Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ፓርላማው አዘዘ

በአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ፓርላማው አዘዘ

ቀን:

ኮሚሽኑ ከ3.8 ቢሊዮን ብር ሰነድ ለኦዲተር አላቀረበም

ከኦዲት ግኝት ጋር በተያያዘ በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስቴር ቅጣት በተጣለበት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ላይ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ምርመራ አድርጎ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ካሉ ክስ እንዲመሠረት ታዘዘ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳዳርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትዕዛዙን ያስተላለፈው፣ ኮሚሽኑ ከሁለት ዓመታት በፊት በኦዲት የተገኘን በቢሊዮን የሚቆጠር ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ባለመሰብሰቡ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ እንቅስቃሴ ሰነድ ለኦዲት በአስረጂነት ባለማቅረቡና በአጠቃላይ ተቋሙ ‹‹አስከፊ የኦዲት ግኝት›› ስላለበት ነው፡፡

- Advertisement -

ቋሚ ኮሚቴው ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው የ2012 በጀት ዓመት፣ የኮሚሽኑ የኦዲት ሪፖርትን አስመልክቶ ስለተሠሩ ሥራዎችና ስለተወሰዱ ዕርምጃዎች፣ የኮሚሽኑ አመራሮችን ምላሽ ጠይቋል፡፡  በተለይ ከውዝፍ ሒሳብ ጋር በተያያዘ ‹‹ምንም ሥራ አለመሠራቱ››፣ ተወስደዋል የተባሉ ዕርምጃዎች ተብራርተውና በማስረጃ አለመቅረባቸው፣ እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር ለኮሚሽኑ የተመደቡት የውስጥ ኦዲተር ከኃላፊነታቸው በተቃራኒ ኮሚሽኑን ወክለው ማብራሪያ መስጠታቸው ቋሚ ኮሚቴውንና በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላትን አላስደሰተም፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የኦዲት ግኝት በስምንት የሒሳብ መደቦች በአጠቃላይ 1.94 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሒሳብ መኖሩ ተገልጾ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 32.8 ሚሊዮን ብር ሳይሰበሰብ ከአሥር ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑን፣ ከ1.27 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ የዕድሜ ቆይታው ምን ያህል እንደሆነ ለኦዲት አለማቅረቡን፣ በተጨማሪም 629.2 ሚሊዮን ብር የምዝገባ ሰነዱ ካለመኖሩም በላይ ከማን እንደሚሰበሰብ እንደማይታወቅ በኦዲቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ ምን ማስተካከያ እንደተወሰደ ለተጠየቀው ጥያቄ በቅድሚያ ምላሽ የሰጡት የኮሚሽኑ የበጀትና ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ሀብታሙ፣ ከ1.93 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የገንዘብ ሚኒስቴር በኮሚሽኑ በኩል ለቅድመ አደጋ መከላከል ወደ ክልሎች የላከው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሄንን ገንዘብ ለማስመለስ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ክልሎች ተልኮ የነበረ ቢሆንም፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ሥራው እንደተቋረጠም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውን ተሰብሳቢ ሒሳብ ደግሞ ዕድሜው ምን ያህል ነው የሚለውን በመለየት፣ የቆዩትን ለመፍትሔ ወደ የሚመለከተው አካል ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የበጀትና የፋይናንስ ዳይሬክተሩን ተክተው ለቋሚ ኮሚቴው ምላሽ መስጠት የጀመሩት የኮሚሽኑ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጩንቻ፣ አብዛኛው ያልተሰበሰበ ሒሳብ የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን በድጋሚ ከተናገሩ በኋላ ኮሚሽኑ እስከ ጥር 2012 ዓ.ም. ያለው ያልተሰበሰበ ሒሳብ 500 ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የምዝገባ ሰነድ የሌላቸውና በድምሩ ከ629 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑትን ያልተሰበሰቡ ሒሳቦች ደግሞ ‹‹የቆዩ ሰነዶች ናቸው፣ መሰረዝ ነው ያለባቸው፣ ለዚህ ደግሞ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል መረጃ ሰብስቦ ወደ የሚመለከተው አካል ለመላክ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳቦች ሊሰረዙ ስለመሆኑ የተሰጠው ምላሽ ግን በውይይቱ ላይ የተገኙትን የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የቋሚ ኮሚቴው አባላትን አስቆጥቷል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ‹‹1.9 ቢሊዮን ብር እንደ ቆሎ ተበትኗል፤›› ካሉ በኋላ፣ ከ629 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ያለበት ሒሳብ ሊሰረዝ ሒደት ላይ ነው መባሉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

ምክትል ዋና ኦዲተሯ፣ ‹‹ዕቃ አቅራቢ የት ሄዶ ነው ሒሳቡ የሚሰረዘው? ለምን ያልሰበሰበው [አካል] ተጠያቂ አይሆንም ገንዘቡ ከሚሰረዝ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ለዕቃ አቅራቢዎች ቅድመ ክፍያና ለተቋራጮች የተከፈለው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ላይ ተጠያቂነት ማምጣት እየተቻለ ሒሳቡን መሰረዝ ተገቢ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የተላላፈ ነው የሚል ምላሽ ስለተሰጠበት በቢሊዮን የሚቆጠር ያልተሰበሰበ ሒሳብም አስተያየት የሰጡት ወ/ሮ መሠረት፣ መዝገቡ በኮሚሽኑ ስም እስከሆነ ድረስ ተጠያቂ የሚሆነው ኮሚሽኑ ራሱ መሆንኑን ተናግረዋል፡፡

ከሁሉም አስተያየቶች በኋላ የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ዋና ኮሚሽር አቶ ምትኩ ካሳ፣ ውዝፍ ሒሳቦቹ ሊሰረዙ እንደሆነ በባልደረቦቻቸው የተገለጸውን ‹‹ስህተት ነው›› በማለት አስተባብለዋል፡፡

በኦዲት ሪፖርቱ ላይ የመነሻ ሰነድ የሌለው 16.8 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወኪሎች በወጪነት ለተመዘገበ 87.5 ሚሊዮን ብር አስረጂ ሰነዶችን ቢጠይቁም እንዳልቀረበላቸው ተገልጿል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ የሰጡት የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን፣ መነሻ ሰነድ የለውም የተባለው 16.8 ሚሊዮን ብር በስህተት ‹‹ተደግሞ የተመዘገበ በመሆኑ ተሰርዟል›› ካሉ በኋላ፣ ለኦዲት ሰነዱ አልቀረበም የተባለው 87.5 ሚሊዮን ብር ደግሞ ሰነዱ ሌላ ቦታ በመደባለቁ እንጂ ሳይኖር ቀርቶ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህም ምላሽ ግን በፌዴራል ዋና ኦዲተር ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌታሁን ዳምጤ፣ መሥሪያ ቤታቸው ኮሚሽኑን ኦዲት ሲያደርግ በስህተት የተደገሙ ሒሳቦችን ለይቶ መሰረዙን አስታውሰው፣ በኦዲቱ ላይ የተጠቀሰው 16.8 ሚሊዮን ብር በተደጋጋሚ ተሰርዟል መባሉ ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በመደባለቁ ምክንያት እንጂ አለ›› የተባለውን የ87.5 ሚሊዮን ብር ሰነድ በተመለከተም ራሳቸውም ጭምር ሰነዱን ፈልገው እንዳጡ ገልጸው፣ ‹‹ሰነዱ አለ›› መባሉን ተቃውመዋል፡፡ አክለውም በ2012 ዓ.ም. 87.5 ሚሊዮን ብር የነበረው ለኦዲተር ያልቀረበ ሰነድ፣ በ2013 ዓ.ም. በብዙ ጨምሮ 3.8 ቢሊዮን መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ የበጀት ዓመቱን ያልጠበቀ ወጪ የተደረገ መሆኑ፣ ተከፋይ ሒሳብን በተመለከተ የተለያዩ ጉድለቶች መታየታቸው፣ 1.8 ቢሊዮን ብር በጀት ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑና ሌሎች የኦዲት ግኝቶች በኮሚሽኑ ላይ ተነስተው ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

