Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በአሜሪካና ሩሲያ መካከል የተደረገው የመጀመሪያ ውይይት

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በአሜሪካና ሩሲያ መካከል የተደረገው የመጀመሪያ ውይይት

ቀን:

በሩሲያና ዩክሬን መካከል ጦርነት ከተጀመረ ሦስት ወራት ሊቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ጦርነቱን ከማባባስ ባለፈ ለማርገብ የተደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

አሜሪካ፣ ምዕራባውያንና ኔቶ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚያሰራጩትም ከዩክሬን ግዛቶች አንዱ አሊያም ከዚያ በላይ ስለመያዙ ወይም ሩሲያ በአንዱ ግዛት ስለገጠማት ጠንካራ የመከላከል ውጊያ፣ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ስለሚቀርብበት ሁኔታ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ከዩክሬን እየተሰደዱ ስለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን እንጂ ጦርነቱ እንዴት ይቁም የሚለው ላይ እምብዛም ያተኮረ አይደለም፡፡

ይህ ደግሞ በጦርነቱ ሰለባ ከሚሆኑት የዩክሬንና የሩሲያ ዜጎች ባለፈ የዓለምን ኢኮኖሚ ጎድቶታል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ገና በማገገም ላይ የነበረው የዓለም ኢኮኖሚ ዳግም መናጋት ጀምሯል፡፡ አገሮችም ለከፍተኛ የኑሮ ግሽበት ተጋልጠዋል፡፡

- Advertisement -

በዓለም አቀፍ ደረጃ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል፡፡ ይህ ደሃ አገሮችን ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ጨምሮ የምዕራባውያኑን ኢኮኖሚ እየተፈታተነ ይገኛል፡፡

በዓለም 30 በመቶ የሚሆነውን ስንዴ የሚያመርቱት ሩሲያና ዩክሬን ናቸው፡፡ ሁለቱም አገሮች በዓለም የምግብ ገበያ ዋና ሚና ያላቸው ሲሆን፣ በተለይ ለአብዛኛው የዓለም ሕዝብ ወሳኝ ምግብ የሆኑትን ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ እንዲሁም በዓለም በአብዛኛው ሕዝብ ጥቅም ላይ የሚውለውን የሱፍ ዘይት በማምረትና በመላክ የዓለምን የምግብ ኢኮኖሚ የሚደግፉ ናቸው፡፡ በጦርነት መቆየታቸው ደግሞ የምግብ ገበያው በግሽበት እንዲጦዝ አድርጎታል፡፡

በጦርነቱ ምክንያትም ኦዲሴን ጨምሮ የጥቁር ባህር ወደቦች በመዘጋታቸው ከዩክሬን ምግብ ማምጣት አልቻለም፡፡ የዓለም ምግብ ድርጅት እንደሚለውም፣ 44 ሚሊዮን የዓለም ሕዝቦች ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ ዓለምም ለምግብ ቀውስ እየተጋለጠች ነው፡፡ የዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለትም ተቃውሷል፡፡ የምግብ፣ የማደበሪያና የነዳጅ ዋጋም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡

በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት ዓለም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መመሳቀሎች ገጥመዋታል፡፡ ምዕራባውያኑ ደግሞ በሩሲያ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ማዕቀቦች ጥለዋል፡፡ አሁንም ተጨማሪ ማዕቀቦች ለመጣል ሌትቀን እየተጉ ነው፡፡

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ከሩሲያ ጋር መምከራ ጥቂት ተስፋን አሳይቷል፡፡ ይህ ለአንድ ሰዓት የቆየ የስልክ ውይይት ሩሲያና ዩክሬን በየካቲት 2014 ዓ.ም. ጦርነት ከገቡ በኋላ የመጀመሪያ ነው፡፡

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎያድ ኦስቲን ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ሼይጉ ጋር የነበራቸውን የስልክ ውይይት ጠቅሶ ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፣ ውይይቱ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት አድማሱን አስፍቶ በሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና በሩሲያ መካከል ሊጀመር ይችላል የሚለውን ፍርሃት ለማለዘብ ያግዛል፡፡

በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ውይይት መደረጉም በሁለቱ ኑክሌር ታጣቂ አገሮች መካከል አለመግባባትንና የጦርነቱን በድንገት መባባስ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርባይ እንዳሉት፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኦስቲን ሩሲያ ተኩስ አቁም እንድታደርግና ሐሳብ ለመለዋወጥም ትኩረት እንድትሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ኦስቲን ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሼይጉ ጋር በስልክ ለመነጋገር ለሳምንታት ያህል ጥረት ማድረጋቸውን፣ በስተኋላም መሳካቱን፣ ነገር ግን ለአንድ ሰዓት የቆየው ውይይት መሠረታዊ ችግሮችን አለመፍታቱንና ግንኙነቱ መፈጠሩ ግን ወደፊት ለሚኖር ውይይት ተስፋ እንደሚጥል አስፍሯል፡፡

በአሜሪካና በሩሲያ መካከል (ፕሮፌሽናል) ውይይት መደረጉን የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣን እንደነገሩት የዘገበው ፋይናንሻል ታይምስ፣ አሜሪካ 10,500 ወታደሮች ወደአውሮፓ እንደምትልክ ጠቁሟል፡፡

ከሩሲያ ጋር የነበራቸውን የስልክ ውይይት ተከትሎ መግለጫ የሰጡት ኪርባይ፣ ወታደሮች ወደ አውሮፓ የተላኩት ከዚህ ቀደም የነበሩትን ለመተካትና ኔቶን ለማጠናከር እንጂ በዩክሬን ሊዋጉ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከኦስቲን አስቀድሞ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት ለመቀልበስ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሁኔታ እንዲመቻችና በዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለውጥ ለማምጣት እንዲሠራም አክለዋል፡፡

የቻንስለር ሾልዝ ቃል አቀባይ እንደገለጹት፣ ሾልዝ እና ፑቲን በዓለም የምግብ ሁኔታ ዙሪያ መክረዋል፡፡ በተለይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ለተከሰተው የምግብ ውድነት ሩሲያ ልዩ ኃላፊነት እንደምትወስድ ሾልዝ አሳስበዋል፡፡

ሩሲያ በአፋጣኝ ተኩስ አቁም እንድታደርግ፣ በዩክሬን ውስጥ ናዚነት (ዘረኝነት) ተስፋፍቷል የምትለው ስህተት እንደሆነና በዓለም ለሚታየው የምግብ ዋስትና መዋዥቅ ሩሲያ ኃላፊነት ትወስዳለች የሚሉት ጉዳዮች ሾልትዝ የመከሩባቸው እንደሆኑ ፋይናንሻል ታይምስ አስፍሯል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