በስንታየሁ ደምሴ አጅበው
በአገራችን ውስጥ የትግራይን ሕዝብና የአማራን ሕዝብ ያህል የጋራ ባህልና ታሪክ ያለው ሕዝብ የለም፡፡ የአማራንና የትግራይን ሕዝብ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ታሪክና ባህል ብቻ ግን አይደለም፡፡ የአገራችን የከፋ ድህነትም የሚገኘው በእነዚህ ክልሎች ነው። የትግራይና የአማራ ምድር ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ያለ ፋታ ለዘመናት ጦርነት የተካሄበት ነው። አሁን ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ አውዳሚ የሆነ ጦርነት በእነዚህ ድህነት ባደቀቃቸው ክልሎች ውስጥ ተከናውኗል። ጉዳቱ እንደ አገር ቢሆንም ጦርነቱ የተካሄደባቸው የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች ላይ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው። እነዚህ ሕዝቦች ተጨማሪ ጦርነት ለማስተናገድ ቀርቶ በዚህ ጦርነት የገቡበትን ሰብዓዊ ቀውስ መወጣት የሚችሉበት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡
መንግሥት ጫና ሲበዛበት ሊያደርግ የሚችለውን እያየን ነው። መንግሥትን ብቻ ተከትሎ ጦርነት ሲል ጦርነት፣ ሰላም ሲል ሰላም ከማለት አንፃራዊ ሰላም ባለበት ወቅት ለዘለቄታዊ ሰላም መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ወደን ወደ ጦርነት አልገባንም። ድጋሚ ወደ ጦርነት እንዳንገባ ግን መሥራት ይቻላል።
ለትግራይ ሕዝብ ከአማራ ሕዝብ የቀረበ ወንድም የለውም። ምንም ያህል ወደ ግጭት ቢገባ ችግር ሲጠናበት የሚሰደደው ወደ አማራ ክልል ነው። በራሱ በመከራ ውስጥ ያለው የአማራ ሕዝብም ስደተኞቹን በጨዋነት ተቀብሎ እያስተናገደ ነው። ይኼ ትልቅነት ነው። እዚህ ላይ መገንባት ያስፈልጋል።
ፖለቲካዊ ችግሮቹን ለታላቅና ታናሽ ወንድማማቾቹ (ሕወሓትና ብልፅግና) ትቶ፣ ሰላም በሆነበት አጋጣሚ ድጋሚ ወደ ጦርነት እንዳንገባ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራ መሥራት፣ ያልተሞከረውን መሞከር ያስፈልጋል። ጎንደር ላይ፣ ‹‹የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የእኛም ደም ነው›› የሚል መፈክር ይዘው የወጡ ወጣቶች፣ የመንግሥትን መንበር የነቀነቀ የኦሮሞንና የአማራ ሕዝብን አንድነት ማምጣት ችለው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሕወሓትን ከመንበር ከመፈንገል ያለፈ ዕድገት ማሳየት ባይችልም፣ የወቅቱ የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብ የኖረን የመለያየት ትርክት ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ለዘመናት የጋራ ባህል፣ ሃይማኖትና ታሪክ ተጋርተው ለሚኖሩት የትግራይና የአማራ ሕዝቦች ፖለቲካዊ ልዩነቶችን አሳድረው የደፈረሰው ሰላም እንዲመለስ መቀራረብ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡
ከዚህ በፊት የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች መምከናቸው አይጠፋንም፡፡ ሕወሓት መጥፋት የሚችል በመሰለን ወቅት ‹‹አሸባሪውን ሳይደመስሱ መመለስ የለም›› ብለን ፎክረናል፡፡ ሕወሓትም አዲስ አበባ መግባት የሚችል በመሰለው ወቅት፣ ‹‹ከማን ጋር ነው ድርድሩ?›› ብሎ በመንግሥት የቀረበለትን ‘ለድርድር በወረራ ከያዛቸው አጎራባች ክልሎች ይውጣልኝን’ ጥያቄ ላይ አላግጧል፡፡ አሁን ከጦርነቱ በኋላ የተረፈን ነገር በሁለቱም በኩል ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስና የመሠረተ ልማት ውድመት ነው፡፡ ከጦርነቱ በፊት የነበረው ቁመና አሁን የለም፡፡ ያ ማለት ለሰላምም ሆነ ለድርድር ነባራዊ ሁኔታዎች በመሠረታዊነት ባይለወጡም እንኳን፣ ተመልሶ የሰላምን መንገድ ለመመልከት ዕድል አለ ማለት ነው፡፡
የጦርነቱም ምክንያቶችም ሆኑ መፍትሔዎቹ ውስብስብ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ ፍፁም ሰላም ማምጣትም የብዙ ደረጃዎች ሒደት እንደሚሆንም ግልጽ ነው፡፡ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በአገራችን፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረገው የመጀመሪያ ያለ መጎዳዳት ስምምነት “Principle Not to Cause Significant Harm” ከአራት ዓመታት በፊት ህዳሴ ግድቡ አሁን ከደረሰበት የግንባታ ደረጃ ሳይደርስ ነበር፡፡ ዛሬ ግድቡ በከፊል ሥራ ጀምሯል፡፡ ወደ ጦርነት ተመልሶ ላለመግባትና ለነገ ዘላቂ ሰላም ዛሬ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን መጀመር አንድ ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡
ብዙ ተባብለናል። ብዙ ተደራርገናል። ሁሉም ነገር አይወራረደም። ይቅርታ የሚፈውሰው ቁስል፣ ጊዜ የሚፈታው ችግር አለ፡፡ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር አንድ ሕዝብ ነን ብለን ሁሉንም ረስተን በዕንባና በደስታ ተገናኝተናል፡፡ ነገ ተመልሶ የሚገናኝ የአንድ አገር ሕዝብ በጦርነት ከከፈለው በላይ አላስፈላጊ ዋጋ ለምን ይከፍላል?
የባንኮች ኔትወርክ ለአንድ ቀን ባይሠራ የሚፈጠረውን ምስቅልቅል የምናውቅ ዜጎች፣ ያለ ባንክና ያለ መንግሥት ተቋማት አገልግሎት የትግራይ ሕዝብ እንዴት እየኖረ እንደሆነ ለመጠየቅ መድፈር አለብን። በጥላቻና በጦርነት ሞክረን ያልተሳካልንን ሰላም በፍቅር መንገድ ልንሞክረው ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ ስንል አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ ሴቶችና የአካል ጉዳተኞች አሉበት፡፡ ሁሉንም በልሂቁ ልክ ማየት ልክ አይሆንም፡፡ ‹‹እንዴት እየኖርክ ነው ወንድሜ?›› ብሎ መጠየቅ ብዙ መንገድ አብሮ ያስኬዳል፡፡ ለሕወሓት ያለን ጥላቻ የሕዝቦችን የኖረ ወንድማማችነት ሊያዘነጋን አይገባም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