Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉጦርነትና ኢኮኖሚ - የማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅትና ትግበራ (ክፍል ሁለት)

ጦርነትና ኢኮኖሚ – የማገገሚያ ፕሮግራም ዝግጅትና ትግበራ (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

3.2 የኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራም ቀረፃና ትግበራ

በጦርነት ውስጥ ላለፈ ኢኮኖሚ፣ ጦርነቱ ከአበቃ ማግሥት ጀምሮ ወደ ኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥራዎች ውስጥ መግባት አማራጭ የሌለው፣ የሕዝብ፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ በተለይ የግል ዘርፍ ኢኮኖሚ ተዋንያን ኃላፊነት ነው፡፡ ኃላፊነቱም አገርን ሳትፈርስና ሉዓላዊነቷ ሳይናጋ በማቆየት የማኖር፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ዕሳቤ ላይ የተመሠረተ ግዴታ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥራ በዕቅድ፣ ሁሉን ዓውድ፣ አካባቢና ክፍለ ኢኮኖሚ ወይም ዘርፍ በሚያካትት መርሐ ግብር የሚመራና የሚተገበር መሆን አለበት፡፡ መርሐ ግብሩ አገራዊ መሠረት ባለው ዕውቀት፣ ተሞክሮና ጥበብ የተዘጋጀ፣  በአገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች የሚመራ መሆን አለበት፡፡

ዕቅዱን የማስፈጸሚያ ፕሮግራም ወይም መርሐ ግብር ቀረፃ፣ በፕሮግራሙ ውስጥ በመደበኛም ሆነ በፕሮጀክት የአፈጻጸም መስመር የተቃኙ ዝርዝር ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሆኖ በጊዜ፣ በሥፍራና በሀብት አጠቃቀም አንፃር በቅደም ተከተል የሚተገበር መሆን አለበት፡፡

በአጭሩ የማገገሚያ መርሐ ግብሩ በአብዛኛው በአራት ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ ከሚከተሉት የዕቀድ ምሰሶዎችና መርህዎች ጋር ተቆራኝቶ መቀረፅና መተግበር አለበት፡፡ ሕይወት ማዳን፣ በተለይም ረሃብ እንዳይከሰት ማድረግ፣ ሰላምና ደኅንነት ማስፈን፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ ማቋቋምና ዘላቂነት ያለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የገበያና ንግድ ሥርዓት መዘርጋት ናቸው፡፡

እነዚህ ምሰሶዎች በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በጦርነት የወደሙና የፈራረሱ አገሮችን መልሶ ለመገንባት በኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራሞች ቀረፃና ትግበራ ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት በአውሮፓ ከፍተኛ ወድመት የደረሰባቸውን አገሮች መልሶ ለማቋቋም የተዘጋጀውንና የተተገበረውን የማርሻል ፕላን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በጀርመኑ መሪ በሒትለር በተጀመረው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በርካታ አገሮች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸው ስለነበር፣ በውቅቱ ብዙም ጉዳት ያልደረሰባቸው አሜሪካኖች ከጦርነቱ በኋላ የአውሮፓ በአፋጣኝ መገንባትና በኢኮኖሚ ማገገም ለራሳቸው ኢኮኖሚ ዕድገትና ጥንካሬ ወሳኝ እንደሆነ ተገነዘቡ፡፡ በዚህም ምክንያት በፕሬዘዳንት ሃሪ ትሩማን መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት የነበረው ጄነራል ጆርጅሲ ማርሻል ለአውሮፓ ማገገሚያ ፕላን አንዳንዴም ፕሮግራም (Economy Recovery Programme) የሚባል ነድፎ ወደ ትግበራ እንዲገባ አደረገ፡፡ ይህም የማርሻል ፕላን ተብሎ ይጠቀሳል፡፡

የማርሻል ፕላን እ.ኤ.አ. በ1948 በ15 ቢሊዮን ዶላር ለአራት ዓመት የትግበራ ጊዜ የተሰናዳ ሲሆን፣ የተመደበው ገንዘብ በወቅቱ ከአሜሪካ የአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ጋር ሲታይ ብዙ ነበር፡፡ ይህ ፕላን 16 አገሮችን መልሶ ለማቋቋም ወይም ለመገንባት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከአገሮቹ መካከል ጦርነቱን የቆሰቆሰችውና በርካታ ውድመት በአውሮፓ አገሮች ላይ ያደረሰችውን ምዕራብ ጀርመንን ጨምሮ እነ ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይ፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስና ኖርዌይ የመሳሰሉ አገሮችን ያካተተ ነበር፡፡

የማርሻል ፕላን በአራት ምሰሶዎችና ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የወደሙ ከተሞችን፣ ኢንዱስትሪዎችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ ማለትም የባቡር መስመሮችን፣ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ወደቦችን መልሶ መገንባት፣ በአውሮፓ አገሮች መካከል የነበረን የንግድ ክልከላና ከለላ ማስወገድ፣ በአውሮፓ የኮሙዩኒዝም መስፋፋትን ማስቆም፣ ለዚህ ተግባር የአሜሪካ ማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) ከተመደበው ገንዘብ የአምስት በመቶ ያህል የተመደበለት ሲሆን፣ በአብዛኛው በጀቱ በወቅቱ (እ.ኤ.አ. በ1948) በዩክሬን ውስጥ ለሚደረግ የስለላና የመረጃ ስብሰባ ሥራ ላይ እንዲውል የታቀደ ነበር፡፡

  1. በጦርነት ማግሥት ረሃብ እንዳይከሰት ማድረግ ነበር

እዚህ ላይ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች የተለያዩ አገሮችን ያማከለ የኢኮኖሚ መልሶ ማገገም ፕሮግራም ተሞክሮ፣ ለኢትዮጵያ በአገር ውስጥ እርስ በርስ ጦርነት ለወደመና ለተደመሰሰ ኢኮኖሚ ምን ፋይዳ አለው ብለው ሊከራከሩ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ምላሹ የጦርነቶቹ ዓይነትና አካባቢዎቹ ሳይሆን በማናቸውም ሁኔታ ከጦርነት ማግሥት ማገገም ስላለበት ኢኮኖሚ የዕቅድ ዝግጅቱ ማጠንጠን ያለበት ምሰሶዎች ምድናቸው የሚለውን ለይቶ ማወቅ ላይ ነው፡፡  ከማርሻል ፕላን እንደምንረዳው ለኢትዮጵያ ዛሬ ከጦርነቱ ማግሥት የሚታቀድ የኢኮኖሚ ማገገሚያና የተለያዩ ከተሞችንና አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ማጠንጠን ያለበት  በሕይወት ማዳንና ሰብዓዊ ድጋፎች፣  የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ግንባታና መልሶ ማቋቋም፣ ዘላቂነት ያለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራና ዳግም ሰላምና ደኅንነት በቀላሉ እንዳይናጋ በሚያደርጉ የአገር መከላከል ሥራዎች ላይ እንደሆነ ነው፡፡

ከማርሻል ፕላን በተጨማሪ በርካታ ከጦርነት ማገገም በኋላ የተሠሩ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራሞችን ከተለያዩ አገሮችና አካባቢዎች ማጥናትና መመርመር ሲቻል፣ ከመርህ አንፃር የምንማራቸው ደግሞ በአራት ነገሮች ላይ ያጠነጥናሉ፡፡ እነዚህም ቅደም ተከተል፣ አመራር፣ ተዋንያንና ሀብት ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የማገገሚያ ዕቅዱ መሆን ያለበት በጥንቃቄና በዝርዝር፣ ቅደም ተከተልን ያማከለና የተዘጋጀ፣ እንዲሁም የሚተገበር፣ በዕውቀት፣ በብቃትና በቆራጥ አመራር የሚመመራ፣ የኢኮኖሚ ተዋንያንን ሚና በሚገባ የለየና ያካተተ፣ ግልጽና ሊያሠራ የሚችል የሀብት ምንጭና የአጠቃቀም ሥርዓት የያዘ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ምሰሶዎች ላይ በመመርኩዝ እነዚህ አራት የማገገሚያ ዕቅድ መርሆዎች እንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡  

  • ቅደም ተከተል ያለው የሚተገበር ዕቅድ

በአንድ ሉዓላዊት አገር ውስጥ ከጦርነት ማግሥት የሚወሰዱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ማገገሚያ ዕርምጃዎች ከአፋጣኝ የደራሽነትና ሰብዓዊ ዕርዳታዎች (Emergency and Relief) ጀምሮ እሰከ ረዥም ጊዜ የዘለቄታዊ ልማት እንቅስቃሴዎች የሚዘልቅ ሥራን ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህንም በሚከተለው ማዕቀፍ ውስጥ ዘርዝሮ መከወን ይሻል፡፡

አንደኛ በጦርነት ማግሥት የኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥራ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ታሳቢ (Assumption) ያልበዛበት፣ ባልተዛባ፣ በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይገባል፡፡ ለዚህም ተገቢና ከፌዴራል እስከ ክልል፣ ብሎም እስከ ወረዳና ከዚያም በታች ተደራሽ መሆን እስካለባቸው የመንግሥት አስተዳደር አካባቢዎች የሚዘልቅ ወጥነት ያለው የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴና ቅጽ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡  ሁለተኛ በዚህ መሰል መረጃና ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ሁሉን አቀፍ፣ የዘርፍ/ሴክተሮች ስብጥርንና ግንኙነትን በሚገባ የለየና ያስተሳሰረ፣ ለማስተባበር የሚያስችል ጥልቅ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድና ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛ በተለያዩ አካባቢዎች በኢኮኖሚ ማገገሚያው መርሐ ግብር መሠረት በነቂስ ተለይተው መልሰው የሚገነቡ፣ የሚጠገኑና የሚታደሱ፣ የጦርነቱ ውጤት በፈጠረው አንድን የከተማ ሆነ የገጠር ማዕከል በዘመናዊና በተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የማምረቻና አገለግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ  የቅደም ተከተል ዝርዝር ባካተተ ሰነድ መሠረት፣ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችን በድርጊት ዕቅድ በጊዜ ሰንጠረዥ ተንትኖ ማሳየት ይገባል፡፡ የጊዜ ሰንጠረዡ ከአፋጣኝ የደራሽነትና ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ሥራዎች ጀምሮ በአጭር፣ በመካካለኛና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለይቶ የሚያሳይና በዚህ መሠረትም የሚተገበር/የሚፈጸም መሆን አለበት፡፡

በሦስተኛው የማዕቀፉ ክፍል እንደተጠቀሰው የቅደም ተከተል አወጣጡ በመጀመርያ ማተኮር ያለበት በጦርነት በወደሙና በተጠቁ አካባቢዎች ረሃብ እንዳይከሰት ማድረግ ነው፡፡ በተለይ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በማግሥቱ ሊከሰት የሚችልን የረሃብ አደጋ አስቀድሞ መከላከልና እንዳይከሰትም ማድረግ፣ በቅድሚያ መሠራት ካለባቸው ሥራዎች መሀል ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቡን ለመመገብ በሚያስችል የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ትኩረት መስጠትን ይሻል፡፡

ረሃብን እንዳይከሰት ከማድረጉ ሥራ ውስጥ በጦርነት ማግሥት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ዕለታዊና ወቅታዊ የምግብ፣ የመጠጥ ውኃና የአልባሳት አቅርቦት ሥራ ነው፡፡ ምግብና አልባሳት በአስቸኳይ መድረስ ወዳለባቸው አካባቢዎች መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ ጊዜያዊ መጠለያዎች ዘላቂነት ሊኖራቸው ከሚችሉ የመጠለያ ግንባታዎች ጋር በተናበበ ሁኔታ ታቅደው ከውኃ አቅርቦትና ተደራሽነት ጋር ተቀናጅተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በማይራራቅ ትኩረት ተያይዞ መሠራት ያለበት  ደግሞ የጤናና ትምህርት ተቋማትን የመጠገንና መልሶ የመገንባት፣ በአደረጃጀት የሚያስፈልጋቸውን ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ቴክኒካዊና ቴክኖሎጂያዊ፣ እንዲሁም የፋይናንስ ግብዓቶችን በማቅረብ ወደ ሥራ ማስገባት ነው፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ሥራዎች ጋር በተጓዳኝ ወይም በአጭር ጊዜ ዕሳቤ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎቶች የመልሶ ማገገሚያ ፕሮግራም መሠረት የከተሞችንና የገጠር ገበያ፣ ከእነዚህ ጋር የተሳሰሩ የንግድና መሰል የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎት ማዕከላትን ከሥፍራም ሆነ ከተቋም አንፃር መልሶ የማቋቋምና የመገንባቱ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህ ሥራ ከሴክተሮችና ከተዋንያን ልየታና ስብጥራዊ ድርሻ አኳያ በሚገባ ተለይቶና ተቀናጅቶ መተግበር አለበት፡፡ የከተሞችም ሆኑ የገጠር ማዕከላት በአንፃራዊ ይዘታቸው ዘላቂነት በሚኖራቸው ዘመናዊነትን የተላበሱ ከመሠረታዊ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ጋር የተቀናጀ የቅየሳ ሥራ ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው፡፡  

የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የስልክ አገልግሎት፣ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ሥራ ከመንገድ ዕድሳትና መልሶ መገንባት፣ እንዲሁም አዳዲስ መንገዶችና ድልድዮችን ከመሥራት ጋር ተጣምሮ መጠናትና በዘላቂና ዘመናዊ የዕቅድ ሥራ ላይ ተመሥርተው  መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ በማገገሚያ ፕሮግራሙ ቀረፃና ትግበራ ወቅት የከተሞችና ገጠርማ አካባቢዎች አስተዳደራዊ ድንበር ዘለል መሠረተ ልማቶችን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ሥራው በአስቻይና አመቺ ሁኔታዎች የጎለበት ይሆን ዘንድ በሀብት አሰባሰብ፣ አቅርቦትና አጠቃቀም ዙሪያ ዘመናዊና ጊዜው የዋጀውን የመረጃ አሰባሰብ፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት በቴክኖሎጂ እንዲታጋዝ ማድረግ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ጦርነት ሲኖር የራሱ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚኖረው ሁሉ፣ ሲቆምም ደረጃው ያንን ባያክልም ተፅዕኖው ጉልህ ይሆናል፡፡ በተለይም ከግንባር ተመላሽ የሆኑ የታጠቁና የሠለጠኑ ሥራ አጦች ይፈጠራሉ፡፡ ለተመላሾቹ ጉዳዩ የመኖር አለመኖር ወይም በቀላሉ የገንዘብ ማግኛ መንገድ ይሆንና ለዘረፋ በጠራራ ፀሐይ ሊያስወጣ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ሰላምን ያናጋል፡፡ ሰላም የሚጠፋው ደግሞ በየመንደሩ ስለሚሆን፣ ክስተቱ አደገኛ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔ መበጀት አለበት፡፡ መፍትሔ ለማበጀት ደግሞ ቢያንስ የሚከተሉት መሠራት አለባቸው፡

ከየክልሉ በወዶ ዘማችነት ከዘመተው ምን ያህሉ እንደተመለሰ መረጃ ማሰባሰብ፣ ከጦርነት መልስ ምን ሊሠራ እንደሚችል ማጥናት፣ በተለይ ክልሎች በዚህ የሰው ኃይል ላይ የሚያደርጉት ጥናት ከወታደራዊ ሥልጠናው፣ ታጥቆት ከነበረው መሣሪያ ዓይነት ጋር ታይቶ፣ ትጥቁን ማስፈታት ወይስ እንደያዘ ማቆየት፣ ወዘተ ጉዳዮች ላይ ዝርዝርና በርካታ ሥራዎች መሥራት አለባቸው፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ ጥያቄው ለጊዜው ሳይሆን ለዘላቂነት ሊፈታ በሚችልበት ሁኔታና አቅጣጫ መቃኘት አለበት፡፡ አለበለዚያ ለመሣሪያ ያገኘው ቅርበትና የተሰጠው ሥልጠና ወደፊት ራሱን በዘርፎ አዳሪነትና በመንግሥት ተቀናቃኝነት ጎራ እንዳያሠልፈው የሚያደርግ ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡

3.4 በዕውቀት የሚመራ፣ በሙያተኞች የሚታገዝና ብቃት ያለውቆራጥ አመራር

የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድ ዝግጅትና ፕሮግራም ነደፋ ወደ ተግባር ተቀይሮ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ከተፈለገ፣ ብቃት ያለውና ውጤት የሚያመጣ አመራር ይሻል፡፡ አመራሩ መንግሥታዊ ሆኖ፣ ሌሎች ተዋንያንን በየዓውዱ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚገባቸውን ቴክኒካዊና ሙያዊ መሪነታቸውንና ተግባሪነታቸውን የሚያከብር መሆን አለበት፡፡ ዕቅዱ በየዓውዱ በዘርፍና ሴክተር በዝርዝር ሲከናወን በሙያተኞች የተደገፈ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሒደትም በዋነኛነት ኢኮኖሚያዊ መሠረት መያዝ አለበት፡፡ ፖለቲካውም የዚህን ዓውድ መሠረታዊነት በሚገባ የተገነዘበና የሚጠቀምበት መሆን አለበት፡፡

ፖለቲካው ውጤታማ ሀብት (ሰዋዊ ሀብትን ጨምሮ) ለማስተዳደርና ለመምራት የመንግሥታዊና  ሕዝባዊ  አካላትን ችሎታና ብቃት የሚያጎለብት ሆኖ፣ በተለይም በዕቅድ አፈጻጸሙ ወቅት የመወሰን ሥልጣንን ከሀብት ድልደላና አጠቃቀም፣ ጊዜና ሁኔታ ጋር በማጣጣም በሚገባ ለመጠቀም በሚያስችል አቅጣጫ ላይ የተቃኘ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ ተገቢና ወቅታዊ የአገርና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችንና ክስተቶችን ያገናዘበ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲና ስትራቴጂን መንደፍ ይኖርበታል፡፡

ፖለቲካዊና መንግሥታዊ አመራሩ ከኢኮኖሚ ማገገም ዕቅዱና ዝርዝር መርሐ ግብር ቀረፃና አፈጻጸም አንፃር፣ ከሀብት ማሰባሰብ ጀምሮ እስከ መደልደልና ተዋንያንን በተግባር ክዋኔው ላይ ከማሰማራት አኳያ ውጫዊና አገራዊ ተዋንያንን የሚስብ፣ የሚያሳትፍ፣ የሚደግፍና የሚያሳልጥ ሆነ እንዲገኝ ግድ ይላል፡፡

ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት እንደተስተዋለው፣ በማገገሚያ ፕሮግራሙ ቀረፃም ሆነ ትግበራ ወቅት ፖለቲካው አብጦና ገኖ፣ መንግሥታዊ በጀት በቅድሚያ ለዴሞክራሲና ፍትሕ ማስፈን ውሎ፣ ይህም የኢኮኖሚ ማሻሻያና ማሳደጊያ ሥራው ሊሳለጥና ውጤታማ ሊሆን የሚችል ዴሞክራሲና ፍትሕ ሲሰፍን ነው በሚል ፈሊጥና ትርክት የሚመራ ከሆነ ኢትዮጵያ በሚፈለገው የጊዜ፣ የሥራ ክዋኔና ጥራት ከገባችበት የጦርነት ኢኮኖሚ ዝቅጠት ውስጥ ልትወጣ አትችልም፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድ ዝግጅትና ትግበራ ወቅት የፖለቲከኞች ጨዋታ፣ በተለይም መንግሥታዊ ሥልጣኑን የያዙት ፖለቲከኞች ዕርባና ቢስ በሆኑ የዴሞክራሲና የፍትሕ ማስፈን እንቅስቃሴ የተጠፈነጉ መሆን የለባቸውም፡፡

በኢኮኖሚ ማገገም ፕሮግራም ወቅት ከፍተኛ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ለተለያዩ መደበኛና ፕሮጀክትን መሠረት ላደረጉ፣ ማለትም ለካፒታል በጀት ሥራዎች ግብዓት ስለሚሆን፣ ይህን ሀብት በሚገባ በብቃትና በውጤታማነት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለአጠቃቀሙ በተለያየ የመንግሥት አከፋፈል ውሰጥ ማለትም በፌዴራል፣ ክልል፣ ዞን፣ወረዳ ብሎም ቀበሌ፣ ብሎም በእነዚህ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ተቋማትና የአደረጃጃት መዋቅር ደረጃ ያሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የአመራር አካላት ተብለው በሚንቀሳቀሱ አካላት ዘንድ በአቅም፣ በችሎታና በብቃት የሚደናቀፍ ወይም ለአሉታዊ ውጤት የሚዳረግ መሆን የለበትም፡፡

የአመራር  አካላቱ የሚከተሏቸው እሴቶችና መስተጋብሮች ከኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከሙሰኝነት፣ ከብሔርተኝነትና ጎጠኝነት፣ እንዲሁም ከቤተ ዘመዳዊነት የራቁ፣ እነዚህን የሚጠየፉና የፀዱ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ወቅት ከእነዚህ እሴቶች በተፃራሪ ቆመው የሚሠሩ ከተገኙ ጥዩፍ ድርጊቶችን ያለ መቋቋም ዜሮ ፖሊሲን መተግበር ይገባል፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ማገገም ሥራ ውጤታማ የሆኑ መርሐ ግብሮችና ስኬቶች የተመዘገቡት ለምሳሌ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር ይህን መሰል ፖሊሲ በመተግበራቸው ነው፡፡

በዓለም ዙሪያ በጦርነት ውስጥ ቆይተው ወደ ተረጋጋና አንፃራዊ ሰላም ወደ ሰፈነባቸው አገሮች በማማተር፣ በእነዚህ አገሮች ከተቀረፁና ከተተገበሩ የኢኮኖሚ ማገገሚያ መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮግራሞች ስኬት መማርና ማስተዋል ከሚገባን ቀዳሚው፣ የማገገሚያ ዕቅዱም ሆነ ፕሮግራም ነደፋውና ትግበራ መሪዎች ማንነት ላይ ነው፡፡

ስኬታማ ከሆኑት አገሮች የምንማረው ለስኬታማነት ዕቀዱን የማዘጋጁትም ሆነ የማስፈጸም ሥራው በአገሪቱ ዜጎች የሚመራ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የቀረፃውም ሆነ የትግበራው መሪነት ለውጭ ኃይሎች ከተተው፣ ወይም እነሱ ለሚያሾሯቸው ዓለም አቀፍ የልማትና የገንዘብ ተቋማት ባላሙያዎች ከተሰጠ አገሪቱና ሕዝቧ ከጦርነቱ በኋላ ለዘላቂና የከፋ ብዝበዛና ጥልቅ ድህነት ራሳቸውን አመቻችተው የሚሰጡ ይሆናሉ፡፡

የማገገም ዕቅድ ዝግጅትና አተገባበር አመራር ከዜጎች እጅ ውጭ ከሆነ መንግሥት በውጭ ኃይሎች የሚቃኝ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በተለይም በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ እንደሆነና  በዓለም አቀፉ በዝባዥ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በሚመራው የኮርፖራቶክራሲ ሥርዓት ውስጥ የታቀፈ አመራርና ሙያተኞች እንደተማከለ ይጠቁማል፡፡ በዚህ ወቅት የአገሬው ዜጋ (በአገር ውስጥ ያለውም ይሁን በውጭ፣ ዳያስፖራውን ጨምሮ) ጥገኛና የኮርፖራቶክራሲ ሥርዓት መሣሪያ የሆነን መንግሥት በመታገስ ዜሮ ፖሊሲ ላይ በተመሠረተ መቅጫ ዘዴ  ሊቀጣው ይገባል፡፡ በተለይም በምርጫ ካርዱ ይህን መሰል የጥገኛ አመራር ያለው የመንግሥት ሥልጣን የያዘውን የፖለቲካ ቡድን ከሥልጣን እንዲወርድ በማድረግ የቅጣት ብይን መስጠት አለበት፡፡

3.5 የዋና ዋና ተዋንያንን ሚና በዘርፍና መንግሥታዊ አደረጃጃት

በማናቸውም ጊዜ፣ በተለይ ግን በጦርነት ማግሥት የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድና ፕሮግራም ቀረፃና ትግበራ የኢኮኖሚ ተዋንያንን ሚና በሚገባ መለየት፣ በሚና ድርሻ ዕውቅናና ክፍፍል ላይ ተመሥርቶ የተቀናጀና ትብብራዊ ሥራን ያካተተም መሆን አለበት፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ የኢኮኖሚ ተዋንያን ሲባል የሚያመላክተው የመንግሥት፣ የሕዝብ፣ የግሉ ዘርፍ  ተዋንያን፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎችን ነው፡፡ እነዚህን መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች (መያድ) የሚባሉትን ጨምሮ በማገገሚያ ፕሮግራሙ ቀረፃና አፈጻጸም ውስጥ የሚኖራቸውን ድርሻ በዝርዝር ለይቶ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚባለው ግለሰብና ቤተሰብ በግብዓት ሆነ በሸመታ ኢኮኖሚው ውስጥ ወይም በማምረትና አገልግሎት ሥራ ውስጥ ያሉትን ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ የሚና ድርሻ ይለይ ሲባል፣ በማገገሚያ ዕቅድ አተገባባር ወቅት ግን የልማታዊ ሥራዎችን እንቅስቃሴ ትስስር የሚያፀና፣ በዚህ መሠረት ዕቅዱም በኢኮኖሚ ዘርፍና ሴክተሮች ቅንጅትና ትስስር ረገድ የተሰናሰለ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በተለይ ከ2013 ዓ.ም. መባቻ ጀምሮ በጦርነት ለተጎዳው ኢኮኖሚዋ የሚዘጋጅ የማገገሚያ ወይም መልሶ ግንባታና ማቋቋሚያ ዕቅድና ፕሮግራም ውስጥ፣ መንግሥት የሚለው ተዋናይ በጥቅሉ የሚገለጽ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በዕቅዱ ዝግጅትም ሆነ በትግበራው ወቅት አግባብነት ባለው መሠረት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በተዋረድም ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስና በሥራቸው ባሉ የተለያዩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሥራ ድርሻቸው ምን እንደሚሆን ተለይቶ መካተት አለበት፡፡

ተቋማት ሲባል በእነዚህ የተለያዩ የመንግሥት አወቃቀሮች ውስጥ ያሉ የዘርፍ/ሴክተር አደረጃጀቶችንና በኤጀንሲ ወይም ባለሥልጣን ደረጃ የተቋቋሙትን አስፈጻሚና ሕዝባዊ የምርትና አገልግሎት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶችን ሁሉ ያካትታል፡፡ በዕቅዱ ዝግጅት ጊዜም ሆነ በመተግበሪያ ምዕራፉ ወቅት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚከናወን ማናቸውም ሥራ የኋልዮሽ ሆነ የፊት ለፊት ግንኙነቱ  (Backward and Forward Link) በሚገባ መለየት አለበት፡፡ ለምሳሌ በአንድ የታሸገ ምግብ አምራች ፋብሪካ መልሶ ግንባታ ወይም አዲስ የማቋቋም ሥራ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር/ቢሮ የንግድ ሚኒስቴር/ቢሮ፣ የግብርና ሚኒስቴር/ቢሮ፣ የመንገድና ትራንስፖርት ሚኒስቴር/ቢሮ፣ የውኃና ፍሳሽ ሚኒስትር/ቢሮ፣ የጤና ሚኒስቴር/ቢሮ፣ ወዘተ ሚናና የሥራ ድርሻ መለየትና ለትግበራ በተቀናጀና በተሳሳረ ይዘቱ መሰነድ አለበት፡፡

  • የዋና ዋና ተዋንያንን ሚና በሥፍራ እና የአስተሳሰብ መልሶ ግንባታ

ከቦታ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. ከተደረገው ጦርነት ማግሥት፣ በኢኮኖሚ ማገገሚያው ዕቅድ ሕዝብንና መኖሪያ ሥፍራውን የማቋቋምና የመሠረተ ልማቱን ግንባታ መርሐ ግብር በሦስት ከፍሎች ለይቶ ማየት ተገቢ ነው፡፡

አንደኛው በጦርነቱ በጣም የተጎዱ አካባቢዎችን እነዚህም በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ ሁለተኛ በትግራይ ክልል ውስጥ መሠራት ያለባቸው የኢኮኖሚ ማገገሚያ ሥራዎች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መታየትና በማገገሚያ ዕቅዱ ዝግጅት ወቅት ውስጥ መካተት ያለበት ከላይ በአንደኛ እና በሁለተኛ ክፍል ውስጥ ያልተካተቱ፣ በቀጥታም ሆነ ቀጥታኛ ባልሆነ መንገድ ግን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማቶቻቸውና  እንቅስቃሴዎቻቸው የተጎዱባቸው ወይም የወደሙባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በዚህ ረገድ ትኩረት የሚደረግባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅዱን በአካባቢያዊ ስብስቦሽ በማደራጀት ዝርዝር የፕሮግራሞችና የፕሮጀክቶች ቀረፃና አተገባባር ሰነድ ማዘጋጀት ጠቀሜታን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በማጥናትና በመማር መረዳት ይቻላል፡፡ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1940ዎቹ ውስጥ ለአውሮፓ አገሮች ከጦርነት ማግሥት ኢኮኖሚያቸው እንዲያገግም ከተቀረፀውና ከተተገበረው የማርሻል ፕላን በተጨማሪ በእስያ በጃፓን፣ ቻይና፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ የተደረገው ዝግጅትና ትግበራ ማጥናት ብዙ ትምህርታዊ ጭብጥ ሊገኝበት ይችላል፡፡

ከእነዚህ አገሮች ተሞክሮ ጥናት በተጨማሪ መዳሰስና መጠናት ያለበት ጉዳይ ኢትዮጵያን በመሰለች፣ በተወሳሰበ የብሔርና የጎጠኝነት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ አደንዛዥ የፖለቲካ ዕፅ እየበቀለ በተለይ ተማርን የሚሉትን ዜጎቿን በሥልጣን ፍለጋ አባዜ እያሰከረ በሚተራመሱባት አገር ውስጥ፣ ከ2013 ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም. ማግሥት ከዘለቀው ጦርነት በኋላ የተለያዩ ግጭቶች ቀጥለው የሕይወት መጥፋት፣ የሀብትና ንብረት ውድመት፣ የከተሞች መቃጠልና መፈራራስ ቀጥለው ባሉበት ሁኔታ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቀስቃሴውን መልሶ ለመገንባት እንቅፋት አንዳይሆኑ መሠራት ያለባቸው የአስተሳሳብና የሥነ ልቦና ለውጥ አምጪ ሥራዎች ምን መሆን፣ የትና በማን መሠራት እንዳለባቸው መለየትና አቅዶ መሥራትም ያስፈልጋል፡፡  

በእርግጥ ኢትዮጵያን በመሰለች የእርስ በርስ ጦርነት በተደረገባት አገር ውስጥ ግጭቱ በቀላሉ ይሽራል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ በግጭቱ ተሳታፊዎች፣ በተለይም ከግጭቱ ለኳሾች ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ጊዜ ወሳጅ ነው፡፡ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ግንባር ለግንባር ፊልሚያው ቢቀር እንኳ፣ ሽምቅ ውጊያው በቀላሉ የሚቆም አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ የመልሶ ግንባታው ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡

የአማራን መሬት የያዘው ሕወሕት እሞታለሁ እንጂ አለቅም ሲል፣ ዓላማው ግልጽ ያልሆነው ሸኔ አጥፊና አፈናቃይ ድርጊቱን  ሲቀጥል በኢኮኖሚ ማገገም ዕቅዱ አፈጻጸም ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ አይቀሬ ነው፡፡ በውጊያው ላይ የተሳተፈውና አሁን ጦርነቱ አብቅቷልና በቃህ የተባለው ሚሊሺያ፣ ፋኖ፣ ሌላም ሌላም ጦር ይዟልና በትንሽ ጉዳዮች አለመርካት ሳቢያ መሸፈትና ሰላም ማሳጣት ያምረዋል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ከጦርነቱ ማግሥት የሚደረግ የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በማርሻል ፕላን ታግዞ እንደተደረገው የተፈናቀሉን መልሶ ማቋቋም፣ የወደሙ ከተሞችንና መሠረተ ልማቶችን መገንባት የሚቀለውን ያህል አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ድንገተኞች፣ አኩራፊዎች፣ ተጠቃን ባዮች፣ ቂመኞች በኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የወደሙ ከተሞችንና መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራን ቀላል አያደርጉትም፡፡ በዚህ ምክንያት ከዕድገትና ኑሮ መሻሻል ይልቅ ድህነት ሲጎለብት፣ የረጂ ወገኖች እጅ ሲዝል፣ የአጥፊዎቹ የኋላ ደጋፊዎች እጅ ሲረዝምና ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነው ድጋፋቸው አሸባሪዎችንና አፍራሽ ኃይሎችን የልብ ልብ ሰጥቶ ግጭቶችን በየቦታው ሲያስፋፉና ሲያፋፍሙ፣ የመልሶ ግንባታውን ሥራና ውጤቱን ያዘገየዋል፡፡ ሒደቱንም ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከቁሳዊ መልሶ ግንባታ ይልቅ በአስተሳሰብና በሥነ ልቦና ግንባታ ላይ በሚገባ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ በርግጥ አንደኛው መጀመርያ ሌላኛው ተከታይ ሥራ ይደረግ ማለት ሳይሆን፣ ቁሳዊውን የግንባታ ሥራ ከአስተሳሰብና ሥነ ልቦና ግንባታው ጋር አቀናጅቶ ማቀድና መተግበር ይቻል ዘንድ ይህ ጉዳይ በመልሶ ግንባታው ፕሮግራም ቀረፃ ወቅት በሚገባ መታየት አለበት ለማለት ነው፡፡

3.7 ግልጽ የሆነ የሀብት ምንጭ፣ አጠቃቀም፣ ክትትልና ግምገማ

የኢኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድና ፕሮግራም ግልጽ የሆነ የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ብሎም ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት የሚከተል መሆን አለበት፡፡ ከመነሻችን በዕሳቤና በአስተምህሮ ክፍል እንደ ተብራራው፣ ሀብት ሲባል ጉልበት ወይም ሰብዓዊ ካፒታል (የሠለጠነ ሆነ ያልሠለጠነ የሰው ኃይልን አቅርቦትና አጠቃቀምን) ያካትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መሬት፣ ማዕድንና ተጓዳኝ የተፈጥሮ ፀጋዎች፣ ቋሚ ተክሎች፣ ደንና የደን ውጤቶችና እንስሳት፣ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ መሠረተ ልማቶችና የቱሪስት መስህቦች፣ ለልማት ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሣሪያዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ተሸከርካሪዎችና ዕቃዎች፣ ገንዘብና ሌሎች የፋይናንስ ክምችቶችን ያካትታል፡፡ ግልጽ የሆነ የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ብሎም ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት የሚከተል መሆን ሲባል፣ እነዚህንና በሥራቸው ተዘርዝረው ሊቀርቡ የሚችሉትን በዓይነትና በብዛት በሚገባ ለይቶ ማወቅና በዕቅዱ የመደበኛ ፕሮግራም ወይም የፕሮጀክት ዝግጅትና አፈጻጸም ጊዜ ውስጥ ከሚሠሩት ሥራዎች አንፃር ለይቶ ማካተትን ያመላክታል፡፡

በእያንዳንዱ የሀብት ክፍል ውስጥ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን ሊለይ የሚችል ክፍተት ካለም ክፍተቱን አቅዶ ለመሙላት መታቀድ አለበት፡፡ ክፍተቱ በሥልጠና ወይም በትምህርት ግኝት ይሟላል በሚል ታሳቢ ግን ሥራዎች መታቀድ የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ ከሰው ኃይል አንፃር በጉልበት፣ በሙያና በዕውቀት ሊሠራ የሚችለውን መለየት፣ በዚህም ሊሠራ የሚችለውን ሥራ ማቀድ እንጂ፣ ገና ለገና ሠልጥኖ ይመጣል ወይም ለትምህርት ተልኮ ይመለሳል በሚል መታቀድ የለበትም፡፡

በአጭሩ በሀብት አቅምና አጠቃቀም ረገድ ዋና መርህ መሆን ያለበት ‹‹ባለ ሀብት፣ የመተግበር አቅም፣ ችሎታና ብቃት ሊሠሩ የሚችሉትን ሥራዎች አቅዶ ውጤታማ ሥራ መሥራት የሌለን አቅም ደግሞ አቅዶ መገንባት፤›› የሚል መሆን አለበት፡፡ 

በተለይ ሙያተኞችን (Professionals) በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉም ሆኑ በውጭ የሚገኙና ለዕቅዱና ለፕሮግራሙ ትግበራ ሥራ ላይ ሊሰማሩ የሚችሉ ሙያተኞች በግልም ሆነ በሙያ ማኅበሮቻቸው በኩል ሆነው ለዝግጅቱም ሆነ ለትግበራው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ተለይቶ መታወቅና መካተት አለበት፡፡ የዕቅዱን ዝግጅትና አፈጻጸምም በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሙያተኞች እንዲመሩት ይገባል፡፡ የውጭ አገር ሙያተኞችን በአማካሪነት መቅጠር ወይም በዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በኩል በቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎት አማካይነት ማካተት ይቻላል፡፡ መሪ ከተደረጉ ግን ዕቅዱ የማይተገበር እንደሚሆን አስቀድሞ መገመት ይገባል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና ደኅንነት እየጎለበተ ሲሄድ በመከላከያ ሠራዊቱ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የሥልጠናና ትምህርት ዲስፕሊኖች ሠልጥነውና ተምረው የሚገኙ ሙያተኛ የሠራዊት አባላትን፣ ማለትም የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንቲስቶች፣ ኢንጂነሮች፣ ወዘተ በመልሶ ግንባታው ሥራ ላይ ሊሠማሩ ይችላሉና በወቅታዊ የድርጊት ዕቅዱ ውስጥ የሚካተቱበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ከመሬት ጀምሮ በማህፀኗ ውስጥ ያሉ ማዕድናት በዕቅዱ ወቅት ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለባቸው፡፡ እነዚህ ሀብቶች በጥሬ ዕቃ ንግዱ ውስጥ ሊያስገኙት ከሚችሉት የፋይናነስ ምንጭነት ጀምሮ፣ በመልሶ ግንባታው ወቅት በሚሠሩ የተለያዩ መሠረተ ልማት ዝርጋተዎች ወቅት ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ አንፃር፣ ከአስቸኳይ ጊዜ የዕርዳታና የመልሶ ማቋቋም እሰከ ረዥም ጊዜ በሚዘልቅ የከተሞች ግንባታ፣ ማስፋፊያና ማዘመኛ ዕቅድ ውስጥ መካተት አለባቸው፡፡

የማይጨበጡና የማይዳሰሱ እንዲሁም የሚጨበጡና የሚዳሰሱ የቱሪዝም ሀብቶችም በመልሶ ግንባታው ሆነ በዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ማስፋፊያው ዕቅድ ውስጥ በሚገባ ተለይተው መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ሀብቶችን በአፋጣኝ መልሶ መገንባት ወይም ማቋቋም፣ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘትም ያስችላል፡፡ ከፋይናንስ አቅርቦትና አጠቃቀም አንፃር አገሪቱ ከሕዝብ ልታገኘው የምትችለው ምን ያህል እንደሚሆን በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆኑ ዘዴዎች ለይቶ ማስላትን ይሻል፡፡

የመንግሥት በጀት ከጠቅላለው የገቢ መጠን ጋር የተዛመደ ስለሚሆን፣ በአገራዊ ገቢና ታክስ ተዛምዶ ቀመር መሠረት ለመልሶ ግንባታው በታክስና ቀረጥ፣ እንዲሁም ከሌሎች መንግሥታዊ ገቢ ምንጮች ጋር የሚናበብ ዕቅድ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በተለይ ሕዝባዊ የቦንድ ሽያጮችን ለዚህ ዕቅድ ማስፈጸሚያነት መጠቀም ይቻላል፡፡ በእነዚህና መሰል ምንጮች ተጠቅሞ በውጭ ኃይሎች የዶላር ስጦታ ምክንያት በዕቅዱ ዝግጅት ጊዜም ሆነ በአፈጻጸሙ ወቅት ሊደረጉ የሚችሉ አሉታዊ ውጤት ያላቸውን መሰሪ ሥራዎችና ተፅዕኖዎች መቀነስ ይቻላል፡፡

ሕዝብ እንዳስፈላጊነቱ ሊሳተፍባቸው የሚችሉ የቦንድ ሽያጮችን በፋይናንስ ምንጭነት መጠቀም ይገባል፡፡ የቦንድ ሥርዓቱ በርካታ ዜጎችን ገቢያቸውን ባማከለ ቦንድ ሊገዙና በዚህም የኢንቨስትመንት ባህልን የሚማሩበት ማድረግ ሲቻል፣ ለየት ባለ ሁኔታም ባለሀብቱን በከፍተኛ የግዥ ተሳትፎ ሊስብ የሚችል ሆኖ ሥርዓቱ ሊደራጅ ይገባል፡፡ በተለይም ለባለሀብቱ በቦንድ ግዥ ወይም ለመልሶ ግንባታው ሊውል በሚችል፣ ከትርፍ ጋር ተያያዥ የሆነ ቅቡልነት ያለው ለመልሶ ግንባታው የሚውል በተመጣጠነ የወለድ ግኝት የሚደራጅ የቦንድ ፋይናንስ ሥርዓት መመሥረት ይገባል፡፡

ከውጭ የሚገኝ ፋይናንስ ከምንጩ ዓይነት፣ ከአቅራቢው ፍላጎትና ተጠቃሚነት ጋር በዝርዝር በሚደረግ ጥናት ተለይቶ፣ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ሥራ ወደ አገር ውስጥ እንዲፈስ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተቆራኝተው በኢንቨስተርነት ሊመጡ የሚችሉ የውጭ ኃይሎችን፣ የውጭ አገሮችን፣ የሁለትዮሽና ብዝኃ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎችን ጨምሮ ለዕቅዱ የገንዘብ ምንጭነት ማካተት ይቻላል፡፡ ይህ መሆን ያለበት ግን ቀደም ሲል  እንደተገለጸውም፣ የማገገሚያው ዕቅድና ፕሮግራሞቹ በኢትዮጵያውያን መሪነት በሚዘጋጁበት ሥርዓት ላይ ከተመሠረቱ በኋላ መሆን አለበት፡፡ የውጭውን ተፅዕኖ ለመግታት ያግዛልና ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተለያዩ የሚዲያ አካለት እንደተገለጸው አንዴ የፈረንሣይ መንግሥት ገንዘብ መድቦ ስለመልሶ ግንባታው ሊያጠናልን ነው፣ ወይም ከአንዳንድ ክልሎች እንደተነገረው የጥናት ቡድን አቋቁሜ የገንዘብም ሆነ የሰው ቅጥር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሊያደርግልኝ ነው፣ ወይም ‹‹ኢትዮጵያን እንከላከል-ከአየርላንድ›› ፈንድ ሰብሰስቤ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የመልሶ ግንባታ ልሠራ ነው፣ ወዘተ. እየተባለ በዚህ ትርምስ መሀል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመልሶ ግንባታው ከዓለም ባንክ ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ብድር ጠይቆ ተፈቀደለት፣ ግን ፈረንሣይና ጀርመን የሚያሾሩት የአውሮፓ ኅብረት ብድሩን ተቃወመ የሚሉትና ተመሳሳይ መረጃዎች የሚጠቁሙን የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩን ጥልቀትና ስፋት በሚገባ አጢኖ እየተዘጋጀበት እንዳልሆነ፣ ቢያንስ ለጥናቱ ራሱ ወጪ አድርጎ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሙያተኞች በግልም ሆነ በሙያ ማኅበሮቻቸው በኩል እንዲሳተፉ እያደረገ እንዳልሆነ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ውጤቱ አስከፊና ለመንግሥት ህልውናም አሥጊ እንደሚሆን መጠቆም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይታሰብበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹ኢኮኖሚው – ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ፣ እንዲሁም ኮርፖራቶክራሲ›› የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባቢያን ያቀረቡ አንጋፋ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል demesec2006@gmail.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...