Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት እንዴት ድርቁን መከላከል እንዳልቻለ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

መንግሥት እንዴት ድርቁን መከላከል እንዳልቻለ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ መረጃዎችን የሚሰበስብና የሚተነትን የቅድመ ትንበያ ሥርዓት ከተዘረጋ በርካታ ዓመታት በተቆጠረበትና የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ የአየርና የዝናብ ሁኔታ የመተንበይ አቅም ባደገበት ሁኔታ፣ መንግሥት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ከ1.7 ሚሊዮን በላይ እንስሳትን የገደለውን ድርቅ ለምን አስቀድሞ መከላከል እንዳልቻለ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

መንግሥት ድርቁ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጣር አለመቻሉን በመጥቀስ ወቀሳውንና ጥያቄውን ያቀረበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሲሆን፣ መንግሥት ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የመረጃ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ቅድመ ማሰጠንቀቂያ ሥርዓት ተጠቅሞ፣ ድርቁን ማስወገድ ወይም መቀነስ ይችል እንደነበር ገልጿል፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተነሳው ጦርነት፣ በርካታ ዜጎች ለዕርዳታና ለረሃብ መጋለጣቸውን ያስረዳው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅም በሶማሌ ክልል በአብዛኛው ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞንና በባሌ ቆላማ ክፍሎች፣ በደቡብ በጥቂት አካባቢዎች ላይ ሰዎችን ለረሃብ፣ እንስሳት ለሞት መዳረጉን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት ድርቁን የተመለከቱ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ባለመሥራቱም በኦሮሚያ ክልል 3.7 ሚሊዮን ሰዎችን እንዳጠቃና በሶማሌ ክልል የዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ወደ 3.4 ሚሊዮን ከፍ እንዳደረገ ተቋሙ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ላይ አትቷል፡፡

በአርብቶ አደርና ከፊል ግብርና በሚተዳዳሩ አካባቢዎች ባለፉት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉና የጣለውም በቂ ባለመሆኑ፣ ለተከሰተው ድርቅ እየተሰጡ ያሉ ምላሾችም ቢሆን በቂ አለመሆናቸውን ተቋሙ አስረድቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውኃ ከሚፈልጉ ከ1.5 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ እየቀረበ ያለው 700 ሺሕ ለማይሞሉ ሰዎች መሆኑ በመግለጫው ላይ በማሳያነት ተጠቅሷል፡፡ ተቋሙ የእንስሳት መኖን በተመለከተም ከሚያስፈልገው 31.2 ቦንዳ ሳር ውስጥ እስካሁን መቅረብ የቻለው  619 ሺሕ ቦንዳ ሳር ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላም በቂ መኖና ውኃ ማቅረብ ካልተቻለ በኦሮሚያ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ሊሞቱ እንደሚችሉ ተቋሙ አስጠንቅቋል፡፡

በሁለቱም ክልሎች በድረቁ ለተጎዱ ዜጎች በቂ የዕለት ደራሽ ምግቦች የየእንስሳት መኖና ውኃ እየቀረበ ካለመሆኑም በላይ በማዕከል ተሰባስቦ የሚገኘው ዕርዳታ በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑም በመግለጫው ላይ ተካቷል፡፡

‹‹አገሪቱ ጦርነት ውስጥ የነበረችበት ሁኔታ ቢኖርም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት (early warning system) መረጃዎችን መሠረት አድርጎ ድርቁ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ማስወገድ ወይም መቀነስ የሚቻልበት ሆኔታ ሊኖር ይገባ ነበር›› የሚል እምነቱን የገለጸው ተቋሙ፣ ድርቁ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ለምን ማስወገድ ወይም መቀነስ እንዳልተቻለ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ለዜጎች በቂ መረጃ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ እንዲሁም አሠራሮች ተፈትሸው ከዳግመኛ ከእንደዚህ ዓይነት ችግር ለመዳን እርምት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ባሳለፍነው ሳምንት ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ያስታወሰው ተቋሙ፣ ውሳኔና አቅጣጫዎቹ በመንግሥት አሠራር ላይ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ገልጿል፡፡

ፓርቲው በጉባዔው ላይ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ፣ የትግራይ ሕዝብን በሚመለከትና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ተቋሙ በመልካም እንደሚመለከተው አስታውቋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉትና ወደ መሬት የሚወርዱት ግልጽ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ሲኖራቸው እንደሆነ በመግለጫው ላይ አስታውሷል፡፡

ዕቅድ ፖሊሲን እንደማይተካ ያስረዳው የተቋሙ መግለጫ፣ መንግሥት የሚወጣቸው ማንኛውም ዕቅድ ወይም ሕግ እንዲሁም የመሪዎች ኦፊሻል መግለጫዎችምና ንግግሮች ከመንግሥት ፖሊሲዎች የሚመነጩ መሆን እንዳለባቸው ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...