Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ለሰላም የሚሠራ የ200 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

በሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ለሰላም የሚሠራ የ200 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ቀን:

በሦስት ዩኒቨርሲቲዎች በግጭት አፈታትና ሰላምን በማጠናከር ላይ የሚሠራ የ200 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡

በጂማ፣ በሐዋሳና በባህር ዳር ዩኒቨርሰቲዎች ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመት የሚተገበረው ፕሮጀክት፣ በዋነኝነት በተቋማቱ የሚኖሩ ወጣቶች በተለይም ሴቶች በግጭት አፈታትና በሰላም ላይ የሚኖራቸውን አቅም የሚያጠናክሩ የሥርዓት ትምህርት ቅየሳ፣ ጥናቶች፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ እንዲሁም የልምምድ ለውጦችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ከአውሮፓ ኅብረትና ከብሪትሽ ካውንስል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ለተደረገው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት፣ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የብርቲሽ ካውንስል ዋና ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ደመወዝ ዓርብ የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በየትኛውም አካባቢ ግጭት በሚከሰትበት ወቅት በዋናነት የችግሩ ሰለባ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ወጣት ተማሪዎች፣ በተለይም ሴቶች ላይ በማተኮር እንደሚሠራ አቶ ነፃነት ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ግጭት በሚፈጠርበት ወቅት ወጣቶች የችግሩ ተጋላጭ ሆነው እያለ ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚያደርጉበት የችግር አፈታት ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ፕሮጀክቱ ወጣቶችን አሳታፊ እንደሚያደርግና በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ወጣቶችን አሳታፊ ያደረገ መፍትሔ ቀርፀው እንዲሠሩ የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ነፃነት አክለውም ችግር በሚከሰትበት ወቅት ወጣቶች ለተሳትፎ ብቻ ተካተዋል ከሚባለው አሠራር ወጣ ባለ መንገድ፣ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለውጥ ማምጣት የሚችሉበትን መንገድ የሚቀይስ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፕሮጀክቱን የሚተገብሩት ሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች በአውሮፓ አገሮች ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት አሠራር ተካቶበታል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት በአገር ውስጥ ግጭትን ለመፍታት ያግዛሉ ተብለው የተደረጉ ጥናቶችን በማየት፣ በመፈተሽና የዩኒቨርሲቲ ወጣቶች ተጨባጭ የሆኑ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በተግባር ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በመሄድ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ጥናት የሚያደርጉበት አሠራር እንደተካተተበት አቶ ነፃነት አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታው በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ይጀመር እንጂ በቀጣይ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚተገበርበት አሠራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ለሰላም የሚሰጠው ትምህርትና የወጣቶች ሚና በሦስት ዓመቱ ፕሮጀክቱ ከተፈተሸ በኋላ፣ እንዳስፈላጊነቱ የፖሊሲ ወይም የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተደርጎበት የተገኘው መልካም ውጤት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚተገበርበት ሥርዓት ይበጃል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአገረ መንግሥት ግንባታ በእጅጉ ያግዛል የተባለለት ፕሮጀክት፣ የሚደማመጥና በንግግር የሚያምን ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሳሙኤል (ዶ/ር) አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ  በዩኒቨርሲቲዎቹ የሰላም ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ተጠናክሮ እየተሰጠ ባይሆንም፣ በትንሹም ቢሆን በተለያየ መንገድ ለተማሪዎች የሚሰጠውን ትምህርት በጥናት ተደግፎ በቅንጅት በመስጠት፣ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር የሚወክሉት ወጣቶች የግጭት መፍትሔ አምጪ እንዲሆኑና የሰላም አቀንቃኝ እንዲሆኑ የሚያግዝ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ሳሙኤል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...