Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለአገራዊ ምክክር አመቻችነት የተሾሙ ኮሚሽነሮች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

ለአገራዊ ምክክር አመቻችነት የተሾሙ ኮሚሽነሮች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

ከታኅሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ በነበረው አገራዊ ምክክር አመቻች ኮሚሽነሮች ጥቆማ ከ642 ተጠቋሚ ግለሰቦች መካከል ተመርጠው የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የተሾሙት 11 ኮሚሽነሮች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ፡፡

  ሹመታቸው በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ አገሪቱ ሰላም እንደተራበችና መፍትሔ እንደሚያሻት በመግለጽ፣ ለዚህም ዋናው መፍትሔ መግባባት በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከጎናችን ይሁኑ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሒሩት ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው፣ ‹‹የዚህች አገር ችግር የሕዝብ ችግር አይደለም፣  ሕዝቡ በሰላም መኖር ነው የሚፈልገው፣ ተምሬአለሁና ትልቅ ቦታ ደርሻለሁ የሚለው ችግር ፈጣሪ በመሆኑ ለዚህ ማኅበረሰብ በደንብ እንሠራለን፣ ጥሪም እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው የኮሚሽኑ አባል መሐመድ ድሪር (አምባሳደር)፣‹‹ትልቅ ሸክም ትከሻዬ ላይ እንደተጫነኝ ነው የሚሰማኝ፣ በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን የማይቻል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም አገራችን ሰላም ያስፈልጋታል፣ ስንነሳ የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳምጠን እንነሳለን፤›› ብለዋል፡፡

ከታኅሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ በነበረው የአገራዊ ምክክር አመቻች ኮሚሽነሮች ጥቆማ በሕዝብ ከተጠቆሙ አጠቃላይ 642 ግለሰቦች መካከል፣ ፓርላማው የሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል ይወክላሉ ያላቸውን 11 ኮሚሽነሮች ሹመት በአምስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ከተሾሙት ውስጥ ስምንት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ሲሆኑ  መስፍን  አርዓያ (ፕሮፌሰር)  የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣  ወ/ሮ  ሒሩት  ገብረ ሥላሴ   ምክትል  ሰብሳቢ፣ እንዲሁም   በአባልነት  ተገኘ ወርቅ  ጌጡ (ዶ/ር)፣  አምባሳደር  አይሮሪት  መሐመድ (ዶ/ር)፣  ወ/ሮ  ብሌን  ገብረ መድኅን፣  ዮናስ  አዳዬ (ዶ/ር)፣ አቶ  ዘገየ  አስፋው፣ አቶ  መላኩ  ወልደ ማሪያም፣   መሐሙድ  ድሪር (አምባሳደር)፣ አቶ  ሙሉጌታ  አጎ  እና  አምባዬ  ኦጋቶ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመሩትና ጥቆማ ሲቀበል የነበረው የፓርላማ ጽሕፈት ቤት፣ ከተጠቆሙት 642 ግለሰቦች መካከል ለኮሚሽነርነት ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን የ42 ዕጩዎች ስም ከሁለት ሳምንታት በፊት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በሕዝብ ጥቆማ የተመለመሉት ግለሶቦች ስም ይፋ በተደረገ ማግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ እስከ ኮሚሽነሮች ጥቆማ አሰጣጥና አለያየት ሒደት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና ሚና ትኩረት አለመሰጠቱን ገልጾ ነበር፡፡ በዚህም በቀጣይ በሒደቱ ሊሳቱፉ እንደማይችሉ የጠቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ሥጋታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ የካቲት 14 ቀን 2014 .ም. ባካሄደው  ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባ 11 አባላት ያሉትን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ሹመት ከተገኙት 335 የምክር ቤት አባላት መካከል በአምስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን፣ ለኮሚሽነርነት በሕዝብ ከተጠቆሙት መካከል 100 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቀጣይ  በሚደረገው አገራዊ ምክክር አወያይ ሊሆኑ እንደሚችሉ በውሳኔ ሐሳቡ ተቀምጧል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ በምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ የተመረጡት ኮሚሽነሮች ሊካሄድ በታሰበው በእያንዳንዱ መድረክ  ሒደቱን እየተከታተሉ በሙያ፣ በሽምግልና፣አገር ውስጥ ባላቸው ልምድና በሰብዕናቸው ከፍ ያሉ፣ ሁሉንም እምነቶችና ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልይን ዓይቶ ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽነሮቹ በዓለም አቀፍ መድረክም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ልምዶችን በመጠቀም ሒደቱን በብቃት አስተባብረው ለመጨረሻ ውሳኔ የሚረዳ ሐሳብ ለውሳኔ ሰጪ አካል እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሹመቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የከሸፈው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ምሥረታ ሕዝብ እንዲቃወመው›› በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ፓርቲው ሰኞ አመሻሹን ባወጣው መግለጫ፣ በገዥው ፓርቲ ብልፅግና የተመረጡት ኮሚሽነሮች ግልጽ በሆኑ የመምረጫ መሥፈርቶች ሳይሆን፣ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ዕጩዎችን መርጦ እንዲሾሙ ማድረጉንና ሕዝቡ ሹመቱን እንዲቃወም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...