Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች የግብርናውን ዘርፍ እንዲደግፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች ግብርናውንፋይናንስ ድጋፍ የሚደረጉበት መንገድ እንዲቀይሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓርብ አመሻሹን በማኅበራዊ ሚዲያ ባወጡት መግለጫ ባንኮች ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የቆጠበውን ገንዘብ በመጠቀም የአገልግሎትና የግንባታውን ዘርፍን ፋይናንስ በማድረግ ለውጥ ማምጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከምርጥ ዘር፣ የግብርና ግብዓትና መሣሪያዎች አቅርቦት ጋር በተገናኘ መሥራት ለሚፈልጉ አካላትና በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮችም ሆኑ፣ በሰፋፊ የመስኖ ግብርና ላይ የሚሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች፣ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን መንግሥት እንደሚያዘጋጅና በተለያዩ መንገዶች እንደሚያበረታታ አመላክተዋል፡፡

ከሰሞኑ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ የሶማሌና የቦረና አርብቶ አደሮችን በመጥቀስ በመኖና የውኃ ዕጦት ከብቶቻቸው እየረገፉ በመሆኑ አፋጣኝ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

በየአሥር ዓመቱ እየተመላለሰ ኢትዮጵያን የሚጎበኘው ድርቅና ረሃብ አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተናት ያለ ጠላት መሆኑን፣ ለበርካታ ዜጎች ሞት ምክንያት ስለመሆኑ፣ በምግብ ራስን ባለመቻል ችግር ሕፃናትን ለመቀንጨር፣ ወጣቶችን ለስደት፣ አረጋውያንን ለጉስቁልና፣ የቀንድና ጋማ እንስሳት ለዕልቂት መዳረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ረሃብ የአገሪቱ ምሥል ላይ ጥቁር ነጥብ በማስቀመጡ፣ በምግብ ራስን ባለመቻላችን ምክንያት ብሔራዊ ህልውናችን ጥላ አጥልቶበት መታየቱ ሊቆጨን ይገባል፤›› ብለዋል።

አክለውም ግብርና ምርቶች ላይ እየታየ ያለው ድክመት በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊም፣ በፖለቲካውም፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ‹‹ለግብርና ተስማሚ ለም መሬትና ወንዞች ኖረውን የዕርዳታ በሮችን የምናንኳኳው፣ ታሪክ ኖሮን ጎልተን የማንታየው፣ ዕምቅ የዲፕሎማሲ አቅም እያለን በዓለም መድረኮች የማንደመጠው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጊዜ እየጠበቀ በሚጎበኘን ድርቅና ረሃብ ምክንያት ነው›› ብለዋል።

ድርቁ ያስከተለው ረሃብ የሕፃናቱንና የአረጋውያኑን ሕይወት እያሳጣ በመሆኑ ለነዚህ ዜጎች ክረምቱ እስኪደርስ እንጠብቅ ከተባለ፣ ብዙ ወገኖች ስለሚሞቱ  ለድርቅና ረሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በመረባረብ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖች፣ ሁሉም ዜጋ አቅም የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች