Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኑሮ ውድነትን በሚመለከት አስፈጻሚው ተቋም ያቀረበው ማብራሪያ ‹‹ፓርላማውን አይመጥንም›› ተባለ

የኑሮ ውድነትን በሚመለከት አስፈጻሚው ተቋም ያቀረበው ማብራሪያ ‹‹ፓርላማውን አይመጥንም›› ተባለ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ‹‹የኑሮ ውድነትን ለመግታት በደላሎች ላይ ወሰድኩ›› ያለውን ዕርምጃ በሚመለከት፣ የምክር ቤቱ አባላት ‹‹ምክር ቤቱን አይመጥንም›› አሉት፡፡

ፓርላማው 247 የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው አምስተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የሚኒስቴሩ የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተገምግሟል፡፡

በሚኒስቴሩ ሪፖርት እንደተመለከተው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ወጭ ከተላከ ምርት 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ዘርፎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከፍተኛውን ድርሻ መያዛቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነቱን ያባብሳሉ ተብለው በተጠረጠሩ 104 ሺሕ የሚጠጉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ በየደረጃው በተዋቀረ የዋጋ ማረጋጋት፣ ሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል በተደረገ ክትትል ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ የምርትና አገልግሎት መቀነስ፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም፣ የፀጥታ ችግር፣ የፍላትና አቅርቦት አለመጣጣምና በርካታ ችግሮችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለታየው የኑሮ ውድነት ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ገብረ መስቀል የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ በሕገወጦች ላይ በተደረገው ክትትል ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት መደረጉን ቢገልጹም፣ የፓርላማ አባላቱ በአገር ደረጃ ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት ከሚኒስቴሩ የተሻለ ማብራሪያ እንደሚፈልጉ በመግለጽ በርካታ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

ዘውዱ ታደሰ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል መንግሥት በውድ ዋጋ ገዝቶ ወደ አገር ያስገባው ድጎማ የሚደረግበት ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገሮች እየወጣ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው፣ የነዳጅ ድጎማን ማንሳት እንደ መፍትሔ ተደርጎ የቀረበው አማራጭ ለአንድ ለችግር የተሻለ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ ለችግሩ ሌላ ተጨማሪ ችግር መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በአገር ውስጥ ለሚታየው የኑሮ ውድነት ችግር ሰበብ አስባብ በመፈለግ ወደ ውጭ የመግፋት አባዜ እንደሚታይበት የገለጹት የምክር ቤት አባሉ፣ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በሕዝቡ መሀል የሚታይ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ልዩነት በተለይም ባለሥልጣናት የሚነዷቸው ቅንጡ መኪኖችና የሚኖሩባቸው ቤቶችን በመጥቀስ፣ ባለሥልጣናቱ የደሃውን ኑሮና ሕመም ሊረዱት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹የዋጋ ንረት ጉዳዩ አሳስቦናል መመለስ አለበት፣ በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የጦርነት ችግር ባሻገር፣ የኑሮ ውድነቱ ድምፅ አልባ ጦርነት ሆኗል፤›› ያሉት ደግሞ ወ/ሮ እታፈራሁ ዘገየ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ አባሏ አክለውም ለኑሮ ውድነቱ ችግር የምርት አቅርቦት እጥረት ነው ከማለት ይልቅ፣ የገባውን ምርት ሥርዓት ባለው መንገድ ለገበያ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም በገበያ ውስጥ የነዳጅ ሽያጭ በሕገወጥ ንግድ እየተመራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ነዳጅ የትም ቦታ ቢካሄድ እጥረት የለም፣ ነገር ግን በዓይኔም እንዳየሁት በሕዝብ ውይይትም እንደ ሰማሁት በማደያዎች የሚደረገው ሕገወጥነትና ጨለማን ተገን ተደርጎ የሚከናወነው ድርጊት አሳፋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ደላሎችን ለመቆጣጠር የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር በሚል ላቀረቡት ምክንያት፣ ‹‹ይህ ለምክር ቤቱ አይመጥንም›› ያሉት የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ጽጌ ዳንጎባ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለኑሮ ውድነት ምክንያት ተብሎ ስለመቅረቡ ሲናገሩ፣ ‹‹ወገን ይህ ምክር ቤት ሊረዳ የሚገባው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲነሳ ሥራ በፈረቃ ሲሠራ በቆየበትና ገበያ በተከለከለበት ጊዜ፣ ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ምርት ባቆሙበት ወቅት እኮ ዘይት 1,000 ብር አልተሸጠም፣ ሳሙና 70 ብር አልተሸጠም፣ ማካሮኒ 70 ብር አልተሸጠም፤›› ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም እንኳን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ግን ለችግሩ መልስ የጠፋው፣ ደሃው እየደረሰበት ያለውን ሥቃይ የከፍተኛ የመንግሥት አመራሩ በሚገባ ሕመሙ ስለማይሰማው እንደሆነ ወ/ሮ ጽጌ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ጽጌ አክለውም  ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ አገር የሚገቡ ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ ወደብ ላይ መክነው ነው የሚቀሩት? ወይስ የት ነው የሚገቡት? በማለት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ወ/ሮ ከድጃ ያሲን የተባሉ የምክር ቤት አባል ድግሞ፣ በቅርቡ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ውይይት ሲያደርጉ ከተሰብሳቢዎች ተነሱልኝ ብለው ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ለ730 ሰዎች 44 ሊትር ዘይት ተካፈሉ ተብሎ እንደተሰጣቸው መስማታቸው አንደኛው ነው፡፡

በስብሰባው የተሳተፉት ሰዎች፣ ‹‹ልታፋጁን ነው ወይ ይህን ያመጣችሁት?›› በሚል ወቀሳ ማቅረባቸውን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በየቀኑ የሸቀጥ ዋጋ እየጨመረ በመሆኑ በነፃ ገበያ ስም ሕዝቡ እየተበዘበዘ፣ ጥቂቶች እየበለፀጉ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ከድጃ፣ ነጋዴው በነፃ ገበያ ስም ሕዝቡ ላይ እንዳገኘ ዋጋ እየጨመረ የሚሄድበት አሠራር ከልካይ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

‹‹ከሕዝብ ጋር በነበረኝ ውይይት ሕዝቡ የኑሮ ውድነቱ ከሕወሓትና ከሸኔ ጋር ከሚደረገው ጦርነት በላይ ይኼኛው የባሰ ጦርነት ሆኖብናል ብሎኛል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ወ/ሮ ዘሙ ተስፋዬ የተባሉ ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ለግብይት ሥርዓቱ መበላሸት በአምራችና በአከፋፋይ፣ በቸርቻሪ ነጋዴና በተጠቃሚ መሀል ያለውን ሰንሰለት በተለይ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ንግድ ሥርዓቱን የሚመራ ደላላ ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡

ብዙውን ጊዜ መንግሥት ቁጥጥር አደረግኩ በሚልበት ጊዜ ምርት ከገበያ እንደሚጠፋና የዋጋ ንረቱ የበለጠ እየጨመረ እንደሚመጣ የተናገሩት ወ/ሮ ዘሙ፣ ይህ የሚያሳየው ገበያውን እየተቆጣጠረ ያለው ደላላ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ሕዝቡ ለማን ይገዛ? ለደላላ ወይስ ለእውነተኛው መንግሥት? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹በየመድረኩ ሌባ አለ እየተባለ ይነገራል፣ ነገር ግን መንግሥት እያለ ይህ ሌባ መቼ ነው ሊቆም የሚችለው?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ መኖር አልቻለም፣ በባለሥልጣኑና በኅብረተሰቡ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ይኼ ነው ተብሎ አይነገርም፡፡ ይህንን ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያውቃል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹በሌላ በኩል ዘይትና ስኳር ወደ ሸማች ማኅበራት ይሄዳል፣ ከዚያ ሸማቹ ወደ እነዚህ ሱቆች ሲሄድ አልቋል ይባልና ወደ መርካቶ ሲሄድ ለሸማች የተከፋፈለው ዘይት ገበያ ውስጥ ይገኛል፣ ያሉት ወ/ሮ ዘሙ፣ በዚህ የተነሳ ኅብረተሰቡ ማንን አምኖ ይኑር? ማነው የሚታመነው? ሕዝቡ ወዴትስ ነው የሚጠለለው? ለኅብረተሰቡ ተብሎ የተደራጀው ሸማች መርካቶ ውስጥ ዘይትና ስኳር የሚሸጥ ከሆነ ከየት መጣ? የሚለውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ራሱን ሊገመግም ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ችግሩ ውጫዊና ውስጣዊ የሚለውን ነገር ትቶ ችግሩን መፍታት ይችላል? ወይስ አይቻልም? የሚለውን ይናገር ብለዋል፡፡

‹‹በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ተወሰደ ተብሎ የቀረበው ሪፖርት በግልጽ ምን ዓይነት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወሰደ ተቆጥሮ ይነገረን?›› የሚል ጥያቄ ያቀረቡት ደግሞ አቶ ብርሃኑ አንካራ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

አቶ ሰንደቅ አዳም የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል ለዋጋ ንረቱ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ሲባል ለኅብረተሰቡ በሚገባ ቋንቋ ምን እየተሠራ እንደሆነ መነገር አለበት ብለው፣ በየካቲትና በመጋቢት 2014 ዓ.ም. የመረጣቸውን ሕዝብ ለማወያየት በሄዱበት ወቅት አንድ በዕድሜ ገፋ ያሉ አዛውንት በኦሮሚኛ ቋንቋ በዚሁ ጉዳይ፣ ‹‹የልጅ መልስ አትስጠን›› እንዳሉዋቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ አርሶ አደሩም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛው ለማን እንናገር በማለት ‹‹ፈጣሪ ያውቃል›› እያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ እንደሚሉት፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ መናር በዋናኝነት በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የዩክሬን የዘይትና ስንዴ አምራቾች ምርት በማቆማቸው፣ ሌሎች አገሮች በጦርነቱ ምክንያት የምርት እጥረት ይኖራል በሚል ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ ባለመሆናቸው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጥን የአቅርቦት ውስንነት መኖር፣ በኬላ መብዛት ምክንያት በሚፈጠር ቀረጥ መናር ሳቢያ ዋጋ በመጨመሩ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና መሰል ችግሮችን አውስተዋል፡፡

በዓለም ገበያ በ2013 ዓ.ም. የነበረው የምግብ ዘይት ድፍድፍ ዋጋ መጨመሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም 672 ዶላር ይሸጥ የነበረው አንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት አሁን 1,900 ዶላር መድረሱን፣ የነዳጅ ዘይትም በርሜል ከ60 ዶላር ወደ 106 ዶላር ማሻቀቡን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በቀጣይ ገበያውን ለማረጋጋት በመንግሥት የሚቀርቡ መሠረታዊ ሸቀጦች ሳይቆራረጡ እንዲገቡ እንደሚደረግ፣ የሸቀጦችን ነፃ እንቅስቃሴ የሚገቱና ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ በየቦታው የተቋቋሙ አላስፈላጊ ኬላዎችን ለማስቀረት ከክልሎች ጋር በመግባባት ይሠራል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...