Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ኃይል ላይ ልዩ ዘመቻ እንዲደረግበት ተጠየቀ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ኃይል ላይ ልዩ ዘመቻ እንዲደረግበት ተጠየቀ

ቀን:

የፀጥታ ሥጋቱ ኢንቨስተሮች ከክልሉ እንዲወጡ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፣ ንፁኃን ዜጎችን በማገት፣ በመግደል፣ በማፈናቀልና የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ እያመሰቃቀለ ያለውን የኦነግ ሸኔ ኃይል፣ የፌደራል መንግሥቱ በተጠናከረ የልዩ ዘመቻ እንዲያፀዳው ተጠየቀ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ማኦከሞ ልዩ ወረዳ፣ በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ እንዲሁም ሌሎች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሰውን የሸኔ ኃይል፣ የፌደራል መንግሥት ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ቦታዎችን ለማፅዳት እየተሠራ ቢሆንም፣ የተገኘው ምላሽ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑንና የዜጎችንም ሰላም በተገቢው ሁኔታ ማስጠበቅ እንዳልተቻለ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የፌደራል መንግሥቱ የጀመረው ጥረት እንዳለ የገለጹት ኃላፊው፣ ለክልሉ ተጨማሪ አቅም ሊፈጥር የሚችል ዕገዛ በማድረግ ዜጎች ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ የማስቻል ሥራና ቀጣናው ወደነበረበት እንዲመለስ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች እስከ ሕይወት ማጣት ድረስ መስዋዕት እየከፈሉ ቢሆንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉ ለፀጥታ ሥጋት የሆኑ የሸኔ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ግን ሊገታ አለመቻሉን አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ከኦነግ ሸኔ ውጭ ያሉና በክልሉ ያለውን ሰላም የሚያውኩ የተደራጁ ቡድኖች ወደ ሰላምና ዕርቅ እየመጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሸኔ ታጣቂዎች እያካሄዱት ያለውን ‹‹የሽምቅ ውጊያ ማፅዳት›› ከባድ መሆኑን የገለጹት አቶ መለሰ፣ በቀጣናው ያለውን ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግሥት የተጠናከረ ዕርምጃ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በኩልም አስፈላጊ የሆነ እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ በተለይም በአሶሳ ልዩ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ እርሻ ልማት ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች በታጣቂዎች ምክንያት የተወሰኑት ከቦታው ለቀው መውጣታቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ይዞ ለመውጣት የሚጠቀሙበት ዋና መንገድ በሸኔ ታጣቂዎች በመያዙ፣ ምርታቸውን በጫካ አቋርጠው መጫን ለሚችሉ ተሸከርካሪዎች ከእጥፍ በላይ እየከፈሉ መሆኑን ለሪፖርተር የደረሰው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአሶሳ ዞን ማዖኮሞ ወረዳ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ በርበሬና መሰል የግብርና ምርቶች ላይ የተሰማሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለሀብት ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በዚህ አካባቢ ምርት ሲያመርቱ የነበሩ ባላሀብቶች ቦታውን ለቀው እየወጡ መሆኑን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ እርሻ ቦታ የእርሻ መሣሪያዎችን ማስገባት አለመቻላቸውንና ምርት ያመረቱት ደግሞ ምርቱን ይዘው ወደ ገበያ ለመውጣት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአንድ መቶ ሄክተር በላይ የእርሻ መሬት እንዳላቸው የገለጹት ኢንቨስተር፣ በዚህ የፀጥታ ስጋት፣ የተነሳ የተስተጓጎለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሊተካ የሚችል መሬት መንግሥት ሰላም ባለበት አካባቢ ካልሰጣቸው ወይም በዚሁ አካባቢ ሰላም ካልመጣ በቅርቡ አጠቃላይ ሥራ ሊያቆሙ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባምበሲ ወረዳ ሸዎና ብረቆሽ በሚባሉ ቀበሌዎች ወደ እርሻ ቦታው ይወሰድ የነበረውና በኦሮሚያ ክልል በኩል አቋርጦ የሚሄደው መንገድ ከግንቦት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሸኔ ታጣቂዎች ምክንያት እንደተዘጋ ለሪፖርተር የገለጹት አንድ ኢንቨስተር እንደሚሉት መንገድ ቀይረው ምርታቸውን በከፍተኛ ዋጋ እየጫኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብትም በመንገዱ መዘጋት ምክንያት 128 ሺሕ ብር መጫን የነበረበትን 1,600 ኩንታል ምርት መንገድ በመዘጋቱ ብቻ በ384 ሺሕ ብር ለመጫን መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...