Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአብን በሁለት ወራት ውስጥ እንደገና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ

አብን በሁለት ወራት ውስጥ እንደገና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በደንቡ መሠረት የሚቀርፃቸውን ሌሎች አጀንዳዎች ጨምሮ፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደገና ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ፣ ከዚህ ቀደም ዕልባት ላላገኘው ‹‹የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ›› ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ አሳሰበ፡፡

ምርጫ ቦርድ አብን መጋቢት 9 እና 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በቅደም ተከተል ያደረገውን ጠቅላላ ጉባዔና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በሚመለከት ያቀረበለትን ሪፖርት፣ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲታዘቡ የመደባቸው ባለሙያዎች ያቀረቡትን ሪፖርት መሠረት በማድረግ፣ ሊፈጽማቸው ይገባል ያላቸውን ውሳኔዎች ለፓርቲው በጻፈው ባለ አምስት ገጽ ደብዳቤ አሳውቋል፡፡

ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ እንዳስታወቀው፣ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ ሒደት እንዲታዘቡ የተመደቡ ባለሙያዎች በሪፖርታቸው እንዳቀረቡት፣ የአመራር ለውጥ (ሪፎርም) ስለማድረግ ከጉባዔው ተሳታፊዎች በአጀንዳነት የቀረበው ሐሳብ ሰፊ ክርክር ከተደረገበት በኋላ፣ በጉባዔው በአጀንዳነት መፅደቁን አረጋግጠዋል፡፡

- Advertisement -

በርካታ የጉባዔ አባላት የአመራር ለውጡ በዕለቱ እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸው በሪፖርት ቀርቦልኛል ያለው ቦርዱ፣ ከመድረኩ ጠቅላላ ጉባዔው የተዘጋጀው ምርጫ ቦርድ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት መተዳደሪያ ደንቡን አሻሽሎ ለማፀደቅ እንደሆነና የአመራር ለውጥን በሚመለከት በዕለቱ በአጀንዳነት ተይዞ ስላልነበር፣ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ጉባዔ ተጠርቶ እንደሚከናወን ማብራሪያ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔ የአመራር ለውጥ እስከሚካሄድ ድረስ በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላይ የአመራር ሽግሽግ ማድረጉን፣ ምርጫውን ለማካሄድ ጊዜ ስለሚያስፈለግ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ጉባዔውን ሲመሩት የነበሩት አመራሮች ቃል መግባታቸውን ቦርዱ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

አብላጫ ቁጥር ያላቸው የጉባዔ አባላት የአመራር ለውጥ አለማካሄዱንና የመድረኩን መዘጋት በመቃወም በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በመቆየት ለቦርዱ ታዛቢዎች አቤቱታቸውን እንዳሰሙ ገልጾ፣ ነገር ግን ታዛቢዎቹ  ጉባዔውን የጠራው አካል በሌለበት የሚካሄድ ምርጫ አግባብነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከላይ የተመለከቱትን ጉዳዮች፣ የተሻሻለውን የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና የጠቅላላና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባዔዎችን ቃለ ጉባዔ ሰነዶችን እንደተመለከተ ያስረዳው ምርጫ ቦርድ፣ ለፓርቲው የላከውን ውሳኔ ካሳወቀበት ማክሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አብን ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያካሂድ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ፓርቲው በደንቡ መሠረት የሚቀርፃቸውን ሌሎች አጀንዳዎችን ጨምሮ በጉባዔው የመነጋገር መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ ቀደም ዕልባት ያላገኘውን አጀንዳ ‹‹የአመራር ሪፎርም ወይም ለውጥ ማድረግ›› የሚለው ለጉባዔው በአጀንዳነት ቀርቦ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበትና አግባብነት ያለው ምርጫ እንዲደረግ ምርጫ ቦርድ ጠይቋል፡፡

ፓርቲው በተጨማሪ በዝርዝር የቀረቡለትን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጾች የተካተቱበት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ጉባዔው ከሚካሄድበት አምስት የሥራ ቀናት አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡

ጉባዔው በተጠናቀቀ በ15 ቀናት ውስጥ የጉባዔው ዝርዝር ሒደትና ውሳኔ የሚገልጽ ቃለ ጉባዔ፣ በጉባዔው የፀደቀውን መተዳደሪያ ደንብና የጠቅላላ ጉባዔውን ሪፖርት እንዲያቀርብ ቦርዱ የወሰነ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በተደረገው የፓርቲው ጉባዔ ሒደቱን በተሟላ ሁኔታ ለመታዘብ ይቻል ዘንድ በቦርዱ የተመደቡት ባለሙያዎች ሒደቱን ለመቅረፅ ሲጀምሩ በፓርቲው አመራር የተከለከሉበት ሁኔታ ፓርቲው ሊያከብረው ከሚገባው፣ በአዋጅ 1162/11 አንቀፅ 161 መሠረት ቦርዱ አዋጁን ለማስፈጸም በሚሠራቸው ተግባራት ከቦርዱ ጋር የመተባበር ግዴታ ተፃራሪ መሆኑ ታውቆ የቦርዱ ባለሙያዎች በቀጣይ ጉባዔ የሚደርጉትን የሙያ ትዝብት ሥራ፣ አስፈላጊ በሆነ መንገድ ሁሉ ያለ ምንም ተፅዕኖ መከወን እንዲችሉ ፓርቲው ተገቢውን እንዲፈጽም ምርጫ ቦርድ ጠይቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ከዚህ በሻገር በባለ 27 ገጽ ተቀንብቦ በቀረበለት የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ ላይ አብን አሻሽሎና በጠቅላላ ጉባዔው አፅድቆ ሊያቀርብ ይገባል ያላቸውን አምስት አንቀጾች አሳውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...