Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የሕዝብ ለቅሶና ዋይታ መቆም አለበት›› የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር፤ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)

‹‹የሕዝብ ለቅሶና ዋይታ መቆም አለበት›› የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር፤ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)

ቀን:

በኢትዮጵያ እርስ በርስ የማያግባቡ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት፣ በመነጋገርና በመደማመጥ ‹‹የሕዝብ ለቅሶና ዋይታ መርገብ ብቻ ሳይሆን መቆም አለበት›› ሲሉ የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ገለጹ፡፡

በየካቲት 2014 ዓ.ም. አጋማሽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሃላ ለፈጸሙት 11 የኮሚሽኑ አባላት፣ ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በሃይማኖት አባቶች ፀሎትና ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በተውጣጡ የአገር ሽማገሌዎችና እናቶች ምርቃት የተከናወነበት የሥራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በሸራተን አዲስ ሆቴል ተከናውኗል፡፡

 በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን እያለፈች መሆኗን በመግለጽ ግጭት፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ሥራ አጥነት፣ የምግብ ረሃብ፣ የመልካም አስተዳድር ረሃብ፣ ቸነፈር፣ ድርቅ፣ የእንስሳት ዕልቂት፣ የኤችአይቪና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎችም ችግሮች ውስጥ እያለፈች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ፣ ግልጽ፣ ምክንያታዊ፣ ተዓማኒና 120 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ በትክክለኛና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በውይይቱ እንዲወከል በማድረግ፣ ግልጽ የሆነ የአመቻችነት ሥራ እንደሚያከናወኑ ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር በመደማመጥ በሚገባ ከተከናወነ ወደ መግባባትና መፍትሔ አዋጭ መንገድ መግባት እንደሚቻል የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት በፊት በሃይማኖት አባቶች፣ በአገር ሽማግሌዎችና በእናቶች አማካይነት ተጀምሮ የነበረው የሰላም ጥረት ተደምጦ ቢሆን ኖሮ አሁን የሚታየው ምስቅልቅል ባልተፈጠረ ነበር ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሁንም ለመስማት ብቻ ሳይሆን ለመደማመጥ አዳጋች የሆኑ፣ ሕዝቡን እየለያዩና እያቆረቆሱ ያሉ አጀንዳዎችን ነቅሶ በማውጣት ለብሔራዊ ምክክር ራስን ዝግጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከተቋቋመ አንድ ወር የሆነው ኮሚሽኑ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በአዋጅ የተሰጠውን 12 ኃላፊነቶች ማስፈጸም የሚችልበትን ደንብና መመርያ በማውጣት ላይ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሚዲያዎች ጋር እንዴት መሥራት እንዳለበት የሚረዳ ስትራቴጂ እየነደፈ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ በሥራ ላይ በሚቆይባቸው ቀጣይ ሦስት ዓመታት በኮሚሽነር የሚመራ የሚዲያ ዘርፍ እንደሚኖር ተገልጾ፣ አሁን በርከት ያለ የሥራ መዘርዝር እየተሰነደ እንደሆነ ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ አሁን የጀመራቸውን ደንብ፣ መመርያ፣ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ  ዕቅድ በጥቂት ወራት በማጠናቀቅ ወደ ቅድመ ውይይት ለመግባት፣ በተለይም ከኅብረተሰቡ አጀንዳ የመሰብበስ ሥራ በማከናወን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚባሉ ጉዳዮችን በመለየት፣ መግባባት የሚደረስበትን መንገድ በማመቻቸት ለብሔራዊ ዕርቅ የሚረዳ ሥራ እንደሚከናወን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው የቀጣይ ተግባራት በውጭ አገር የሚኖሩና ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ኃላፊነቶች እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...