Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥት ይዞታዎች ላይ 15 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት የአልሚዎች ፍላጎት እየተጠና ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዋጅ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረውና በ15 ሠራተኞች ብቻ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ተቋማት በሚገኙ ይዞታዎች ላይ 15 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችለውን የአልሚዎች ፍላጎት እያጠና መሆኑን አስታወቀ፡፡

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሌንሳ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘርፉ ለመሰማራት አቅም ያላቸው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የቤት አልሚዎች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በሽርክና ቤቶችን ለመገንባት የአልሚዎችና  ገበያው ውስጥ ያለውን ፍላጎት እየተጠና ነው፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት በወጣው የፍላጎት መግለጫ መሠረት፣ በጥሩ የፋይናንስ አቅምና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመታገዝ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመሆን አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው አልሚዎች ከመጡ፣ በቅርቡ ወደ ሥራ በመግባት ቤቶቹ ተገንብተው ለገበያ እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡

ኮረፖሬሽኑ ባደረገው ጥናት መሠረት ቤቶችን ለመገንባት አስቻይ አቅም እንዳለ ቢታወቅም፣ የአልሚዎችን ፍላጎት መለየት አስፈላጊ በመሆኑ ለቀጣይ አንድ ወር በሚቆየው የፍላጎት መግለጫ የሚቀርቡ ቤት ገንቢዎች ሁኔታ ታይቶ እንደሚወሰን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

ከታሰበው የቤት ግንባታ በተጨማሪ የስብሰባ ማዕከልና የፈረስ ግልቢያ ሜዳ ለመገንባት የአልሚዎችን ፍላጎት ለማወቅ የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቶ፣ በዘርፉ ለመሰማራትና ከኮርፖሬሽኑ ጋር ለመሥራት ፍላጎት የሚያሳዩ አካላትን ለማወቅ ይፋ መደረጉንም ወ/ሪት ሌንሳ አክለው አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ከ4.6 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ይዞታ ሥር እንዳለ ቢታወቅም፣ ኮርፖሬሽኑ አለ ተብሎ የሚታሰበውን መሬት በማጣራት የመመዝገብ ሥራ ተጀምሯል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ተቋማት ሥር የሚገኙ ይዞታዎችን በማጣራት  ያለውን ሀብት በአንድ የመሬት መረጃ ቋት በማድረግ፣ ማንኛውም አካል እየገባ ማየት የሚችልበት የመሬት ዳይሬክቶሬት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በዕቅድ ላይ እንዳለ የገለጹት ወ/ሪት ሌንሳ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አሉ ብለዋል፡፡ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው ሁለት አልሚዎች ደግሞ በአሥር ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ሀብት አውጥተው የአዋጭነት ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን፣ ጥናታቸውን እንደጨረሱም የኩባንያዎች ማንነትና የሚሰማሩበት ዘርፍ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ እ.ኤ.አ. 2022 መጨረሻ አካባቢ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የዘርፉ ባላሙያዎችን ያካተተ ‹ኢንቨስት ኦሪጅን› የሚል ዓለም አቀፍ የመሬት ፎረም ለማዘጋጀት ቅደመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ወ/ሮ ሌንሳ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ከተቀላቀለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር አብረው ለመሥራት በመስማማት፣ በጋራ እንዴት ሊሠማሩ የሚችሉባቸው ዘርፎች ላይ እየተነጋገሩ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት ሥር ያሉ ተቋማትን የማልማትና የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቆዳ ስፋት 5.48 በመቶ ሽፋን ያላቸውን የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ይዞታዎች ባሉበት ሊያለማ መሆኑን በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም ‹ሸገርን ማልማት› በሚል ዕቅድ ከቦሌ ጫፍ እስከ ሽሮሜዳና ከግዮን ሆቴል እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሉ ሁለት መስመሮች በሚገኙ የመንግሥት ይዞታዎች ላይ፣ ውብ የከተማ ላይ ፕሮጀክቶች ለመገንባት የሚያሰችል ተመራጭ የዲዛይን ንድፈ ሐሳብ ሊያመጡ የሚችሉ በ11 ቡድን የተዋቀሩ ተወዳዳሪዎች ተለይተው፣ እስኪያጠናቅቁ እየተጠበቀ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ይዞታዎችን ለከተማ ውበት ጥቅም ላይ ለማዋል በታቀደበት ውድድር፣ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል የተሻለው የዲዛይን ንድፈ ሐሳብ በኤግዚቢሽን መልክ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ከተመረጠ በኋላ፣ ለታሰቡት ሁለት መስመሮች ይመጥናሉ የተባሉት ዲዛይኖች ወደ ፕሮጀክትነት ተቀይረው ወደ ሥራ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ተቋማት የተያዙ የመሬት ይዞታዎችን የመለየትና የመመዝገብ፣ የባለቤትነት ይዞታቸውን ማረጋገጥና በይዞታዎቹ ላይ ተገቢ የሆኑ ልማቶች እንዲለሙበት የማድረግ ኃላፊነት ተስጥቶት በአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች