Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላይ የተነሱ እጆች ይውረዱ

በአገራችን ዘመናዊ ግብይት ሥርዓትና የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴዎችን በመተግበር በቀዳሚነት ስማቸውን ልንጠቅስ ከምንችለው ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከሚካሄድባቸው ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይገኝበታል፡፡ ሻጭና ገዥ ከተለመደው የገንዘብ ቅብብሎሽ ወጥተው ክፍያዎችን በባንኮች በኩል እንዲያካሂዱ በግብይት ሥርዓት ውስጥ መካካድ እንዳይፈጠር በማድረጉም ረገድ ምርት ገበያው እንደ ፈር ቀዳጅ ሊጠቀስለት የሚችል ታሪክ አለው፡፡ በዘመናዊ መንገድ ክፍዎችን እንዲፈጽሙ ለማስቻል ከሁሉም የኢትዮጵያ ባንኮች ጋር በመተሳሰር በሻጭና በገዥ መካከል ያለው ግንኙነት ሕጋዊ መስመር እንዲይዝ፣ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን አሠራር በመዘርጋትም ቢሆን የዚህ ተቋም ድርሻ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የአገሪቱ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ መደረጉ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በዘፈቀደ የሚካሄደውን አሠራር ከማስቀረቱም በላይ አገሪቱ የወጪ ንግድ ምርቶችም ሆኑ ለአገር ውስጥ የሚቀርቡ ምርቶች የገበያ ዋጋቸውን ለመለካት ያስቻለ ዕድል ይፈጥራል፡፡  

በቡና ግብይት የጀመረውን ሥራ በአሁኑ ወቅት ከአሥር በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የእርሻ ምርቶችን በማከል ሥራውን እያሰፋ የመጣው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በየዓመቱ የሚገበያየውን የምርት መጠንና የግብይቱ የገንዘብ መጠን ከፍተኛ በሚባል ደረጃ አድጓል፡፡ መረጃዎች የሚሳዩት በዓመት በመቶ ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች በማገበያየት የጀመረው ሥራ አሁን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ማገበያየት ችሏል፡፡ በዓመት የሚገበያየው የምርት መጠንም ከ700 ሺሕ ቶን በላይ መድረሱ በራሱ ተቋሙ በአገሪቱ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ድርሻ ሊያመለክት ይችላል፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ ሲሠራ የቆየው ይህ ተቋም ሌሎች ምርቶችንም ለማገበያየት ያቀደ ሲሆን፣ በቅርቡም የማዕድን ምርቶች በዚሁ ገበያ በኩል ለማገበያየት ስምምነት መደረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡

ምርት ገበያው እንዲህ ካሉ በመልካም ከሚጠቀሱለት ተግባሩ ባሻገር ከአሠራር ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳበትና የሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች ግን የሉም አይባልም፡፡ በአገር ደረጃ እነደ ወረርሽኝ እየሰፋ ያለው ሙስና እዚህም ቤት አለ፡፡ ተቋሙ ዘርግቼዋለሁ ካለው አሠራር ወጣ ያሉ ያልተገቡ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው የሚለውም እሮሮ አዲስ አይደለም፡፡ በተለይ ለግብይት የሚቀርቡ ምርቶች የደረጃ አወጣጥ ለሌብነት የተጋለጠ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከጀምሩ የዚህ ተቋም መመሥረት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል ይቀርብ የነበረው የመረረ ሐሳብ ዛሬም ይነሳበታል፡፡ የምርት ገበያው መመሥረት የጠቀመው ነገር የለም የሚል አቋም ያላቸው እነዚህ ወገኖች ኧረ ጭራሽ መፍረስ አለበት እስከማለት ይደርሳሉ፡፡

እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ተገበያዮች የምርት ገበያው አሠራር ለምን እንዳልተመቻቸው ወይም ከእርሱ የተሻለ ምን ዓይነት አሠራር እንዲተገበር እንደሚፈልጉ ግልጽ ባይሆንም፣ የተቋሙ ዕድሜ ያጥርላቸው ዘንድ አሁንም ፀሎት ላይ ናቸው፡፡ ምርት ገበያውን ቡርዣ አድርጎ በመሳል የሚራመዱ አስተሳሰቦችም አሉ፡፡

ለማንኛውም ተቋሙ በውስጡ ብልሹ አሠራሮች ቢኖሩበትም የተለያዩ ችግሮች በአገሪቱ ወሳኝ የሚባለውን ሥራ እየሠራ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ተቋም ችግር ሊኖርበት እንደሚችልም ይታመናል፡፡ ነገር ግን በሕግ የተቋቋመን አንድን ተቋም ባልተለመደና ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ ለማደነቃቀፍ መሞከር ፈጽሞ ሕጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ በፌዴራል ደረጃ በሕግ የተቋቋመውን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ወደ ማሰርና ቅርጫፎቹን ወደ ማሸግ የተደረሰበት ምክንያትስ ምንድነው? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ተቋም ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አንዳንድ ተግባራት እጅግ ግራ የሚያጋቡ ሰባት የምርት ገበያው ቅርንጫፎች ታሽገው ሠራተኞቹ ለእስር መዳረጋቸው ማሳያ ነው፡፡ ቅርንጫፎቹም ሥራ አቁመዋል፡፡

በዚህ ዕርምጃ በየመጋዘኑ ያሉ ምርቶች ለብልሸት እየተጋለጡ ነው፡፡ ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶች ተቆልፎባቸዋል፡፡ አገር በውጭ ምንዛሪ ረሃብ ላይ ባለችበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶችን ችግር ገጥሟቸዋል እየተባለ ቅርንጫፎችን እስካሁን አሽጎ ማቆየት አግባብ አይሆንም፡፡ በአጠቃላይ በዚህ አካባቢ የሚሰማው ሁሉ አሳዛኝ ነው፡፡ ተቋሙም ሆነ ሠራተኞች ሕግ ጥሰው ከሆነ በሕግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ማንም ከሕግ በላይ መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግራ ተጋብቶ ኧረ ባላወቅሁት መንገድ እንዲህ ሆኛለሁ ብሎ ምልጃ የሚሄድበት ምክንያት በራሱ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

በእርግጥ ተቋሙ እየሠራ ያለው ሥራ ለአገር ካልጠቀመ፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ካመዘነ እንዴት ይስተካከል ብሎ መምከርም የአባት ነበር፡፡ ነገር ግን ከመሬት ተነስቶ አንድን በአዋጅና በሕግ የተቋቋመን ተቋም ባልተለመደ ሁኔታ ሥራውን ማስተጓጎል፣ ይህም እየታየ ዝም መባሉ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ምርት ገበያው ባልተገባ ሁኔታ ቅርንጫፎቼ ተዘጉብኝ ሠራተኞቼም ታሰሩ በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አቤት ቢልም ከአንዳቸውም ምላሽ አላገኘም፡፡ ይህ ምን ያሳያል? ስለዚህ ይህ ጉዳይ ለምን እንደ ቀላል እንደታየ ግራ የሚያጋባ ሲሆን፣ ነገ ከነገ ወዲያ ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ምርት ገበያው ካላስፈለገ በሕግ ማፍረስና የተሻለ ተቋም መገንባት ይችላል፡፡ ነገር ግን በሕግ የተቋቋመን ተቋም በጎን ገብቶ ለማፍረስ ዲጅኖ ይዞ መነሳት ሕጋዊ አይሆንም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ትልቅ የአገሪቱ ተቋም ችግር ውስጥ ነኝ እያለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ዝም ማለታቸው እንዴት እየተዳደርን ነው? ያሰኛል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት