Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመምህራንና የትምህርት አመራሮች የሙያ ብቃት እስከምን ድረስ?

የመምህራንና የትምህርት አመራሮች የሙያ ብቃት እስከምን ድረስ?

ቀን:

የትምህርት ጥራት ውስንነትን ለመቅረፍና በዘርፉ ላይ የሚታየውን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት መንግሥት ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሠራ ቢሆንም ችግሩ ሥር የሰደደና ከዓመት ዓመት ሲንከባለል የቆ በመሆኑ ክፍተቱ አልተቀረፈም፡፡

የትምህርት ጥራት ችግሩ ከታች ከመዋለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ የዘለቀ፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን፣ በአጠቃላይም ከመማር ማስተማሩ ሒደት መሰነካከል የመነጨ እንደሆነም በተለያዩ መድረኮች ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ዘንድሮ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ይተገበራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ከችግሮቹ መካከል የመምህራን ብቃት ማነስ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረና ይህንን ችግር ለመቅረፍ ለመምህራን ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ሙከራም ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም እንደ ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች በከተማዋ ያሉ መምህራን ክህሎታቸው የዳበረና በመማር ማስተማሩ ሒደት ብቁ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመግታትና የመምህራንን የማስተማር ክህሎት ለመፈተሽ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣንም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሙያ ብቃት ምዘና ፈተናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

የምዘና ፈተናውም፣ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ሙያ ፈቃድም ከአፀደ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ የመንግሥት፣ የግልና ሌሎች መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሠሩ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች እንዲሁም በመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ መምህራንን የሚካተቱበት መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹የትምህርት ቤት አመራሮች ብቃት ለትምህርት ጥራት›› በሚል መሪ ቃል፣ ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ መምህራንና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን የሙያ ብቃት ምዘና ውጤትን ይፋ አድርጓል፡፡

የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ሙያ ፈቃድ ቡድን መሪ አቶ ሰንደቁ ያዛቸው እንደገለጹት፣ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠትና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት መምህራን ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ለመምህራን የሚደረገው ምዘናም የግል ትምህርት ቤቶችን ጭምር ያካተተ መሆኑን ይህም ለነባርና ወደ ሙያው ለሚገቡ ጀማሪ መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራር ከትምህርት ይዘትና ከማስተማር ሥነ ዘዴ አንፃር የነበረባቸውን ክፍተት የሚፈትሽ አሠራር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመመሪያው መሠረት ምዘናው በግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ላይ መተግበሩን የገለጹት አቶ ሰንደቁ፣ በዚህም የተነሳ መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ለመመዘን የሚያስችለውን መሥፈርት ለማሟላት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው አድርጓል ብለዋል፡፡

በምዘናው መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በትምህርት ቤት የሚያካሂዱትን የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ከተዘጋጁት ስታንዳርዶች አንፃር እንዲሆን ጉልህ ሚና እየተጫወተ ሲሆን ከተከናወኑት የምዘና ውጤቶች አንፃር ሲታይ የተመዛኞች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. 4,116 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የጽሑፍ ምዘና መውሰዳቸውን፣ ከዚህ ውስጥም 1,600 የማኅደረ ተግባር ምዘና ፈተና እንደወሰዱና 1,584 ብቁ እንደሆኑ አቶ ሰንደቁ አብራርተዋል፡፡

ከ2005 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ 11,106 የመጀመርያ ደረጃ ትምርት ቤቶች ነባር መምህራን የተመዘኑ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥም 35 በመቶ ተመዛኞች ማለፊያ ውጤቱን ከ62.5 በመቶ በላይ ማስመዝገብ እንደቻሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

በዘጠኝ ዙር የጽሑፍ ምዘና ከወሰዱት 11,106 የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነባር መምህራን ውስጥ 49.5 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ፣ 50.5 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ምዘናውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ 17,849 የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የወሰዱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥም 5,913 በጽሑፍ ምዘና ማለፊያ ውጤት ከ62.5 በመቶ በላይ ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ መምህራንም ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ለመፈተን ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ በቀጣይም ሁሉም መምህራን  እንዲፈተኑ የሚያደርግ አስገዳጅ ሕግ ለማውጣት ዕቅድ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ምዘናውን ለማከናወን መምህራኑ የፔዳጎጂ ሥልጠና መውሰድ እንዳለባቸው፣ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ ስላላቸው ብቻ ወደ ምዘና እንደማይገቡ የቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡ የፔዳጎጂ ሥልጠናን ከወሰዱ በኋላ ወደ ጽሑፍ ምዘና እንደሚቀርቡ ይህንን ፈተና ከ62 በመቶ በላይ ማምጣት ከቻሉ ለማኅደረ ተግባር ምዘና እንደሚቀርቡ አክለዋል፡፡

የማኅደር ተግባር ምዘናው ከ20 በመቶ እንደሚያዝ የተናገሩት የቡድን መሪው፣ የጽሑፉን ደግሞ ከ62 በመቶ በላይ ማምጣት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

በምዘናው የወደቁ መምህራንም ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች መመሪያው ላይ በተቀመጠው ሕግ መሠረት የአቅም ግንባታ እንደሚሰጣቸውና በቀጣይ ዓመትም ደግሞ እንደሚመዘኑ ገልጸዋል፡፡

ከሦስት ጊዜ በላይ ፈተና ወስደው የወደቁ መምህራን ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች ወደ ሌላ ሙያ እንዲዘዋወሩ የማድረግ ሥራ በቀጣይ ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የአቅም ግንባታውንም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ሰንደቁ፣ በዚህም መሠረት አብዛኛዎቹ መምህራን የአቅም ግንባታውን ወስደው ወደ ፈተና እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ለአምስት ዙር ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት የሙያ ብቃት የጽሑፍ ምዘና የወሰዱት 2879 መምህራን ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 206 ወይም ሰባት በመቶው ብቻ ማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በአራት ዙር 2,805 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነባር መምህራንና የጽሑፍ ምዘና መውሰዳቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 1,700 ወይም 61 በመቶ የሚሆኑ መምህራን ለማኅደረ ተግባር ምዘና ማለፊያ ውጤት ተፈትነው 62.5 እና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ ችለዋል ብለዋል፡፡

አጠቃላይ በትምህርት ጥራት ምዘናው ላይ የመምህራንም ሆነ የትምህርት ቤት አመራር የሙያ ብቃትና የጽሑፍ ምዘና ውጤት የሚያሳየው የመምህራን ሆነ  የትምህርት ቤት አመራሮች ብቃት ሲታይ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የሙያ ብቃት ሰርተፊኬት ያገኙትንና ያላገኙን የሚለይ አሠራር ባለመኖሩ እንዲሁም የማበረታቻ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የአብዛኛው መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ብቃት አናሳ ሊሆን እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዱ ተመዛኝ ራሱን በማደራጀት እንዲሁም ያለውን አቅም አውጥቶ ክፍተቶችን በመሙላት የዕለት ከዕለት ተግባር ማድረግ እንደሚያስፈልግ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሕይወት ጉግሳ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ተመዛኞች ፈተናውን እንደሚወድቁና ያላቸው አቅምም አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም የተመዛኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የትምህርት ጥራቱ ላይ ለውጥ እንዲኖር ያደርገዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት የትምህርት ተቋማት ግንባታ ከመፈጸም ባለፈ፣ የመምህራንና የትምህርት ቤቶች አመራሮች ብቃት ምን ይመስላል የሚለውን እየፈተሸ መሆኑን ይህም በዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ወ/ሮ ሕይወት አስረድተዋል፡፡

የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ምዘናም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን፣ በ2014 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ትምህርት ቤት መምህራንና አመራሮች ፈተናውን እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የምዘናው ሒደትም አዲስ ተመራቂ መምህራንን ያካተተ መሆኑን፣ በቀጣይም ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አክለዋል፡፡

ከምዘናው ሒደትና ውጤት በመነሳት የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ትኩረት አናሳ መሆኑን፣ ከመረጃ ልውውጥ፣ መምህራን ሰነዶችን በተሟላ መልኩ እንዲጠቀሙባቸው ከማድረግ አኳያና የምዘና ጣቢዎችን ከማመቻቸት አንፃር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

በተለይም የምዘና ሒደቱን ለማከናወን በግል ትምህርት ቤቶች የሚያገኙ መምህራን ሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮች ከቦታ ቦታ ሲቀይሩ ምዘናውን እንደማይወስዱ እንዲሁም የጽሑፍም ምዘና ከተመዘኑ በኋላም ለማኅደር ተግባር ምዘና ለመፈተን እንደሚገጥማቸው በወቅቱ ተገልጿል፡፡

የምዘና ውጤቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ለ23 የምዘና ጣቢያዎች ለ34 ተመዛኞች ለ320 መዛኞች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...