Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የጦርነት ያክትም›› እናታዊ ተማፅኖ

‹‹የጦርነት ያክትም›› እናታዊ ተማፅኖ

ቀን:

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነትና በየቦታው የሚነሱ የብሔር ግጭቶች  በሴቶች፣ በወጣቶችና በሕፃናት ላይ ስቃይና ሰቆቃን አስከትለዋል፡፡ እናቶች እንባቸውን የሚያብስላቸው አጥተዋል፡፡ ሕፃናት ተሳቀዋል፡፡ ወጣቶች የጦርነት ሰለባ ሆነዋል፡፡

በየአካባቢው በሚነሱ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፡፡ ሕፃናት ያለ ወላጅ ቀርተዋል፡፡ በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከዓመት በፊት የተነሳው ጦርነት ዛሬም አልሻረም፡፡ የብዙዎችን ሕይወት ነጥቆ፣ አካል ጉዳተኛ አድርጎ፣ ሥነ ልቦና ሰልቦ በተለይም የአካባቢውን ነዋሪዎች ለሰቆቃና ሰቀቀን ዳርጓል፡፡

ዛሬም የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ነው፡፡ ይፋዊ ጦርነት ዳግም ይጀመር ይሆን? የሚለው የበርካቶች ሥጋት ሆኗል፡፡ በተለይ የእናቶችን ልብ አርዷል፡፡ በእንባ እንዲታጠቡ ምክንያት ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጦርነትና ግጭት ምክንያት ለዓመታት ያፈሩት ንብረቶች የወደመባቸው፣ ልጆቻቸውንና ባሎቻቸውን በጦርነት ያጡና ግራ የተጋቡ እናቶች በአግባቡ እንኳን እግዚአብሔር ያፅናችሁ ሳይባሉ፣ የሚገርፋቸው ረሃብና ጉስቁልና ከትከሻቸው ሳይወርድ ሌላ የጦርነት ፍዳ ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡ ሆኖም የእናቶችን እንባ የሚያብስ ጠፍቷል፡፡ የታሰረ አንጀታቸውን የሚፈታም ናፍቋቸዋል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የተከሰተው አሰቃቂና አሳዛኝ ምዕራፍ እንዲዘጋ ምኞታቸውና ፍላጎታቸው ነው፡፡ ይህ እንዲሳካ ደግሞ በጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች ሁሉ ጆሮ እንዲሰጧቸው፣ ልባቸውን ከፍተው ችግራቸውን እንዲያዳምጧቸው ይማፀናሉ፡፡

የዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት ከምቹ ቤት መልቲ ሚዲያ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ‹‹ልጆቼ በጡቴ፣ ልጆቼ በሞቴ፣ ልጆቼ አፈር ስሆን›› መድረክ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ እናቶች እንባቸውን እያፈሰሱ ‹‹መንግሥት ስማን፣ ጦር ያነሳችሁ ስሙን›› ብለዋል፡፡

‹‹የሰላምና የፍቅር መልዕክት›› በተጋባዥ እናቶችና ታዳሚ ወጣቶች በግጥምና በንግግር ‹‹እባካችሁ ከጦርነት አውጡን፣ የጦርነት ምዕራፍ ይዘጋ›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራችና አማካሪ አህመድ ዘካሪያ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንዳሉት፣ ዛሬ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም እናቶችን ያስጨነቀውና ያስጠበበውን ጦርነት ‹‹የኢትዮጵያ ችግር መነሻውም መድረሻውም እልህ ነው ሌላ አይደለም፤›› ሲሉ ገልጸውታውል፡፡

‹‹እህል ለምነን፣ ጥይት ለምነን ምንድነው የምንሆነው? ምን ይሻላል? ብለን ዛሬ ተሰባስበናል፤›› ያሉት አህመድ (ረዳት ፕሮፌሰር) ሰላም እንዲሰፍን፣ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ትግራይና አማራ ክልል በመገኘት መለመናቸውን፣ ሰላም እንዲሰፍን ብዙ መጣራቸውን፣ ግጭቶች እንዲወገዱና የሰላም መንገድ እንዲሰፍን መሥራታቸውን ነገር ግን እንዳልተሳካ ጠቁመዋል፡፡

