Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኅብር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክሩ ሳይጀመር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጠየቀ

ኅብር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክሩ ሳይጀመር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጠየቀ

ቀን:

ገዥው ፓርቲ የአገር አንድነት ሥጋት ነው ብሏል

ኢትዮጵያ ውስጥ ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ ምክክር ‹‹በመንግሥት ተጠልፏል›› ያለው ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ከምክክሩ በፊት የሽግግር መንግሥት ተመሥርቶ ምክክሩ በሽግግር መንግሥቱ እንደሚመራ ጠየቀ፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ፣ ዕጣ ፋንታው ከዚህ በፊት ተመሥርተው እንደነበሩ ኮሚሽኖች ይሆናል የሚል ሥጋት እንዳለው ገልጿል፡፡

መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ካካሄደ በኋላ የመጀመሪያ መግለጫውን ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የሰጠው ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የብሔራዊ ምክክርን ሐሳብ ከዚህ በፊትም ሲያቀነቅነው የነበረ መሆኑን አስታውሷል፡፡ ይሁንና ምክክሩ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ሥር ሆኖ የሚደረግ፣ ሁሉንም ወገኖች ያላካተተ፣ ሥልጣንንና የፖለቲካ ፍላጎትን አስቀድሞ ግምት ውስጥ ያስገባ ከሆነ ‹‹ሳይጀመር የከሸፈ ነው›› የሚል ሐሳብ እንዳለው አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

የኅብር ኢትዮጵያ ምክትል ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ የምክክር ኮሚሽኑ በመንግሥት ፓርላማ ተዋቅሮ በፓርላማው ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ፣ ‹‹መንግሥት ራሱ የአገሪቱ ችግር አካል ሆኖ ራሱ ብቻ የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ምክክር የአገሪቷን ችግር የሚፈቱ መፍትሔዎችን ሊወልድ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ ምክትል ሊቀመንበሩ ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ የየመንን ሒደት በምሳሌነት አንስተው፣ በየመን አገራዊ ውይይቱ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ ቢቆይም የመንግሥት ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት ተቀላቅሎበት ስለነበር ከሽፎ ወደ ጦርነት ማምራቱን አስረድተዋል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ሌሎች ፓርቲዎች በተናጠል ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ አስታውሰው፣ ሒደቱን ‹‹እኔ ብቻዬን ነው የምመራው ብሎ መንግሥት፣ ገዥው ፓርቲ ነጠቀው፤›› ብለዋል፡፡ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ፓርቲ ግን የመንግሥት አካሄድ የሚያሻግር ነው ብሎ እንደማያምን፣ ሒደቱን የሚመራው የሽግግር መንግሥት መሆን አለበት የሚል አቋም እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

ይልቃል (ኢንጂነር) የምክክር ሒደቱ በሽግግር መንግሥት ሊመራ የሚገባበትን ምክንያቶች ሲዘረዝሩ፣ የአገሪቱ ሁኔታና ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ከዚህ ቀደምም የነበሩ መሆናቸውን፣ የአገሪቱ ሁኔታ እየተባበሰ መምጣቱን፣ ኮሚሽነሮች የተመረጡበት መንገድ ከዚህ ቀደም ከነበረው አካሄድ የተለየ አለመሆኑንና ዋና ዋና ባለድርሻዎች እምነት ያልጣሉበት መሆኑን አውስተዋል፡፡ አክለውም ምክክሩ፣ ‹‹በአንድ ፓርቲ የበላይነት፣ ሊወድቅ ባለ መንግሥት፣ በሥልጣን እየቃዡ ባሉ ሰዎች ከተመራ ፍሬያማ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ከምክክሩ በፊት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መቅደም እንዳለበትና ብሔራዊ ምክክሩ በሽግግር መንግሥቱ ሥር ሆኖ መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ ከብሔራዊ ምክክሩም በላይ ላሉ የአገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ነው ብሎ እንደሚያምን ያስታወቀው ኅብር ኢትዮጵያ፣ አገሪቱ ከተጋረጠባት ‹‹የመፈራረስ አደጋ›› ለመቀልበስም የሽግግር መንግሥት ‹‹በአስቸኳይ›› መመሥረት እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ፓርቲው ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ ‹‹እጅግ በጣም አስቸጋሪና ተመጋጋቢ በሆኑ ችግሮች የተሞላ ነው፤›› በማለት፣ አገሪቱ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ክስረት፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ፣ በተለይም ሰላምና መረጋጋት የሌለበት ቀውስ ውስጥ መውደቋን ለጋዜጠኞች በተነበበው መግለጫው አስረድቷል፡፡

ፓርቲው ኢትዮጵያ ገብታበታለች ላለው ቀውስ ገዥውን ፓርቲና መንግሥትን ወቅሶ፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ የመንደር ጎበዝ አለቆችና በሕዝብ ስም የጥቅም ነጋዴዎች ያስከተሉት ቀውስና እያስከተሉ ያሉት ጥፋት መንግሥት አለ ወይ ብሎ ከሚያስጠይቅ ደረጃ ማለፉን አስታውቋል፡፡

አክሎም ከብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ‹‹የሥልጣንና የፖለቲካ ሽኩቻ›› መንግሥት ራሱ ‹‹ጽንፈኛ፣ አሸባሪ፣ ጁንታ… ብሎ ከፈረጃቸውና የአገራችን ሥጋት እያለ ፕሮፖጋንዳ ከሚሠራባቸው ባልተናነሰ›› የአገሪቱ ህልውና፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ከፍተኛ ሥጋት እንደዳረገው ገልጿል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ መፈናቀል፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነው ሙስናና የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነትና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረባቸው ተስፋ መቁረጥ፣ ፓርቲው ለሚያነሳቸው ሥጋቶች በማስረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ‹‹ገዢው ፓርቲ ወይም መንግሥት እንኳን ሊያሻግረን፣ ራሱም ከገባበት የመፈራረስ አደጋ ሊሻገር አይችልም፤›› ያለው ኅብር ኢትዮጵያ፣ አመራሩ አገሪቱን ከተደቀነባት የመፈራረስ አደጋ ታድጎ ለመምራትና ማስተዳደር አለመቻሉን በማመን፣ ለሽግግር መንግሥት ምሥረታ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያሳይ ጠይቋል፡፡

ምክትል ሊቀመንበሩ ይልቃል (ኢንጂነር) ፓርቲው ያዘጋጀው የቆየ የሽግግር መንግሥት ሰነድ እንዳለ ተናግረው፣ የሽግግር መንግሥቱ አንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ሥልጣን የሚይዝበት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ በፓርቲው ዕቅድ መሠረት የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት አገራዊና ብሔር ተኮር ፓርቲዎች፣ እንዲሁም መንግሥት የሽግግር ሥርዓቱ ውስጥ እያንዳንዳቸው ከ20 እስከ 25 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ደግሞ ድርሻቸው ከ40 እና 50 በመቶ ያላነሰ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ይልቃል (ኢንጂነር)፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብና የአገሪቱ ክፍሎች በሚወከሉ ሰዎች የሚሳተፉበት የብሔራዊ ሸንጎ ተመሥርቶም ጠቃሚ ዘርፎችን ያያዙ ኮሚሽኖችን አቋቁሞ ሊመራቸው ይችላል የሚለውን የፓርቲያቸውን ሐሳብ አጋርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...