- የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ልምምድ አቁመዋል
- የኦዲት ሪፖርት ባለማቅረብ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ክለቦች አሉ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙ ክለቦች በተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ መናር ምክንያት ለከፋ ችግር እየተዳረጉ መሆኑ ታወቀ፡፡ ‹‹ወርኃዊ ክፍያ አልተከፈለንም›› በሚል የጅማ አባ ጅፋር ክለብ ተጫዋቾች ልምምድ ለማቆም መገደዳቸውን ተጫዋቾቹ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የሒሳብ ሪፖርት ማቅረብ ያልቻሉ ክለቦች ከፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ማግኘት የሚገባቸው ክፍያ ያልተፈጸመላቸው መኖራቸው ታውቋል፡፡
ከተመሠረተ ከሁለት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከዓምና ጀምሮ በአክሲዮን ተደራጅቶ ‹‹ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ›› በሚል ውድድሩን በራሱ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ይሁንና በጥናት ላይ ባልተመሠረተውና በየዓመቱ እየናረ በመጣው የተጫዋቾች ወርኃዊና የፊርማ ክፍያ ክለቦች ለከፋ ችግር እየተዳረጉ መሆኑ የክለብ አመራሮችና ተጫዋቾች እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ይገልጻሉ፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የወሰደው ጅማ አባ ጅፋር የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት ክለቦች ይጠቀሳል፡፡ የክለቡ ተጫዋቾች ‹‹ከሦስት ወራት በላይ ወርኃዊ ክፍያ እየተፈጸመልን አይደለም›› በሚል መደበኛ ልምምድ ማቆማቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የክለቡ ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሳ ለማ በበኩላቸው፣ ክለቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡
ለቀጣዩ የእግር ኳስ ሕይወታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በበኩላቸው፣ ‹‹እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል እኛም የቤተሰብ ኃላፊነት ያለብን ተጫዋቾች መሆናችን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሥራችን ኳስ ተጫዋች በመሆኑ ሌላ የገቢ ምንጭ እንደሌለን ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ለክለቡ ኃላፊዎችና አመራሮች ደግመን ደጋግመን ለመግለጽ ሞክረናል፣ ግን የሚሰማን አላገኘንም፡፡ በአንደኛው ዙር ከደመወዝና ከፊርማ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞን ልምምድ አቁመን ነበር፡፡ አሠልጣኙና አንዳንድ የክለቡ የሥራ ኃላፊዎች አግባብተውን ጥያቄያችንም ተገቢ እንደሆነና የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ዙር ውድድር እንደተጠናቀቀ በአካውንታችን ገቢ እንደሚደረግልን ተማምነን ነው ወደ ዝግጅት የገባነው፤›› ብለው፣ ፊርማና ተያያዥ ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር ከሦስት ወራት ወርኃዊ ክፍያ እንኳን እንዳልተፈጸመላቸው ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው የ12ኛው ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር በኋላ መደበኛ ልምምድ አቁመናል፡፡ በጣም የሚገርመው አንድም የክለቡ አመራሮች ብቅ ብለው ችግራችሁ ምንድነው ብለው አልጠየቁንም፤›› የሚሉት የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች፣ ችግሩ እስካልተቀረፈ ድረስ ከወላይታ ድቻ ክለብ ጋር በሚኖራቸው የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ እንደማይሳተፉ ይናገራሉ፡፡
ስለጉዳዩ ሪፖርተር በእጅ ስልካቸው ያነጋገራቸው የክለቡ ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሳ ለማ በበኩላቸው፣ ‹‹ተጫዋቾቻችን ያነሱት ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡ እውነት ነው የሦስት ወራት ክፍያም አልተፈጸመላቸውም፡፡ ቅሬታቸውም ተገቢ ነው፡፡ ችግሩ በጀት ካለመለቀቁ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እየሠራን ነው፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሁሉንም ተጫዋቾች ሙሉ ደመወዛቸውን እንከፍላቸዋለን፤› ብለዋል፡፡
ከወርኃዊ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግሩ የጅማ አባ ጅፋር ብቻ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ከሦስትና ከአራት ክለቦች በስተቀር ብዙዎቹ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር በተገናኘ ችግር እንዳለባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ የችግሩን አሳሳቢነት ከሚገልጹት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ክለቦች ለተጫዋቾች መክፈል ስለሚገባቸው ወርኃዊ ክፍያና የዝውውር ጉዳይን የሚመለከተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመሆኑ፣ ይህንኑ ከክለቦች ጋር ተነጋግሮ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት አቶ ክፍሌ ያሳስባሉ፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩን ኃላፊነት በሚመለከት አቶ ክፍሌ፣ ውድድሩን በበላይ ከመምራት ባለፈ በዚህ ጉዳይ እንደማይመለከተው ጭምር ያስረዳሉ፡፡
አቶ ክፍሌ ሌላው ያነሱት ጉዳይ፣ ክለቦች ካለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በዲኤስቲቪ አማካይነት በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፉ በመሆኑ፣ ክለቦቹም በሊጉ በሚያስመዘግቡት ውጤት መነሻነት ዲኤስቲቪ ከአክሲዮን ማኅበር ጋር በገባው ውል መሠረት የሚያገኙት ክፍያም መኖሩን ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ክለቦቹ ባለፈው የውድድር ዓመት ክፍያው የተፈጸመላቸው መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፣ ‹‹በዚህ ዓመት የሚከፈለውን ክፍያ በተመለከተ ግን አክሲዮን ማኅበሩና ክለቦቹ በተስማሙት መሠረት ክፍያው ተፈጻሚ የሚሆነው ክለቦች ቀደም ሲል የተከፈላቸውን ክፍያ ኦዲት አስደርገው፣ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ክለቦች ለአክሲዮን ማኅበሩ ማቅረብ የሚጠበቅባቸውን የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ባለመቻላቸው ክፍያ ያልተፈጸመላቸው አሉ፤›› ይላሉ፡፡ የክለቦቹን ማንነት በተመለከተ ኃላፊው ለጊዜው ከመግለጽ እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡
ክለቦች ለተጫዋቾች ስለሚገቡት ውል፣ እንዲሁም ወርኃዊ ክፍያን ጨምሮ ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተገናኘ ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ በጅማ አባ ጅፋር እግር ኳስ ክለብና በተጫዋቾቹ መካከል ከክፍያ ጋር ተያይዞ ተፈጥሯል ስለሚባለው ጉዳይ ከተጫዋቾቹም ሆነ ከክለቡ የደረሰው ምንም ዓይነት አቤቱታ እንዳልቀረበለት፣ ሆኖም በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት፣ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ከወርኃዊ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር አለመግባባት ውስጥ መግባታቸውን በሚመለከት መረጃው እንዳለው ይገልጻል፡፡
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጉዳዩን በሚመለከት፣ ክለቦች የተጫዋቾችን ዝውውር በሚመለከት ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው ገደብ ከመነሳቱ ጋር ተያይዞ፣ ክለቦች በተለይ የተጫዋቾችን የዝውውር ጉዳይ ባላቸው የገንዘብ አቅም ልክ አሥልተውና አስበው የማያከናውኑ ከሆነ ችግሩ በሁሉም ክለቦች ላይ ከዚህም የባሰ የገንዘብ እጥረት ሊያስከትል እንደሚችል ጭምር ነው ሥጋታቸውን የሚገልጹት፡፡