Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዜጎችን በማንነታቸው እየለዩ ከክልሎች ማባረር መሠረታዊ የፖለቲካ ብልሽት ነው›› እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የፌዴራል ዋና ዕንባ ጠባቂ

 

በሰኔ 2010 ዓ.ም. ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) ይመሩት ለነበረው የፌደራል ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሕዝብ በተደረገ ጥቆማ በዋና ዕንባ ጠባቂነት በፓርላማ የተሾሙት የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የሕዝብ አስተዳደርና ፖሊሲ ባለሙያው እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ በተለያዩ አካባቢዎች በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በዋና ዕንባ ጠባቂነት ከመሾማቸው አስቀድሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ የኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ሲሳይ ሳህሉ ከዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ጋር ተቋማቸው ስለሚያከናውናቸው ተግባራትና እያጋጠማቸው ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ያደረገው ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል ዕንባ ጠባቂ ተቋምን እንዴት እንደተረከቡ ቢነግሩን?

ዶ/ር እንዳለ፡- ከዚህ በፊት በተለያዩ ተቋማት በመምህርነት የሠራሁ ሲሆን፣ ወደ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እስክመጣ ድረስ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ነበር የምሠራው፡፡ ነገር ግን ወደ እዚህ ተቋም እስክመጣ ድረስ ስለተቋሙ ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረኝም፡፡ ተቋሙን እንድመራ ማን በዕጩነት እንደ ጠቆመኝም መረጃው የለኝም፡፡ በጥቆማው መሠረት መረጃውን እንድልክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጠይቀኝ ጉዳዩ አዲስ ስለነበር አላሰብኩትም፡፡ ነገር ግን እንዳስብበት ምክር ቤቱ ትንሽ ጊዜ ሰጥቶኝ ስለተቋሙ ሥልጣንና ተግባር በኢንተርኔት ላይ ብቻ ነበር መጀመሪያ መረጃ ያገኘሁት፡፡ በእርግጥ የእኔ የትምህርት ሙያ የሕዝብ አስተዳደር ስለነበር፣ ከማስተማር ወደ እዚህ ብመጣም ሕዝብን ማገልገል ነው በማለት ተቀብዬ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙን እንዴት አገኙት?

ዶ/ር እንዳለ፡- ተቋሙን በሚመለከት ውጭ ተሁኖ የሚወራውና ወደ ውስጥ ስትገባ የተለያየ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ሰዎት አስተዳደራዊ በደል ተፈጽሞባቸው ነው፡፡ ተፈጸመብን ብለው የሚያቀርቡት በደል በሰው ላይ ይደርሳሉ ብለህ የማትጠብቃቸው ዓይነት ናቸው፡፡ ለምሳሌ የትኛውም ተቋም ብትሄድ የሚያስተናግዱህ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የሚፈጸመው በደል ግን ሌላ ባዕድ አካል የሚፈጽመው ነው የሚመስለው፡፡ በዚህ ሒደት ይህን ተረድቻለሁ፡፡ ሌላው ጉዳይ ተቋሙ ከተሰጠው ኃላፊነት አንፃር በሕዝብ ዘንድ አልታወቀም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በተለይም ከቀበሌ አንስቶ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን እንዲያይ ነው በአዋጅ የተሰጠው፡፡ ነገር ግን በዚያ ልክ መንግሥትም ዕውቅና አልሰጠውም፡፡ ይህ በሕዝብ ያለመታወቅም ሆነ በመንግሥት ተገቢ የሆነ ዕውቅና አለመሰጠት አንዱ መሠረታዊ ምክንያት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ችግር ነው፡፡ አደጉ በሚባሉ አገሮች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂና ዋና ኦዲተር ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ግዙፍ ተቋማት ናቸው፡፡ በእዚህ አገር ግን ገዝፈው የሚታዩት ከጠቀስኳቸው ተቋማት ይልቅ የትምህርት ሚኒስቴር ወይም የጤና ሚኒስቴር ዓይነት ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ ማለት ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን ወደኋላ እየጎተተ ያለው ለዴሞክራሲ ተቋማት የሚሰጠው ትኩረት ማነስ ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ፣ ስለመልካም አስተዳደር ፖለቲከኞችም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር ያወራሉ፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት ይገነባል? መልካም አስተዳደር እንዴት መስፈን አለበት? ለሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ አንድ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገለልተኛ ሆነው እንዲቋቋሙ መደረግ ባለባቸው ተቋማት ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳለ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በዕንባ ጠባቂ ተቋም ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አለ ወይ?

ዶ/ር እንዳለ፡- አዎ፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በተለይ ደግሞ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት ነፃ፣ ገለልተኛና ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው መሠረታዊ መሥፈርቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ተቋማዊ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነፃና ገለልተኛ መሆን አለባቸው ሲባል የሚያቀርቡት የመፍትሔ ሐሳብ ከማንኛውም የመንግሥት አካል ጣልቃ ገብነት እንዳይኖርበት መደረግ አለበት፡፡ በተለይ ከአስፈጻሚው ነፃ እንዲሆን የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ተቋሙ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በራሱ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ብሔር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሒደት ውስጥ የግላቸው የሆነውን ነገር ከሥራው ጋር መቀላቀል የለባቸውም፡፡ ማለትም የሚደርሱበት ውሳኔ ከብሔር ማንነት፣ ከፖለቲካ እምነት፣ ወይም ከሃይማኖት ሳትወግን ነፃና ገለልተኛ ሆነህ ትሠራለህ ማለት ነው፡፡ ከለውጡ በኋላ ትልቅ መሻሻል ታይቷል፡፡ እኔ ወደ እዚህ ኃላፊነት ከመጣሁ ጀምሮ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ምናልባት ሊያኮርፉህ ይችላሉ እንጂ፣ በግለሰብ ደረጃ ከዚያ ውጪ ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢወስን ወይም እንደ እዚህ ጻፍክ ብሎ የሚመጣ የለም፡፡ በእርግጥ ከለውጡ በፊት በተለይ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሐፈት ቤትና ከአፈ ጉባዔው ጭምር እየተደወለ እነዚህን ጉዳዮች ለምን አትተዋቸውም ተብለው የሚገደዱበት አሠራር እንደነበር መጥቅሰ ይቻላል፡፡ አሁን እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ትልቁ ፈተና አስፈጻሚ አካላት ውሳኔ ከሰጠናቸው በኋላ ያለ መፈጸም ይታያል፡፡ ከተቋም ተቋም ይለያያል እንጂ የብሔር ጉዳይም ይቀላቀልበታል፡፡ ለምሳሌ እንደ አገር ሲታይ ኦሮሚያ ክልል በብሔር ማንነታቸው ዜጎች ይፈናቀላሉ፡፡ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ሀብትና ንብረታቸው ይወሰድባቸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸን የመፍትሔ ሐሳብ ስናቀርብ፣ በግለሰቦች ላይ ጥቃት የሚደርስበት አጋጣሚ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ካልሆኑ በስተቀር ከገለልተኝነትና ከነፃነት ጋር የሚያያዙ ችግሮች አይገጥመኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት የዕንባ ጠባቂ ተቋም እንደ ስሙ ዕንባ የሚያብስ አይደለም በማለት ከፓርላማ አባላት ጭምር  ይነገር ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ይገልጹታል?

ዶ/ር እንዳለ፡- እኛ ነን እነሱን የምንላቸው፡፡ ‹‹ባለቤቷን የተማመነች በግ ባቷን ውጭ ታሳድራለች›› እንደሚባለው፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ፓርላማውን ተማምነው ነው ውሳኔ የሚሰጡት፡፡ ለምትወስደው ውሳኔ ምክር ቤቱ ዘብ ይሆንልኛል ብለህ ስለምታስብ ነውና የቀድሞው ፓርላማ አባላት በቅንነትና በፈቃደኝነት እኔን በመርዳት ረገድ ብዙም ችግር አልነበረባቸውም፡፡ ከገጠሙን ትልልቅ ጉዳዮች መካከል ለምሳሌ በይርጋለም የደቡብ ፖሊስ ማሠልጠኛ አለ፡፡ ይህ ማሠልጠኛ በሚሠራበት ጊዜ በጣም ብዙ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ካሳ ወደ 100 ሚሊዮን ብር ነው የተገመተው፡፡ በዚህ መሀል የተወሰኑት ካሳ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን 80 ሚሊዮን ብር አልተከፈለም፡፡ ስለዚህ ይህን ስታይ ከበጀት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ወደ ፓርላማው ይመራል፡፡ በተመሳሳይ በሲዳማና በደቡብ ብሔር ብሔሰቦች ክልል መካከል የሚፈጠሩ ጉዳዮች ለምክር ቤቱ ይመራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ለምክር ቤቱ የምንልካቸው የውሳኔ ሐሳቦችን ያለ መፈጸም መሠረታዊ ችግር ነበረ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝቡ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን እንዴት ይመለከተዋል? ምናልባት ያካሄዳችሁት ጥናት ይኖር ይሆን?

ዶ/ር እንዳለ፡- ከዚህ በፊት ጥናት ሠርተናል፡፡ ውሳኔ የተወሰነላቸው ቢሯችን ይመጡና ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ሄደው ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ እኛ አንዱ የማናየው በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ሲሆን፣ እንዲሁም ከፀጥታና ከኦዲት፣ ከሙስና ጋር የተገናኝ ከሆነ እኛ አይመለከተንም፡፡ ነገር ግን ሰዎች ወደ ተቋማችን ይመጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እኛን አይመለከተንም ብለን ስንልካቸው ታዲያ ምኑን ነው ዕንባ ልታብሱ የተቀመጣችሁት ይሉናል፡፡ እኛም አዋጁን አውጥተን እናሳያቸዋለን፡፡ በአጠቃላይ እንደ አገር ስታስብ የዕንባ ጠባቂ ተቋም አቅም አለው፣ ውሳኔ ያስገኝልኛል የሚለው አስተሳሰብ ገና ነው፡፡ ይህ ከሁለት ነገሮች ይመነጫል፡፡ አንደኛ የዴሞክራሲ ዕድገት፣ በሁለተኛ ደረጃ በታዳጊ አገሮች ላይ የሚታየው የአስፈጻሚ አካላት ተፅዕኖ ነው፡፡ የሚገርመው ከፓርላማውና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማን የተሻለ ይወስንልሃል ብትለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው የሚልህ፡፡ ይህ ከአጠቃላይ አስተሳሰብ ጋር የሚሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ2013 ዓ.ም ወደ ሥራ በገባው የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በአሥር ዓመት ውስጥ በአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የዕንባ ጠባቂ ተቋም ለመገንባት የሚል ትልም  ይዟል፡፡ ይህ የሚቻል ነው?

ዶ/ር እንዳለ፡- ይሳካል አይሳካም ስትል የዚህ ተቋም መሠረታዊ ችግር የራሱ የሆነ ሕንፃ የለውም፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ መሥራት እየተቻለና ፍላጎት እያለ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ይገጥመዋል፡፡ ለአፍሪካ ተምሳሌት እንሆናለን ስንል ሁሉም ቦታ ተደራሽ እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚያግዘን ጥናት ሠርተናል፡፡ ቢያንስ በዞን ደረጃ በአምስት ዓመታት ውስጥ የት የት መድረስ እንዳለብን አስቀምጠናል፡፡ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ስታይ በተለይም የፌደራል ሥርዓት የሚከተሉት ያላቸው እስከ ክልል ደረጃ ነው፡፡ እኛ ቢያንስ እስከ ዞን ድረስ ለመድረስ ነው ዕቅዳችን፡፡ ሌላው ጉዳይ አብዛኛውን አገልግሎታችንን ዲጂታል አድርገን ለሕዝብ በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን ነው፡፡ አሁን 7502 የጥሪ ማዕከል በመጀመራችን በመሠራቱ የቅበላ አቅማችንን ወደ 24 በመቶ አድርሰናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዳታ ቤዝና የጉዳይ አፈታት ሲስተም እየሠራን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ሁሉ ሥራዎች የራስ ሕንፃ ያስፈልገናል፡፡ ምክንያቱም ሕንፃ ከሌለ ነገ ከዚህ ስንለቅ ትልልቅ ሰርቨሮችንና የገነባናቸውን ሲስተሞች እንደገና አፍርሰን ልንገነባ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የራሳችሁን ሕንፃ ለመገንባት ለምን ከበዳችሁ?

ዶ/ር እንዳለ፡- አንዱ መሠረታዊ ችግር ምንድነው? በተለይ የቀድሞው አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በነበሩበት ወቅት፣ ሁሉንም የዴሞክራሲ ተቋማትንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን የሚይዝ አንድ የሕንፃ ግንባታ ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ከለውጡ በኋላ የታሰበው የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ እኛ እየጠየቅን ያለነው የራሳችን ሕንፃ እንዲኖረን ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላለንበት ቢሮ በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን ብር ነው የምንከፍለው፡ ነገር ግን ለእኛ 50 እና 60 ሚሊዮን ብር ቢሰጠን ያን ያህል አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ገንዘቡም ሲታይ አስፈጻሚ አካሉ ለአንድ ዋጋውን ልትገምተው ለማትችለው ጉዳይ የሚያወጣው ነው በ50 እና 60 ሚሊዮን ብር የራሳችን ሕንፃ ቢኖረን ብዙ ሥራዎችን ማከናወን እንችል ነበር፡፡ በተለይ ሥራችን ለመደገፍ ፈንድ ይመጣል፡፡ ነገር ግን የሚጠየቀው አንዱ ትልቅ ጉዳይ ቢሮ አላችሁ ወይ የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምርመራና በክትትል ሥራችሁ የምትጠቀሙት ዘዴ ምን ዓይነት ነው? በቂ የሰው ኃይልስ አላችሁ?

ዶ/ር እንዳለ፡- ከምርመራ አንፃር ሲታይ ባለሙያዎቻችን የሕግ ሙያተኞች ናቸው፡፡ የራሳችን የምርመራ መመርያ አለን፡፡ ይህን ተከትለን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ነው የምንሠራው፡፡ መጨረሻ ላይ የውሳኔ ሐሳብ ስንሰጥ ክፍተቶችን ለይተንና አውቀን በማስቀመጥ ነው፡፡ ባለሙያዎቻችን ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ የተረዱና የተሻለ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ችግር የሆነብን ከዚህ በፊት ወደ እዚህ ተቋም ለሚመጡ ባለሙያዎች በወቅቱ ከነበረው የዳኞችና የዓቃቤ ሕግ ደመወዝ አንድ ዕርከን ተሻሽሎ ነበር፡፡ አሁን ግን የዳኞችና የዓቃቤ ሕግ ደመወዝ ወደ ላይ ወጥቷል፣ የእኛዎቹ ታች ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ የማሻሻያ ሐሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበናል፣ ምንም እንኳ ውሳኔ ያልተሰጠው ቢሆንም እስካሁን ድረስ፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳይ አጣርታችሁ ወደ ክስ ስትልኩ ያለው አፈጻጸም ሒደት እንዴት ነው?

ዶ/ር እንዳለ፡- እኛ መረጃ አደራጅተን ለዓቃቤ ሕግ ነው የምንሰጠው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከሰጠነው በኋላ ወደ ፍሬ ነገር አይገባም፣ ቀጥታ ወደ ክስ መመሥረት ነው የሚሄደው፡፡ እኛ በዚህ ጊዜ ችግር እየገጠመን ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ የሚመስለኝ፣ እኛ ክስ መሥርቱልን ብለን ስንጠይቅ እነሱን እንዳዘዝናቸው አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ክስ እንዲመሠረትለት ከሚጠይቅበት የሕግ ሥርዓት ውስጥ፣ አንዳንድ ቃላት ለምሳሌ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ ክስ ይፈጽማል የሚሉ ወደ አምስት አንቀጾች እንዲስተካከሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልከናል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይም የአሁኑ የፍትሕ ሚኒስቴር የአስፈጻሚው የመንግሥት አንዱ አካል ነው፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ሥራ ደግሞ በመንግሥት አስፈጻሚና በሌሎች ተቋማት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን መስማትና መመርመር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሁለታችሁ መካከል መገፋፋት የለም?

