Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአጎአ የሚጎዱ ኩባንያዎች ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲያቀርቡ ጥናት እየተደረገ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎአ) ተጠቃሚነት በመሰረዟ ምክንያት፣ ጉዳት የሚደርስባቸው የውጭ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በአገር ውስጥ የሚያቀርቡበት አማራጭ ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ፣ እስካሁን ድረስ በአጎአ ምክንያት ሥራውን ያቋረጠ ኩባንያ እንደሌለ የገለጸ ቢሆንም፣ ከግንቦት ወር በኋላ የዕድሉ መቋረጥ ተፅዕኖ በኩባንያዎቹ ላይ በግልጽ ይታያል የሚል ሥጋት አለው፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ 82 በመቶው የአጎአ ዕድል ተጠቃሚዎች እንደነበሩ የገለጸው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከዕድሉ መቋረጥ በኋላ ባጋጠማቸው የዋጋ መጨመር ሳቢያ ከዚህ ቀደም የተቀበሉትን ትዕዛዝ ለማቋረጥ የተገደዱ እንዳሉ አስረድቷል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፣ ኩባንያዎቹ ወደ አገር ውስጥ የገቡት ሁሉንም ምርታቸውን ወደ ውጪ ለመላክ ውል ገብተው ቢሆንም ከምርቶቻቸው ውስጥ የተወሰነውን ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፣ ኮሚሽኑ ይህንን ጥናት እያደረገበት ያለው ብዛት ያላቸው ኩባንያዎች ይኼ አማራጭ እንዲታይላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ጥያቄን ካቀረቡት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የቻይናው ሁዋጂያን የጫማ አምራች ፋብሪካ (Huajian shoe factory) ሲሆን ኩባንያው በኮቪድ-19 ምክንያት ምርት ካቋረጠ በኋላ ወደ ሥራ መመለስ ቢፈልግም የአጎአ ዕድል መቋረጡ ምርት እንዳይጀምር አድርጎታል፡፡

‹‹በቆዳ ላይ የተሰማሩ ሦስት አራት ኩባንያዎች [ምርታቸውን በአገር ውስጥ ለማቅረብ] ጠይቀው የተወሰነ ያህል በአገር ውስጥ ገበያ ላይ እንዲንቀሳቀሱ በማኔጅመንት የተፈቀደላቸው አሉ፤›› ያሉት አቶ ተመስገን፣ ኮሚሽኑ የኩባንያዎቹን ጥያቄ በተናጠል ከመመለስ ይልቅ በሁሉም ዘርፍ ላይ ያሉ የውጭ ኩባንያዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወጥ ሥርዓት የሚዘረጋበትን መንገድ እያጠና መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ለአገር ውስጥ ገበያ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ‹‹ውላቸው ይሻሻል ወይስ ሌላ አማራጭ ይታይ›› እና ‹‹ከምርታቸው ውስጥ ምን ያህሉን በአገር ወስጥ ይቅረብ›› የሚሉት በጥናቱ ውስጥ የሚታዩ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ተመስገን አስረድተዋል፡፡

ምርቱን በአገር ውስጥ ለማቅረብ ጥያቄ ካቀረቡት ውስጥ አንዱ የሆነው ሁዋጂያን የጫማ ፋብሪካ የምርቱን 50 በመቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን ጥያቄ ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመራው ፋብሪካው ‹‹የምርቱን 20 በመቶ ለማቅረብ እንዲፈቀድለት›› በሚል መሆኑን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፍርጀቦ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዘጠኝ ወር ውስጥ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አቅዶ 2.43 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ማሳካት የቻለው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኤክስፖርት አፈጻጸምም ካቀደው 223 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ያገኘው 156.7 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ኮሚሽኑ በኤክስፖርት ዘርፉ ዕቅዱን እንዳይሳካ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው የአጎአ ዕድል መታጣት ምክንያት ትዕዛዞች መሰረዛቸው ነው፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ወራት የአጎአን ዕድል የሚተኩ ሌሎች ገበያዎችን ለማፈላለግ የአውሮፓ፣ ጃፓንና ቻይና ገዢዎችን እያነጋገረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ከተደረጉት ንግግሮች ውስጥ ፍሬያማ ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ያለው በአውሮፓ የሚገኘው የኤች ኤንድ ኤም (H&M) እና ዲካትሎን (Decathlon) ገበያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ኢትጵያ ውስጥ ያሉት ኢንቨስትሮች ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ቷሟልተው የሚቀርቡ ከሆነ የኤክስፖርት አፈጻጸሙ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የአጎአ ዕድል ተጠቃሚነት መመለስ ጉዳይ ኮሚሽኑ በእጅጉ ትኩረት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች ውስጥ እንዱ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፣ ለዚህም ሲባል በተለይ መሠረታቸው አሜሪካ የሆኑ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታን ለአሜሪካ መንግሥት እንዲገልጹ ኮሚሽኑ እየጎተጎተ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ኢንቨስተሮቹ ከዚህ ቀደምም ሎቢስቶችን ጭምር በመጠቀም የአጎአ ዕድልን በተመለከተ ሲሠሩ እንደነበር አክለዋል፡፡

በቅርቡ ወደ አሜሪካ የተጓዙት የኢትዮጵያ ልዑካንም የአጎአ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ንግግር እንደተደረገ የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ የአሜሪካ ገዢዎችንም በማግኘት ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከዘሪፖርተር እንግሊዘኛ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል መንግሥት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የመተካት ጉዳይን ቅድሚያ እንደሰጠውና የኤክስፖርት በቀጣይነት እንደሚታይ ተናግረው ነበር፡፡ አሁን በአገር ውስጥ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የሚፈቀድላቸው የውጭ ኩባንያዎች ከውጭ የሚገባ ምርትን በአገር ውስጥ እንዲተኩ እንደሚደረግ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች