Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየዓድዋ ድል ማክበሪያ ቦታን ለመቀየር የተደረገው ሙከራ ለአገራዊ ምክክሩ እንቅፋት እንዳይሆን ማሳሰቢያ...

የዓድዋ ድል ማክበሪያ ቦታን ለመቀየር የተደረገው ሙከራ ለአገራዊ ምክክሩ እንቅፋት እንዳይሆን ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

ሰሞኑን የታየው የዓድዋ ድል በዓልን ለዘመናት ሲከበርበት ከነበረው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር የማድረግ ፍላጎት፣ በቅርቡ ሊደረግ ለታሰበው የአገራዊ ምክክር ሒደት አፍራሽ እንዳይሆን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አሳሰቡ፡፡ ዘግይቶም ቢሆን በዓሉ በተለመደው ሥፍራ እንደሚከበር ቢገለጽም፣ በብዙዎች ዘንድም ቁጣ ቀስቅሶ ነበር፡፡

በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን በድምቀት የሚከበረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ እየተከበረ እዚህ የደረሰ ቢሆንም፣ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተጽፎ የወጣ ደብዳቤ፣ ክብረ በዓሉ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድልድይ ተዛውሮ እንደሚከበር በመግለጽ ለሚዲያዎች ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ፣ የቦታ ለውጥ የማድረግ ውሳኔው በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በበርካታ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ የቀረበበት ይህ ውሳኔ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ከፍተኛ ኃላፊዎችና በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጭምር ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ፣ የዓድዋ ድል በዓልን ሲከበርበት ከኖረው ዋነኛ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመቀየር የሚደረገው ሙከራ ከታሪክ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው ብለዋል፡፡

አንድ የታሪክ ቅርስ መጠበቅ ያለበት በመጀመርያ ቦታው ላይ መሆን ሲገባው የፖለቲካ ሥርዓትና ፍልስፍና በተቀያየረ ቁጥር በካድሬዎችና በፖለቲከኞች ፍላጎት መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ አቶ አበበ አክለው ተናግረዋል፡፡

ከዓድዋ በላይ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ጉዳይ እንደሌለ የገለጹት አቶ አበበ፣ የዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ምልክትና የድል ነፀብራቅ የሆነው ታሪክ ተረስቶ በማክበሪያ ቦታ ላይ መጨቃጨቅ ትውልዱ ሊያፍርበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹የእኛ አያቶች የሕይወት ዋጋ ከፍለው በቦታው ተገኝተው በመዋጋት ታላቅ ድል አስረክበውን እኛ ባልተዋጋንበት፣ ባልደማንበትና ባልቆሰልንበት ዛሬ በተፈጠረ የፖለቲካ መስመር ልዩነት እንዲህ ዓይነት ውዝግብ ማጋጠም አልነበረበትም፤›› ብለዋል››፡፡

አቶ አበበ ሁሉም ነገር የሚያምረው በቦታው ላይ ሲሆን እንደሆነ አስረድተው፣ መንግሥት የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ቆም ብሎ እንዲያስብ በመጠየቅ፣ አካሄዱ ካልተስተካከለ ችግሩ ለተያዘው አገራዊ ምክክር ሳንካ ይሆናል ብለዋል፡፡

የአክሱም ሐውልት ከጣሊያን ሲመለስ ቀድሞ በነበረበት ቦታ መተከሉ የራሱ የሆነ ምክንያት እንዳለው ሁሉ፣ የዓድዋ በዓልም በቦታው እንዲከበር የጠየቁት አቶ አበበ፣ ‹‹ከፊታችን ለታሰበው አገራዊ ምክክር ለምን እሾህና አሜኬላ እንተክላለን?›› ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሕዝቡ ሥነ ልቦና ጋር የተገናኙ ሁኔታዎችን ነቅሎ ለማውጣት መሞከር መግባባት እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ማጨለም እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ገዥው የብልፅግና ፓርቲ ካለፉት የኢሕአዴግ ዘመን የተለየ አይደለም፣ አገር የማፍረስና ታሪክን ማጥፋት ነው የተያያዘው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የዓድዋ ድል በዓል በዳግማዊ አፄ ሚኒልክ አደባባይ ላይ እንዳይከበር መሞከር ማለት፣ ታሪካዊ የሆነውን የበዓሉን ዳራ የማጥፋት ዓላማ ያዘለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ፓርቲያችን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሕዝብን የማደንዘዝ ስትራቴጂ እንደሆነ ቢያምንም፣ የዓድዋ ድልን ያለ ቦታው ለማክበር መሞከር ሊፈጥር የሚችለው አንድምታ መንግሥት ያሰበውን የምክክር ሒደት በተገላቢጦሽ የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ አቶ ደመወዝ ካሴ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የሚከበርበትን ቦታ ለመቀየር የተሄደበት እንቅስቃሴ የፖለቲካ አቋም ተይዞ የታሰበ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በዓሉን በተሻለ አከባበርና ድምቀት በማስፋትና ውበት በመስጠት፣ ‹‹የአፍሪካ አገሮች እንዲያከብሩትና እንዲመኩበት የሚያደርግ ሥራ ማከናወን ሲገባን፣ የሚያሳፍር ተግባር ላይ መሰማራት አልነበረብንም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ድርጊቱ ሕዝብን የሚለያይ፣ ለምክክር ሒደቱ አፍራሽ ምልክት ነው ካሉ በኋላ፣ በታሪክ ረገድ ምንም ዓይነት ችግሮች ቢኖሩም እንኳ ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ሲገባቸው፣ የፖለቲካ መሪዎች የጉዳዩ ፈትፋች መሆን ስህተት ውስጥ የሚያስገባና ቁርሾ የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ውሰኔው ላይ ተቃውሞ ካሰሙ የመንግሥት ኃላፊዎች ውስጥ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሑፍ፣ ‹‹የታሪካዊው ዓድዋ በዓል ማክበሪያ ቦታ መቀየር በዓሉ እንዳይከበር አዋጅ እንደ ማውጣትና እንደ መሰረዝ ይቆጠራል፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የማክበሪያ ቦታው መቀየር በዓሉን ለመታደም ለሚመጡ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ቱሪስቶች ላይ ውዥንብር እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ 126ኛው ዓመት የዓድዋ ድል በዓል ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድልድይ እንደሚቀየር የሚገልጽ ደብዳቤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከወጣ በኋላ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት መምህሩ ነብዩ ባዬ (ረዳት ፐሮፌሰር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ፣ በሕግ ተደነግጎ የኖረውን፣ ብሎም ድሉ በብሔራዊ ደረጃ መከበር ከጀመረበት ከዓድዋ ድል ሰባተኛ ዓመት ጀምሮ ላለፉት 119 ዓመታት የተከበረበትን የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ፣ ከመከበሪያ ሥፍራነት ለመቀየር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የጥሪ ወረቀት መሞከሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከብሔራዊ የመከበሪያ ሥፍራ በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት እንዲከበር በታላቅ ድካም የዓድዋ በዓል እንዲያንሰራራ የተደረገውን ጥረት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የሚደረገውን ተጋድሎ የጥርጣሬ ንፋስ በማንፈስ ለማዳከም ይሞክራል፤›› በማለት ገልጸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎችን በባህል አመራር ረገድ፣ ‹‹መንግሥት ናችሁና ሕግን፣ ታሪክን፣ ልማድን አክብሩ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበባትና ቱሪዝም ቢሮ በየዓመቱ በዕቅዱ አካቶ፣ ኃላፊነት ወስዶና በጀት መድቦ የሚያከብረው በዓል በተለመደው መንገድ እንዲከበር በመጠየቅ፣ ‹‹ያ ካልሆነ ግን በሕዝብ ተወካይነታችን በአፈጻጸሙ በምክር ቤት ተጠያቂ እናደርገዋለን፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሥፍራና ጊዜ የሳይንስና የፍልስፍና አስኳል ብቻ ሳይሆን፣ የማንነትና የምንነት ገመድም ጭምር ነው። ዓድዋ አገር ነው። ዓድዋ ማንነት ነው። ዓድዋ ነፃነት ነው። ዓድዋ እኩልነት ነው። ዓድዋ ወንድማዊነት ነው። ዓድዋ እህታዊነት ነው። ዓድዋ ትዕምርት ነው። ያውም የሰውነት። መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ አኑሩት እንደተባለው ዓድዋን በዓድዋ ሥፍራ፤›› በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ለበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ፣ ‹‹በዓሉ እንደ ቀድሞው ሁሉ ላለፉት 125 ዓመታት ይከበርበት በነበረው በገናናው ጀግና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ፣ በኢትዮጵያ ውድ ልጆች በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፣ ለዚህም አንዳች ጥርጥር የለውም፤›› ብሏል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበርና የባህል ትራንስፖር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የሚመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከበርካታ ተቃውሞዎችና የሐሳብ ምልልሶች በኋላ፣ በዓሉ በተለመደው የዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ እንደሚከበር ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳ ዘግይቶም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በዓሉ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ እንደሚከበር ቢያስታውቅም፣ ከሁለት ቀናት በፊት ለሚዲያዎች በተላከው መጥሪያ በዓሉ በዓድዋ ድል እንደማይከበር ተገልጾ የነበረውን በማስተባበል ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ጠቁመው በዓሉ በተለመደው ሥፍራ ይከበራል ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...