Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየደቡብ ሱዳን መንግሥትና ታጣቂዎች ውጊያ በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል

የደቡብ ሱዳን መንግሥትና ታጣቂዎች ውጊያ በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል

ቀን:

የሱዳን መንግሥትና መንግሥቱን የሚቃወሙት (Sudan People’s Liberation Movement-in-Opposition-SPLM-IO) በጋምቤላ ክልል፣ በኢትዮጵያ ድንበር የሚያደርጉት ውጊያ፣ ድንበር አካባቢ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ መጣሉ ተገለጸ፡፡ ታጣቂቹ ከዚህ ቀደም ድንበር ተሻግረው ውጊያ ሲያካሂዱ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ በውጊያው የተተኮሱ የከባድ መሣሪያ አረሮች ድንበር አልፈው መግባታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የሚገኙት ጂካዎና ላሬ ወረዳዎችን የሚያዋስኗቸው የደቡብ ሱዳን ወረዳዎች፣ የታጣቂዎቹ ካምፖች የሚገኙባቸው መሆናቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት፣ የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ፣ ሁለቱ ኃይሎች እርስ በርስ ሲዋጉ የሚተኮሱ ትልልቅና ርቀት ያላቸው መሣሪያዎች በድንበር አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ሥጋት ላይ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ውጊያው ሲነሳ በነዚህ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ወደ አጎራባች ወረዳና ቀበሌዎች ለመሸሽ እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡

በመጋቢት ወር መጀመርያ ላይ ከመንግሥት አካላት ውጊያ የተከፈተባቸው ታጣቂዎች በመሸሽ ድንበር ተሻግረው ወደ ክልሉ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ድንበር ተሻግሮ በተደረገው ውጊያ አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ ስድስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ላይ በተደረገ ውጊያ ደግሞ ታጣቂዎቹ ድንበር ባይሻገሩም፣ የተተኮሱ መሣሪያዎች ወደ ጋምቤላ ክልል መዝለቃቸውን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ባለፈው ሳምንት የተደረገው ውጊያ የመንግሥትን ካምፕ ለመቆጣጠር የተደረገ እንደነበር የገለጹት አቶ ኡጌቱ፣ ታጣቂዎቹ ካምፑን ከተቆጣጠሩ በኋላ ‹‹ትልቅ ውጊያ›› ተደርጎ መንግሥት እንዳስመለሰው አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው ይህ ሥጋት በመኖሩ በአካባቢው ልዩ ኃይሎች እንዲሰፍሩ መደረጉን፣ በድንበር ኬላ ላይ የነበሩ የፌዴራል ፖሊሶች ጥበቃ እንዲያጠናክሩ ንግግር መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአካባቢው ከሚገኙ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮች  ውጊያ፣ ወደ ጋምቤላ ክልል እንዳይመጣ ለማድረግ ንግግር መደረጉንና ወደ ክልሉ የሚደርሱ ትላልቅ መሣሪያዎች እንዳይተኩሱ ሐሳብ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

አቶ ኡጌቱ፣ ‹‹ድንበር አቋርጠው ወደኛ ገብተው ውጊያ እንዳያደርጉ የተሰጣቸው መመርያ አለ፡፡  ይህንን የሚያደርጉ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝም እንደማይልና ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው  ንግግር ተደርጎ አንድ ሐሳብ ላይ ተደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን መንግሥትና በታጣቂዎቹ መካከል የሚደረገው ውጊያ በድጋሚ እንደማይነሳ የማይታወቅ በመሆኑ፣ አሁንም ሥጋት መኖሩን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ውጊያው የደቡብ ሱዳን ውስጣዊ ጉዳይ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ‹‹አትዋጉ›› ማለት እንደማይቻል ጠቁመው፣ ሕዝቡ ግን በአቅራቢያው ውጊያ ሲደረግ እንደሚሸሽ አስረድተዋል፡፡

‹‹አማፂም ሆነ መንግሥት ወደ እኛ ግዛት አቋርጠው መግባት የለባቸውም፡፡ ወደ እኛ ግዛት ስትገቡ የእኛ ማኅበረሰብ ሥጋት ትሆናላችሁ በማለት ነው የተናገርነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ይህንን ግን እንዳታደርጉ ብለን ካደረጉት የኢትዮጵያ መንግሥት የማይሳተፍበት ምክንያት አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን ጋር ትልቅና ክፍት ድንበር የሚጋራው የጋምቤላ ክልል፣ በአጎራባች አገር በኩል የሚመጣበት ችግር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ድንበር ተሻግረው በመግባት የሕፃናትና ከብቶች ዝርፊያ፣ እንዲሁም ግድያ አድርሰዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ከመስከረም እስከ የካቲት 2014 ዓ.ም. 18 ሰዎችን ገድለው ስምንት ሕፃናትን የወሰዱ መሆናቸውን፣ ከ300 በላይ ከብቶችን መዝረፋቸውም ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት ሳቢያ 20 ሺሕ የክልሉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል፡፡

ከሙርሌ ታጣቂዎች የሚመጣው ጥቃት አሁን ላይ መቀነሱን የሚናገሩት አቶ ኡጌቱ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳልጠፋና እሑድ ሚያዝያ 9 ቀን  2014 ዓ.ም. ታጣቂዎቹ አንድ ሰው መግደላቸውን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ድረስም የተወሰዱትን ሕፃናት በሙሉ ማስመለስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...