Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዋጋ ንረት ምክንያት ግንባታቸው ላልተጠናቀቁ መንግሥታዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች የውል ማሻሻያ ሊደረግ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍና አገራዊ ምክንያቶች የተነሳ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የተፈጠረን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ሲባል፣ ውላቸው ላይ የዋጋ ማስተካከያን ያላካተቱ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ከኮንትራክተሮች ጋር ያላቸው ውል ማሻሻያና ዕድሳት ሊደረግለት መሆኑ ተገለጸ፡፡

መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ለወራት ሲያደርገው በቆየው ጥናት ላይ ተመሥርቶ ሲሆን፣ ውሳኔው በማክሮ ኢኮኖሚክ ኮሚቴ ስምምነት ተደርሶበት ከገንዘብ ሚኒስቴር የመጨረሻ ፊርማ እየተጠበቀ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያን በተመለከተ ለአምስት ወራት ገደማ ጥናትና ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ለሪፖርተር የተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ በውሳኔው ማሳለፍ ሒደት ውስጥ የገንዘብ፣ የፍትሕ፣ የፕላንና ልማት፣ የከተማና የመሠረተ ልማት ሚኒስቴሮች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በአገር ውስጥም ከፍተኛ የዋጋ ንረት መታየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሒደት ላይ ያሉና ግንባታቸው የተቋረጡ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ አለመቻሉንና ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ 15 ዓመታት ያስቆጠሩ እንዳሉ የገለጹት መስፍን (ኢንጂነር)፣ (በፀጥታ ችግር ምክንያት ፕሮጀክታቸው የተቋረጠ) በሒደት ላይ እያለ የዋጋ ንረት ያጋጠማቸው እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የዋጋ ጭማሪ አድርጎ ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ባደረገው ጥናት እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ነዳጅ፣ ሴራሚክና የመሳሰሉ ስምንት ዋነኛ ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪያቸው ተካቶ መቅረቡንና ጥናቱም ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ማመላከቱን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ብዙዎቹ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከተቋራጮች ጋር የገቡት ውል የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ ላለማድረግ የዘጋ ስለሆነ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በጥናቱ በናሙናነት የቀረቡት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ 758 የግንባታ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሆኑት ከተቋራጮች ጋር የገቡት ውል የዋጋ ማስተካከያ እንደማይፈቅድ ገልጸዋል፡፡

ተቋራጮቹ ሥራውን ሲረከቡ በገቡት ውል መሠረት ግንባታውን የማጠናቀቅ ግዴታ እንዳለባቸው አስታውሰው፣ ‹‹መጀመርያ በነበረው ውል መሠረት የሚኬድ ከሆነ ፕሮጀክቶቹ ማለቅ አይችሉም፡፡ አንዳንዶቹ ውል ሲገቡ የአንድ ኪሎ ብረት ዋጋ 50 ብር ነበር፣ አሁን ግን ከ100 ብር በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ “ውሉ አይፈቅድም” በሚል የዋጋ ጭማሪ አለማድረግ ጉዳቶች እንዳሉት ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህም በኋላ የግብዓቶች ዋጋ እየጨመረ ስለሚሄድ ግንባታዎቹን አሁን ማጠናቀቅ የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ዓመት የዘገየ የ14 ብሎኮች ግንባታ አለ፡፡ አንዱ ብሎክ 500 ተማሪ ያስተናግዳል፡፡ ግንባታው ቢያልቅ ዩኒቨርሲቲው ሰባት ሺሕ ተማሪዎች ይቀበላል፡፡ ካልሆነ ግን የዚህን ያህል የገበሬ ልጆች ሳይገቡ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ አንፃር ነው ከሌለው በጀት ላይ ይህንን የፈቀደው፤›› በማለት ግንባታዎቹ ተጠናቀው መስጠት የነበረባቸው አገልግሎት መጓተቱን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የዋጋ ጭማሪው የማይደረግ ከሆነ በሥራቸው ብዛት ያላቸው ሰዎችን የሚቀጥሩትንና ግብር ከፋይ የሆኑትን ተቋራጮች እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች መሠረትም ውላቸው ውስጥ የዋጋ ማስተካከያን ያላካተቱ የፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ይህን ማስተካከያ ማድረግ በሚያስችል መሠረት ውላቸውን ለማስተካከል ስምምነት ላይ መደረሱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ውሳኔ ለማስተላለፍ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊርማ ብቻ እንደሚጠበቅ አክለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ውላቸው ከተስተካከለ በኋላ ከተቋራጮቹ አስተዳደራዊ ወጪና ከሚያገኙት ትርፍ በስተቀር እያንዳንዱ ግብዓት ውሉ ከመፈጸሙ 28 ቀናት በፊት የነበረው ዋጋና ከብሔራዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከሚገኝ የአሁናዊ የዋጋ ኢንዴክስ ጋር ተነፃፅሮ ጭማሪው ይደረጋል፡፡ የፌዴራል ግዥና ንብረት ባለሥልጣንም ውላቸው ላይ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግን የሚፈቅዱ ፕሮጀክቶች የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉበት ቀመር (Formula) የሚያሳይ ደብዳቤ ከ150 በላይ ለሆኑ የፌዴራል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች መጻፉን፣ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ ገላን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም በግንባታ ፕሮጀክት ውሉ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ቢፈቀድም፣ የየዋጋ ጭማሪው ከተቀመጠው ገደብ በላይ ከሆነ የጭማሪውን ተገቢነት ዓይቶ ውሳኔ የሚያስተላልፈው ባለሥልጣኑ ነው፡፡ አሁን ግን የግብዓቶች ዋጋ ጭማሪው ከፍተኛና በግልጽ የሚታይ በመሆኑ፣ መሥሪያ ቤቶቹ ባለሥልጣኑን ሳያስፈቅዱ በቀመሩ መሠረት እያሰሉ ጭማሪ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያስተላለፈው ውሳኔ በውላቸው ላይ የዋጋ ማስተካከያን ለፈቀዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ብቻ ቢሆንም፣ ሌሎቹም ፕሮጀክቶች በቅርቡ ውላቸው የሚስተካከል በመሆኑ፣ በባለሥልጣኑ መመርያ መሠረት ማስተካከያ ማድረግ ይችላሉ፡፡

የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ጭማሪ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለማሳደሩ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ በመንገድ ግንባታ ላይ ለተሰማሩ ኮንትራክተሮች ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ያገናዘበ ማካካሻ እንዲነሳላቸው፣ እስካሁን የነበረውን አሠራር እንዲቀር ውሳኔ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

እስካሁን በነበረው አሠራር ኮንትራክተሮች ለሚገጥማቸው የዋጋ ንረት የሚፈቀድላቸው የዋጋ ማካካሻ ከፕሮጀክቱ ጠቅላላ ገቢ ከ20 በመቶ በላይ መብለጥ እንደሌለበት የሚደነግግ ቢሆንም፣ ሚኒስቴሩ ይህ ጣሪያ ተነስቶ በዓለም አቀፉ ዋጋ ማካካሻ አሠራር መሠረት ጥያቄያቸው እንዲስተናገድ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በደብዳቤ ማሳወቁን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች