Wednesday, July 24, 2024

የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ የቤትሥራዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መስከረም 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ፣ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች እንዲዋሀዱ የሚለውን ትልም ለመወሰን የሚያግዝ ጥናት እንዲደረግ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ፣ በኅዳር 2012 ዓ.ም. ሦስት የኢሕአዴግ አባልና አምስት አጋር ድርጅቶች የተሳተፉበት የብልፅግና ፓርቲ ምሥረታ ይፋ ሆነ፡፡

ከተመሠረተ ከሦስት ዓመት በላይ ዘግይቶ ከመጋቢት 2 አስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. አንደኛ መደበኛ ጉበዔውን ሲያካሂድ፣ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመክፈቻ ጉባዔ የተናገሩት፣ ጉባዔው በቀደመው ኢሕአዴግ ዘመን እንደነበረው አካሄድ ሳይሆን ሁሉም ብሔሮች በሚገባቸው ቁጥር ልክ የሚሳተፉበት መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሚታወቁ ፓርቲዎች 90 በመቶ ኦሮሞ፣ አንድ ወላይታ፣ አንድ ጋምቤላ፣ አንድ ሲዳማ፣ ወዘተ ይዘው ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ይባሉ እንደነበር በመግለጽ፣ ‹‹ዛሬ ግን ብልፅግና ፓርቲ ሁላችሁም እንደምታውቁት ከሁሉም ብሔርና ሁሉም አካባቢ በቂ የሆነ ውክልና ያለው የስም ብቻ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሳይሆን፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ በመሆንና ኢትዮጵያን በመምሰል ኢትዮጵያን ሊያበለፅግ የመጣ ፓርቲ ነው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህም ከእስካሁኖቹ በእጅጉ የሚለይና በሚያመጣው ውጤት በታሪክ ውስጥ በአሻራው የሚታወስ እንደሚሆን አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ  ቅንጅት፣ ኢሕአዴግ፣ ኅብረት፣ እንዲሁም በደርግ ጊዜ ኢጭአት፣ ማሌሪድና መሰል ፓርቲዎች ለመሰብሰብና የጋራ ፓርቲ ለመመሥረት የሞከሩት ሙከራ ሁሉ ሳይሳካ ቀርቶ፣ በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ በርከት ያሉ ታዋቂ ፓርቲዎች በአንድ ፕሮግራም ሥርና በኢትጵያ ጥላ ሥር ሰብሰብ ብለው አንድ የሆኑበት የመጀመርያ ፓርቲ ነው፤›› ሲሉ ዓብይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ፓርቲውን በበላይነት ይመራሉ ተብለው ከተመረጡት 45 የሥራ አስፈጻሚዎች መካከል ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አሥር፣ ከአማራ ስምንት፣ ከደቡብ ሰባት፣ ከሶማሌ አራት፣ ከትግራይ ሦስት፣ ከአፋር ሦስት፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሁለት፣ ከሐረሪ ሁለት፣ ከሲዳማ ሦስት፣ ከጋምቤለ ሁለት፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሁለት ይገኙበታል፡፡

በዚህም የፓርቲው ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት ክልሎች በሕዝብ ብዛታቸው ልክ በኮታ የሚገባቸውን ያገኙ ሲሆን፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ምንም ኮታ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ በተጨማሪም ጉባዔው ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት 225 ሰዎችን ከሁሉም ክልሎች የተመረጡ ሲሆን፣ ብዛታቸውም ለሥራ አስፈጻሚ በተደረገው የኮታ ድልድል አማካይነት ከየክልሉ የተውጣጣ ነው፡፡ በአንደኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ በድምፅ ከተሳተፉት 1,600 ተሳታፊዎች መካከል ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) 1,486 ድምፅ በማግኘት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ከተጠቆሙት ሦስት ግለሰቦች መካከል አቶ አደም ፋራህ በ1,330 ድምፅ፣ እንዲሁም አቶ ደመቀ መኰንን በ970 ድምፅ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ 509 ድምፅ በማግኘት ሳይመረጡ ቀርተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የፓርቲው የኢንስፔክሽንና ሥነ ምግባር ኮሚሽን አባላት ሆነው የተመረጡት ደግሞ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ሰብሳቢ፣ ደስታ ተስፋው (ዶ/ር) ምክትል ሰብሳቢና ሁሴን አብዱላሂ (ዶ/ር) ጸሐፊ ሲሆኑ፣ በአባልት ደግሞ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፣ አቶ ቢንያም መንገሻ፣ አቶ ያሲን ሃቢብ፣ አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሄር፣ አቶ ኡኬሎ ኡማን፣  አቶ አድማሱ አወቀ፣ አቶ አብዱላኪም አ/ማሊክና አቶ ዮናስ ኬና ናቸው፡፡

ፓርቲው በጉባዔው መጨረሻ፣ ‹‹ትንንሽ ልዩነቶቻችንን በማቻቻል፣ ከጎጠኝነትና ከቡድንተኝነት አስተሳሰብና ድርጊት በመውጣት ለአገርና ለአገራዊ አንድነት ቅድሚያ መስጠት ከተቻለ በእርግጥም የበለፀገች ኢትዮጵያን በጋራ ድካም መገንባት ይቻላል፤›› የሚል የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

በተጨማሪም ብልፅግና ፓርቲ ካከናወናቸው ሥራዎችና ካመጣቸው ለውጦች ይልቅ፣ ገና ወገብ የሚያጎብጡ ዘመን ተሻጋሪ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውጤት ለማምጣት ርብርብ እያደረገ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን፣ ብልፅግና በዕውቀትና በእውነት ላይ የቆመ ፓርቲ እንደሆነ በመግለጽ፣ ፓርቲው ህልሙ ትልቅና ሰፊ እንጂ በትንንሽ ነገሮች ረክቶ የሚቀመጥ እንዳልሆነ በፕሮግራሙ በሕገ ደንቡ መጠቀሱን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ይህን ይበል እንጂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ልምድ ያላቸውና ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምሁራን እንደሚሉት፣ በብልፅግና ፓርቲ የበላይ አመራሮች መካከል የሚስተዋል የውስጥ አለመግባባት አለ፡፡ እነዚህ አለመግባባቶች አገርን ቅድሚያ ከመስጠት ባለፈ፣ በውስጣቸው የሚታየውን ሽኩቻ መፍታት ካልቻሉ ረዥም ርቀት ሊያስኬዳቸው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

ፖለቲከኛው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ወጥ ወደ ሆነ ፓርቲ ሊለወጥ ነው ሲባል ከደገፉት ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ድጋፍ ያበቃቸው ዋነኛ ምክንያትና ግምት ደግሞ በብሔር ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በትንሹም ቢሆን ወደ ማዕከል ይስበዋል የሚል ትልቅ ግምት ስለነበራቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ብልፅግና ከተመሠረተ ጀምሮ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተከሰተ ወዲህ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በፓርቲው ውስጥ ያለውን ፉክክርና ፍትጊያ ስትመለከት፣ ይጠፋል ብዬ የጠበኩት ነገር በቀላሉ ሊጠፋ አልቻለም፡፡ በተለይም ከአሰያየሙ ጀምሮ ሲታይ ከድሮው ባልተለየ ኦሮሚያ ብልፅግና፣ አማራ ብልፅግና፣ አፋር ብልፅግና እየተባለ ክፍፍል ተፈጥሯል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አቶ ኤፍሬም በተለያዩ መድረኮችና ጊዜያት በግንባር ቀደምትነት ሲናገሩ የሚደመጡት የኦሮሚያና የአማራ ብልፅግና የበላይ ኃላፊዎች ቃላት ሲወራወሩ መታየታቸውንም አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ይህ አማራ ብልፅግና ወይም ኦሮሞ ብልፅግና የሚለው ስያሜ ጠፍቶ፣ የአካባቢ ጽሕፈት ቤት በሚል ቢሰየም የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የቦታ ሰያሜዎች ከማንነት ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ቦታ እየጠሩ የፓርቲ ስም መለጠፍ፣ አሁንም በድሮም ጊዜ የነበረውን ስህተት መድገም እንደሚሆን ጠቆም አድርገዋል፡፡ በአንድ በኩል የተዋሀደ ፓርቲ በሌላ በኩል ደግሞ በክልል የተከፋፈለ ፓርቲ ከመደመጡ ባለፈ፣ አሁን በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች መካከል የሚታየው ሽኩቻና የቃላት መወራወር እንደተዋሀደ ፓርቲ ሲታይ በቀጣይ በአንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት አቋም ይኖራቸዋል ብሎ መወሰን እንደማያስችል ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ ፓርቲ ሲባል የተለያዩ ሐሳቦችን የሚያንፀባርቁ ግለሰቦች የሚገናኙበት መዋቅር ቢሆንም፣ በትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን የጋራ የሆነ አቋም ሊይዙ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹እኔ እንደ አንድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያውቅና ሒደቱን የሚከታተል ሰው፣ የሁለቱ ክልል የፓርቲ ተወካዮች በኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው ብዬ በፍፁም አላምንም፤›› ያሉት አቶ ኤፍሬም፣ ለአብነትም ‹‹ብልፅግና በአገራዊ ምክክር ሒደቱ የሚወከለው በየትኛው ሐሳብ ነው፤›› የሚለው ጉዳይ በጉባዔው ጎልቶ መውጣት እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡

ከ16 ዓመታቸው ጀምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲከታተሉ እንደቆዩ የሚናገሩት ፖለቲከኛው አቶ ኤፍሬም፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ብልፅግና እንዲፈርስ ከማይመኙ አካላት መካከል ነኝ ይላሉ፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልፅግና ፓርቲን ለመምራት በድጋሚ ሲመረጡ በብዙ ድክመቶች መካከል ሆነውም ቢሆን ደስ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ብልፅግና የሚባለው ፓርቲ ከኢሕአዴግ የወረሰው ግራ ዘመምነት አሁንም እንዳልለቀቀው የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፣ በጉባዔው የተላለፉ ውሳኔዎች በቅድመ ጉባዔ ተጨርሰው ለሚዲያ ያቀረቡት እንጂ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተስተዋለባቸው ሁነቶች እንዳልነበሩ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረክ ላይ ሆነው ራሳቸውን ያስመረጡበት ሒደት፣ እንዲያው ለሚዲያ ፍጆታ ሲባል እንኳ አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጦ ሒደቱ መመራት ነበረበት ብለዋልም፡፡ በጉባዔው የታየው በተለይም ውሳኔን ጨርሶ ወደ መድረክ ማምጣት፣ በደርግም በኢሕአዴግ ጊዜም ይታይ የነበረ አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓብይ በደንብ መርቷል ወይም አልመራም የምትሉ ሰዎች በማለት መድረክ ላይ ተቀምጠው ሲመሩት የነበረው አሠራር እኔ እውነት ለመናገር ድራማ ነው የመሰለኝ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በዓመት አንድ ጊዜ በራሳቸው ላይ የሚቀልዱበት ቀን አለና እኔም እሱ ቀን ነበር የመሰለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም እንዲህ ዓይነት የፓርቲ ጉባዔዎችና አካሄዶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ትልቅ ቢሆንም፣ ‹‹በተሠራው ድራማ አዝኛለሁ›› ብለዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተነሳው የታሪካዊ ውህደት በተመለከተ አቶ ኤፍሬም ብልፅግና ከመጀመርያ ሲዋሀድ በግልጽ ውህደቱን የፈጠሩት ፓርቲዎች፣ የሚሳሳቡና በብዙ ጉዳይ አብረው ሲሠሩ የነበሩ እንጂ የተለያየ አጀንዳ ይዘው በየራሳቸው የተመሠረቱ ፓርቲዎች ያቋቁሙት ፓርቲ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢሕአዴግ ጊዜ የነበሩ አባል ድርጅቶች ኋላ ላይ አዴፓ፣ ኦዴፓ ዓይነት ስሞች ቀይረው መጨረሻ ላይ ብልፅግናን መሠረቱት ተባለ እንጂ፣ በግልጽ ውህደት አድርገዋል የሚለውን ድምዳሜ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ነገር ግን አጋር ተብለው የታዩ የነበሩት እኩል ባይሆንም አብረው ተቀምጠው ውሳኔ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡  

