Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሃይማኖት ሰላማችንን ምን ነካው?

የሃይማኖት ሰላማችንን ምን ነካው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በዓለም ዙሪያ ሲታይ ከኖረውና አሁንም ከሚታየው አሳሳቢ ችግር አኳያ፣ በአገራችን ያለው የሃይማኖት ሰላም ምን ያህል ውድና ብርቅ ሀብት እንደሆነ ለመገንዘብ አሁን አሁን እየተዘረገፉ መጥተው መብትና ነፃነትን ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን የአገር ህልውና እያስፈራሩ ያሉትን አደጋዎች ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ብዙዎቻችን ሲወርድ ሲወራረድ በመጣ እምነት ላይ ተመሥርተን የት አለ ያ ሁሉ የአባቶቻችን የእርስ በርስ መፈቃቀር? ሰላም? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ለዘመናት ተፋቅሮና ተከባብሮ የኖረው ሕዝብ፣ አገሩን የጋራ ሃይማኖትን የግል አድርጎ በፍቅር የኖረ ልዩ ልዩ እምነት ያለው ሕዝብ ተብሎ ሲነገር እንሰማለን፡፡ በዚህም እንስማማለን፡፡

አሁን በቅርብ ጊዜ በተለይም በዚህኛው የ2014 የካሊንደር ዘመን የተስተናገዱትና የኖርንባቸው ታላላቅና ልዩ ልዩ የሃይማኖት ግዴታዎችና ክብረ በዓላት ውስጥ እንደመሰከርነው፣ እንዲህ ያሉ አስደንጋጭና ታይተውና ተሰምተው የማያውቁ፣ አምሳያም የሌላቸው ችግሮች መዘርገፋቸው እውነት ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ውድና ብርቅ የሃይማኖት ሰላም ኖሯል፡፡ ይህ የነበረ ጉዳይ እንዳይሆን ደግሞ የአገራችንን የሃይማኖት ሰላም እንዴትና በምን ምክንያት ህልውና አግኝቶና ተጠብቆ እንደኖረ መመርመርና መገንዘብ አለብን፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሁሉንም እውነት፣ እውነቱን ሁሉና እውነቱን ብቻ መረዳትና መገንዘብ ከፈለግን የአገራችንን የሃይማኖት ሰላም አንድም በደኅንነትና በጥርነፋ መረብ ተጠብቆ የኖረ፣ ከዚህም ጋርና ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የልማት የማደግ ጥማት፣ ትርምስንና ንቁርያን መታከት፣ በቱግታ ለመግለብለብ አለመቸኮል የታገዘ የሃይማኖት ሰላም ነበር፡፡ አደጋ ላይ የወደቀው ይህ ሰላማችን ነው፡፡ የሃይማኖት ሰላማችንን ምን ነካው?  ምንስ ይሻለናል?  መፍትሔውስ ምንድነው?  የሚለውን ጥያቄና አጠቃላይ ጭንቀታችንን ለመመለስና መፍትሔም ለመስጠት የምንገኝበትን ምዕራፍ ወይም የዕድገት ደረጃ መቃኘት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ የተለያዩና እንዲያውም ተቃራኒ ሐሳቦች መነገራቸውንና መስተጋባታቸውን ሳንክድ ለውጡ፣ ሽግግሩ ተቀልብሷል፣ ከተቀለበሰም ቆይቷል የሚባል መሆኑን ከቁጥጥር ሳናስወጣ፣ ይህ የሚባለው ማለትም ለውጡ ከተቀለበሰ ቆይቷል የሚባለውም ከተለያዩ ‹‹ቀኝ›› እና ‹‹ግራ›› አቋሞች መሆኑን ሳንዘናጋ፣ ኢትዮጵያ አሁንም ለውጥና ሽግግር ምዕራፍ ውስጥ ናት ብለን እናምናለን፡፡ ምንም እንኳን ለውጡና ሽግግሩ በየጊዜው እየተባባሰ እየከፋ የመጣ አደጋ ቢያጋጥመውም፣ ለውጡና ሽግግሩ አሁንም በሕይወት አለ ብለን እናምናለን፡፡

ያለንበት ምዕራፍ የለውጥና የሽግግር ጊዜ ነው የሚባለው ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ውስጥ ስላለን፣ ቢያንስ ቢያንስ ስለገባን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲጎሳቆል ከነበረበት ምዕራፍ ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ወደየሚሆንበት ምዕራፍ የመተላለፍ ጉዞ ዋናው ቁልፍ መነሻ፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታንም ያካትታል፡፡ ይህንንም የጥበብ መጀመርያው ያደርጋል፡፡ በየትኛውም በሃይማኖትም ሆነ በሌላ በሌላ የ‹‹ማንነት›› የልዩነት ካምፕና ካብ ተበታትኖና ተቧድኖ ፍጅት ውስጥ ላለመግባት፣ ይህን ከመሰለ እያስፈራራን ካለ ዓይነት ፍጅትና ዕልቂት ለማምለጥ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የአገር ሕግ ውስጥ ተዘርዝረው የኖሩትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መኗኗሪያ ለማድረግ ለውጡንና ሽግግሩን አጥብቆ መያዝ ይሻል፡፡ የለውጥ ጅምሩን ካነጣጠረበትና ከተጠናወተው ቅልበሳ ማዳንና መከላከል ይገባል፡፡

በዚህ የሽግግርና የለውጥ ሒደት ውስጥ ዴሞክራሲያችን ገና መሠረት አልያዘም፡፡ ዴሞክራሲያችንና ሰብዓዊ መብቶችን ከማንም ፍላጎትና በጎ ፈቃድ ውጪ የሥርዓት መተማመኛ ባገኘ አሠራር የምንገለገልበት ደረጃ ገና አልደረስንም፡፡ ከመንግሥት ከራሱ የግል መገልገያነትና ከተቃዋሚ  እልህ መወጣጫነት ነፃ የወጣ መንበረ መንግሥት የማነፅ ሥራችን ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ጦርነት ተከፍቶበታል፡፡ ዴሞክራሲው ገና መሠረት አልያዘም ብቻ ሳይሆን፣ አገራችንና ሥርዓተ መንግሥቱን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ የለውጡና የሽግግር ምዕራፍ የሚገኘው ገና ጅምሩ ላይ ነው፡፡ ለውጡ የጀመረው አፈናንና ጥርነፋን በማስወገድ ነው፡፡ ዛሬ የምናጣጥመውና የምንገለገልበት ዴሞክራሲ የሥርዓተ መሠረት የያዘ ሳይሆን፣ ያ ገና ለውጡ ሲጀመር አፈናውና ጥርነፋው የተነሳለት/የተወገደለት ጭላንጭል መፈናፈኛና መላወሻ ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ በመብቶችና በነፃነቶች የመገልገል የሰዎች ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ መብቴ ነው፣ ነፃነቴ ነው ከማለት ጋር ኃላፊነቴ ነው ማለትም ሌላው መረማመጃ እግሩ፣ አጠቃላይ የእግሩ መንገድና የዓይኑ ብርሃን ማድረግ አለበት፡፡

የዴሞክራሲያዊ ለውጡ ሥራ ገና ጅምሩ ላይ ላለ፣ አፈናንና ጥርነፋን አስወግዶ ከዚህ በላይ ብዙ ላልተጓዘ ሽግግር ደግሞ ዋናው ግዳጅ ዴሞክራሲውን ማጥለቅ፣ መብቶችና ነፃነቶች የሥርዓት መተማመኛ የሚያገኙበትን የተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ በማያውቁትና ገና የተጠናወተውን ጣጣና ዝባዝንኬ አራግፎ ባልጠራና ባልጠነከረ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ውስጥ ሲላወሱና ሲነቃነቁ፣ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን የንግግርንም ሆነ የሃይማኖት ነፃነትን ከመብት መነካት ጋር ማሳከር ሳያውቁት ፈተና ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከፖለቲካም ከሃይማኖትም ገለልተኛ በሆነና ይሁን ባልነው፣ ይሁን ብለን በተስማማንበት ሙያዊ ኃላፊነቱም የመንግሥት ተቋምም ውስጥ ሳት ብሎ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ሙያዬ›› እና ግዳጄ ብሎ ወገናዊነት ፖለቲካዊ ፍትፈታ ውስጥ መግባት ይመጣል፡፡ መብትን ከበጎ ፈቃደኝነትና ከአንድ ወይም ሌላ ፓርቲ/ተቋም ቁርጠኝነት ወይም ከእርጥባን የዘለለ፣ ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር የዕድገት ደረጃ ላይ ሳንደርስ መተራረድን የሚደግሱ መብትና ነፃነት ባይነት ውስጥ ዘለን እንገባለን፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ በአንድ በኩል ተጭኖብን የኖረው የደኅንነትና የጥርነፋ መረብ ጠብቆት የኖረውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከችግርና ከረሃብ የመውጣት፣ የልማትና የማደግ ጥማት፣ ትርምስንና ንቁሪያን የመታከት ልማድ በቱግታ ለመግለብለብ ያለመቸኮል፣ ወግ አቅፎና ደግፎ ያቆየውን ሰላማችንን ለአደጋ ያጋለጠውና  ጤና የነሳው የአራት ዓመት ዕድሜ ካለው የዛሬው መንግሥት የቀድሞው ባለ 27 ዓመት ዕድሜው መንግሥት የተሻለ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወይም ዴሞክራሲውና መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን ከስም ጌጥ ይልቅ ህልውና ያላቸው ይሁን ማለታችን እንቢ ለመብትና ለነፃነት ብለንም ትግል ውስጥ መግባታችን ጥፋት ወይም ስህተት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲው የሚመሠረትበትንና መብቶቻችን ነፃነቶቻችን ህልውና የሚይዙበትን የሥርዓት ግንባታ ዋና ተቀዳሚ ሥራችንን ዘንግተን የእዚህን በቅድሚያ መታነፅና መጠናከር በሚጠይቀው በመብትና በነፃነት መገልገል ላይ ብቻ በማተኮራችን ነው፡፡ አውታረ መንግሥቱን ከገዥው ፓርቲ አሻንጉሊትነትና ከተቃዋሚዎች እልህ መወጣጫነት መገላገል የሚያስችል ሥርዓት ግንባታችንን እርግፍ አድርገን ትተን፣ መብትንና ነፃነትን (ይህ የንግግርና የሃይማኖትን መብትና ነፃነት ይጨምራል፣ ከሁሉም በላይ እነሱን ይመለከታል) ከእርጥባን ሻል ባላለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ላይ ሳንደርስና ይህንን ማረጋገጥ ሳንችል ዝም ብሎ ሃይማኖቴ፣ ሐሳቤ (የሐሳብ ነፃነቴ) ቢሉ ትርፉ ዞሮ ዞሮ ‹‹ተንጋለው ቢተፉ…›› ነው፡፡ በራስ ጉዳይ ላይ የሚባርቅ የትግል ሥልት ነው፡፡

ባለ ብዙ ሃይማኖት በሆነችው በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ በገዥዎች ምንም ተደረገ ምን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉንም ችለውና ተቻችለው እያሳለፉ አብሮ በመኖር እዚህ አድርሰውናል፡፡ ይህንን ተደጋግሞ ከዚህ በላይ የተገለጸው የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ትርምስንና ንቁርያን፣ መባላትንና መተራረድን እንቢ ያለና መናቆርን የታከተ በቱግታና በግርታ ለመግለብለብ አልቸኩልም በማለት ባህል የታገዘ፣ በሰላም አብሮ የአሁኑ ትውልድ ዘላቂ መሆኑን የሚያረጋግጠው ዛሬ ያለንበት የመብትና የመኖር ቅርስ የነፃነት የንቃት ደረጃ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ተግባር መሸከም ከቻለ ብቻ ነው፡፡

የትም ቦታ አደገኛና ጠንቀኛ የሆነውን ሃይማኖትን የሚመለከተውን የኢትዮጵያን የሰላም ጉዳይ የአደጋ ጉዳይ፣ አገራችንን ኢትዮጵያን ከዓረብ አገሮችም ሆነ ከአውሮፓ አገሮች ከሚለየው የሃይማኖት ጥንቅር ጋር አገናዝቦ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ እምነት አገር ከመሆኗም በላይ ክርስትናና እስልምና በቁጥርም በሥርጭት ስፋትም ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በየትኛውም ማዕዘን ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ብንጓዝ፣ ሁለቱን ሃይማኖቶች ተዳብለው ወይም አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ ተካተው ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሃይማኖት ፅንፈኛ ትንኮሳም፣ አሸባሪነትም ሆነ የመብትና የነፃነት ጠንቀኝነት እዚህም፣ እዚያም አለሁ ቢልና ሃይማኖታዊ ግጭት አንድ ቦታ ቢቀጣጠል እዚህ ቦታ ይገታል ማለት አዳጋች ነው፡፡ እዚህ ቦታ ተጠቅቶ ይኼኛው ይተርፋል ማለትም ዘበት ነው፡፡ ይህንን ልብ ማድረግ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ አገራችን የሃይማኖት ሰላም ዕጦት ዝም ብሎ እንደ አጋጣሚ ሊመጣ የሚችል ማኅበራዊ ችግር ብቻ፣ እንዲያውም ከምድረ ገጽ የሚያጠፋ እዚያ ሊሆን እንደሚችል የሚያስገነዝብ ይመስለኛል፡፡ የሃይማኖት ሰላማችንን እንደ ሰበበኛ ተሰባሪ ዕቃ ከአስፈላጊ ለውጥና ከተገቢው የሥርዓት ግንባታ ጋር መንከባከብ የሚገባን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ከጨበጥንና ከተረዳን ቀጣዩ ነገራችን ለእንዲህ ዓይነት እንክብካቤ የሚሆን ነባራዊና ህሊናዊ ጥሪት አለን? ጉድለታችንስ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ከአንድ በጎ ነገር እንጀምር፡፡ መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኝነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ይህ የመጀመርያውን የሕግ መልክና ይዘት ያገኘው በደርግ ዘመን በዚያም ውስጥ በ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ዛሬ ሆነው ሲመለከቱት የሚገርም ‹‹የውጣ ውረድ›› ታሪክ ያለው የዓለማዊ (የሴኩላር) መሠረት የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ከእነ ግብስብስ ቅራኔዎቹ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ ሆኖ የፀደቀው ይህ መንግሥትንና ሃይማኖትን የተለያዩ አድርጎ ለማዋቀር ኢትዮጵያን የተዋወቀ ነገር፣ የኢትዮጵያን የሕግ ወግና ባህል ይተዋወቅ ተብሎ ሐሳብ የቀረበው ገና ዛሬ ቢሆንስ የሚል ጥያቄ ማንሳት የደረስንበትን የ‹‹ዕድገት›› ደረጃ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ያኔ እንደ ዋዛ ኢትዮጵያን የተዋወቀውና ቢያንስ ቢያንስ በሕግ (በተጻፈ ሕግ ደረጃ) የተወሰነው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ነገር እንደ አዲስ፣ አዲስ ሆኖ፣ የሕግ ሐሳብ ሆኖ የቀረበው ዛሬ ቢሆን ኖሮስ? ወይስ ትክክለኛው ጥያቄ የሕግ ሐሳብ ሆኖ የመቅረብ ዕድሉ ዛሬ ተሻሽሏል ወይስ ለይቶለት ተበላሽቷል የሚለው ነው?  ይህን ያህል የተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ የደረስንበት ዴሞክራሲን የመገንባት የዕድገት ደረጃም ያን ያህል ሲበዛ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለማንኛውም ወደ መጀመርያውና ቀደም ብለን ወዳነሳው ጥያቄ እንመለስና በሕገ መንሥቱ አንቀጽ 11 የተደነገገውን ማዕቀፍ እንመልከት፡፡

መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ ይህ ማለት የትኛውም ዓይነት ሃይማኖት ፖለቲካ ሆኖ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት (ስቴት) ላይ ሊወጣና መንበረ መንግሥቱን የእምነቱ መሣሪያ ሊያደርግ አይችልም፡፡ የሃይማኖት ፓርቲ ሊሆን፣ ፓርቲም የሃይማኖት አቀንቃኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ከብሔርተኛነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚያን ዓይነቱን ቀዳዳ ደፍኖታል፡፡ ያ ቀዳዳ ክፍት ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ገለልተኝነት የሚፈርስበት ዕድልም አብሮ ይኖር ነበር፡፡

መንበረ መንግሥትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅ መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት ሳይሆን፣ የትኞቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት (ጫና) ሥር እንዳይወድቁ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኙ መጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የቆነጠጠ፣ እምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገደብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና የዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ ሕገ መንግሥት ሊያዋቅር መቻሉ ሁነኛ ጥንካሬ ነው፡፡ እናም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን ወይም መንግሥት ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትኛውም ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት ነፃነት ሳይጋፋ እምነቱን የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የቆሙለትን እምነት በተመለከተ፣ ትክክለኛ አተረጓጎሙና አያያዙ ይህ ነው ብሎ መስበክ፣ የምዕመናንን ግንዛቤና የእምነት አተገባበር በማስተማር ማበልፀግ መብት ነው፡፡ በግድ መጫን ግን መብት መድፈር ነው፡፡ መስበክ መብት እንደሆነ ሁሉ መሰበክም የማይገድቡት መብት ነው፡፡ የተሰበኩትን (የተቀበሉትን) እምነት ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣ ላላ አድርጎ መያዝ፣ ወይም መቀየርና አለመቀየር የግለሰቡ መብት ነው፡፡ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆቻቸውን በእምነታቸው ማነፅ መብታቸው ነው፡፡ የወላጅን እምነት ይዞ ለመቆየት ግን ተወላጅ አይገደድም፡፡ እነዚህን መብቶች ለመጣስ ማንም አልተፈቀደለትም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት ነባር አማኞቹን ይዞ ከመቆየት ባሻገር፣ አዲስ ተከታዮችን ለማፍራት የማስተማር ሥራ ማካሄድን ትርጉም የሚሰጡትም እነዚህ የግል መብቶች መኖራቸውና መረጋገጣቸው ነው፡፡

ይህ ማለት ግን ፖለቲካና ሃይማኖት ጭራሹኑ አይደራረሱ ማለት አይደለም፣ ቢባልም የማይቻል ነው፡፡ ከእምነት ነፃናትና እኩልነት ጋር የተያያዙ መሠረታዊ መብቶች ተደፍረው ይህንን በማውገዝ መንገድ ላይ ፖለቲካ፣ ፓርቲና ሃይማኖት ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲ አጥፊ ቅስቀሳ አድርጎ ሃይማኖታዊ አምባጓሮ ቢከሰት አነሳሹ ፓርቲ ተወጋዥ ከመሆን አያመልጥም፡፡

መንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትንም የሚያገናኛቸው ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ወደ መንግሥት አካላት ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቶች ሰላም ጉዳይ ሃይማኖቶችንና መንግሥትን ያገናኛሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚኖራቸው የበጎ ሥራና የልማት ዕቅድ ከመንግሥት የልማት ዕቅድ ጋር ተጋጭቶ ብክነት እንዳይሆንባቸው የልማት ዕቅዳቸውን ከመንግሥት ጋር ቢያገናዝቡ አስተዋይነት ነው፡፡ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው (ከሚደግፋቸው) የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥም የሃይማኖት ጉዳይ ተደርገው ሊምታቱ የሚችሉ (የሃይማኖት መሪዎችን ማብራሪያና የቅርብ ድጋፍ የሚሹ) ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተም አብሮ መሥራት ይኖራል፡፡

 ከየትኛውም ሃይማኖት፣ ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና በኩል የሚመጣ ፅንፈኝነት ነገረኝነት የሚጀምረው ከአመለካከቱ ነው፡፡ ሌሎች እምነቶች ከእሱ አጠገብ እኩል የመኖር መብትና እኩል ክብር ያላቸው ሆነው አይታዩትም፡፡ በራሱ ሃይማኖት ውስጥ ሳይቀር ለዘብተኛ አማኝ ወይ ሌላ ስንጣሪ መኖር ብሎ ነገር አይቀበልም፡፡፡ ‹‹ትክክልና የተቀደሰ›› ከሚለው እምነት ውጪ ያለ ሁሉ የክህደት/የርኩሰት ወይም የሰይጣን ዓለም ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት አያኗኑርም፡፡ ‹‹የገሃነም/የሰይጣን›› ዓለምና ‹‹የቅድስና›› ዓለም እንዴት ይኗኗራል? ከሰይጣን ማደሪያ ጋር መነካካት መርከስ ወይም ከገሃነም ጋር መነካካት ይሆናል፡፡ ይህን የእርኩሰትና የዘለዓለም ሞት ሠፈር የማስወገድ፣ የማፅዳትና በቅድስና የመተካት ኃላፊነትና ተግባር ከሰማይ የተሰጠው ደሞ ለእሱ (ለፅንፈኛው) ነው፡፡ ሲሰብክ እንኳ ድርጊቱ ሆኖ የሚታየው ማስተማር ሳይሆን ከዘለዓለም እሳት/ሞት የማትረፍ ሥራ ነው፡፡ ቅድስና እኔ ዘንድ ብቻ ያለ (ሌላው ሁሉ የርኩሰት ጎዳና) ብሎ የሚል እምነት ንዑስ እንኳ ቢሆን ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ተሰቅዘውለት እሱ ለመናኘት፣ የሥርዓተ ትምህርት ሰፋሪና የትምህርት ቤቶች ቃኚ ለመሆን ዕድሉን ቢያገኝ አያቅማማም፡፡ የዚህ ዓይነት ፅንፈኛ ፍላጎቶች በኦርቶዶክስ ክርስትና፣ በፕሮቴስታንት ክርስትና ፍልቃቂ እምነቶችም ሆነ በእስልምና ውስጥ ያጋጥማሉ፡፡

 የዓለማዊ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት በሃይማኖት እንዲቃኝ፣ ፀሎትና ስግደት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገባ መፈለግ የሃይማኖት ጭቆናንና የመንግሥትና የሃይማኖት ዝምድናን መልሶ መጥራት ነው፡፡ እንደ አካባቢው ሁኔታ ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ትምህርት ቤት ውስጥ ይግባ ቢባል በዚያ አካባቢ ያሉ ንዑስ ሃይማኖቶች ተጨቋኝ ይሆናሉ፡፡ አንዱ ጋ ዋና የሆነ ሃይማኖት ሌላ ቦታ ላይ ንዑስ ሆኖ ይገኛልና ጭቆናው ለራሱም መድረሱ አይቀርም፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች በየበኩላቸው የሚሰማሩባቸው የየብቻ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሯቸው ማሰብ በመንግሥትም ሆነ በግል ሊሟላ የማይችል ቅዠት ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ የትምህርት ቤት ልዩነት ሳይኖር ለየትኛውም እምነት ተከታዮች የፀሎት፣ የስግደትና የእምነት ክበብ መብት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈቀደ ይሁን ማለትም የትምህርት ሥራ ይመሳቀል፣ የትምህርት ቤቶች ሰላም በእምነት ንቁሪያና መሸራደድ ይበጥብጥ ብሎ መልቀቅ ነው፡፡