‹‹አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ጦርነት ስለሆነ ጦርነት ይበቃናል ብለን እንውጣ፣ እልህ ነው የሚያጨራርሰን›› ያሉት አማካሪው አሁን ደግሞ ሴቶች እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል ሐሳብ ለመስጠት ዕድል ያገኙ እናቶች ብሶታቸውን በእንባ ነበር የገለጹት፡፡ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነት፣ ግጭትና አለመረጋጋት ይበልጡኑ እናቶች፣ ሴቶችና ልጆችን ለመከራ መዳረጉን አውስተዋል፡፡

‹‹እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና ልጆቻችን እያለቁ ነው፡፡ እኛም እያለቅን ነው፣ እዚህ የምንበላው እያነቀን ነው፣ ሰው መብላት አቅቶታል፡፡ መንግሥት ጩኸታችንን ይስማን፣ እናቶች እንጩህ!›› ያሉ የመድረክ ተሳታፊዎችም ነበሩ፡፡

‹‹መንግሥት ምን እየሠራህ ነው? የሃይማኖት አባቶች ምን እየሠራችሁ ነው፡፡ እንደ ዳዊት፣ እንደ ሰሞን ማቅ ልበሱ፣ ወገን እየተቃጠለ ነው፡፡ እየተራበ ነው እናንተ ምን እየሠራችሁ ነው?›› ሲሉም እናቶች ጠይቀዋል፡፡

እናቶች በእንባና በሳግ በታጀበ ድምፀት በኢትዮጵያ ያለው ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃ አብዝተው በገለጹበት በዚህ መድረክ የተገኙት፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ በዕለቱ ሴቶች የተሰማቸውን ስሜት የአስፈጻሚ አካላት ሰምተው እንዲፈጽሙት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹እኔ እንድትሰሙ እፈልጋለሁ››ም ብለዋል፡፡

 የዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት አባል አቶ ሱሌማን ከድር በበኩላቸው፣ በርካታ የሰላም ውይይቶች እንደተደረጉ፣ ነገር ግን ስለ ሰላም የሚያደርጉት ጥረትና ውይይት ከአዳራሽ እንደማይዘል ተናግረዋል፡፡

መንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የፖሊሲ ግብዓት አይወስድም ወይ? ሚዲያዎች የመንግሥትን ሐሳብ ነው የሚያስተጋቡት፣ የኛን ሐሳብ ሕዝብና ዓለም እንዴት ይስማልን? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የተጋበዙ እናቶች ጦርነት ይቆም ዘንድ፣ ነፍጥ ያነሱ ይዘቀዝቁ ዘንድ፡- ‹‹ልጆቼ በጡቴ፣ ልጆቼ በሞቴ፣ ልጆቼ አፈር ስሆን፣ ኧረ ስለ ወላጅ፣ ኧረ ስለ ልጆች የአገር መሥራች ልጆች ናቸውና ወጣት ልጆቻችን ሰላምን ፍጠሩ፣ ፀብን አስወግዱ፣ አታሳዝኑን፣ አታስለቅሱን፡፡ ጦርነት ልጅ አይወልድምና የወንድማማች መገዳደል በቶሎ ይቁም፡፡ እናቶች ሁላችሁም በያላችሁበት የሰላም ጥሪያችንን አስተጋቡልን፤›› ሲሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መልዕክትን አስተላልፈዋል፡፡

‹‹አሁን ለጦርነት እየተዘጋጀን ነው፡፡ ከዚህ ምን እናተርፋለን?›› ሲሉ የሚጠይቁት አህመድ (ረዳት ፕሮፌሰር) ከመድረኩ የተሰበሰበውን ሐሳብ አጠናቅረው የሚዋጉ ወገኖችን ሁሉ ወደ ሰላም ሊያመጣ የሚችል ምክረ ሐሳብ በጥቂት ቀናት  ውስጥ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...