Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ17 ዓመታት በኋላ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ በመንግሥትና በትራንስፖርት ማኅበራት መካከል አለመግባባት ፈጠረ

ከ17 ዓመታት በኋላ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ በመንግሥትና በትራንስፖርት ማኅበራት መካከል አለመግባባት ፈጠረ

ቀን:

በ1997 ዓ.ም. ወጥቶ በሥራ ላይ ያለውን የትራንስፖርት አዋጅ በማሻሻል፣ እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ በውይይት ላይ የሚገኘው ረቂቅ የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣ በትራንስፖርት ማኅበራትና በመንግሥት መካከል አለመግባባት ፈጠረ፡፡

አሁን በሥራ ላይ ካለው የትራንስፖርት አዋጅ ውስጥ ራሱን ችሎ እንዲወጣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል፡፡

የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች፣ የትራንስፖርት ማኅበራትና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም.  ይፋዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሁለትና ከሁለት በላይ ክልሎችን በሚያገናኙ መንገዶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና መሠረተ ልማቶች፣ በመንገዶች በሚገለገሉና በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም የመንገድ ተጠቃሚዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ማብራሪያው ላይ ሠፍሯል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ አቶ አበጀ ማሞ ረቂቁን አስመልክተው ማብራሪያ ሲሰጡ አዋጁ በትራንስፖርት ዘርፍ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖርን የመንገድ ትስስር ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ክልሎች ከሚያስተዳድሩት ውጪ ያሉ መንገዶችንና ክልሎችን ከክልሎች በሚያወሰኑ መንገዶች ላይና የአገሪቱ ዋነኛ  የኢኮኖሚ መሠረት በሆኑ መንገዶች ላይ መሠረት የሚጥል አዋጅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በረቂቁ እንደተመላከተው በቀድሞው የትራንስፖርት ባለሥልጣን  ተመዝግበው ማንኛውም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የትራንስፖርት ማኅበራት ፈርሰው፣ አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ንግድ አደረጃጀት ተቀይረው በሽርክና ወይም በግል የንግድ ድርጅት በድጋሜ እንዲመዘገቡ አስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ በውይይቱ የተሳተፉ በርካታ የትራንስፖርት ማኅበራት አሁን   በማኅበር ተደራጅተው ከሚሰጡት አገልግሎት ወደ ንግድ ተቋምነት ይቀየራሉ የሚለውን አሠራር ተቃውመውታል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ አግልግሎት ለ45 ዓመታት አገልግያለሁ የሚሉትና ከተባበሩት ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር አቶ ተወልደ ብርሃን ዓለማየሁ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ማኅበራት ወደ ንግድ ይቀየራሉ የሚለው አንቀጽ ላይ፣ ‹‹ከትራንስፖርት ማኅበራት ጋር ባደረግነው ውይይት በአዋጁ ላይ ችግር የለብንም፡፡ ነገር ግን ማኅበራት ወደ ንግድ ተቋም ይቀየራሉ የሚለውን አልቀበለውም፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበራት የግለሰብ ተሸከርካሪዎች የሥምሪት ማዕከላት ሆነው፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡

ወደ 75 የሚደርሱ በግለሰብ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች የተዋቀሩ ማኅበራትና ከ15 ሺሕ የማያንሱ ተሸከርካሪዎች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ከዚህ በኋላ በማኅበር ሳይሆን በንግድ ተቋምነት ተንቀሳቀሱ ተብሎ በግዴታ መቀመጡ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡

ባለንብረቶች ተሸከርካሪዎቻቸውን አስገምተው ወደ አንድ አክሲዮን ድርጅት እንዲገቡ ተብሎ በረቂቁ መደንገጉ፣ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ግለሰቦች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከቢለን ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ 1-ሀ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር የመጡት ተወካይ በበኩላቸው፣ ‹‹የትራንስፖርት ማኅበራት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ሚና አግዝፎ እንኳ ባይታይ፣ አኩስሶ ማየቱ ለእኔ ጥሩ ነገር አልተሰማኝም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መዘመንና መሻሻልን የሚጠላ የለም፤ ነገር ግን በአማካይ ወደ 95 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱን ወጭና ገቢ ደረቅ ጭነት ተሸክመው ያሉት እነዚህ ማኅበራት በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ንግድ ይዛወራሉ መባሉን እቃወማለሁ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የዩናይትድ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ወልደ ሥላሴ፣ ‹‹አንድ ጎማ 30 ሺሕ ብር እየገዛን ባለንበትና ሥራ በሌለበት ተሸከርካሪዎችን ለሽርክና ማኅበር አስገቡ ከተባለ፣ ንብረቶቻችንን አስረክበን እኛ እጃችንን አጣምረን በዓመት ትርፍ ይመጣል ብለን ስንጠብቅ ምን ልንበላ ነው? ምንድነው የምናደርገው?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ ባለንብረት ማለት ደሃ ነው፣ ምንም ነገር የለውም፡፡ አንድ ተሸከርካሪ አሥር ቢያጆ ጂቡቲ ደርሶ ሲመጣ ስምንቱ ጎማ ባዶ ነው፡፡ መንገድ በሌለበት ነው እየሠራን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይሉ ፀጋዬ የተባሉ የአዲስ ትራንስፖርት ባለቤት አዋጁ ተዘጋጅቶ በዚህ መልክ መቅረቡ መልካም የሚባል ቢሆንም፣ መንግሥት የትኛውንም ዓይነት ጥሪ ሲያደርግ ፈጥነው የሚደርሱትና የአገሪቱን ጭነት ተሸክመው ያሉት የተሸከርካሪዎች ባለንብረቶች ልጆቻቸውን አብልተው ለማደር እየተቸገሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወራት ወስጥ ከማኅበር ወደ ንግድ በአንድ ጊዜ ትቀይራላችሁ ሲባል፣ እንዲያው ተሽከርካሪ ሲባል ሾፌርና ባለንብረቱ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ማኅበሩ ውስጥ ያሉ በርካታ ሠራተኞች መኖራቸው እየታወቀ ማኅበሮች ሲፈርሱ ሠራተኞችን ሊበትኑ ነው ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙ በርካታ የማኅበራት ተወካዮች አሁን በሥራ ላይ ያሉ ማኅበራት ፈርሰው በአዲስ የንግድ አሠራር በስድስት ወራት ውስጥ ይገባሉ የሚለውን አሠራር ሠራተኛ ሊበተን ነው፣ ጊዜው አጭር ነው፣ ሽርክና መግባት ገቢ ያሳጣናል፣ የሚሉና መሰል አቤቱታዎችን አሰምተዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪው አቶ አበጀ በሰጡት ምላሽ ማኅበራት ሠራተኛ ልንበትን በሚል ያቀረቡትን ሐሳብ፣ ‹‹ሲጀመር ሠራተኛ አላቸው ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም የአዋጁ አንድምታ ማኅበራቱ ሠራተኛ ወደሚቀጥር ጠንካራ ወደ ሆነ የንግድ አደረጃጀት እንዳይዞሩ በማሰብ የተቀረፀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ ማኅበራት አይደለም ሠራተኛ ቢሮ እንኳን የላቸውም ያሉት አቶ አበጀ፣  እንደ ተቋም ሊቀርብ የሚችል ማኅበር እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡

ከጅምሩ ይህን ውዝግብ የፈጠረው ማኅበራት በመመርያው መሠረት መደራጀት የነበረባቸው በማኅበራት ማደረጃ ቢሆንም፣ ከማኅበራት ማደራጃ ወጥተው በትራንስፖርት ባለሥልጣን ሲቋቋሙ ለጋራ ዓላማ የተሰበሰቡበትን ወደ ጎን በመተው ሌላ ሥራ ውስጥ እንደገቡ አቶ አበጀ አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ማኅበራቱ የሥራ ዕድል እንደሚቋረጥ በሚል ያቀረቡትን ምክንያት ሲጀመር የተፈጠረ የሥራ ዕድል ስለመኖሩም እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ነገር ግን ወደፊት እነዚህ ማኅበራት ድርጅትና ነጋዴ ሲሆኑ የሚፈጠር የሥራ ዕድል መኖሩ ግልጽ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ጠንካራና ተወዳዳሪ የሚሆን፣ ኦዲት የሚደረግ ሕጋዊ አሠራር በመግባት ሕገወጥ መስመራቸውን ትተው እንደሚመጡ የታቀደበት ረቂቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የማኅበራት አመራሩ ራሳቸውን እንደገና ሊያዩ ይገባል፡፡ ማኅበራት ከጅምሩ የተሳሰተ መስመር ውስጥ ገብተዋል፤›› ካሉ በኋላ የተሰጠው የስድስት ወራት የሽሽግር ጊዜ በቂ መሆኑን  አመልክተዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ደኅንነት አገልግሎተ ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፣ ማኅበራቱ ወደ ንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ለሽግግር የተሰጠው ጊዜ ከበቂ በላይ መሆኑን በመግለጽ አሁን በሥራ ላይ ባለው የማኅበር አሠራር ከቦርድ አባላት ውጪ ሌላ ተጠቃሚ አካል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

አንድም ማኅበር የተቋቋመበትን ዓላማ ያሳካ አለመኖሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የተሸከርካሪ ባለቤቶች ማኅበራት ውስጥ ካልገቡ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት ዕድል ስላልነበረ፣ ተሽከርካሪዎችን ወደ ማኅበር አስገብተው በተሽከርካሪዎቻቸው ሲጠቀሙ የነበሩት ግን ማኅበሩ ውስጥ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች ቤተሰቦች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም አንድ ተሽከርካሪ ጂቡቲ በደርሶ መልስ ከ100 እስከ 140 ሺሕ ብር ገቢ እያስገባ መንግሥት ግን ከማኅበራቱ ማግኘት የነበረበትን ግብር እያገኘ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱልበር፣ አንድ ተሸከርካሪ በቁርጥ ግብር እየከፈለ ያለው ዓመታዊ 7,000 ሺሕ ብር ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ አብዛኞቹ ማኅበራት ብልሹ አሠራር ውስጥ የገቡ በመሆናቸው ወደ ትክክለኛው መንገድ በመምጣት በንግድ ሥርዓት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው፣ አዲሱ አዋጅ የግድ ሽርክና ውስጥ አንዲገቡ የማያስገድድ በመሆኑ በግል ንግድ ፈቃድ አውጥተው መሥራት አንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...