‹‹…በጣም የደነቀኝ የዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ቋንቋ የሚላክ ቴሌግራም ሁሉ በላቲን ፊደል ነበር የሚተየበው፡፡ ለምሳሌ ‘እመጣለሁ’ ለማለት ሲፈለግ emetalehu ተብሎ ነበር የሚጻፈው፡፡ እንዴት የራሳችን ፊደል እያለን በላቲን ፊደል ይጻፋል ስል ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ለምን በራሳችን ፊደል መጻፍ አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ባነሳም አበረታች መልስ አላገኘሁም፡፡ ‘ፈጽሞ አይቻልም፤ ብዙ ሰዎች ሞክረው ትተውታል’ [የሚል] ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር የገጠመኝ፡፡ በኋላም ኦሊቬቲ የተባለ ኩባንያ የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመሥራት ሞክሮ አልቻለም ሲሉ ሌላ መረጃ አቀበሉኝ፡፡ እኔም ‘በኢትዮጵያ ፊደል ቴሌፕሪንተር’ ሊኖር አይችልም የሚባለውን ተስፋቢስ ዜና ልቀበለው አልቻልኩም፡፡››
ከስድስት አሠርታት ጥቂት አለፍ ባለ አንዱ ዓመት አንድ የሃያ አምስት ዓመት ወጣት በባህር ማዶ በአሜሪካ የተከታተለውን የምሕንድስና ትምህርት አጠናቅቆ ከተመለሰ በኋላ የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን መሥርያ ቤትን ነበር፡፡ ወጣቱ ቴሌ በሚሠራበት ጊዜ አብዛኛው መልእክት ይተላለፍ የነበረው በቴሌግራፍ ስለነበር ያንን በራስ ፊደል ወደ ቴሌፕሪንተር የማሳደግ ፈር ቀዳጅ ሥራን ነበር ለመሥራት የተነሳው፡፡
ይህ ወጣት ማን ነው ቢሉ በኋላ ላይ ከደቂቅነት ወደ ልሂቅነት የተሸጋገሩት ታላቁ ኪነ ጠቢብና መሐንዲስ ተረፈ የራስ ወርቅ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ ‹‹ፊደላችን የራስ ወርቃችን›› የሚል እሳቤ የነበራቸውን የመሐንዲስ ተረፈ የራስ ወርቅ ዜና ሕይወታቸውን በኦዲዮም በቪዲዮም እስከ ኅትመት የሰነደው በዕዝራ ዕጅጉ የሚመራው ተወዳጅ ሚዲያ፣ ስለ ኢንጂነሩ ቴሌፕሪንተር እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡፡
‹‹……የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከልኩት በኋላ በዚያን ጊዜ የአዕምሯዊ ንብረት ሕግ የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አስመዘገብኩ፡፡ በኋላም፣ ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም. መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የስራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡
‹‹ወዲያው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፡፡ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተ-መንግስት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡
‹‹በዋናነት አንድን መልእክት በመተየብ ለማሠራጨትና ለመቀበል የሚያገለግለው ቴሌፕሪንተር የተባለው መሣሪያ ሶፍትዌሩን ፈጥረው ፊደሎቹ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸውና የቁመታቸውን መጠን በዝርዝር አጥንተው ያቀረቡት ኢንጂነር ተረፈ ሲሆኑ፤ የቴሌፕሪንተሩን ቅርፅ ያወጣው ኩባንያ ደግሞ ሲመንስ ነው፡፡
ኢንጂነር ተረፈ፣ በኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከ1950ዎቹ ጀምሮ፣ ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊነትን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች አገርንና ዓለምን ማገልገላቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በሌላኛው የታሪክ ገጻቸው መሐንዲሱ የራስ ወርቁ ተረፈ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ በመሰማራትም ተጠቃሽ የሚያደርጋቸው ታላቁ ሥራቸው ከእህታቸው ልጅ ከትምህርት ከፍተኛ ባለሙያው ኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ጋር በታሪካዊው የአንኮበር ቤተ መንግሥት ላይ ሎጅ መገንባታቸው ነበር፡፡
ኢንጂነሩ የአንኮበር ሎጅን ለመሥራት የወሰኑበትን አጋጣሚ በአንድ ወቅት እንዲህ መተረካቸውን የባለ ታሪኮች መድበል በሆነው ተወዳጅ ሚዲያ ከሳቸው አንደበት የወሰደውን እንዲህ ገልጾታል፡-
‹‹…..የአንኮበርን ታሪካዊነት በመገንዘብ እፊታችን ደግሞ የወደመውን የታላቁን የንጉሥ ምኒልክን ቤተ መንግሥት ስመለከት ያለፉት መንግሥታት መልሰው ባይሠሩትም እኔ ራሴ እንደገና አሠርቼ ላገሬው ሥራ በመፍጠር፣ የቀድሞውንም ታሪክ በመዘከር የጎብኝዎች መስህብ እንዲሆን አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ወሰንኩ። አንኮበር ከአዲስ አበባ እምብዛም ስለማትርቅ፣ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ብዙ ያገር ውስጥና የውጭ አገር ነዋሪዎች መናኸሪያ በመሆኗ ለእንግዶች የሚስማማ የመስተንግዶ ቤት (ሎጅ) ቢሠራ አዋጭ ይሆናል ብዬ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።››
ሎጁን ዕውን ያደረጉትም ከዶ/ር ኃይለ ገብርኤል ዳኜ ጋር በሽርክና አምባ ኤኮቱሪዝም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በማቋቋም ነው፡፡ ፋሺሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. በወረረች ጊዜ በጦር አውሮፕላን ያወደመችውን የአፄ ምኒልክ ሕንፃ በባህላዊ መንገድ እንደገና ከማሠራታቸውም ባሻገር በዙሪያው የነበሩትን የሹማምንቱን መኖሪያ መሰል ቤቶችን በጥንቱ አሠራር እንደገና በመገንባት የእንግዶች መኝታ ቤቶች እንዲሆኑ አድርገዋል። እያንዳንዳቸውን ክፍሎች በታዋቂ ሰዎች ሰይመዋቸዋል፡፡
የሊቃውንት መናኸርያ በሆነችው አንኮበርም የአብነት ትምህርት ቤትንም ነፍስ እንዲዘሩ ማድረጋቸው፣ በተጨማሪም አንኮበር የሚገኘውን የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባህል ማዕከል እንዲመሠረት በአሳብና በልዩ ልዩ መልክ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይወሳል፡፡
ከአባታቸው ከመምሬ ራስወርቅ ወልደመስቀልና ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለ ማርያም ገብረ ጊዮርጊስ ረቡዕ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ.ም. በአንኮበር ውስጥ በምትገኝ አፈርባይኔ በምትባል መንደር የተወለዱት ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ፣ ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ኰመቀጠልም በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
የሦስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (በኋላ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው) በሳይንስ ዘርፍ የሦስት ዓመት ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸው ለቀጣይ ትምህርት ወደ አሜሪካ በመሄድ ከሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት የመጀመርያ ዲግሪ፣ ከሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በአድቫንስድ ማኔጅመንት ዲፕሎማ ማግኘታቸው በገጸ ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ባለፈ በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ባለሙያዎች ዘንድ ከበሬታን ያተረፉትና ያሳለፉትንም ሕይወት ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› ብለው መጽሐፍ ያሳተሙት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ እሑድ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በተወለዱ በ86 ዓመታቸው በድንገት አርፈዋል፡፡ሥርዓተ ቀብራቸውም ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ከወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው ጋር ከስድሳ ዓመት በፊት ጎጆ የወጡት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የሦስት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆኑ፣ ስምንት የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