Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሊባባ ከአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ጋር ያደረግኩት ስምምነት የለም አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሸናፊ እንዳለና ብሩክ ጌታቸው

የቻይናው የበይነ መረብ ግብይት ቴክኖሎጂ አሊባባ ግሩፕ፣ ከኢትዮጵያዊው የሥራ ፈጣሪ ኤርሚያስ አመልጋ ጋር ምንም ዓይነት የሥራ ስምምነት አልተፈራረምንም ሲል አስታወቀ፡፡

በጥር ወር 2014 ዓ.ም. አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከአሊባባ ጋር መፈራረማቸውንና በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ግዙፍ የበይነ መረብ ግብይት ድርጅት ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እያጠናቀቁ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ዜናው በሚዲያ ከወጣ በኋላ ግን አሊባባ ለሪፖርተር በላከው የኢሜይል መግለጫና የስልክ ልውውጥ፣ እንዲህ ዓይነት ስምምነት እንዳልገባና ዕቅድም እንደሌለው ገልጿል፡፡

በአሊባባ የዓለም አቀፍ ኮርፖሬት ግንኙነት ኃላፊ ሉይሻ ማክ፣ ‹‹ምንም ዓይነት የኢኮሜርስ ቢዝነስ ስምምነት ከኤርሚያስ ጋር አላደረግንም፤›› ብለዋል፡፡

የአሊባባ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና የአውሮፓ ቢሮ የኮርፖሬት ጉዳዮች  ኃላፊ ማጃ ሀውኬ በበኩላቸው፣ አሊባባ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የበይነ መረብ ግብይት የማስጀመር ዕቅድ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

የአሊባባን ምላሾች መሠረት በማድረግ ለሳምንታት ሪፖርተር ጉዳዩን ለሁሉም አካላት በመላክ የማጣራት ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ስለጉዳዩ በድጋሚ የተጠየቁት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹ስምምነቱን የፈጸምኩት ከአሊባባ የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ነው፤›› ቢሉም፣ የተባሉት ሰዎች ግን ለሪፖርተር ምንም ዓይነት መረጃ መስጠት አልቻሉም፡፡

በድጋሚ ከሪፖርተር በተላከላቸው ደብዳቤ ስለስምምነቱ መረጃ እንዲያቀርቡ የተጠየቁት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹ስምምነቱ ከዌል ክላውድ ጋር ነው  የተፈጸመው፡፡ ዌል ክላውድ የአሊባባ የራሱ ድርጅት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህኛውም ላይ የስምምነቱን ዶክመንት አሳያችኋለሁ ካሉ በኋላ፣ ያሳዩት ግን የአሊባባና የዌል ክላውድ ሎጎ (ምልክት) ያለበት የኮምፒዩተር ጽሑፍ (Slide Presentation) ነበር፡፡

ስለጉዳዩ ድጋሚ የተጠየቁት ሉይሻ፣ ‹‹ማንም ሰው የእኛን ሎጎ እንደዚያ ሊያደርግና ሊጠቀም ይችላል፣ ግን በፍፁም ስለዚህ ዶክመንት አናውቅም፡፡ ዌል ክላውድ የገባው ስምምነትም ከሆነ እንደ አሊባባ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ለሪፖርተር ‹‹አሊባባን ወደ ኢትዮጵያ ላመጣው ነው›› ብለው ከተናገሩ በኋላ ግን፣ ከተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ንግግር እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከአሊባባም ሆነ ከቻይናው ዌል ክላውድ ጋር አለኝ ስላሉት ስምምነት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኃላፊዎችም እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡

‹‹አቶ ኤርሚያስ ከየት አምጥተው እንደተናገሩ አላውቅም፡፡ ደፍረው የተናገሩ ይመስለኛል፡፡ እስከማውቀው ድረስ አሊባባ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ እንዲሠራ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ብሔራዊ ባንክም አሊባባ ቢመጣ በብር ይሁን በዶላር እንዴት መገበያየት እንዳለበት ሕግ አላወጣም፤›› ሲሉ በሚኒስቴሩ የዲጂታል ቴክ ከባቢ ልማትና ቁጥጥር ኃላፊ ካሊድ አህመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የኢኮሜርስ ድርጅት ከሚኒስቴሩ የብቃት ማረጋገጫና ከንግድ ሚኒስቴር ደግሞ የንግድ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡

‹‹እስካሁን ከአሊባባም ሆነ ከአቶ ኤርሚያስም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አልቀረበልንም፤›› ሲሉ በሚኒስቴሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቤል ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ከካሊድ (ዶ/ር) ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡

ስለዚህኛውም ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹ሚኒስቴሩን የሚመለከት አይደለም፡፡ ግብይቱ የሚካሄደው በብር ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሪፖርተር ዘጋቢዎች ጉዳዩን ለሳምንታት በሚያጣሩበት ጊዜ አቶ ኤርሚያስ በበቂ ሁኔታ ለማናገር ካለመፈለግም ባሻገር ጋዜጣውን እንደሚከሱ በማስጠንቀቅ አስፈራርተዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የአሊባባ መሥራች ጃክ ማ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተፈራረሙት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ኢንጂነር) ጋር ሲሆን፣ ስምምነቱም የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና በበይነ መረብ ሽያጭ እንዲቀርቡ የሚያስችል (eWRP) (Electronic World Trade Platform) ይሰኛል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡና በዚህ ከመሸጡ ውጪ ለሌሎች ምርቶች መጠቀም እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

‹‹eWTP በሁለት ዓመታት ዘግይቷል፡፡ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም፤›› ሲሉ ካሊድ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች