Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የእኛ ድርጅት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ብዥታም ጥያቄም የለውም›› መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ የኦፌኮ ሊቀመንበር

መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከተቀሰቀሰው የተማሪዎች አመፅ ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ትግል ተሳትፏቸው ይታወቃሉ፡፡ በደርግ ዘመን ለዓመታት የታሰሩ ሲሆን፣ በኢሕአዴግ ዘመንም ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት መረራ (ፕሮፌሰር) ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ ጀምሮ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ድረስ ካለፉበትና ከኖሩበት የፖለቲካ ሕይወት እንጀምር ፕሮፌሰር?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ያው እንግዲህ በመጀመርያው የለውጥ ጊዜ ማለትም በንጉሡ ዘመን በነበረው ተካፍያለሁ፡፡ በአምቦ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ተካፍያለሁ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት የፖለቲካ ትግሎችም እየተሳተፍኩ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ትልቁ ችግር እዚህ አገር ገዥዎቻችን ለሥልጣን ያላቸው ስስት ወይም ጉጉት ወሰን የሌለውና ያልተገደበ ስለሆነ፣ ብዙውን ጊዜ ለሥልጣናቸው ብቻ ስለሚያደሉ እስካሁን ድረስ በተደረጉት ለውጦች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ስንሸጋገር ኖረናል፡፡ በተለይ ከንጉሡ መጨረሻ ዓመት ጀምሮ፡፡ ለምሳሌ ከእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ንጉሡ ለውጥ እንዲያመጡ ቢመከሩም አልሰማ አሉ፡፡ እናም ያ የሥልጣን ጉጉት ዓይናቸውን ስለጨፈነው በሕገ መንግሥት የተገደበ ንጉሣዊነት  ሳይቀበሉ እስከ መጨረሻው ቆዩ፡፡ ያው መጨረሻቸው የሆኑት ይታወቃል፡፡ ደርግም ለ17 ዓመታት ኤርትራ አትገነጠልም በማለት ለሥልጣን ብሎ ከራሱ በላይ ጥሩ ጭንቅላት ያላቸውንና በኢትዮጵያ በጊዜው ምሁራን የተባሉትን የመኢሶንን፣ የኢሕአፓንና የብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትን ጨርሶ አጥፍቶ በመጨረሻ ራሱ ጠፋ፡፡ ኢሕአዴግም እንግዲህ በአብዛኛው ለ27 ዓመታት የተመከረውን ምክር ሳይቀበል ቀርቶ ያልሆነ ዕልቂት፣ መጠላለፍና መገዳደል እንዲፈጠር አድርጎ እሱም መጨረሻው እንደምታየው ነው፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የሚታየው የአሁኑ መንግሥትም ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት ያለፉበትን መንገድ የሚከተል ጥሩ ተማሪ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የተሻለ መፍጠር አልቻለም፡፡ እዚህ ለውጥ ውስጥም ተሳትፌያለሁ፡፡ እንዳልኩህ ትልቁ ችግር የለውጥን ምንነትና ሕዝብ ለውጥ መፈለጉን ብዙ ጊዜ ለመሪዎቻችን ዓይታይም፡፡ ወደ አጥፍቶ መጥፋት ድረስ ይሄዳሉ፡፡ አሁን እንደምናየው ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደሚባለው ለሦስት ሺሕ ዓመታትም ሆነ ለ150 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ዕልቂትና መገዳደል ውስጥ የገባችው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለፈበትን መንገድ እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ዞሮ ዞሮ ለውጡ ከሞላ ጎደል ከኢሕአዴግ አንድ ወደ ኢሕአዴግ ሁለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሁለት ደግሞ በአብዛኛው ሕወሓት ለ27 ዓመታት ሥራ ላይ ያዋላቸውን ነገሮች ሥራ ላይ ለማዋል ነው የፈለገው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም የኢሕአዴግን መጥፎ ጎን ብቻ ሥራ ላይ ለማዋል እንደሚፈልግ ነው የሚናገሩት፡፡ መማር ሲባል ባለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት የተሠሩ ስህተቶችን ማረም ነበር፡፡ በተለይም የጋራ ፍኖተ ካርታ ውስጥ አንገባም ያሉት ብልፅግናዎች በራሳቸው ኢትዮጵያን እናሻግራለን ብለው የገፉበት መንገድ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሊሠራ አልቻለም፡፡ የዕውቀት ችግር አለ፣ የልምድ ችግር አለ፣ የችሎታ ችግር አለ፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊና ብዝኃ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያሉባት አገር በመሆኗ ይህን ሁሉ አሰባስቦ የጋራ የሚባል ፍኖተ ካርታ ከማስገባት ይልቅ፣ በሥልጣን ጉጉት ተይዞ ላለፉት አራት ዓመታት ያደረግናቸውን ሙከራዎች፣ ድርድሮችና ክርክሮች አልተቀበሉም፡፡ መጨረሻው ይህ ሆነ፡፡ ኋላ ላይ ወደ ጦርነት ሊሄዱ ሲሉም ሞክረናል፡፡ ለምሳሌ ኮቪድ-19 ተከስቶ ምርጫው ለአንድ ዓመት ይተላለፍ ሲባል አንድ ዓመት መተላለፉን እንደግፋለን ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን ሒደቱ የጋራ ይሁን የአንድ ቡድን ሥራ አያወጣም ስንል፣ በሕገ መንግሥት ውስጥ የሌለ የሆነ የሕግ ክርክርና የፖለቲካ ቴአትር ሠሩና ለአንድ ዓመት አስተላልፈናል አሉ፡፡ በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ተሞክሮ በራስህ ጉዳይ ላይ ዳኛ አትሆንም፡፡ ምክንያቱም የጥቅም ግጭት የሚፈጥር በመሆኑ፡፡ ነገር ግን እነሱ እንቢ አሉ፡፡ በራሳቸው አንደበት አስተላለፉና ሕጉ ይፈቅድልናል አሉ፡፡ ጉልበት እስካላቸው ድረስ ይችላሉ ነገር ግን  ጉልበት አለን ማድረግ አትችሉም፡፡ የሚሉት ደግሞ ወደ አመፅ ሄዱ፡፡

እዚያ ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ ኧረ እባካችሁ ትርጉም በሌለው ጦርነት አንጨራረስ ወደ ድርድር እንሂድ ስንል እኛን ወደ መክሰስ ሄዱ፡፡ እዚህ አገር ደግሞ ድሮም ሲባል እንደነበረው በአብዮቱ ጊዜ አርሶ የሚበላ አርሶ አደር የሚባል ነበር፣ ወዛደር የሚባል ደግሞ ፋብሪካ ውስጥ ሠርቶ የሚኖር አለ፡፡ ኋላ ደግሞ ስንሠለጥን በደርግ መጨረሻና በኢሕአዴግ መጀመርያ አካባቢ ከብቶችን እያረቡ የሚኖሩ አርብቶ አደር የሚባሉ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን አውርተው የሚኖሩ አውርቶ አደሮች ተፈጠሩ፡፡ በተለይ ደግሞ በኢሕአዴግ ዘመን ማንንም ያለ ምንም ርህራሔና ይሉኝታ ቢያንስ ቢያንስ ከእኛ ጋር ተቀራራቢ ዕውቀት አላቸው የሚባሉትም ጭምር ወደ መክሰስ፣ ወደ መሳደብና ወደ ማዋረድ ውስጥ ገቡ፡፡ ስለዚህ እንግዲህ በዕውቃታቸው ልክ ሞከሩ ማለት ነው፡፡ ውጤቱም አገሪቱ ዓይታ በማታውቀው መጠን ጦርነቱ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነቱን ለማስቆምና አገራዊ አለመግባባቶችን ለማስታረቅ እየተሄደበት ያለውን ጥረት እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ለምሳሌ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብሎ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ አጀንዳ ላይ ከማንም በላይ በኢሕአዴግ ጊዜ ዕርቅ ብለን፣ በአሁኑ ዘመን ደግሞ ብሔራዊ መግባባት ብለን ስንንቀሳቀስ ነበር፡፡ ይህን አጀንዳ ቀምተው እንዲያው ብሔራዊ መግባባት ከተባለ ፈረንጆችን ለማጭበርበር ይሁን አላውቅም ወሰዱና ብቻ ከግድግዳ ጋር አላተሙት፡፡ ያ ደግሞ ጉዳዩን ወደ ቅርቃር ገፋው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲታሰብ ዓለም አቀፍ ልምዱም የሚያሳየው ሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች ናቸው ሁለቱን ወገኖች የሚያቀራርቡት፣ የሚያግባቡት፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህንን ጉዳይ እንቢ ብሎ ራሱ ኮሚሽን ፈጠረና ቁጭ አሉ፡፡ የእዚህ ኮሚሽን አባላቱ 98 በመቶ የአንድ ፓርቲ ደጋፊ ናቸው፡፡ የቀሩትም ቢሆኑ 98 በመቶው የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች ባሉበት ፓርላማ የተመለመሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ የት እንደመረጣቸው ሳይታወቅ ተመረጡ አሉ፡፡ እና በእንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች ማለፍ አንችልም፡፡ በእነዚህ ቀልዶች በጣም ሰፊ የሆነ፣ አስቸጋሪ የሆነ፣ አደገኛ የሆነ የኢትዮጵያን መኖርና አለመኖር የሚወስን ቀውስ ውስጥ ገብተናል፣ ከዚያ ዝም ብለን አንወጣም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን የተሻለ አማራጭ ሐሳብ አላችሁ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ሁለቱም ወገኖች በጋራ መምከር አለባቸው፡፡ ፍቅረኛሞች ፓርላማ ውስጥም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥም መወያየትና መነጋገር ይችላሉ፡፡ የተፈለገው ተቀናቃኝ ወገኖች፣ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው ወገኖች፣ ጠመንጃ አንስተው ጫካ የገቡ ወገኖች ጭምር እንዲያሳትፍ ነበር፡፡ ሁኔታው ዓለም አቀፍ መሥፈርትን የሚያሟላ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የሽምግልናና የዕርቅ ባህል የተከተለ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሁለቱም ካልሆነ የአንድ ቡድን ሽምግልና የት ይደርሳል? አሁን ለምሳሌ እነዚያኛው ወገኖች ጠብመንጃ አስቀምጡ ቢባሉ እነዚህን ወገኖች ማን ይቀበላቸዋል? እነሱ ይቅሩና እኛም አልተቀበልናቸውም፡፡ በነገራችን ላይ ከተሾሙት 11 የኮሚሽን አባላት ስድስቱን አውቃቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም አንዳቸው ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ናቸው፡፡ ከዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ዋና ኮሚሽነሩ የቀድሞው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ውስጥ አብረን ሠርተናል፡፡ ከምክትል ኮሚሽነሯ ጋር ደግሞ በደርግ ዘመን በመኢሶን ጉዳይ ለአምስት ዓመታት አብረን ታስረናል፡፡ አንዱ ደግሞ ተማሪዬ ነው፡፡ እንዲህ እያልክ ስትሄድ ከአሥሩ አንዱ ስድስቱን አውቃቸዋለሁ፡፡ ሲጠይቁኝ ይህንን ችግር ተሸክማችሁ የትም አታደርሱም ብያለሁ፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹Dead on Arrival›› ስለሚሆን፣ ስለዚህ ከዚያ የተሻለ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግሥት ሰላም ለመፍጠር የፖለቲካ ሜዳውን ሁሉም ሊቀበል በሚችል ደረጃ የእነዚህን ኮሚሽኖች አወቃቀር ጭምር በሥርዓቱ አልመራም፡፡ ስለዚህ የአንድ ወገን ቡድን፣ የአንድ ወገን ሽማግሌዎች ገለልተኛ ለመሆን ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሽማግሌው ቆጥሮ የሚመጣው የአንዱን ወገን ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን እያልን ያለነው ከሒደቱ ጀምሮ ለሁሉም ተቀባይነት ያለው፣ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ተቋም መፈጠር አለበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ እርስዎ እንደሚሉት ብዙ ተቃውሞ ከገጠመው እንዴት ሊቀጥል ይችላል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ያው ነዋ፡፡ ያው የለመድነው ላለፉት 50 ዓመታት የቆየንበት ቀውስ ውስጥ እንቀጥላለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ብልፅግና የሚመራበትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመደመር ‹‹ፍልስፍና›› ወይም መጽሐፍ እንዴት ይገመግሙታል? ከፖለቲካ ርዕዮት ዓለም አንፃርስ እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳይቀየሙኝ እዚያ ውስጥ አታስገባኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ኢትዮጵያ  ወይም ተስፋ የሚያደርጓት ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ነው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- እኔ እኮ እንደ መጽሐፍ ቅዱስና እንደ ቁርዓን ባለፉት 27 ዓመታትም ይሁን፣ አራት ዓመታትም ይሁን፣ ምንም ይሁን ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያ መፈጠር አለባት ነው የምለው፡፡ ሁላችንንም በጋራ የምታስተናግድ መሆን አለባት ነው የምለው፡፡ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ መፈጠር አለባት፡፡ ከዚያ ውጪ ምንም መፍትሔ የለም፡፡ ዴሞክራሲ ብለን የምናካሂደው ምርጫ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን መፍታት ይቻላል፡፡ አንደኛው ሰላምና መረጋጋት መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ሁለተኛው መልካም አስተዳደርና ዴሞክራቲክ አስተዳደር መፍጠር መቻል አለብን፣ ሀቀኛ ፌዴራሊዝም መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ሦስተኛውና ትልቁ ጉዳይ ትርጉም ወዳለው ልማትና ብልፅግና መፈጠር አለበት፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሦስት ነገሮች የማይፈታ ምርጫ በደርግ ጊዜ፣ በንጉሡ ጊዜና በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጊዜም አካሂደናል፡፡  እነዚህን የማይፈቱ ቅርጫ እንኳን ያልሆኑ ምርጫዎች ናቸው፡፡ አሁን ያለፈው ምርጫ አይደለም ምርጫ ቅርጫ እንኳን አልሆነም፡፡ ከ50 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊ አልተሳተፈበትም፡፡ በኦሮሚያ ለምሳሌ አንድ ፓርቲ ነው ከራሱ ጋር የተወዳደረው፡፡ ትግራይ ከጨዋታ ውጪ ነበር፡፡ ሶማሌም አንድ ፓርቲ ነው የተወዳደረው ከራሱ ጋር፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ ምርጫ ተደረገ ከተባለ አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔና አማራ ክልል የሚባለው ነው፡፡ ያውም እነዚህ ውስጥ መራጮች 40 ምናምን በመቶ ቢሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል እንደምናየው በጣም በርካታ የሆኑ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በምርጫው አልተሳተፉም፡፡ አሁንም ተለያይተው ነው የሚታዩት፡፡ ኦሮሚያን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ ፓርቲዎች ለምን ወደ አንድ መምጣት አቃታቸው? ፍላጎታቸው ምንድነው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- መጥተናል እኮ፣ መጥተን ነበር፡፡ እስከ ብልፅግና ፓርቲ ድረስ ሄደን ነበር፡፡ አብረን ‹‹ጋዲሳ ኦሮሚያ›› የሚባል ፓርቲ ፈጥረን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት፡፡ እስከዚያ ድረስ ሄደናል፡፡ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የኦሮሞ ብልፅግና ማለቴ ነው፡፡ አንድ በል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ትልቁ የኦሮሞ ድርጅት ወይም ፓርቲ ከሚባለው ከኦነግ ጋር በምርጫ ለመወዳደር፣ እንዲሁም አብረን ደግሞ ምርጫ ውስጥ ለመግባትና ሕዝቡንም በጋራ ለመምራት ከእነሱ ጋር ተፈራርመናል፡፡ ምርጫ ቦርድ እስከሚያውቀው ድረስ ተፈራርመን ድርድር ውስጥ ገብተን ነበረ፡፡ እንዲያውም መንግሥት የዘመተብን በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ላይ ለመሥራት ማለት ነው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- አዎ፣ በዚህ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ማን ነው የሸሸው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- እንግዲህ ብልፅግና ነው የሸሸው፡፡ መሸሽም የሚችለው እሱ ነው፡፡ ሌላው አቅም የለውም፣ ፍላጎቱም አይደለም፡፡ ይመስለኛል ሁለቱ አንድ ላይ እርስ በርሳቸው ካልተወዳደሩ በስተቀር የኦሮሚያ ብልፅግና የማሸነፍ ዕድሉ የመነመነ መሆኑን እነሱም ያውቃሉ፣ እኛም እናውቃለን፡፡ ለዚያ ነው ምክንያት ፈጥረው የሸሹት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኦሮሞ በመሆናቸው፣ የኦሮሞ ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ ተመልሷል፣ ቢያንስ በኢሕአዴግ ጊዜ ከነበረው በተሻለ የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ መሪና ቋንቋ እያስተዳደረ በመሆኑ የለውጥ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ነገር ግን ክልሉ ውስጥ አሁንም እዚህም እዚያም የሚታይ ቁርሾ አለ፡፡ አሁን ያልተመለሱት የኦሮሞ ጥያቄዎች ምንድናቸው ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የኦሮሞ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር፣ አገርን ደግሞ በጋራ ለማስተዳደር የመረጣቸው መሪዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ የምንላቸው የቋንቋም ይሁን፣ የራስን ማስተዳደር ይሁን፣ ራስን የማበልፀግ ይሁን፣ በሀብቱ ላይ የተሻለ ቁጥጥር የማግኘት ይሁን ብዙ ጥያቄዎች በእኛ እምነት ሕዝቡ በፈለገበት መንገድ አልተመለሱም፡፡ የቋንቋውንም ሁኔታ እስካሁን ድረስ ይጎትታሉ አራት ዓመት ሞላው ወዴት እንደሚጎትቱት አላውቅም፡፡ ብቻ ሲጎትቱት ነው የሚኖረው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ራስን በራስ ማስተዳደር ለሚባለው ነገር፣ ሁላችንም እንደምናውቀው ኦሮሚያን የሚያስተዳድሩት በብዛት የኢሕአዴግ ልጆች ናቸው፡፡ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ይተዋወቃሉ፣ የኦሮሞ ሕዝብም ያውቃቸዋል፣ ሁላችንም እናውቃለን፣ እነሱም ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ እንደዚህ እንደዚህ እየተባለ ነው የሚወራው፡፡ እኔ ለምን እንደዚያ እንደሚያወሩም አላውቅም፡፡

ከልጅ ኢያሱ ጀምሮ ብዛት ያላቸው የኢትዮጵያ መሪዎች እኮ የደም ጥያቄ ብቻ ከሆነ የኦሮሞ ደም አላቸው፣ ልጅ ኢያሱ አለው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ እኛ ባለን ታሪክ ውስጥ ከተመዘገበው መረጃ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያነሱ ኦሮሞ አይደሉም፣ ቢበልጡ እንጂ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ የኃይለ ማርያም ወልዴ አያና ልጅ ነው፡፡ የትውልድ ቦታውም እዚህ ተፍኪ ነው፡፡ የተደባለቀ የኦሮሞና የአማራ ልጅ ይመስለኛል፡፡ ጄኔራል ተፈሪ ባንቲ እዚህ ለገጣፎ አለፍ ብለህ የምታገኘው የአለልቱ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እሱን ደም ብቻ እየቆጠሩ የኦሮሞ ተወካይ የሚሉት ፖለቲካ ያልገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ማንንም ይሁን ብቻ የኦሮሞ ሕዝብ ይኼ ይሻለኛል፣ ያስተዳድረኛል ብሎ ማንንም ሊመርጥ ይችላል፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ስንል እኮ ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሰዎች የመምረጥ መብት አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት መብቴንና ፍላጎቴን ይጠብቅልኛል የሚለውን መምረጥ አለበት፡፡  ስለዚህ የእነዚህ ነው የእነዚያ ነው የሚለው ብቻውን አይበቃም፡፡ እሱን ደግሞ መወሰን ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡ በቃኝ ጥያቄዎች ተመልሰውልኛል ማለት የሚችለው ራሱ ሕዝቡ እንጂ ሌላ አፈ ቀላጤ አያስፈልገውም፡፡ ተመልሶልኛል ካለ ጥሩ አልተመለሰልኝም ካለ ደግሞ ለሕዝቡ ተቀባይነት ባለው መንገድ ከጠብመንጃ አገዛዝ ውጪ መመለስ መቻል ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ይሆናል ሐረር፣ አርሲና ባሌ ስንንቀሳቀስ በሰላማዊ ሠልፍ ለእኛ ድጋፍ ይወጣ የነበረው ምን ዓይነት ሰው እንደነበር እናውቃለን፡፡  እኔ እኮ ከእስር ቤት ተፈትቼ አምቦ ስሄድ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ይሆናል በሰላማዊ ሠልፍ የወጣው፡፡ ይህን ስታይ ማን ምን እንዳለው፣ ሕዝቡ ከማን ጋር እንዳለ እኮ ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ለምን ያን እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ መሠረታዊ ጥያቄዎች አልተመለሱልኝም ለምን እንደሚል እኮ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ መፍትሔው ጥያቄውን ተቀብሎ መመለስ እንጂ፣ የለም ተመልሶልሀል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኮ የኦሮሞ ልጅ ነው ማለት መልስ አይሆንም፡፡ እንደዚያ ቢሆንማ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እኮ አገሪቱን ለ58 ዓመታት ያህል ገዝተዋል፡፡ እሳቸው ከሞላ ጎደል እኮ የኦሮሞ ልጅ ናቸው፡፡ እንደዚያ ተደርጎ የሚወሰድ ከሆነ በአልጋ ወራሽ ጭምር ይህን ያህል ዓመት የገዙት አፄ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ዘር በምትቆጥረው ደረጃ ኦሮሞ ናቸው፡፡ ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ ነው አያታቸው በታሪክ የተመዘገበው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በስፋት የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ በተለይም በአማራ፣ በደቡብ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየታየ ነው፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ለውጡ ድሮም ችግር ነበረበት፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ችግር እየፈጠረ ስለሄደ የተሻሉ አካባቢዎችም ወደ ችግር እየገቡ መጡ፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመምጣታቸው የተጠቀመው አካል ማን ነው ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጭምር የተጠቀሙ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ታሪክ መቼም መሪ ሰው ይጥላኝ ብሎ አይሠራም፡፡ መጥፎ መሪ ልሁን ብሎ የሚሠራ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተሳካለትም፡፡ ስለዚህ ለእሱም ቢሆን ተሳክቶለታል፣ ተጠቅሞበታል የሚል ዕሳቤ የለኝም፡፡ የዛሬ አራት ዓመት እኮ ዓብይን ነብይ የሚሉ ሰዎች መንገድ ዘግተውብን ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- አገሪቱ አሁን ከገባችበት ቀውስ በተለይም በሰሜን ከሕወሓት ጋር፣ በምዕራብ፣ በማዕከልና በደቡብ በኩል ከሸኔ በሚሰነዘር ጥቃት ንፁኃን እየተገደሉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፓርላማው በተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ተቃውሞ እያሰሙበት ነው፡፡ ወደ ሥራ ከገባ በኋላም እንኳ በዚህ ሁኔታ አገርን እንዴት አረጋግቶ ማስቀጠል ይቻላል ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- በጋራ ፍኖተ ካርታ ላይ መስማማት አለብን፡፡ ይህች አገር ወዴት መሄድ አለባት? ምን መሆን አለባት? በሚለው ጥያቄ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት ቦታ ጭምር ደጋግሜ አንስቻለሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለበት አንስቻለሁ፣ መስማማት አስፈላጊ ስለመሆኑ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎች ታሪክን እያነሱ የግጭት መንስዔ ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡  አገርን በጋራ ለመገንባት አዋጭ መንገድ ነው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- እሱ ብቻ አይደለም፣ በእርግጥ ታሪክ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ታሪክ ላይ ያሉ ችግሮችን እያረሙ፣ አሁን ያለውንም ሁኔታ እየገመገሙ መሄድ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ዝም ብሎ እንደሚያነሳው ችግሩ የታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም የተለያየ ነገር ሊያነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሚፈልገውን አያገኝም፡፡ መሀል መንገድ ላይ ግን ይህ አገር እንዴት ይሂድ? ወዴት ይሂድ? ምን ይደረግ? የሚለው ላይ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከተስማማህ ተስማማህ፣ በጣም ጥሩ፡፡ ካልተስማማህ ሕዝብ ይወስን፡፡ ከዚያ ውጪ ግን እኔ አውቅልሀለሁ የሚለው ጨዋታ አያዋጣም፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በቅርቡ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ከዚህ ጉባዔ ለደጋፊዎችዎና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን የሚጠቅም ነገር ይዛችሁ መጣችሁ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- በዋናነት ወደፊት መደራጀትና እንዴት መቀጠል እንዳለብን ተነጋግረናል፡፡ ለአገራችን ደግሞ ሰላምና መረጋጋት እንዴት መፈጠር እንዳለበት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት መገንባት እንዳለበት፣ ብሔራዊ መግባባት የሚባለው መልክ ይዞ በሀቅ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተን ውሳኔዎች አሳልፈናል፡፡ አቋማችንንም በመግለጫ አስታውቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ብልሽት የተማረውና ልሂቃን የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይወሳል፡፡ ይህ እንደተባለው እውነት ነው? ከሆነስ አገርን ይመራል የተባለ አካል የችግር መንስዔ ከሆነ እንዴት ለውጥ ይመጣል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- በዋናነት ልሂቃን የምንላቸው መስማማት አልቻሉም፣ በሁሉም በኩል ያሉት፡፡ ልሂቃን ካልተስማሙ ደግሞ ፖለቲካ ሠልጥኖ አገርን ወደፊት ማራመድ ያስቸግራል፡፡ በየትኛውም አገር ልሂቃን የሚባሉት ናቸው አገርን የሚመሩት፡፡ ልሂቃን የሚባሉት ግን እንዲያው በዘፈቀደ ሳይሆን የሕዝብን ብሶት መስማት አለባቸው፡፡ ሕዝቡም መሪው ከሠራለት ነገም መልሶ የሚመርጠው፣ ካልሠራለት ደግሞ ማውረድ የሚችል መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራንና አዋቂዎች የሚባሉት እዚህ ውስጥ አንገባም አሉ፡፡ ሥልጣን የያዘ ሁልጊዜ ሀቀኛና የአገር አንድነት ጠባቂ አድርጎ ራሱን ይሰይማል፣ ሌላውን ይከሳል፣ ወንጀለኛ ያደርጋል፡፡ አገር አጥፊና ባንዳ እያለ ስም ያወጣል፡፡ ይህን ባንዳ ምናምን የምትሉትን ቀልድ ተው ብዬ ነበር፡፡ በጋራ ይህችን አገር ማሻገር ካልቻልን አንድ ቡድን ብቻ ማሻገር አይቻልም ብለናል በግልጽ ቋንቋ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ እኔ ድሮ ከእነ በረከት ስምኦንና ከአቦይ ስብሃት ጋር ጭምር ክርክሮች አድርጌ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ፕሮፌሰር መረራ በኢሕአዴግ ጊዜ የሚከተሉት የፖለቲካ መስመር ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነበር፣ ነገር ግን አሁን የሚያራምዱት የፖለቲካ  አቋም ድሮ ያሳዩት ያራምዱት ከነበረው ዴሞክራሲዊ አቋማቸው መቀየሩን የሚያወሱ አሉ፡፡ ይህን አስተያየት እንዴት ተቀበሉት?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ምን መሰለህ? በግልጽ ቋንቋ ደረጃ መዳቢዎች ተፈጠሩ፡፡ አሁን ኢሳቶችን እያቸው ደረጃ ሲመድቡ ቆይተው አሁን ‹አንተ ሌባ፣ አንተ ሌባ፣› መባባል ጀምረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ደረጃ መዳቢዎች ናቸው ሁኔታውን ያበላሹት፡፡ ደረጃ መዳቢዎች አትሁኑ፣ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ሰጪና ከልካይ አድርጋችሁ ራሳችሁን አትሹሙ ብዬ ተናግሬ ነበር፡፡ ነገሩን ስታየው የቡዳ ፖለቲካ ነው፡፡ የቡዳ ፖለቲካ ታውቃለህ? መጽሐፌ ላይ ጽፌዋለሁ፡፡ ቡዳ የሚባለው ምን መሰለህ? አንድ ሰው ቡዳ ይኖርበታል ወደ ተባለ ሠፈር ሄዶ ያገኘውን ሰው፣ ‹እዚህ አካባቢ ቡዶች አሉ ይባላል የት አሉ?› ብሎ ቡዳውን ይጠይቀዋል፡፡ ቡዳው ደግሞ ፈራና የሚለው ሲጠፋበት፣ ‹እኛ እዚያ ማዶ ያሉትን ቡዶች እንላለን፣ እነሱ ደግሞ መልሰው እኛን ይሉናል› አለ ይባላል፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካም እንደዚያ ነው፡፡ ቡዳዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን እያወቁ እኛን ቡዳ ይሉናል እንጂ፣ የእኛ ድርጅት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ብዥታም ጥያቄም የለውም፡፡ ነገር ግን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያ ካልተፈጠረች ተስፋ የላትም ብሎ ያምናል፡፡ ጨዋታው እዚያ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ምንም ካላገኘን፣ እኛ ምንም ካልሆን ብለው ራሳቸውን ደረጃ መዳቢ አድርገው ያስቀመጡ ሰዎች እኛን ሲከሱ ነበር፡፡ አሁን ለምሳሌ እኔ አራት ዓመት ሆኖኛል ከኢሳት ጋር ቃለ መጠይቅ ካቆምኩ፣ ወዳጆቼ ነበሩ፡፡ በፊት እኔ አንድ ዓመት ተኩል ስታሰር እኮ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ሁለተኛ ተከሳሽና ኢሳት አራተኛ ተከሳሽ ነበርን፡፡ ያን ሁሉ አበላሽተው አሁን ደረጃ መዳቢ ሆነው መረራ እንዲህ አደረገ የሚሉት እነሱ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ ባለፈው ሳምንት ኢሳት ምን እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ ታይቷል፡፡ ከብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ጋርም ስንት ዓመት አብረው ሲፈተፍቱ ቆይተው፣ አሁን እንዴት እንደሚከሱት እየፈለጉ ነው፡፡ እናም ስለዚህ መካሰሱ እንዳለ ሆኖ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ ስለሆነ ማለት ነው፣ ነገር ግን በጋራ አገር ላይ ተደራድሮና ተነጋግሮ መሠረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮቹን አብሮ ፈትቶ መሄድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦፌኮ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- እሱ ውስጥ አልገባም፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ኢየሩሳሌም እንዳትሆን ከተፈለገ መፈታት ያለባቸው ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ ብናወራ ጥሩ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት አካባቢ ተፈጥሮ ብዙም ያልሰነበተውን ኦሮ-ማራ የተባለ የአማራና ኦሮሞ የጋራ ንቅናቄ እንዴት ያስታውሱታል?

ፕሮፌሰር መረራ፡- አዎ እኛ አንድ ዓመት ለፍተንበት ቆይተን ብልፅግና ይዞት ሄደ፡፡ እኛም የትም እንደማይደርስ ስናውቅ ወጣን፡፡ ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ነገር ግን  መጨረሻ ላይ ብልፅግና ጠልፎ ሲወስደው ትርጉም አጣንበት፡፡  

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አሜሪካ ሄደው በነበረ ጊዜ ላይመለሱ ይችላሉ የሚሉ ሰዎች ነበሩ?

ፕሮፌሰር መረራ፡- እነሱ እኔን የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ በፊት እኮ በኢሕአዴግ/ወያኔ ጊዜ ትታሰራለህ አትመለስም ስባል ይሰሩኝ ብዬ መጥቼ ታስሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሞን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች እንዴት መንቀሳቀስ አለባቸው?

ፕሮፌሰር መረራ፡- ሕጋዊ ሆነው ይንቀሳቀሱ ነው የምንለው፡፡ ነገር ግን ወደ ጫካ እየገፋቸው ያለው ራሱ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሚገርምህ ለምሳሌ ቦረናና ጉጂ ጫካ ውስጥ ያሉት የእኛ የቀድሞ የፓርላማ አባላት አሉ፡፡ በመንግሥት ተገፍተው ማለት ነው፡፡ በማዕከላዊ ኦሮሚያ የሸኔ ጦር አዛዥ ተብሎ የሚጠረጠረው ግለሰብ በኦሮሚያ ምክር ቤት ለአምስት ዓመት አባል ነበር፡፡ እኛን ትተው የጠፉ በርካቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግም ሆነ ብልፅግና ሰውን ወደ ጫካ እየገፋው ነው፡፡ ሕጋዊ ማድረግን እያፈነ አንዳንድ ጊዜ ዳያስፖራ ሆነው የአንቂነት ሥራ ይሠራሉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ጫካ እየተገፉ ጫካ ውስጥ የሚኖሩ አሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂውና ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ሰላማዊ የትግል ሜዳ ካለ ማን ጫካ መግባት ይፈልጋል?

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...