ዶ/ር እንዳለ፡- እኛ አደራጅተን ክስ እንዲመሠርቱ ነው የምንሰጣቸው፡፡ ነገር ግን እንዳልከው መሠረታዊ ችግሩ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብትሄድ ዋና ዓቃቤ ሕጉን የሚሾሙት ከንቲባዋ ናቸው፡፡ ስለዚህ እሳቸው እየሾሙ እሳቸውን ለመክሰስ ሞራል የለውም፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ይህን የምታየው በኢትዮጵያ ሲሆን፣ በአደጉ አገሮች ግን አይታይም፡፡ በሌሎች አገሮች በተለይም በዴሞክራሲ የበለፀጉ በሚባሉት አስፈጻሚ አካላት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደ ሥልጣን ስለሚወጡ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ምክረ ሐሳብ ነው የሚያቀርቡት በሚል ነው እንጂ፣ አስገዳጅ የሆነ የሕግ መሠረት የለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር አስገዳጅ የሆነና አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችለው አንደኛ በሚዲያ በማጋለጥ፣ ሁለተኛ በልዩ ሪፖርት ለፓርላማው በማቅረብና ሦስተኛ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ የሆነ አስፈጻሚ አካል ካለ ደግሞ በዓቃቤ ሕግ በኩል ክስ መሥርቶ ተጠያቂ በማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለጋዜጠኞች መረጃ የማይሰጡ ተቋማትን እንዴት ነው የምትከታተሉት?

ዶ/ር እንዳለ፡- በአጠቃላይ መረጃን ለኅብረተሰቡ ከማድረስ አንፃር ከሚዲያዎች የሚመነጭ ችግር አለ፡፡ እንዲሁም ከአስፈጻሚ አካላትም የሚነጭ ችግር አለ፡፡ የመረጃ ነፃነት አዋጁ በግልጽ እንዳስቀመጠው አስፈጻሚው አካላት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከሕዝብ በሚሰበሰብ ሀብት የሚተዳደሩ ከሆነ ስለሠራተኛቸው፣ ስለመዋቅራዊ አደረጃጀታቸው፣ ስለፖሊሲያቸውና ስለሚሰጡት አገልግሎት ለኅብረተሰቡ በየወቅቱ ይፋ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ያ ዜጋ ለዚህ ጉዳይ ግብር ስለከፈለበት፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚ አካላት አንድም ለጥሩ ነገር ብቻ መረጃ የመስጠት ፍላጎትና ዝንባሌ አላቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የዕድገት ምልክት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የዴሞክራሲ አንደኛ መገለጫ መርሆች ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ የሕግ የበላይነትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መርሆች ካልተሟሉ በአንድ አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችልበት ሁኔታ ስለማይኖር፣ የአስፈጻሚው አካል ላይ የፈቃደኝነት ችግር ይኖራል፡፡ ሁለተኛ በየተቋሙ ያሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በሚጠበቅባቸው ልክ ራሳቸውን ያዘጋጁ አይደሉም፡፡ ከሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚጠበቀው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ናቸው ተብሎ ነው፡፡ ከለውጡ በፊት በፖለቲካ ሹመት ነበር የሚመጡት፡፡ በተለይ የመንግሥትን ፖለቲካ የተቀበሉ፣ በግልጽም የተሰጣቸው እንደ አገርና እንደ ተቋም የገጽታ ግንባታ ተብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ገጽታ ግንባታ በሚል ጥሩ ነገርን ብቻ ማጉላት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የግብርና ሚኒስቴርን ብንወስድ ሚኒስቴሩ ዘንድሮ ይህን ይህን መልካም ሥራ ሠርቷል፣ ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች በሚሠራበት ወቅት ደግሞ እነዚህ ጉዳዮችን አልፈጸማቸውም ብለህ ለሕዝብ ብትገልጽ የተቋሙን ገጽታ አይጎዳም፡፡ ነገር ግን በአስፈጻሚ አካሉ ውስጥ ያለ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ችግር በመለወጥ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አጠናክሮ የሚጠበቅባቸውን ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ፣ ኃላፊዎችም በጣም ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ መግለጫም ሆነ መረጃ እንዲሰጡ አዋጁ ያስገድዳል፡፡

