Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንቷ ለምክር ቤቶቹ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ...

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንቷ ለምክር ቤቶቹ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአምስት ወራት በፊት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርና የእሳቸውንም ምላሽ በሚፈልጉ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማክሰኞ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 356 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባለት በተገኙበት፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተመረጡ 20 የምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የመንግሥት አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ያሏቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የመንግሥትን አቅጣጫና አካሄድ በአምስት ከፍለው  ያስቀመጡ ሲሆን፣ በዚህም የመጀመርያው ጉዳይ መከላከል በሚል የተቀመጠ ነው፡፡ ይህም በሁሉም ዘርፍ መከላከል ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር፣ ሉዓለዊነትን ለመከላከልና ሰላምን ለማስጠበቅ ያለመ ነው፡፡  ውይይትና ንግግር በሚል ያስቀመጡት ሁለተኛው ጉዳይ ሲሆን፣  በዚህ ረገድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሕዝብ ወይም ከሌሎች አገሮች ጋር መወያየትን የተመለከተ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የመንግሥት አቅጣጫና አካሄድ ዴሞክራሲ ሲሆን፣ ይህንንም ጉዳይ የኢትዮጵያ የመጨረሻው ዋስትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ በመሆኑ፣ አሁን በሁሉም መስክ የተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት በአግባቡ ከተሠራበት  የኢትዮጵያን ችግር ግማሹን ይፈታል ብለዋል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ልማትና ብልፅግናን ለማምጣት በትኩረት እንደሚሠራ የገለጹ ሲሆን፣ በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ ያስቀመጡት ዲፕሎማሲን ነው፡፡ ለዲፕሎማሲ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና ከሌሎች አገሮች ጋር በመነጋገር በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የተሻለ ነገር ለማምጣት ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የእስረኞችን መፈታት አስመልክተው ጥያቄ ያቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ መንግሥት በእነ አቶ ስብሃት ነጋ ላይ መሥርቶት የነበረውን ክስ ያቋረጠው ከሕግ አግባብና ሕገ መንግሥቱን በሚጣረስ መንገድ በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት በማለት ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ‹‹ጠላቶቻችን በቀየሱልን መንገድ መጓዝ አሸናፊ አያደርገንም፣ በመሆኑም እኛ ለድል የሚያበቃንን መንገድ መቀየስ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ከእስር የተፈቱ ሰዎችን አስመልክተው ምክንያቱን ሲናገሩ በዋነኘነት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ የታሳሪዎችን ሁኔታ ከግምት በማስገባትና የተገኘውን ድል ለማፅናት ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጦርነት አደገኛ ነገር በመሆኑ ከዓለም ልድም ከራሳችንም ተምረናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግጭት በየጊዜው የሰው ሕይወትን እየቀጠፈ፣ ሀብትና ንብረት እያወደመ የሄደ መሆኑን ለአብነትም የቀደመውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት አውስተዋል፡፡

የእስረኞቹ መፈታት ለኢትዮጵያ ጥቅም መሆኑን ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ጥቅሙን እዚህ ቦታ ዘርዝሬ የማልችለውና የማልፈልገው ጉዳይ ቢሆንም፣ እነዚህ ሰዎች በመፈታታቸው በጣም፣ በጣም፣ በጣም፣ ከምትገምቱት በላይ አገሪቱ ተጠቃሚ ናት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በግል ጉቦ ተቀብለን አለቀቅናቸውም፣ እንደዚያ ካደረግን ጥፋት ነው፣ ጓደኞቻችን ወይም ዘመዶቻችን ስለሆኑ አላደረግነውም፣ ያደረግነው ለኢትዮጵያ ጥቅም ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጥቅሙን በተግባር ዓይተነዋል፣ ስለዚህ የሚጠቅም ነገር ሲኖር ምክንያታዊ መሆን ቢወደድ ጥሩ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹የምንሞተውም፣ የምንፈታውም፣ የምንነጋገረውም ለአገር ነው፤››  በማለት ለአባላቱ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም አገርን የማያስነካ ጉዳይ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች ሲወሰዱ በክፉ ባይታይ ጥሩ እንደሚሆን አክለው ገልጸዋል፡፡

ከሕወሓት ጋር ስለሚደረገው ድርድር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ እስካሁን የተደረገ ድርድር ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን አልተደረገም ማለት ከእነአካቴው ድርድር የሚባል ነገር አይኖርም ማለት አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹ድርድርና ውይይት ማለት ችግር ተወግዷል አለመሆኑን፣ ነገር ግን ችግርም ለማስወገድ አማራጭ መንገድ አለ ብሎ ማየት ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በድርድር፣ በንትርክም ሆነ በውጊያ ዋጋ የሚከፈለው ኢትዮጵያን ለማፅናት ከሆነና ኢትዮጵያን ለማፅናት ሕይወትና ገንዘብ የሚገበር ከሆነ፣ ኢትዮጵያን ለማፅናት ስሜትን አምቆ መነጋገር ከተቻለ ጉዳዩን በደስታ ማየት ጥሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ በውጊያ ጊዜ የነበረንን አቋም ለዚህ ምክር ቤት መግለጽ አይጠበቅብኝም፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በምንም የማንደራደር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የምናደርገው የዚያ ተገላቢጦሽ ተደርጎ መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ድርድር የሚባል ነገር ከመጣና የሰላም አማራጭ ካለ፣ ሕወሓት ቀልብ ከገዛ፣ በጦርነት እንደማያዋጣውና እንደማያሸንፍ ከተገነዘበ ይህንን በደስታ እንደሚያዩት አብራርተዋል፡፡ 

‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የገዛ ቂማችን አጉብጦን ለመጓዝ ምርኩዝ የምንጠይቅ ከሆነ መገንዘብ ያለብን ነገር፣ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ምርኩዝ ሳይሆን ጉድጓድ እየቆፈሩ የሚቀብሩን ናቸው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቂምና በጥላቻ ምክንያት አገሪቱ የምትጠፋበት መንገድ እንዳይሠራ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል እየተቋቋመ ያለውን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስመልክተው፣  ኮሚሽኑን የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የምክር ቤት አባላቱ በቀላሉ ሊያዩት እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን ዕድል እንዳያባክኑት በመጠየቅ ከባከነ ሌላ ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ፣ አጋጣሚውን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኮሚሽነሮቹ ሥራ ሁሉንም ማኅበረሰብ ለማወያየት መደላድል መፍጠር መሆኑን በመጠቆም፣ ምንም የተለየ ሥልጣን እንደሌላቸው የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁሉም አካል ሐሳብ ያነሳል እንጂ ብልፅግና እንደዚህ አደረገ ወይም አብን እንደዚህ አደረገ የሚለው ንትርክ ዋጋ እንደሌለው በመጠቆም፣ ሕዝቡ ካልተግባባ በሕዝበውሳኔ የሚወስነው በመሆኑ ምርጫ ቦርድም ሆነ ፓርላማው ወደ ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግን ጉዞ በቅርበት መምራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

አገራዊ የውይይቱ ሒደት ግልጽ፣ ሁሉን አካታችና ሕዝብን የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመሠረታዊነት ያስፈለገበት ምክንያት በዋነኛነት አገራዊ  የፖለቲካ ቀውስ ወይም ሽኩቻ ሲኖር በመሆኑ፣ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለ ጉዳይ ስለሆነ፣ ውይይት ከጦርነት በኋላ አስፈላጊ በመሆኑና የፖለቲካ ሽግግር አስፈላጊ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያውያን የሚጨቃጨቁበትን አጀንዳ በውይይት መግደል አለባቸው ብለዋል፡፡

የሕወሓት ጉዞ ተመልሶ ድንጋይ ላይ ውኃ መጨመር እንዳይሆን ተጨማሪ ስህተት ባይሠራ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵን የወከሉ የምክር ቤት አባላት በፓርላማው ጥያቄ ሲያቀርቡ የትግራይ ሕዝብንም ጉዳይ እንደ ሕዝብ ተወካይ ሆነው አብረው  እንዲጠይቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በአሸባሪነት የተሰየመውን ኦነግ ሸኔን በተመለከተ፣ ግልጽ ዓላማ የሌለው፣ መሪ የሌለው፣ ከምን ዓይነት ሁኔታ እንደተፈጠረ የማይታወቅና ግራ የሚያጋባ  ስብስብ  እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሸኔ የተጻፈ ነገር እንደሌለው በመጥቀስ፣ ሕዝቡ ለምን እንደ ተሸከመው ሕዝቡን ማድመጥና ማወቅ፣ እንዲሁም ማረም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዲፕሎማሲና ከውጭ ግንኙነት ጋር ያለውን ሁኔታና በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያለውን ሒደት ሲያብራሩ፣ ‹‹አሜሪካ ወዳጅ አገር በመሆኗ ለጋራ ጥቅም በጋራ እንሠራለን፤›› በማለት በአጭሩ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ የተደረገውን የአምባሳደሮች ሹመት በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹በዋናነት የፖለቲካ አመራሩ የእኔን ፖሊሲና ጉዳይ እንደ እኔ በመሆን ይሠራልኛል ወይም ይነግረኛል የሚለውን ሰው የሚሾምበት ቦታ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሹመቱ መመዘኛ ብቃትና ልምድ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፓርላማው የውጭ ግንኙነትና የሰላም ኮሚቴ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት 30 ዓመታት ሲደረግ ከነበረው በተለየ ለመጀመሪያ ጊዜ 70 በመቶ የሚሆነውን የአምባሳደሮች ሹመት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋም ውስጥ መሰጠቱን እንዲገመግምና ሪፖርት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡

ስለኢኮኖሚው ዘርፍ ሲናገሩ የጦርነት ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መልካም የሚባል እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 185.8 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 171.3 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 92 በመቶ መሰብሰብ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 14.6 በመቶ ብልጫ እንዳለውና ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ የነበረው አገራዊ ወጪ በአጠቃላይ 297 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የስድስት ወር ወጪ ጋር ሲወዳደር የ39 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በሌለ በኩል የወጪና የንግድ ሚዛንን በተመለከተ በስድስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የላከችው ምርት በ25 በመቶ ማደጉን ጠቁመው፣ በዚህም ወደ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ መላኩን አስረድተዋል፡፡

   ባለፉት ስድስት ወራት ከውጭ ተገዝተው ሲገቡ የነበሩ ምርቶች በአገር ቤት ተመርተው መተከታቸውን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት የተተኩ መሆናቸውን፣ በዋነኝነት የቢራ ብቅል ከውጭ ይመጣ የነበረውን ሙሉ በሙሉ፣ ጨርቃ ጨርቅ በተለይም የመከላከያ ጫማ፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ዳይፐርና የሲሚንቶ ግብዓት፣ መድኃኒት፣ ሴራሚክና ዕምነ በረድ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በስድስት ወራት ውስጥ 147 ቢሊዮን ብር ከባንኮች በብድር መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥ 70 ቢሊዮን ብር ለአገልግሎት፣ 50 ቢሊዮን ብር ለኢንዱስትሪ፣ እንዲሁም 27 ቢሊዮን ብር ለግብርና ዘርፍ መዳረሱን ተናግረዋል፡፡

ከአጠቃላይ ብድሩ ውስጥ 69 በመቶውን ለግል ዘርፍ፣ 31 በመቶውን ደግሞ ለመንግሥት ብድር መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ባለፈው ዓመት ክረምት ከታረሰው 13 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርት፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በበጋው የእርሻ ልማት በሁለት ዙር እየለማ ካለው 600 ሺሕ ሔክታር የስንዴ መስኖ ልማት ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪን አስመልክተው ማብራሪያ ሲሰጡ ለዋጋ ንረት በዋናነት ከጠቀሷቸው ምክንያቶች አንዱ የፍላጎት መጨመር እንደሆነ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የወለድ ምጣኔን ያዝ በማድረግ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን ገታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር፣ የነጋዴዎች ምርትን መደበቅ፣ የአቅርቦት ውስንነት የሚሉት ምክንያቶች ለዋጋ መጨመር አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አስረድተዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተገናኘ ካለፈው ዓመት ዋጋቸው ጋር ሲነፃፀሩ ጭማሪ ያሳዩ ገቢ ምርቶች በተለይም ማዳበሪያ 176 በመቶ ብልጫ፣ ፓልም ዘይት 60 በመቶ፣ ብረት 65 በመቶ፣ ኮንቴይነር 283 በመቶ፣ ስኳር 33 በመቶ፣ ጭማሪ ማሳየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ 1.63 ቢሊን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ኢንቨስትመንት እንደተገኘ፣  ከ2013 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር 23 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...