ጭንቀታችን ፅንፈኛ ፍላጎት ቦታ አግኝቶ እንዲረካና እንዲያድብ ከሆነ ፅንፈኝነት አልገባንም ማለት ነው፡፡ ለፅንፈኝነት የሚታየው መብትና የመብት መጣስ ብሎ ነገር ሳይሆን ገሃነምና ገነት ነው፡፡ ፅንፈኝነት መብት አክብሮና ተቻችሎ ኗሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ገሃነም የመግባት መብትን ከማክበር ይልቅ በግድ ገነት ማስገባት ይበልጥበታል፡፡ ሃይማኖት ለወጥክ ብሎ ከዝምድና ማግለልና ካልገደልኩ ባይነት የሚከሰተው፣ ለውጡን መብት አድርጎ ከማየት ይልቅ ወደ ቅስፈት (እርኩሰት) መግባት አድርጎ ከመቁጠር ነው፡፡ ፅንፈኝነት ባለጉልበት በሆነበት አካባቢ እምነትን በግድ ማስቀየርና ማባረር፣ ሲከፋም ግድያ የሚያካሂደው ለዚህ ነው፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ እምነቶችን የማራመድ ነገር ያሳሰበን ለመብት ማሰብ ከሆነ፣ ከትምህርት ቤት ውጪ መብቱን ማስከበሪያ መንገዶች መች ጠፉና፡፡ መኖሪያ ቤት፣ ቤተ አምልኮ፣ የሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ጋዜጣና መጽሔት፣ ወዘተ. ሁሉ አሉ፡፡ ተማሪዎቻችንን (ልጆቻችንን) በሃይማኖታዊ ግብረ ግብነት ለማነፅ አማራጮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ትምህርትም ከሥነ ምግባር ጋር አይቃረንምና ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር መጣበቅ ሳያስፈልጋቸው፣ ተማሪዎችቸውን በመልካም ምግባር ማነፅ ይችላሉ፣ በደንብ ከተሰናዱ፡፡

ከትምህርት ቤቶች ባሻገር፣ ሃይማኖታዊ ያልሆነ የሥራ ገበታን ለእምነት ማሠራጫነት መጠቀም አደገኛ የምግባር ጉድለት ነው፡፡ የገበያና የመጓጓዣ ሠልፎችን፣ አውቶቡሶችን የስብከት መድረክ አድርጎ መጠቀም፣ ወደ ሥራ የሚበር ሰውን ‹‹አንዴ ላናግርህ›› ብሎ ወይም ቤት አንኳኩቶ ልስበክህ ማለት ከትንኮሳ ይቆጣጠራል፡፡ በእነዚህ ዓይነቶቹ ስብከቶች ውስጥ አልፈናል፣ ስድድብ፣ ንጭንጭ፣ የድብደብ ክስቶችም አጋጥመውናል፡፡ አግባብ ባልሆነ ቦታ ልስበክ ከመባሉ ይብስ የአሰባበኩ፡፡ እምነትና ፅድቅን ከቶ ከዚህ በፊት ሰምቶ ለማያውቅ ከኃጢያትና ከዘለዓለም ሞት እኔ ላድናችሁ፣ ሌላ መዳኛ የላችሁም የሚል የዚህ ዓይነት አተያይ ‹‹እኛን ያልዳንን አድርጎ መዳቢ አንተን ማን አደረገህ?! እኛ ሃይማኖት የለንም?!›› የሚል ቱግታን ይቆሰቁሳል፡፡ መንገድ ላይ እምነትን ማሠራጨት ቢያስፈልግ እንኳ፣ የሚሻ እንዲወስድ ጽሑፎችን በመደቀን ብቻ መቆጠብ ጨዋነትን የተላበሰ ነው፡፡

አግባብ ባለው ሥፍራና የመገናኛ ዘዴ እምነትን በመስበክ ረገድም፣ የሌላውን እምነት በመንቀፍ ላይ መመሥረት በእኛ ሁኔታና የሥልጣኔ ደረጃ ጤናማ አይደለም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የትኛውንም ሃይማኖት ከመተቸትም ባለፈ ማሽሟጠጥም የንግግር ነፃነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሃይማኖት ስላልተቸንና ስላላሽሟጠጥን የሚጎድልብን የለም፡፡ ነቀፋና ሽሙጡን እንሞክር ብንል ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ እስከ ማስነሳት የሚሄድ ጣጣ ልንጎትት እንችላለን፡፡ ምዕራባውያኑም አሽሟጠውና ተሳልቀው ፅንፈኛ አሸባሪነት ጥርስና ጥቃት ውስጥ ከመግባት በቀር ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ከፋይዳቢስ ሽሙጥ ፋንታ፣ ዴሞክራሲና የሐሳብ ነፃነታችን ለምን በፅንፈኛ አሸባሪነት ተጠመደ? ከወጥመዱስ እንዴት መውጣት ይቻላል? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ላይ ቢያነጣጥሩ ፍሬው ለሌላውም የሚፈይድ ውጤት ባመጡ ነበር፡፡

የሃይማኖት መተቻቸት ፀብ ያማዝዛል ብሎ መጠንቀቅ፣ ትችትን በዱላና በጥይት መቅጣትን ተገቢ ብሎ መፈጸም በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ መምታታት የለባቸውም፡፡ ነቀፋና ዘለፋ፣ አምባጓሮ የመጀመር ወይም በቱግታና በጋጋታ የመቅጣት መብትን አያጎናፅፉም፡፡ የዚህ ዓይነት ዕርምጃ (በአንድ ሰው ተፈጸመ፣ በሺሕ ሰው) መብት የሚረግጥ ወንጀል ነው፡፡ እምነቴ ወይም ብሔረሰቤ ተነካ ብሎ በጋጋታና በግንፍልነት የኃይል ዕርምጃ መውሰድን ተገቢ መብት አድርጎ ማሰብ እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ተሠራጨ ማለት ወደ ሕግ መሄድን የጋጋታና የቱግታ ዕርምጃ እየተካ፣ በየአሉባልታው ሁሉ ዘራፍ እንዲል መሠረት አገኘ ማለት ነው፡፡ የጋጋታ ዕርምጃ አዙሪት ውስጥ ከተገባ በሕግ የተፈቀደ መብት እስኪመስል ድረስ ሊያምስ ይችላል፣ ፓኪስታንን የሚያብጣት አንዱ ችግር ይህ ነው

የሃይማኖቶችን የእምነት ስንክሳር ለየራሳቸው ብንተውም፣ በታሪክ ውስጥ ስለነበራቸው አኗኗር ሚዛናዊና እውነታዊ ዕውቀት መያዝ ግን ጭፍን ፈራጅ ላለመሆን ያስፈልገናል፡፡ ነባር እምነትን ተጋፍቶ ብቅ የሚል እምነትም ሆነ ሳይንሳዊ ግኝት በቀድሞ ጊዜ የህልውና ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡ ክርስትናም ሆነ እስልምና በየተነሱበት ወቅት መሳደድ ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱም በስብከትና በሰላም መንገዶች እንደተስፋፉ ሁሉ፣ በሰይፍና በጎራዴም እየዘመቱና እየተዘማመቱ ተስፋፍተዋል፡፡ አገርና አኅጉር ለተሻገረ ዘውዳዊ ኤምፓየር መስፋፋት ክርስትና ርዕዮተ ዓለም ሆኖ እንደነበር ሁሉ፣ እስልምናም እንደዚያ ሆኖ ሠርቷል፡፡

በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዞች ሁሉም ዘንድ የመንግሥትና የሃይማኖት ቁርኝት የነበረና ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አስገባሪ ሥርዓት ታሪክ ውስጥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የአገዛዙና የገዥዎቹ ዓይንና እስትንፋስ ሆኖ መኖሩ ወቸው ጉድ የሚያሰኝ ክስተት አይደለም፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖትነት ሥር ሌሎች ሃይማኖቶች ተጨቁነው መኖራቸውም የማይመለጥ ክስተት ነበር፡፡ በኃይል ሃይማኖት ማስለወጥ፣ እንቢ ያሉትን መግደል፣ አንዱን እምነት ተናቂ ሌላውን ተከባሪ ማድረግ ከሥር በዋሉ ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥታዊው ሃይማኖትም ውስጥ በተፈጠሩ  አፈንጋጭ ዝንባሌዎች ላይ ተካሂዷል፡፡

ተጨቋኝነቱ ከእምነቶች ተፈጥሮ (ባህሪ) ጋር ግንኙነት እንደሌለው ሁሉ፣ ጨቋኝነቱም የጭቆና መንበር ላይ ከተቀመጠው ሃይማኖት ዓይነትነት (ማንነት) ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ የትኛውም እምነት ከላይ በተቀመጠበት (የመንግሥት ሃይማኖት በሆነበት) ሥፍራ ጭቆናውን አስነክቶታል፣ እያስነካውም ነው፡፡ በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዝ ውስጥ ስለምን የሃይማኖት ጭቆና ተደረገ የሚል ቁጭት  ግራር ለምን እሾህ ኖረው ብሎ የመቆጨት ያህል ከንቱ ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነትን ባለማክበሩ ያለፈውን ዘመን ለመውቀስ መነሳትም በድሮ ጊዜ ላይ የዛሬ ፍርድ መስጠት ይሆናል፡፡ ያኔ እንኳን በሥርዓት ደረጃ፣ በግለሰብ ደረጃ እንኳን ‹‹ሃይማኖቶች እኩል መሆን አለባቸው፣ መንግሥት ሃይማኖት ሊኖረው አይገባም፤›› የሚል አሳቢ የሚፈጠርበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እንደዚያ ዓይነት ግለሰብ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ እንኳ አዕምሮው የተነካ ወይ ጋኔል የሰፈረበት የጉድ ፍጥረት ተደርጎ ከመታየት አይዘልም ነበር፡፡ ዛሬ ስለሐሳብና ስለእምነት ነፃነት እያወራን ባለንበት ጊዜ እንኳ፣ እኩልነትንና ነፃነትን ከማክበር የሚጎትቱ ዝንባሌዎች እየተፈታተኑን ሳለ፣ የእኩልነትና የፍትሕ እሴት ያልነበረውን ዘመን ባልነበረው ግንዛቤና እሴት መፍረድ አግባብ የለሽ ከመሆንም በላይ ሙልጭ ያለ አድሎኛነት ነው፡፡

