Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዒድ አልፈጥር ሲከበር

ዒድ አልፈጥር ሲከበር

ቀን:

በሕዝበ ሙስሊሙ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነው ዒድ አልፈጥር ሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ይከበራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዓለም ዙሪያ ሙስሊሞች ዒዱን ለማክበር ሲዘጋጁ ሰንብተዋል፡፡

ከረመዳን ወር ሙሉ ጾም በኋላ የሚመጣው ዒድ አልፈጥር የሦስት ቀናት ክብረ በዓል ነው ይላል ስታንዳርድ ዩኬ የተሰኘ ድረ ገጽ፡፡ ክብረ በዓሉ የሚጀመረው ሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን መሆኑንና የሚዘልቀውም እስከ ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን ድረስ እንደሆነም ያክላል፡፡

በፀሓያዊዎቹ የኢትዮጵያም ሆነ የጎርጎርዮሳዊው ቀመር ኢስላማዊ ዒዶች (በዓሎች) በየዓመቱ የሚውሉበት ቀን የሚቀያየረው አቆጣጠሩ የሚከተለው ሐሳበ ሒጅራ (የሒጅራ ካሌንደር) በመሆኑ ነው፡፡ የሒጅራ አቆጣጠር ሙሉ ለሙሉ የጨረቃ አቆጣጠር የተመሠረተ ሲሆን፣ ጨረቃ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ የምታልፍበትን ጊዜ ያሰላል፡፡ የማንኛውም እስላማዊ ወር መባቻ ጨረቃ በምትበቅልበት ጊዜ ሲሆን፣ ይኼም  የሚረጋገጠው በሃይማኖቱ ባለሥልጣት ነው፡፡

- Advertisement -

የጨረቃ ዓመት 12 ወራት ሲኖሩት ቀኖቹም 354 ናቸው፡፡ ይህም ከፀሐይ ዓመት በ11 ቀናት በማነሱ የእስልምና በዓላት ቀናት በዓመት ከ10 እስከ 11 ቀናት ወደፊት ይሄዳሉ፡፡

በእስልምና አቆጣጠር ዒድ አልፈጥር ሁልጊዜ የሚውለው በአሥረኛው ወር በሸዋል የመጀመሪያ ቀን ነው፡፡

ዒድ አልፈጥር ምንድነው?

የዚህ ኢስላማዊ ክብረ በዓል ስያሜ ጾምን ከማቆም ጋር ይያያዛል፡፡ የረመዳን ጾም መጠናቀቁን የሚያመላክት ነው፡፡ ዒድ አልፈጥር ረመዳን ካለቀ በኋላ በማግሥቱ ይጀመራል፡፡

ዒስራ አራሁ የተባሉ ጸሐፊ በስታንዳርድ ዩኬ ድረ ገጽ እንደገለጹት፣ ‹‹ይህ ዒድ ሙስሊሞች የረመዳንን ጾም እንዲያልፉ የሚያስችል የአላህ የብርታትና የፅናት ስጦታ መንፈሳዊ በዓል ሆኖ ይታያል፡፡›› ወቅቱ ዘካት አል ፈጥር በመባል የሚታወቀው የችሮታ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ለድሆች ምግብም ሆነ ገንዘብ እንዲለግሱ ይጠበቃል፡፡

ሙስሊሞች ዒድ አልፈጥርን እንዴት ያከብራሉ?

የዒድ አከባበር የሚጀምረው ጎሕ ሲቀድ ነው፡፡ እሱም ብዙውን ጊዜ በመስጊድ ውስጥ ይከናወናል፡፡ ከሶላት በኋላ ሙስሊሞች በተለያዩ መንገዶች ያከብራሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በአንድነት ሆኖ ጣፋጭ ምግብን ይቋደሳል፡፡

ሁሉም እንደ ባህሉ በምርት ልብሶቻቸው ይዋባሉ፡፡ በዓሉ ለልጆች በተለይ አስደሳች ጊዜ ነው፡፡  ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በስጦታ (ዒድያ) ያንበሸብሿቸዋል፡፡

ረመዳን የሚያበቃው መቼ ነው?

ረመዳን በእስልምና የጨረቃ አቆጣጠር መሠረት ዘጠነኛው ወር ሲሆን፣ ሙስሊሞች ከ29 እስከ 30 ቀናት የሚጾሙበት ከዓመቱ ቅዱሳን ወራት አንዱ ነው፡፡

ምክንያቱም በዚህ ወር ውስጥ የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ ቁርአን፣ ለነቢዩ መሐመድ በፍርዱ ሌሊት (ላኢል – ቀድር) በተባለች ሌሊት እንደወረደ፣ ሙስሊሞች ያምናሉ ሲል ዒስራ አራሁ ጽፏል፡፡ ዘንድሮ የጾሙ ወቅት ሚያዝያ 23 ቀን 2014 እንደሚጠናቀቅ የተተነበየ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ እንደ ጨረቃ ዕይታ ሊለወጥ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ መንዙማና የዒድ ዝግጅት

‹‹መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው፡፡ መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አወሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተአምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው፤›› ይላል በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀ አንድ የጥናት መድበል፡፡

እንደ መድበሉ፣ አብዛኛውን የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ የመንዙማው አቀንቃኝ በተሳታፊዎች ፊት ሲያቀነቅን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአከዋወን ስልት በመከተል የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳያል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ከቀኝ ወደ ግራ ሰውነቱን ያወዛውዛል፣ ታዳሚዎችም አስፈላጊውን አጸፋና ምላሽ በድምፅና በጭብጨባ ይገልጻሉ፡፡ የመንዙማ አጨፋፈር እንደ ዜማዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ዝግ ያለ የድቤ መምቻ ያላቸው መንዙማዎች የአጨፋፈር ስልት ምቱን ተከትለው እየዘለሉና እጅን ከአናት በላይ እያሳለፉ ማጨብጨብ ሲሆን፣ ፈጣን የድቤ ምት ያላቸው መንዙማዎች ደግሞ እያጨበጨቡ ከወገብ በላይ አካላቸውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ማወዛወዝ ናቸው፡፡

ከዜማ ቅብብሎሹ/ከዝማሬው ለአብነት የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹‹አሏሁም መሶሌ አላሙሀመዴ(2x)

ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ፣

ተቆጥሮ የማያልቀው የሱማ ገለታ፣

ለሙሐመድ ኡመት ያደረገን ጌታ፣

መሻሪያ ሰጥቶናል ከወንጀል በሽታ፣

ሰላምና ሶላት ይጉረፉ ጠዋት ማታ፣

በአህመድ በኛ ጌታ በአዘሉውድ፡፡››

የረመዳን ጾም ካለቀ በኋላ የሚከበረው የዒድ አልፈጥር በዓል ቀን ከጨረቃ ጋር ተያይዞ ከተወሰነ በኋላ እናቶች በዓሉን ለመቀበል የሚያደርጉት ደፋ ቀና ይቀጥላል፡፡ ጨረቃ እስክትወጣ ድረስ ግን ሁኔታቸው በጥርጣሬ የተሞላ መሆኑ ነው፡፡ መምህራኑ እንደሚናገሩት፣ ምንም እንኳ ረመዳን ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ቢሆንም አንዳንድ ወራት 30 ቀናት ሳይሆኑ 29 ብቻ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም የጾም ጊዜ ማብቃቱንና ቀጣዩ ቀን ዒድ መሆኑ የሚበሰረው ምሽት ላይ በምትወጣው ጨረቃ ይሆናል፡፡ ጨረቃን አይቶ የማፍጠር ሱና የተጀመረው ነቢዩ መሐመድ የጨረቃን ገጽታ አይተው በማፍጠራቸው እንደሆነ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ፡፡

በዚህ መሠረትም በዓሉ በማግስቱ እንደሆነ በማረጋገጥ ለበዓሉ የሚውል ምግብ የማዘጋጀት ሒደቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ዚያራ

በዒድ ዚያራ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህም ከቅርብ ቤተሰብ በመጀመር ሌሎች ቤተሰቦቻቸውን ይዘይራሉ፡፡ ‹‹ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትና ክዋኔዎች›› በሚለው የሀረሪ ድርሳን እንደተገለጸው፣ ዚያራ በቀጥተኛ ትርጉሙ ጉብኝት ማለት ሲሆን ለበዓላት እና ለተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰብንም ሆነ የጀመዓ አባላትን መጎብኘትን ያካትታል፡፡

ይሁንና በሀረር ዚያራ ሲባል በስፋት የሚታወቀው ለጸሎት፣ በዓላትና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ አዋቾች የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ አዋቾች የተቀደሱ ቦታዎች እንደመሆናቸው በነዚህ ቦታዎች ዚያራ የሚደረገው በአብዛኛው በበዓላት ወቅት ሲሆን አልፎ አልፎ ለተለየ ጉዳይ አላህን የሚለምንላቸው የሚፈልጉ ሰዎች አዘቦት ቀናት ዚያራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ሸዋል ዒድ

በሀረሪዎች ዘንድ በዋናነት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ ሸዋል ዒድ ነው፡፡ ሸዋል ዒድ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር በሸዋል ወር፣ የረመዳን ጾም ተጠናቆ ዒድ አልፈጥር በዋለበት በስምንተኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው፡፡ ይህም ዒድ አልፈጥር ከተከበረ በኋላ ስድስት ተከታታይ ቀን ተጹሞ በቀጣዩ ቀን የሚከበርበት ምክንያቱ በእስልምና አስተምህሮ ሴቶች በረመዳን ጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ስለሚያቋርጡ ያጎድሉትን የጾም ቀናት ለማካካስ እንዲችሉ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወንዶች ተጨማሪ እጅሪ (ምንዳ) ለማግኘት ጾሙን የሚጾሙ በመሆናቸው በዓሉ ዒድ አልፈጥር በተከበረ በስምንተኛው ቀን ይውላል፡፡

የሸዋል ዒድ ክብረ በዓል በተለያዩ ሥርዓቶች የታጀበ ሲሆን፣ አከባበሩ የሚጀምረው ከዋናው በዓል ሁለት ቀን ቀድሞ ነው፡፡ በየቤቱ እንዲሁም አው አቅበራ እና አው ሹሉም አህመድ በተባሉ አዋቾች ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በአዋቂዎች ዝክሪ (መንዙማ) ይከናወናል፡፡

‹‹ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትና ክዋኔዎች›› በሚባለው የሀረሪ ድርሳን አገላለጽ፣ ዚክሪ በምስጋና መዝሙሮች የተሞላ አላህ፣ ነቢዩ መሀመድና ቅዱሳን የሚመሰገኑበት ሥርዓተ ጸሎት ሲሆን፣ ቃሉ የምስጋና መዝሙሩ (መንዙማ) መጠሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ የዚክሪ ክዋኔ ግጥም በዜማ የሚያወጡ ሸኽ እና ዚክሪውን በሚቀበሉ ታዳሚዎች እየተመራ በድቤ (ከረቡ) እና ከእንጨት የተሠሩ ማጨብጨቢያዎች (ከበል) የሚታጀብ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች እየተነሱ ክብ ሠርተው በመወዛወዝ (በመጨፈር) ያደምቁታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