ከዚያ ውጪ ተከታታይና የዕለት ተግባራትን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መስጠትና አትሞ የማውጣት ኃለፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የምናያቸው የታተሙ መረጃዎች በፎቶ የታጨቁ ናቸው፡፡ የፎቶ ጋለሪ ነው የሚመስሉት፡፡ መረጃን አትሞ ለማድረስ ያለ ችግርን በተመለከተ ተቋማት የሚያነሱት ጉዳይ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ለተቋማት ወጪ ቆጣቢ ሆነው እንዲሠሩ የላከውን ደብዳቤ ነው፡፡ ነገር ግን በደብዳቤው የተገለጸው ስለተቋሙ መረጃ አትስጡ አይልም፡፡ ይልቁንም ኮፍያ፣ ቲሸርት፣ አላስፈላጊ ድግስና መሰል ጉዳዮች ላይ ገንዘብ አታጥፉ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ሁሉም ተቋማት ዌብሳይት አላቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ ዌብሳይት ከሦስትና ከአራት ዓመት ወዲህ ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑን ታያለህ፡፡ ከዚያ ይበልጥ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ታያለህ፡፡ ሌላው እንደ ትልቅ ችግር በየተቋማቱ ያሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚያነሱት ነው፡፡ ኃላፊዎች ጠንክረን እንድንሠራ ዕገዛ አያደርጉልንም፣ ከእኛ የሚፈልጉት የእነሱን ገጽታ እንድንገነባ ነው መረጃ እንድንሰጥ የሚፈልጉት የኃላፊዎችን ማንነት ሊያገዝፉ የሚችሉ ድምፆችን በሶሻል ሚዲያ ወይም በሌሎች የመረጃ መለጠፊያዎች ላይ እንድንለቅ፣ ተቋሙ ስለሠራው ጥሩ ነገር  ብቻ እንድንናገር እየተደረግን ነው የሚሉ አቤቱታዎች ያሰማሉ፡፡ በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተና ተፈላጊ መረጃዎችን እንድንሰጥ አይፈልጉም ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ አንድ ተቋም ብንሄድ የፋይናንስ ዳይሬክተርና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በመዋቅር እኩል አይደሉም፡፡ ሙያውን እንደሚፈለግበት እየሠራንበት አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይበዛሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በመረጃ አሰጣጥ ክፍተት ላይ እየሠራችሁት ያለ ነገር ካለ?

ዶ/ር እንዳለ፡- እንደሚታወቀው ሚዲያዎች ወቅታዊ መረጃ ነው የሚፈልጉት፡፡ ለምሳሌ ለዛሬ ዜና የሚሆንህን መረጃ ዛሬ ማግኘት አለብህ፡፡ ነገር ግን በ2000 ዓ.ም. በወጣው የመረጃ ነፃነት አዋጅ አንድ ሚዲያ መረጃ ሲፈልግ እስከ አሥር ቀናት ድረስ ማግኘት አለበት ተብሎ ነው የተደነገገው፡፡ ይህ ከጋዜጠኛው የዜና ጥንቅርና የመረጃ ፍላጎት አኳያ እንቅፋት በመሆኑ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ አዋጆች እንዲሻሻሉ በሚል በቀረበው መሠረት ከዚህ በፊት የሲቪክ ድርጅቶች አዋጅ፣ የምርጫ አዋጅና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይሻሻል ተባለ፡፡ በተለይ በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት አዋጅ ጋዜጠኞች እስከ አሥር ቀን እንዲጠብቁ የሚያደርገውን ወደ ስድስት ቀን በማድረግ ሌሎች ማሻሻያዎች ተደርገውበት፣ በተቻለ መጠን የመረጃ አቅርቦቱን ችግር ሙሉ በሙሉ ባይፈታው እንኳ በተወሰነ ደረጃ እንዲፈታ ተሻሽሎ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ አዋጁ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ተይዟል፡፡ በቶሎ ለምን ሊፀድቅ እንዳልቻለ ግልጽ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አዋጅ ምን ይዘት አለው?