በሌላ በኩል ብልፅግና ፓርቲ በተለያዩ አካላት ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የመቀየር አዝማሚያ ይታይበታል የሚሉ ሐሳቦችን አስመልክቶ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ጉደታ ከበደ፣ ‹‹መደበኛ ባልሆኑ መስመሮች ሐሳቡን ሰምተነዋል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን የማምጣት ፍላጎት ቢኖረውም ውሳኔው በፓርቲው ፍላጎት ብቻ የሚወሰን አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ይሁን ቢባል እንኳ ሕገ መንሥትን ማሻሻል የግድ ከመሆኑም በላይ፣ አሁን በየጊዜው አንዱን ተቋም አፍርሶ ሌላ ተቋም እንደ መገንባት ሒደት የፓርላሜንታዊ ሥርዓቱን አፍርሰህ በቀጥታ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የምትገባባት ቀላል ጉዳይ አይደለም፤›› ብለው፣ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ስብጥር ብሔር ብሔረሰቦች ላቀፈች አገር የፓርላሜንታዊ ሥርዓት የተሻለና ተመራጭ እንደሆነ አቶ ጉደታ አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድገትና አቅም ውስን በመሆኑና አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ እንደ አገር ተደራሽ ለመሆንና የታችኛው የመንግሥት እርከንና ሕዝቡ ድረስ ወርዶ ለመሥራት ትልቅ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ሊወዳደሩ የሚችሉ ፓርቲዎች በጣም ጠንካራ አቅም ላይ የደረሱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

   አቶ ጉደታ የፓርቲው ውህደትና ለክልሎች በፌደራል ደረጃ በሕዝብ ብዛት የተሰጠውን የፓርቲ ሥራ አስፈጻሚነት ውክልና አስመልክተው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ድሮ ከነበረው በሦስት ክልሎች በበላይነት ተይዞ የነበረውን አሠራር በመቀየር የተሻለ ተብሎ ሁሉንም እንደ አቅሙ የሚወክል ሥርዓት መፍጠር መቻሉ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን አናሳ ብሔረሰቦች ተሳትፈዋል ሲባል እኩል ተዋናይ ናቸው ተብሎ ሊወስድ እንደማይቻል የጠቀሱት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፣ ሒደቱ መነሻ እንጂ መጨረሻ ተደርጎ መደምደም እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

የኦፌኮ ሊቀመንር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በብልፅግና ጉዞ ሒደት ዋነኛ ቁልፍ የሚባሉ የነበሩት ሰዎች መጀመሪያ አቶ ለማ መገርሳ፣ አሁን ላይ ደግሞ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተገፉበት አካሄድ መኖሩን በመጠቆም፣ ታሪካዊ ውህደት ከሚባለው በላይ ፓርቲው የተሻለ ሥራ መሥራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

‹‹ፓርቲዎች ከማዋሀድና ብልፅግና ብልፅግና እያሉ ከመዘመር ባለፈ፣ በተለይ በኢሕአዴግ ዘመን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ኢትዮጵያን በቀን ሦስት ጊዜ አበላለሁ›› በማለት ሲናገሩት የነበረው፣ በተመሳሳይ አቶ በረከት ስምኦን በጻፉት መጽሐፍ ‹‹ኢትዮጵያን የአፍሪካዊ ኩራት እናደርጋለን›› የሚሉ መፈክሮች ብቻቸውን የትም እንዳላደረሱ ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ ከፉከራ ባለፈ መሬት ላይ ያለውን እውነት መለወጥ ካቃተው፣ አሁን በገባበትና በሚታየው የመገዳደር ፖለቲካ አገሪቱን የትም ማድረስ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

‹‹ፓርቲው አንዳንድ ሰዎች ሲያነሱት የምንሰማውን የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያ ካመጣ አደጋው ነው የሚታየኝ፤›› ያሉት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በአፍሪካ አኅጉር ያመጣው አደጋ ብቻም ሳይሆን፣ በፖለቲካ ሳይንስ ቋንቋ የአፍሪካ ኅብረትን ጭምር የአምባገነን መሪዎች ኅብረት (The Trade Union of Dictators) የሚል ቅጥያ እንደሰጠው አመላክተዋል፡፡

በርካታ የአፍሪካ አገሮች የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት እንደሚከተሉ የጠቀሱት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ኅበረቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችን መብት ይጠብቃል፣ ብዙ ለውጥ ያመጣል፤›› በሚል ታስቦ የተመሠረተውና አደገኛ ወደሆነ የመሪዎች ኅብረት የተቀየረው ‹‹በርካታ የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በሚከተሉ መሪዎች ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ሰፊና በርካታ ብሔረሰቦች ያሉበት አገር የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ተመራጭነቱ አጠያያቂ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹በፓርላሜንታዊ ሥርዓት አሁን አገሪቱ የገባችበትን ችግርና ያሉትን በርካታ ጣጣዎች እስኪፈቱ ድረስ፣ ብልፅግናዎችን ከወዲሁ አደራ የምለው እዚያ ጨዋታ ውስጥ ከታችሁን የበለጠ ችግር እንዳታመጡብን፤›› ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -