Saturday, March 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት በነዳጅ ድጎማ ውሳኔ አተገባበር ላይ ቅሬታ አነሱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግሥት ማኅበራቱ ያነሱት ሐሳብ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን አስታውቋል

መንግሥት በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ሊያነሳ ስላሰበው የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ገለጻ የተደረገላቸው፣ የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት፣ ‹‹የነዳጅ ድጎማና የታሪፍ አተገባበር ለጉዳት የሚዳርገን ነው›› ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

የትራንስፖርት ማኅበራቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መንግሥት በሒደት የነዳጅ ድጎማን ለማስቀረት የወሰነው ውሳኔ አተገባበር ላይ ከማኅበራቱ ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት እንደሚገልጹት፣ የነዳጅ ድጎማ አነሳሱ ‹‹ልዩ›› በሚባሉትና በመደበኛ የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪዎች መካከል የተለያየ መሆኑ አላስደሰታቸውም፡፡ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ ያሉባቸውን ሌሎች ወጪዎች ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ልዩ›› የሚባሉት የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እንደ ዓባይ፣ ዘመን፣ ግዮንና ሌሎች ያሉ ዘመናዊ ባስ የሚጠቀሙ አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፡፡ በአዲሱ የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ አነሳስ ውሳኔ መሠረት፣ እነዚህ ልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. አንስቶ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ አገልግሎት የሚሰጡበትን ዋጋ በተመለከተም ከዚህ ቀደም በመንግሥት ታሪፍ የማይወጣላቸው በመሆኑ በዚሁ ይቀጥላሉ፡፡

እንደ አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ያሉ መደበኛ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪዎች፣ በአንፃሩ የሚደረግላቸው ድጎማ ከሐምሌ ወር አንስቶ ቀስ በቀስ ይነሳና በአምስተኛው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይቀራል፡፡ ይሁንና እነዚህ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አሁንም እንደሚደረገው በመንግሥት ታሪፍ እየተቀመጠላቸው አገልግሎት መስጠት ይቀጥላሉ፡፡

ማኅበራቱ አሁን ያነሱት ቅሬታ ታሪፍን በተመለከተ ልዩ ከሚባሉት አገልግሎት ሰጪች ጋር መለያየታቸውን የተመለከተ ነው፡፡ ማኅበራቱ መንግሥት የሚያደርግላቸው ድጎማ ተጠቃሚ ሳይሆኑ፣ መንግሥት የሚያስቀምጥባቸው የታሪፍ ተመን እንዲቀር ይፈልጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የህዳሴ አገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንሰፖርት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኔ ዘሩ፣ ውሳኔው የትራንስፖርት አግልገሎት ሰጪዎች ከነዳጅ ሌላ ያሉባቸውን ወጪዎች ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ የመለዋወጫ ዕቃዎች ግዢና አስተዳደራዊ ወጪዎች ላይ የዋጋ ንረት እንደሚያጋጥማቸው የገለጹት ሰብሳቢው፣ መንግሥት አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ሰዎችን እንደሌሎቹ የዋጋ ንረት የሚነካቸው የኅብረሰተብ ክፍሎች እንዳልተመለከታቸው አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ የታሪፍ ተመን በመንግሥት የሚወጣላቸው በመሆኑም፣ ከነዳጅ ውጪ ባሉ ወጪዎች ላይ የሚከሰቱ የዋጋ ንረቶችን ለመቋቋም አገልግሎት የሚሰጡበትን ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ አብራርተዋል፡፡ አስተዳደራዊና የዕቃዎች ግዢ ወጪዎች ላይ ዋጋ የሚጨምረው ያለምንም ልዩነት መደበኛና ልዩ ትራንስፖርት ሰጪዎች ላይ ሆኖ ሳለ፣ ልዩ በተባሉት መኪናዎች አገልግሎት የሚሰጡት ግን እንደዚህ ዓይነት ማስተካከያ የማድረግ ዕድል እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የዓለም አገር አቋራጭ አንደኛ የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ገንዘብ አስማማውም ማኅበራቸው በዚህ በቀረበው የቅሬታ ሐሳብ ላይ እንደሚስማማ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ መንግሥት አገልግሎት ሰጪዎቹን በነዳጅ ከሚደጉም ቀጥታ ሕዝቡን ቢደጉም የአገልግሎት ዋጋ ቢጨመርም ሕዝቡ መክፈል ይችላል፡፡

መንግሥት እንደ መከላከያ ሠራዊትን ማጓጓዝ ያሉ ልዩ ሥራዎችን እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት አቶ ገንዘብ፣ በዚህን ጊዜ ተጠቃሚዎች ልዩ በተባሉት መኪናዎች እንደሚጓዙና በዚህም ነዋሪዎች ከዋጋ ጭማሪው እንደማያመልጡ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማኅበራቱ የነዳጅ ድጎማ ውሳኔ አተገባበር አስመልክቶ የተሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መሆኑን በመጥቀስ፣ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ሐሳባቸውን ሊጠየቁ ይገባ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ሪፖርተር የማኅበራቱን ቅሬታ አስመልክቶ ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ኃላፊ ‹‹ታሪፍ ይነሳልን የሚል ጥያቄ በምንም መንገድ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ‹ነዳጅ ያለድጎማ እንግዛ ታሪፍ› ይነሳ የሚባለው የትራንስፖርት ዋጋን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እንደሆነ ሁላችንም ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡

ድጎማ የሚደረገው ሕዝቡን ለመጥቀም እንጂ ለአገልግሎት ሰጪዎቹ ተብሎ አለመሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ድጎማን በማንሳት አገልግሎት ሰጪዎቹ ዋጋ እንዲያወጡ ማድረግ ለሕዝቡም አለማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ልዩ የተባሉትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በተመለከተም ‹‹ልዩዎቹ ድሮም የቅንጦት አገልግሎት ስለሆኑ ድጎማ ሰጥተህ በታሪፍ ሥራ ማለት አይቻልም፣ የቁጥጥር ሥርዓት ግን ይኖራቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቁጥጥሩና ድጎማው እንዴት አብሮ ይሂድ የሚለው ነው እያሳሰበን ያለው›› ያሉት ኃላፊው፣ ድጎማው በአምስት ዓመት ውስጥ የሚነሳበት ዝርዝር ዕቅድ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አገር አቋራጭ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች፣ ኮድ አንድ ኮድ ሦስት ታክሲዎች እንዲሁም ባጃጆች ‹‹በምን መልኩ ይደጎሙ›› የሚለው በቀጣይ እንደሚወሰን አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች