Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የቱሪስቶቹ መንገድ መሪዎች

‹‹በአዶላ፣ በዩብዶ፣ በምድርዜን፣ በዑጋሮና እነሱን በመሳሰሉ ቦታዎች፣ የወርቅ ማዕድኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን የጠቀስኩ ለአርዓያ ነው እንጂ፣ በአገራችን እነሱ ብቻቸውን እንዳይደሉ አያጠራጥርም፡፡ ኢትዮጵያችን ሀብታም አገር ናት፡፡ ሀብትዋም በያይነቱ ነው፡፡ በመሬቷ ሆድ ውስጥ ብዙ ማዕድኖች በያይነቱ ብረቶችና ነዳጅ ዘይቶች ይገኙበታል፡፡ በምድረ ገጽዋ ላይ ደግሞ የሚበቅልበት እህልም፣ የሚለማበት ተክልም ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የሚሠማሩባት እንስሳዎችስ ማን ቆጥሮና ዘርዝሮ ሊጨርሳቸው? ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በላይም አንድ ልዩ ሀብት አላት፡፡ እሱም የተፈጥሮ ውበቷ፣ ታሪኳ፣ ኪነ ጥበቧ፣ ባህሏ ሥነ ሥርዓቷ፣ መጻሕፍቷ፣ አድባራቷ፣ ገዳማቷ በማለት አንዳንዱን ለማስታወስ ያህል እምንገልጸው፣ ለእኛ ምሥጢር ሆኖ የተደበቀን የወርቅ ማዕድንን ነው፡፡ ይህ የወርቅ ማዕድን መቆፈሪያ አያሻውም፡፡ ላብን ማፍሰስ አያስፈልገውም፣ አሸዋን ከውዱ ማዕድን ፍጥረት ለይተው የሚያወጡ መኪናዎች አይፈለጉበትም፣ ድንጋዩን የሚፈጩ ኃይለኞች ወፍጮዎችን አይጠይቅም፣ ይህ ማዕድን፣ ድሮ ሰው የሠራበት የደከመበት ወርቅን አምርቶ ማፈስን የሚያስችለው ብልኃትና ዘዴን ብቻ ይጠይቃል፡፡ ይህ ዘዴ የቱሪዝም ብልኃት በሚል ቃል የተጠቀለለ ነው፡፡ ይህ ዘዴ የወንድማማችነት ፍቅር፣ በጎ ፈቃድ፣ መልካም ጠባይ፣ ቅን መንፈስ፣ ስላገሬው መቅናትና መሥራት፣ ኑሮን ለማሻሻል የሚያሳስብ አስተዋይ መንፈስ እንጂ ሌላ ሰፊ ጥናትም ጥልቅ ዕውቀትም ብዙ ትምህርት አያስፈልገውም፡፡››

ይህ ዓቢይ ጥቅስ፣ ከሃምሳ አራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በበላይነት ይመራ ከነበረው የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የሥራ ትስስር የነበራቸው ሊቁ አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለቱሪስት መስህብነት፣ መዳረሻነት ትልቅ ገበታ መሆኗን በገለጹበት መጽሐፋቸው ውስጥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹የማያልቅ የወርቅ ማዕድን (የኢትዮጵያ ውበት)›› በሚለው መጽሐፋቸው ሊቁ፣ እንዳመለከቱት በወርቅ ማዕድን የተመሰለው ቱሪዝም የማያልቅ ሀብት የማይደርቅ ምንጭ መሆኑን መላው ዓለም ተገንዝቦታል፡፡

ኢትዮጵያ አገራዊ የቱሪዝም ተቋምን ከስድስት አሠርታት በፊት በወቅቱ የሥራ  ሚኒስትር በነበሩበት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም አሳሳቢነት ማቋቋም ስትጀምር፣ ኃላፊነቱን የተቀበሉት ከዘመናት ድንቅ አገልግሎታቸው በኋላ ‹‹የቱሪዝም አባት›› የተሰኘውን ቅፅል ስም ያተረፉት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ናቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሠርቲ መንዝ ስኦቭ ሰንሻይን›› (ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ) የሚለውና እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ አገራዊ መለያ (ብራንድ) ሆኖ የዘለቀውን ማስተዋወቂያ ያበረከቱ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡

ከንጉሠ ነገሥት መንግሥት እስከ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ ከሕዝባዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) እስከ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ድረስ የቱሪዝም ተቋሙ በተለያዩ አደረጃጀቶች ሲያልፍ ከ13 ወር ፀጋ እስከ አሁኑ ‹‹ምድረ ቀደምት›› እስከሚለው አገራዊ ማስተዋወቂያ ድረስ የቱሪዝሙ ባለድርሻ አካል ሆነው ከሚንቀሳቀሱት መካከል አስጎብኚዎች ይገኙበታል፡፡ ከታሪካዊ የጉዞ መስመር ከአክሱም ላሊበላ፣ ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከስሜን ተራሮች እስከ ባሌ ተራሮች፣ ከአዋሽ ሸለቆ እስከ ኦሞ ሸለቆ እንዲሁም በሌሎች ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ጭምር የውጭ አገርም ሆነ ያገር ውስጥ ቱሪስቶች ሲንቀሳቀሱ፣ በማስጎብኘት፣ በማብራራት ከሚሠለፉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ አስጎብኚዎች፡፡ በተናጠልና በቡድን ለዘመናት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት እነዚህ ባለሙያዎች ከሁለት ዓመት ወዲህ የራሳቸውን ማኅበር መሥርተዋል፡፡ ስሙንም የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ብለውታል፡፡

መሰንበቻውን ማኅበሩ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ አካሄድኩት ያለውን ዓለም አቀፍ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያ ቀንን አክብሯል፡፡

ሙያውን ባከበረና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነትን ባማከለ መልኩ በእግር መንገድ ጉዞና በደም ልገሳ ማክበሩን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ካሳ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የማኅበሩ አመራሮች የሰጡትን መግለጫ ሔኖክ ያሬድ አጠናቅሮታል፡፡

  •  የማኅበሩ ምሥረታና ዓላማዎች

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የመዝገብ ቁጥር 5694 ተመዝግቦ፣ ከሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቱሪዝም ዘርፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማዕከል በመሆን እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ራዕዩ የአገሪቱን የታሪክ፣ የተፈጥሮና የባህል መስህቦች/እሴቶች በመጠበቅና በማስተዋወቅ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይሆናል፡፡

ሙያው በሚጠይቀው ሰብዕና፣ ዕውቀት እንዲሁም ክህሎት ደረጃ በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ የሆነ በትምህርት ዕድሎችና ዝግጅቶች የታገዘ ባለሙያ ማፍራትም ተልዕኮው ነው፡፡ እንዲሁም ማኅበሩ የአባላቱን መብትና ጥቅም ማስከበር፣ በዕውቀት የሚመራ፣ በባለሙያነት ሥነ ምግባር የታነፀ፣ የሙያተኞች መገናኛ ማዕከል መሆንንም፣ ያልማል፡፡

  •  ያከናወናቸው ተግባራት

ማኅበሩ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ከስምንት ወር የሆነው ሲሆን በዚህ አጭር ጉዞው ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቀዳሚው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማኅበሩ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ የተመሠረተ እንደመሆኑ አስጎብኚ ባለሙያው ከችግር የሚወጣበት መንገድ ከመፈለግና ሐሳቦችን ከማመንጨት ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ በማኅበራዊ ኃላፊነት ረገድም ኢትዮጵያን በልምላሜና ልብስ በሚል ዘመቻ ከ300 በላይ ችግኞችን ከየካ ክፍለ ከተማ በተረከበው ቦታ ላይ አባላቱን በማስተባበር ተክሏል፡፡ ሁለት ጊዜ የደም ልገሳ መርሐ ግብር በማዘጋጀት የማኅበሩ አባላት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

ማኅበሩን ከማሳወቅና ቱሪዝሙን ከማነቃቃት አንፃር ‹‹ኢትዮጵያን በቱሪስት አስጎብኚዎቿ ዕይታ›› የሚል ለሳምንት ያህል ለሕዝብ ክፍት የሆነ የፎቶ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሙዚየም አዘጋጅቷል፡፡ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የክህሎት ማዳበሪያ ሥልጠናም በባህር ዳር ከተማ አከናውኗል፡፡

  •  ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስላለው ግንኙነት

ማኅበሩ ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር የዓለም ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያ ማኅበራት ፌዴሬሽን ሙሉ አባል ሆኗል፡፡ በዚህም ጥቅሞችን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል፡፡ በፌደሬሽኑ አማካይነት ሊገኙ የሚችሉ ዓለም አቀፋዊ መብትና ጥቅሞችን ማረጋገጥ፣ ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማኅበረሰቡ ጋር ግንኙነት መፍጠር ብቁ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያ ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ ማመቻቸትና በዓለም አቀፍ የንግድ ባዛር መሳተፍ ቀዳሚ ትኩረቱ ነው፡፡ የዓለም የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ቀንን ሙያውን በሚያሳድግና ሚናውን በሚያጎላ መልኩ ማስተዋወቅና ማክበርም የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡

ከፌዴሬሽኑ በሚገኘው የትምህርት፣ ሥልጠናና ምክክር መድረኮች ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ፣ በቱሪዝም ላይ የሚከሰቱ አዳዲስ አሠራሮችን፣ ሥልጠናዎችንና ሕጋዊ ጉዳዮችን እንደ መረጃ መጋራት ጠቀሜታው ይጎላል፡፡ በተለይ ኩልቱር ካርድ (Cultour Card) በሚባል መንገድ የጉብኝት ቅናሾችን ማግኘት አንዱ ግቡ ይሆናል፡፡

በአገር ውስጥም ከመንግሥታዊና ከግል የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ጋር የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም ወደ ተግባር ለመግባትም አልሟል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...