አንድ ሃይማኖት የአገርና የመንግሥት መታወቂያ የተደረገበትን ዘመን የሃይማኖት ጫና (በደል) የሌለበት አድርጎ ማድበስበስ እንደማያግባባ ሁሉ፣ ስንት ነገር ተፈጽሞባችኋል እንካችሁ እያሉ በደል መደርደርም ከታሪክ ተምሮ ዛሬን ለማቃናትና አስማምቶ ለማኗኗር አንዳችም ድርሻ አያዋጣም፡፡ ጭቆናን ሲዘረዝሩ ጨቋኝነቱ ከመንግሥት ባለ ሃይማኖትነት የሚመጣ መሆኑን ግራ ቀኝ እያጣቀሱ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ዓይነት አተያይ እስካላበጁ ድረስ በክርስቲያናዊ የበላይ ገዥነት ውስጥ የተካሄደውን የውድና የግድ የክርስትና መስፋፋትና በእስላማዊ የበላይ ገዥነት ትግል በኩል የተደረገውን የእስልምና መስፋፋት በአንድ ዓይነት ሚዛን ለመረዳት እንቸገራለን፡፡ ከየሃይማኖቱ አኳያ የተወረወሩ አድሏዊ ፍርዶችንም ማቃናት ይሳነናል፡፡ የአህመድ ኢብራሂምን የበላይነት ዓመታት አንዱ የቁጣና የውርጅብኝ ዘመን አድርጎ ሲስል፣ ሌላው የእስልምና ሃርነት ትግል አድርጎ መቁጠሩ አመለካከትን የሆድና የጀርባ ያህል እንዳራራቀ ይቆያል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ፍንክርክር ፅንፈኞች ይነግዱበታልና የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በስተመጨረሻ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 11 ሁሉም ሃይማኖቶቻችንና እምነቶች የመብቶቻቸው፣ የነፃነቶቻቸው አብሪ ከከብ አድርገው ሊቀበሉትና ሊጠብቁት እንደሚገባ መግለጽ ተገቢ ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነት የሚረጋገጠው መንግሥትና ሃይማኖት ሲለያዩ እንጂ፣ የተቋቋመ (Established) ሃይማኖት ሲኖር መንግሥት ሃይማኖት ሲኖረው አይደለም፡፡ በተለይ በመንግሥት አኳያ ከሃይማኖት ጋር ያለውን ግንኙነት በጥሩና በመልካም የማይደፋፈር ዝምድና መቃኘት አለበት፡፡ አሁን አሁን በለውጡና በሽግግሩ ወቅት እንደምናየው በዚህ ረገድ ብዙ ይቀረናል፡፡ ይቀረናል ከማለትም በላይ እዚህ ውስጥ ብዙ ተትረክርከናል፡፡ ሁሉንም እምነቶችና ሃይማኖቶች እኩል ‹‹አከብራለሁ›› እኩል ‹‹አውቃለሁ›› ብሎ መንግሥት ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣኖቹ ከፍተኛና አደገኛ ‹‹ፈንጂ›› ሠፈር ውስጥ ኳሽተዋል፣ ወይም ዘንዶ ጎርጉረዋል፡፡ የሃይማኖት ሰላማችን ከዚህም በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ለሕገ መንግሥቱ ይገዛ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ መንግሥትም፣ ሕዝብም፣ ሃይማኖትም፣ ፓርቲም ሕግ ያቋቋመው ገደብና ዳር ድንበር እንዳለበት ይወቅ፡፡ አላውቅም ማለትም መከላከያም መከራከርያም አለመሆኑን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መብቴና ነፃነቴ ነው፣ ሥልጣኔም ነው ማለት ጭምር ኃላፊነቴ ነው ከማለት ጋር መስማማቱን፣ ይህን ኃላፊነት መሸከም ከሚችል ጨዋነት ጋር መዋደድን ያረጋግጥ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...