‹‹እነዚህ ግኝቶች ላይ ምን ዕርምጃ ተወሰደ?›› ለሚለው የተሰጡት አብዛኞቹ ምላሾች በፌዴራል ዋና ኦዲተርም ሆነ በቋሚ ኮሚቴው ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ኮሚሽኑ በ2012 ዓ.ም. ተስማምቶ የፈረመበትን የኦዲት ሰነድ ማስተባበሉን ወቅሰዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነት መከታታያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ በበኩላቸው፣ የኦዲት ግኝቶቹ ከፍተኛ መሆናቸውንና ኮሚሽኑ ግኝቶቹን ከማስተካከል ይልቅ ማስተባበል ላይ ማተኮሩን በማውሳት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመነጋጋር ምርመራ እንዲደረግ አቅጣጫ እንዲሰጥ ጠይዋል፡፡

ከዚህ በላይ ውይይቱ ላይ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ያስነሳው፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነው በሚኒስቴሩ ለኮሚሽኑ የተሾሙት የውስጥ ኦዲተር ኮሚሽኑን ወክለው ምላሽ መስጠታቸው ነው፡፡

‹‹የውስጥ ኦዲተሩ አቀራረባቸው የፋይናንስ ኃላፊ ነው የሚመስሉት፤›› የሚል አስተያየት የሰጡት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ወ/ሮ መሠረት፣ ድርጊቱ ከመርህ የተቃረነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ሱመያ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባልም እንዲሁ፣ ‹‹ምላሽ መስጠት የውስጥ ኦዲተር ኃላፊነት ነው ወይ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር የመጡት ወ/ሮ ዓይናለም ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹የውስጥ ኦዲተር ኃላፊነቱ የበላይ አመራሩን ማገዝ ነው፡፡ በዚህ ሕግና አግባብ ይኬድ ማለት  አለበት እንጂ፣ ራሱን የሥራው አካል አድርጎ ማየት የለበትም፡፡ ሥነ ምግባሩም አይፈቅድም፡፡ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ነው ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሆነው፤›› ብለዋል፡፡

ቋሚ ሰብሳቢው አቶ ክርስቲያን በበኩላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር የኦዲት ግኝትን አስመልክቶ በቅርቡ ከ38 ሌሎች ተቋማት ጋር ለኮሚሽኑ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንና ቅጣት መጣሉን አስታውሰው፣ በሚኒስቴሩ የተሾሙት የውስጥ ኦዲተር ግን አንዳንድ ችግሮች በገንዘብ ሚኒስቴር ምክንያት የተፈጠሩ መሆናቸውን መናገራቸው የሚጣረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ላይ ዘጠኝ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ከኦዲት ግኝቱ አንፃር የወንጀል ተጠያቂነት የሚስከትሉ ጥፋቶች ካሉ እስከ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በቂ ምርመራ አድርጎ ክስ እንዲመሠረት አዘዋል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ከሥነ ምግባር ብልሹነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ካሉ በሁለት ወራት ውስጥ ረፖርት እንዲያቀርብም አሳስበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርም የአሠራር ብልሹነት በፈጸሙ ሠራተኞችና አመራሮች ላይ ተጨማሪ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን ወስዶ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀነ ገደብ ተቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ለኮሚሽኑ ልዩ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ካለበት የኦዲት ችግር እንዲወጣ እንዲያደርግ ያዘዘው ቋሚ ኮሚቴው፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተቋማትን ለመደገፍ የተመደቡ የውስጥ ኦዲተሮችን የሙያ ሁኔታ በወጉ ፈትሾ ማስተካከያ እንዲያደርግ መመርያ ሰጥቷል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ደግሞ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የኦዲት ማስተካከያ አድርጎ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ ታዟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...