Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው ያወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በመጣስ የቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ

ፓርላማው ያወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በመጣስ የቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ዓ.ም. ያፀደቀውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በመጣስ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን ሹመት አፀደቀ፡፡

ፓርላማው መጋቢት 29 ቀን 2014ዓ.ም. ባካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርጠው የተላኩ ዘጠኝ የቦርድ አባላትን፣ በስብሰባው ከተገኙ 243 የምክር ቤቱ አባላት መካከል በ11 ተቃውሞና በ17 ድምፀ ተዓቅቦ በአብለጫ ድምጽ ሹመቱን አፅድቋል፡፡

መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 መሠረት የሚቋቋመው ቦርድና የቦርድ አባላቱ አሰያየምና አሿሿም በአዋጁ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ ሁለት (ሀ) መሠረት፣ የቦርድ አባላት ዕጩዎቹን የመመልመልና የማፅደቅ ሒደት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡ ዕጩ ግለሰቦችን ለመጠቆምና በዕጩዎች ላይ አስተያየቶች እንዲሰጡ ዕድል እንዲሰጣቸው ይደረጋል ይላል፡፡

ይሁን እንጂ ለፓርላማው ሸሙታቸው እንዲፀድቅ የተላኩትና የተሾሙት የቦርድ አባላት ያለምንም ሕዝብ ጥቆማና አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰይመው ለፓርላማው የቀረቡ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በዚሁ አንቀፅ ሥር የዕጩዎች አመራረጥ ሒደትና የተመረጡ ዕጩዎቹ ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌሎቹ ኤሌክትሮኒክ ማሠራጫዎችም ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ቢገለጽም፣ የተሾሙ የቦርድ አባላት ወደ ፓርላማ ከመላካቸው በፊት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ የተደረገበት ጊዜ የለም፡፡

መገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንቀጽ አምስት መሠረት ከቦርዱ አባላት መካከል ሁለቱ ከሲቪል ማኅበረሰብ ሁለቱ ከመገናኛ ብዙኃንና ሁለቱ ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ጠቀሜታና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሦስቱ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት የተውጣጡ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡

ነገር ግን ሹመታቸው በምክር ቤቱ ቀርቦ የተሾሙት የቦርድ አባላት ከላይ በአዋጁ መሠረት ስለመመረጣቸው ግልጽ የሆነ መሥፈርት አልተቀመጠም፡፡

በሌላ በኩል የቦርድ አባላት የሚመረጡበትን መንገድ በአዋጅ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ ስድስት መሠረት የቦርድ አባል ለመሆን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆነ ሰው መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ይሁን እንጂ ለፓርላማው ሹመታቸው ከፀደቀላቸው የቦርድ አባላት የተወሰኑት የብልፅግና ፓርቲ ተመራጮችና የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡

ለአብነትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡

ቀሪዎቹ ተሿሚዎች ሀሰን አብዱልቃድር (አምባሳደር)፣ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)፣ መሳይ ገብረማርያም፣ ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ፣ ቀሲስ ታጋይ ታደለና ኡስታዝ ያሲን ኑሩና ናሲሴ ጫሊ (አምባሳደር) ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ላይ በሕዝብ ዘንድ ተቃውሞ እየተሰማባቸው ነው፡፡

የቦርድ አባላቱ አሰያየም ሕግ የጣሰ አካሄድ የተከተለ መሆኑን ተከትሎ ለሚዲያ ዘርፍ ተዋናይ የሆኑ በርካታ አካላት በተለያዩ መንገዶች ፓርላማው ውሳኔውን እንዲቀይር እየጠየቁ ይገኛል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት የሚያቋቁመውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አርቃቂ የነበሩትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለሙያ፣ ይህ አዋጅ መጀመርያ ሲረቀቅ የነበረው አንድምታ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ከፖለቲካም ሆነ መሰል ዓይነት ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲቆም ማስቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከጅምሩ የሚዲያ ሕጉን ለማሻሻል የነበረው ዕሳቤና አዋጁ ያስፈለገበት ምክንያት በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት ጫና ውስጥ በመግባቱና በዚህ ምክንያትም የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንቅፋት በመሆኑ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ልምዱም እንደሚያሳየው እንደዚህ ዓይነት የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካላት ነፃ ሆነው እንደሚቋቋሙ የገለጹት ባለሙያው አዋጁ በግልጽና በደንብ ታስቦበት የመገናኛ ብዙኃንን ነፃ ለማድረግ በሚል የተዋቀረ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ከአዋጁ በተቃራኒ የፖለቲካ አባል የሆነ ግለሰብ የቦርድ አባል ሆኖ ሲቀርብ በጣም አስደንጋጭና የሚያሳዝን ሁኔታ መሆኑን የገለጹት እኝህ የሪፖርተር ምንጭ ይሄ ንቀት ለሕግ የበላይነት አለመገዛት ለዴሞክራሲ ሥርዓት፣ ለሕዝቡና ለሚዲያው በአጠቃላይ ንቀት የታየበት አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በግልጽ በአዋጅ የተቀመጠን ጉዳይ ‹‹ማን ይከለክለኛል›› በሚል በማን አለብኝነት ‹‹ማን ያዘኛል? ማን ተጠያቂ ያደርገኛል?›› በማለት የተደረገና በምንም መልኩ ሊብራራ የማይችል ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ስለዚህ በዚች አገር ላይ ሕግ መከበር አለበት ከተባለ፣ ሁሉም የሚመለከተው አካል የአገሪቱ ትልቁ የሕግ አካል ሕጉን ሲጥስ ዝም ብሎ መታየት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

በሚዲያ ዘርፍ ልማት ባለሙያ የሆኑትና ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት ‹‹ጉዳዩ ዓይን ያወጣ የሕግ ጥሰት ስለመሆኑና ስንት ጊዜ ተለፍቶበት የተዘጋጀውን አዋጅን በዚህ መልኩ ሲጣስ መጮህ ያለበት አካል ሁሉ መጮህ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሊጨነቁ የሚገባቸው ሚዲያና የሚዲያ ተቋማት ብቻ ሳይሆን  የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር ሕጉ ሲጣስ ለምን ዝም ይላሉ? መጠየቅ አለባቸው ሲሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የሚዲያ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያ ላይ የሚሠሩ አካላት እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ድምፃቸውን ካላሰሙ በቀጣይ መንግሥት ነገሮችን እንደፈለገ ሲጠመዝዝ እንደሚኖር ማወቅ አለባቸውም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ መጮህ እንዳለበትና ሒደቱ በሕገወጥ መንገድ የተከናወነ የምልመላና የአሿሿም ሥርዓት እንደሆነ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ጉዳዩ በዝምታ ከታለፈ መንግሥት ዛሬ በሚዲያው ዘርፍ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ሲያስተላልፍ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በቀጣይ ሊደግመው እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡

‹‹የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሲሾም ሕጉ ከሚፈቅደው ውጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ማንም የጠየቀና የጮኸ አካል አልነበረም፡፡ አሁንም በዚያ ዓይነት አሠራር ለማለፍ እየተሞከረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ፓርላማው ያወጣውን ሕግ እንኳን በትክክል መፈጸሙን መከታተል አልቻለም፤›› ያሉት ባለሙያው፣ ጉዳዩ መቀጠል የለበትም ፓርላማው የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ማኅበራትና ሚዲያ ላይ የሚሠሩ ተቋማትና አካላት መጮህና መጠየቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

ቦርዱ የባለሥልጣኑን ውሳኔዎች በይግባኝ የመከታተል፣ አመልካቾችና ባለፈቃዶች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች፣ ባለፈቃዶችን አስመልክቶ ከሕዝብ የቀረቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን መርምሮ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አፈጻጸም በሚመለከት በሚቀርቡ በማናቸውም የፖሉሲ ጉዲዮች ላይ ይመክራል፤ እንደአግባብነቱ ለመንግሥት የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...