Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ እንግልት እያደረሰብን ነው ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲ እንግልት እያደረሰብን ነው ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

  • ፓርቲዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ እውነት መሆኑን ምርጫ ቦርድ አረጋግጧል

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በተለያዩ መንገድ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአገራዊና ከክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር፣ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በገዥው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅር አማካይነት፣ በአባላቶቻቸው ላይ እስራት፣ ግድያ፣ የተለያዩ ዓይነት ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች፣ እንዲሁም ከሥራ ገበታቸው እየታገዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 የራያ ራዩማ ፓርቲ፣ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የቅማንት ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን)፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና ሌሎችም ፓርቲ ተወካዮች አቤቱታቸውን ለቦርዱ አሰምተዋል፡፡

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ በገዥው ፓርቲ ምክንያት የኢዜማ አባላት ከሥራ መፈናቀል እንደገጠማቸው፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የፓርቲው አባል ሕዝብ ለማወያየት ወደ ተመረጡበት ቦታ ሄደው ማወያየት አለመቻላቸውንና በርከት ያሉ ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል ስለመፈጸማቸው አስረድተዋል፡፡

የቤሕነን ፓርቲ ተወካይ መሐመድ እስማኤል በበኩላቸው በብልፅግና ፓርቲ 23 አባላቱ ታስረው እንደነበረ፣ አሁን ግን 17 የሚሆኑት ያለ ምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች አባላቱም በገዥው ፓርቲ እየተሳደዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ እስር ቤት ስለመሆናቸውና ደጋፊዎቹም ጫካ ውስጥ በሥጋት እየኖሩ እንደሆነ የተናገሩት፣ የቅማንት ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ ናቸው፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በበኩላቸው፣ ቦርዱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን ካደመጠ በኋላ፣ ችግሩን ለማረም ቅሬታ ወደ ቀረበባቸው ቦታዎች መርማሪ ቡድን መላኩን፣ በዚህም በተለያዩ የፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ በደል መድረሱን መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል በሆለታ፣ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በወሊሶና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮችና አባላት ለእስር መዳጋቸውን እንዳረጋገጠና አብዛኞቹም ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አቶ ውብሸት ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት የኦነግ አባላት የሆኑ ስድስት ሰዎች በአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ሦስት ሰዎች በፌዴራል ፖሊስ፣ 17 ሰዎች በሰበታ ፖሊስ ጣቢያ ስድስት ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤት፣ ሰባት ሰዎች በሱሉልታ ፖሊስና፣ እንዲሁም የታሰሩበት ያልታወቁ ሰዎች አሉ፡፡

በእስር ላይ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አብዛኞቹ ፍርድ ቤት ያልቀረቡና ‹‹በሕገወጥ መንገድ›› የተያዙ እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

ክስ የቀረበበትን ብልፅግና ፓርቲ አመስልክቶ ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ተወካይ ‹‹የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ሁኔታውን እያጣራን ነው፡፡ በቀጣይ በዝርዝር እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ብልፅግና ፓርቲ ጉዳዩን አጣራለሁ ማለት ከጀመረ በርከት ያለ ጊዜ እንደወሰደበት፣ በተለያዩ ጊዜያት በቦርዱ በሚጠሩ ውይይቶች ብልፅግናን የሚወክሉ አካላት እየተቀያየሩ መምጣታቸው እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ቦርዱ በጠራው ስብሰባ ተሳትፈው የነበሩት የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ ጉዳዩን አጣርተን ዕርምጃ እንወስዳለን ብለው እንደነበረ ወ/ሪት ብርቱካን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም በብልፅግና ፓርቲ በኩል ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እየተሰጠው አለመሆን፣ ይህም ምክንያታዊ አለመሆኑንና ተቀባይነት እንደሌለው ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...