ዶ/ር እንዳለ፡- አዋጁ ከፀደቀ ተቋማት ሚስጥራዊ የሚሉትን መረጃ ያስመዘግባሉ፡፡ የሚዲያ ተቋማትም ማግኘት ያለባቸውን መረጃ በሕጉ መሠረት እንዲያገኙ ያግዛል፡፡ በቀጣይ ልንሠራ ባሰብነው ጉዳይ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በፌደራል ያለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴርና በክልል ያሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮዎች አንድ ካውንስል መሥርተዋል፡፡ በመረጃ ተደራሽነት ረገድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ በተቋማችሁ ባለፉት ስድስት ወራትና ከዚያም በፊት እየገጠማችሁ ያለው ችግር ምንድነው?

ዶ/ር እንዳለ፡- የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ አንድ ዜጋ በአገሪቱ ክልል ውስጥ የመኖርና ሠርቶ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ነገር ግን የዜጎችን ሰላም ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ምንም እንኳ የሰሜኑ ጦርነት ልዩ ሁኔታ ፈጥሮ ከመንግሥት አቅም በላይ ቢሆንም፣ ከዚያ ውጪ ጦርነቱ ሲቆምና ጦርነቱ በሌለባቸው አካባቢዎች መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት አስጠብቃለሁ በማለት ቃል ገብቶ ነው፡፡ በተለይ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጡትን የዜጎች መብት ማስጠበቅ ቢኖርበትም፣ በርካታ ችግሮች ታይተዋል፡፡ እዚህ ላይ የማነሳልህ የሕግ የበላይነትን ከማስጠበቅ ባለፈ በአንዳንድ ክልሎች ዜጎች የብሔር ማንነታቸው እየተለየ ወደ ክልላቸው እንዲሄዱ ይደረጋሉ፡፡ ዜጎችን በማንነታቸው እየለዩ ከክልሎች ማባረር መሠረታዊ የፖለቲካ ብልሽት ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ያየነው ከወለጋ ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ሸዋ አማራ ክልል ሲላኩ፣ ሰሜን ሸዋ ደግሞ አልቀበልም ብሎ ወደ ኦሮሚያ ይልካቸዋል፡፡ ከዚያ ኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ ይልካቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ መጀመርያ ከደረሰባቸው ኢሰብዓዊ ድርጊት በበለጠ የሚያበሳጭ ነው፣ መስተካከል አለበት፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት ተቋማት መሀል ሥራቸውን በአግባቡ በተሰጣቸው ልክ የሚፈጽሙ አሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በአዋጅ የተሰጣቸውን ተግባራት በአግባቡ የማይወጡ ተቋማት አሉ፡፡ በአጠቃላይ በመንግሥት ተቋማት ዜጎች በሚፈልጉት ልክ አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ መሠረታዊ ችግር አለ፡፡ በተለይም አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ሊሆን ይችላል፣ ተቋማት በተነሳሽነት ሥራን መሥራት አለብኝ ብለው እየሠሩ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በሲቪል ሰርቪሱ ላይ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ባሉበት ቆመዋል፡፡ በሠራተኛው መሀል የሚታየው ጥቅማ ጥቅም ልዩነት አለ፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሚያተርፉት ለሠራተኞቻቸው ድጎማ ያደርጋሉ፣ ማበረታቻ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ይህን መሰል ጥቅማ ጥቅም እያገኙ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ በሁለቱም ተቋማት ያሉ ሠራተኞች ለአንድ አገር የሚሠሩ ቢሆንም፡፡ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ካስተናገዳቸው መካከል ከታክስ ክፍያ ጋር በተገናኘ፣ ከከተሞች መስፋፋት፣ በተለይም አርሶ አደሮች ሲፈናቀሉ ካሳ ያለ ማግኘት፣ ተቋማት ያላግባብ ሠራተኞችን ከማባረር ጋር የተገናኙ አስተዳደራዊ በደሎች፣ እንዲሁም ከመሬት ልማትና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተገናኙ አቤቱታዎች ይበዛሉ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....