Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የምርምር ሥራና ሽያጭ ላይ እንዲሰማሩ ተፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሥር ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ የፀደቀው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ የውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የምርምር ሥራና ሽያጭን በቢዝነስ መልክ እንዲያካሂዱ ፈቀደ፡፡ ፖሊሲው የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ የማበረታቻ ሥርዓት የመዘርጋት ዓላማም ይዟል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የፀደቀው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ በሥሩ ከያዛቸው ስምንት ቁልፍ የትኩረት መስኮች ውስጥ አንዱ ምርምርና ልማት የሚለው ነው፡፡ ፖሊሲው በመንግሥትም ሆነ በግል ሴክተሩ እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠውን የምርምር ዘርፍ ለማነቃቃት ማሰቡን ለሪፖርተር የተናገሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ስትራቴጂካዊ አማካሪ አቶ ሔኖክ አህመድ፣ ፖሊሲው የምርምር ውጤቶች ኢኮኖሚያዊ ዋጋ እንዲኖራቸው ሥርዓት እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡

አቶ ሔኖክ ከዚህ ቀደም የምርምር ዘርፉ ለመንግሥት ብቻ የተተወ እንደነበር አስታውሰው፣ የግሉ ዘርፍ የምርምር ውጤቶችን ለመሸጥ ቢፈልግ እንኳን፣ የንግድ ሕጉ የምርምር ሥራ ሽያጭን እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ ዕውቅና እንዳልሰጠው ገልጸዋል፡፡ አሁን በፀደቀው ፖሊሲ መሠረት ግን፣ የግል ዘርፎችም ሆኑ የውጭ ኩባንያዎች የምርምር ውጤቶችንና በምርምር የተገኙ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች መሸጥ ይችላሉ፡፡

እንደ አዲስ የሚቋቋሙ ኩባንያዎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ አዳዲስ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ የሚገቡበት ዘርፍ ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን በራሳቸው ከማጥናት ይልቅ፣ ለዚህ ተብለው የተቋቋሙ ተቋማት ያደረጓቸውን ጥናቶች መግዛት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ አንድ ምርት በደንበኞች ዘንድ ያለው ተጠቃሚነት ምን ያህል ነው? ደንበኞች ምን ይፈልጋሉ? የገበያ ትስስሩ ምን ያመስላል? እንዲሁም በዘርፉ ላይ ያሉ ተወዳዳሪዎች ተደራሽነታቸው ምን ያህል ነው የሚሉትን መረጃዎች ምርምር ከሚያደርጉት ተቋማት ይገዛሉ ብለዋል፡፡

ምርምር አድርገው የሚሸጡ ተቋማት ሥራቸው ከኢትዮጵያም ውጪ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥበት ዕድል እንደሚኖር አክለዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ የተለያዩ ማበረታቻዎች ይቀርቡላቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ጥናቶች ሲደረጉ የቆዩት በመንግሥት ብቻ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሔኖክ፣ አንዳንድ ሰዎች ከሚያደርጓቸው በጣም ትናንሽ የሚባሉ ምርምሮች ውጪ የግሉ ዘርፍ እንዳልተሰማራበት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ዘርፉ የተደራጀ ሥርዓት ስላልተፈጠረለት ቁጥጥር እየተደረገበት፣ ዕውቅና እየተሰጠው የሚንቀሳቀስ እንዳልነበረ አክለዋል፡፡ አሁን ግን ሚኒስቴሩ ይኼንን ሥርዓት የማምጣት፣ አገራዊ ምርምሮችን የመምራትና የመቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸው በጥናት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ እንዲሳተፉ እንደማያግዳቸው የሚያወሱት አማካሪው፣ አሁን የፀደቀው ፖሊሲ ኢንዱስትሪዎች ጥናትና ምርምርን አንድ የሥራ ክፍላቸው የሚያደርጉበትን ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡ ይኼንን ፖሊሲ የሚያወርድ አዋጅ እንዲሁም ማስፈጸሚያ ደንብና መመርያ እንደሚወጣለት ተገልጿል፡፡

ከዚህም ባሻገር ፖሊሲው የአዕምሮአዊ ንብረቶች ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ኖሯቸው በራሳቸው የገንዘብ አቅርቦት እንዲያገኙ የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ ፖሊሲው አንድ አዕምሮአዊ ንብረት በራሱ ዋስትና የሚሆንበትን ሥርዓት እንደሚዘረጋ የተናገሩት አቶ ሔኖክ፣ ይኼ ጉዳይ በተለይም ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰማሩ ጀማሪ ቢዝነሶች (startup) ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

እንደ አማካሪው ገለጻ ጀማሪ ቢዝነሶች (startup) ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ፖሊሲ ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ ፖሊሲውን ተከትሎ የሚፀድቀውን ቀድሞ የተዘጋጀው የስታርትአፕ ረቂቅ አዋጅ ጀማሪ ቢዝነሶች ንግድ ፈቃድ አውጥተው ታክስ መክፈል ከመጀመራቸው በፊት ሁለት ዓመት የሽግግር ጊዜ ይሰጣል፡፡ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር የሚቋቋም የኢኖቬሽን ፈንድ ደግሞ በጣም ጥቅም ላላቸው፣ ኩባንያ ቢሆኑ ሊሳካላቸው ለሚችልና በምርምርና ሙከራ ተፈትነው ማለፍ ለሚችሉ ነገር ግን የገንዘብ እጥረት ያለባቸውን ጀማሪ ቢዝነሶች በአገር አቀፍ አወዳድሮ ፈንድ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ፈንዱ በተለያዩ አማራጮች የሚቀርብ መሆኑን፣ እንደ ቢዝነሱ ዓይነትና ጥንካሬ የማይመለስ ገንዘብ የሚሰጣቸው ቢዝነሶችም ይኖራሉ ብለዋል፡፡ አቶ ሔኖክ ረቂቅ አዋጁ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተልኮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመፅደቅ ተራ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች