተቋማት በየፊናቸው ዕርምጃው ያመጣል ያሉትን ተፅዕኖ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የሰሞኑን ‹‹በተቀናጀ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር›› ብሎ መንግሥት የጠራውን ዘመቻ በተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፣ ‹‹ይህ ዓይነቱ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢነት የለውም፤›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ልክ እንደ ኢሰመኮ ሁሉ የሰሞኑ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደሚያሠጋው የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተባለው ሲቪክ ማኅበርም ድምፁን ያሰማል፡፡ የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ታዋቂው ጠበቃ አቶ አመሐ መኰንን፣ የአሁኑን የመንግሥት ዕርምጃ ተገቢውን ማጣራትና ሕጋዊ ሒደት የተከተለ መሆኑን እንደሚጠራጠሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹መንግሥት እንደሚለው ተጨባጭ የሕግ ጥሰት ካለ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የአሁኑ በጣም በጥድፊያና በጅምላ ሲካሄድ ነው የምንሰማው፡፡ የታሰሩት ሰዎች ጥፋት ማጥፋታቸው ተለይቶ መያዛቸው፣ በቤተሰብ መጎብኘታቸው፣ ፍርድ ቤት መቅረባቸውም ሆነ ጠበቃ ማግኘታቸው በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ የት እንደታሰሩ፣ የታሰሩበት ሁኔታ፣ ምግብና ውኃ ብቻ ሳይሆን የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ በስህተት የተያዙም ካሉ በአስቸኳይ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሁሉ ኃላፊነት የሚወድቀው ደግሞ በራሱ ሕግ አስከብራለሁ በሚለው በመንግሥት ላይ ነው፤›› ሲሉ ነው አቶ አምሐ የሰሞኑን ዘመቻና የፈጠረውን ሥጋት የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ የሕግ ችግር እንደሌለ ተደጋጋሞ ይነገራል፡፡ አገሪቱ ሕግ በማውጣት ሰንፋ አታውቅም የሚለው ሂስም ጎልቶ ይደመጣል፡፡ አገሪቱ ሕግ በራሷ ከማውጣት በተጨማሪ በርካታ አኅጉራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሕጎችንም የራሷ አድርጋ በመቀበል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ያወጣቻቸው ሕጎች ወይም የፈረመቻቸውና የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፋዊ ሕጎችና መርሆዎች ግን በተጨባጭ ወደ መሬት ወርደው የሚተገበሩበት ዕድል ደካማ ነው እየተባለ ይተቻል፡፡ ይህ ድክመት በተጨባጭ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ፈተና መሆኑን አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው በኢትዮጵያ ሕግ በአግባቡ ወደ መሬት የማይወርድበትን ምክንያት ሲያስረዱ የሚከተለውን ይላሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ሕግ ያጣች አገር ሳትሆን ሕግ ተለይቶ በሆኑ አካላት ላይ የሚፈጸምበት አገር ናት፡፡ አሁን ላይ እነ ማን ናቸው እየታፈኑ ያሉት? እነ ማን ናቸው የሚታሰሩት? ወይም እነ ማን ናቸው የሚታፈሱት? ሲባል የሆኑ አካላት ናቸው፡፡ በዋናነት ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት የተጋፉና የሚቃወሙ ከመሆናቸውም በላይ በዘርና በፖለቲካ ተለይተው ነው፡፡ ሥርዓቱ የሕግ አተገባበሩ አድሏዊ ብቻ ሳይሆን፣ በጅምላ ውንጀላና ሁሉንም ሥልጣን በጠቀለለ አካል የሚፈጸም ነው፡፡ ይህን መሰል የሕግ አተገባበር ደግሞ ዞሮ ዞሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያስከትል ሆኖ ነው የምናገኘው፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አድሏዊ የሕግ አተገባበር አለ የሚል ተቃውሞ የሚያቀርቡ አንዳንድ ወገኖች፣ ፋኖና የኦነግ ሸኔ አያያዝን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ ኦነግ ሸኔ በአገሪቱ ፓርላማ ሳይቀር በአሸባሪነት የተፈረጀ ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት በቡድኑ ላይ የተጠናከረ ዕርምጃ ለመውሰድ ዳተኝነት ይታይበታል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አሁን ያለው መንግሥት በሽምግልናና በዕርቅ ለመፍታት ከኦነግ ሸኔ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎችና ከሕወሓት ኃይሎች ጋር ሲነጋገር ቢታይም የፋኖን ጉዳይ በአገር ወግና ባህል እንኳ ለመፍታት ምንም ጥረት አላደረገም እየተባለም ይወቀሳል፡፡ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው ፋኖ አገርን ከወረራ ለማዳን መታጠቁ እንጂ፣ የአካባቢ ፀጥታን በማደፍረስም ሆነ የነዋሪዎች ሥጋት በመሆን የፈጠረው ችግር አለመኖሩን በመግለጽ የሕግ ማስከበሩ ሰሞነኛ ዕርምጃ አሻሚ ሁኔታ እንደሚታይበት ይናገራሉ፡፡
ይህንን ፈፅሞ የሚቃወመው መንግሥት ግን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ከሕግ ማስከበር ባለፈ ‹‹የአገርን ቀጣይነት የማረጋገጥ ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ብቸኛው መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነው በማለት አስታውቋል፡፡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአማራና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሕግን በተከተለ መንገድ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ይህ የመንግሥት መግለጫ የማያሳምናቸው ግን፣ መንግሥት እንዳለፉት ሥርዓቶች ሁሉ ሕግን ለፖለቲካ መገልገያ መሣሪያ እያዋለ ነው ሲሉ ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡ መንግሥት የሚወስዳቸው የሕግ ማስከበር ዕርምጃዎች በሕግና በአግባቡ መሆናቸው መፈተሽ እንደሚኖርበትም ያሳስባሉ፡፡
በቀደመው የኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት የፖለቲካ እስር ለተፈጸመባቸው በተለይ የሽብር ክስ ለቀረበባቸውና መነጋገሪያ ለሆኑ የሕግ ሙግቶች ጥብቅና ሲቆሙ የቆዩት አቶ አምሐ፣ ተመሳሳይ ዝንባሌ አሁን እየተፈጠረ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ‹‹አሁን አሁን የት እንደሄዱ፣ በማንና ለምን እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ሰዎች ይሰወራሉ፡፡ አንዳንድ ታዋቂ ጋዜጠኞችና ግለሰቦች ታፈኑ ይባላል፡፡ ታዋቂ ስለሆኑና በሚዲያ ስለተነገረ የጥቂቶችን ሰማን እንጂ፣ ብዙ ግለሰቦች ተመሳሳይ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህ ሁኔታ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች እንዲጣስ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ሥርዓት ይታይበት የነበረው ችግር መልሶ እያቆጠቆጠ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበሩም ሆነ በማረሚያ ቤቶች ያለው አያያዝ መፈተሽ እንዳለበት አንዳንድ ሁኔታዎች ይጠቁማሉ፤›› በማለት የተናገሩት አቶ አመሐ የመንግሥት ሕግ ማስከበር ዘመቻ ሊጠየቅ የሚገባው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አቶ አምሐ እሳቸው የሚመሩት ‹የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች› ተቋምም ሆነ በሕግ ዙሪያ የሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራት፣ መንግሥትን የመከታተልና የመጠየቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ ‹‹አንዳንድ ጉዳዮችን አጣርተን ወደ ሕግ ለመውሰድ የሚያስችል ሥራ መሥራት አለብን፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ አምሐ ነገሩ አዲስ ባህል መሆኑንና አቅምና አደረጃጀትን ማጠናከር እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
አቶ አበባው በበኩላቸው፣ ‹‹እያወራን ያለነው ስለሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት ደግሞ ዓለም አቀፍ መግባቢያና ሕግ ያለው ነው፡፡ ስለዚህ በሕግ ማስከበር ሥራ ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሚፈጠሩ የሕግ ጥሰቶች ዞሮ ዞሮ መንግሥት ተጠያቂ ነው፤›› ይላሉ፡፡
የሕግ ባለሙያዎቹ ይህን ቢሉም መንግሥትም ሆነ የመንግሥት አካል በሕግ ጥሰት ተወንጅለው ፍርድ ቤት ሲቀርብ የታየበት ሁኔታ አለመኖሩን ብዙዎች ያወሳሉ፡፡ በሕግ ወይም በመርህ ደረጃ መንግሥት ለሚፈጽማቸው ጥፋቶች ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ቢናገሩም፣ ይህን ሁኔታ በተጨባጭ ገፍቶ መንግሥትን ለጥፋቱ ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት ያደረገ አካል አለመኖሩን ነው የሚገልጹት፡፡