Thursday, September 28, 2023

ለ20 ዓመታት ያልተመለሱት የአፍሪካ ኅብረት ግዙፍ ጥያቄዎችና አጀንዳ 2063

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ ኅብረት 35ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ በመሪዎች ደረጃ ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ በጉባዔው ላይ 20 የተለያዩ አገሮች መሪዎች ታድመዋል፡፡ የጉባዔው ጭብጥ፣ ‹‹በአፍሪካ አኅጉር የሥነ ምግብና የምግብ ዋስትናን ማጠናከርና አይበገሬነትን መገንባት፣ የግብርናና ምግብ ሥርዓትን፣ እንዲሁም ለሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ለኦኮኖሚ ካፒታል ልማት የጤናና ማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓትን ማጠንከር›› የሚል ሲሆን፣ በርካታ ንግግሮች ግን ትኩረታቸው በዚህ ጭብጥ ላይ አልነበረም፡፡

ከሳህል በላይ በሚገኙ የአኅጉሪቱ አገሮችና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ተንሰራፍቶ የሚታየው ወቅታዊ አጀንዳ በጭብጥነት አለመያዙ ጥያቄን የሚያጭር ቢሆንም ቅሉ፣ በመድረኩ ንግግር ያደረጉ መሪዎች የአኅጉሪቱ የሰላም ዕጦትና የዴሞክራሲ ምኅዳር መሟሸሽ አሳሳቢ እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ይኼም እንኳን ደኅና መጣችሁ ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) አንስቶ፣ የአኅጉራዊ ተቋሙን ሊቀመንበርነት ባስረከቡትና በተረከቡት የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና የሴኔጋል ፕሬዚዳንቶች ተስተጋብቷል፡፡

የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች

የአፍሪካ የተለያዩ ቀጣናዎች ከጦርነትና ግጭቶች እስከ መፈንቅለ መንግሥት ያሉ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮችን እያስተናገዱ ሲሆን፣ የኅብረቱ ስብሰባም ይኼንን ጉዳይ አሳሳቢ ነው በማለት ብቻ አልፎታል፡፡ በቅርቡ ብቻ በቡርኪና ፋሶ፣ እንዲሁም ያልተሳካ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በጊኒ ቢሳው የተከናወነ ሲሆን፣ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት መውጣት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተሞከሩ መፈንቅለ መንግሥት ወደ 200 ገደማ እንዲደርሱ አድርጓል፡፡ ማሊና ጊኒም በተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት አስተናግደዋል፡፡ ማዳጋስካር፣ ኮት ዲቯር፣ ቶጎ፣ ጊኒ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ወዘተ በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ዓይተዋል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ክስተት እ.ኤ.አ. በዓመት አራት ድረስ እንደነበረ፣ ይኼም ቁጥር እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ተመሳሳይ ሆኖ እንደቆየ የተለያዩ ሪፖርቶች የሚያሳዩ ሲሆን፣ መፈንቅለ መንግሥቶቹ በቁጥር ቢቀንሱም ሊወገዱ ግን አልቻሉም፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት መዛመት በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ተቀዛቅዞ እንደነበር በጥናታቸው የሚጠቅሱት የኮፊ አናን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተመራማሪ ኤማ ቢሪኮራንግ፣ ለመፈንቅለ መንግሥት ምክንያት የዴሞክራሲ ውድቀት እንደሆነ ያስረግጣሉ፡፡ ይኼንንም ከምርጫ መጭበርበር ጋር በማያያዝም ጉዳዩ አፍሪካውያን ያለፉት ክስተት ሳይሆን ያለ፣ የቀጠለና ነባራዊ ሥጋት ነው ይላሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2022 ባሉ ዓመታት ብቻ ከሰባት በላይ መፈንቅለ መንግሥቶች በአፍሪካ ምድር ታይተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተለያዩ የአኅጉሪቱ ቀጣናዎች ግጭቶችንና ጦርነቶችን እያስተናገዱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ግጭቶች እየተካሄዱባቸው ናቸው፡፡ የሶማሊያና የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የሽብርተኝነት ሥጋቶችም በንፁኃን ላይ እያስከተሉ ያለው ሥቃይና እንግልት የትየለሌ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ግን የኅብረቱ ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ በዚህም ሳቢያ ጥርስ አልባ አንበሳ ሲባል ይወቀሳል፡፡ ለዚህም ይመስላል በአዲስ አበባው ጉባዔ ላይ የኅብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሐመት በኅብረቱ የተሠሩ የለውጥ/ሪፎርም ሥራዎች ቢኖሩም፣ የተደረገው ለውጥ ግን ኮሚሽኑንና ፕሬዚዳንቱን ሽባ ባደረጉ አሳሪ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ዝምታን መርጧል ሲሉ ያማረሩት፡፡

ለዚህ አንደኛው እንቅፋት የሆነው ክስተት ኅብረቱ ከቀጣናዊ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት በበታችነት የሚያሳየው እንደሆነ፣ ኅብረቱ የወሰናቸው ውሳኔዎች በቀጣናዊ ተቋማት ሲጣሱ መታየታቸውና ይኼ ከበታችነት ወደ መተጋገዝ መሸጋገር አለበት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም የኅብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በማሊ ላይ ያስተላለፈው የዕግድ ውሳኔ በኤኮዋስ አለመከበሩን ለማሳያነት ያነሳሉ፡፡ በሁለተኛነት ሙሳ ፋቂ መሐመት ያነሱት አገሮች ሉዓላዊነትን የሚረዱበት መንገድ የተዛባ መሆኑን ነው፡፡

‹‹ይኼ በአባል አገሮች ውስጥ ለሚደረጉ ሁሉም ዓይነት ጥሰቶች መሸፈኛ ሆኖ እየዋለ ነው፡፡ ገዳቢና ተጨባጭ ያልሆኑ የሉዓላዊነት መርሆዎች በአባል አገሮች የሚተረጎሙበት አግባብ አኅጉራዊ ተቋሙ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመከለካከልም ሆነ ቀውሶች ሲከሰቱ መፍትሔ ለማበጀት እንዳይችል የብረት መጋረጃ ይጋርዱበታል፡፡ በዚህም ሳቢያ እዚህም እዚያም ኮሚሽኑ እንደ አገሮች ጸሐፊ ተደርጎ መወሰዱ ቢታይ የሚስደንቅ አይደለም፤›› ሱሉ ያማርራሉ፣ ኮሚሽነሩ አክለውም፣ ‹‹ሉዓላዊነት ለድርጅታችን ብቻ የሚሠራ ጉዳይ አይደለም፡፡ አውቀዋለሁ፡፡ ሁሉም ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር የሚሠራ ቢሆንም፣ ጉልበቱና የአፍሪካ ኅብረትን የሚመለከተው ገዳቢ ትርጉሙ እጅግ የበዛ ሲሆን፣ ለተቋሙ ሙሉ አቅም ተነሳሽነትና ተግባር ወሳኝነት አለው፤›› ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበኩላቸው በጉባዔው ባደረጉት ንግግር፣ የሰላምና የፀጥታ መጓደል ለአኅጉሪቱ አሳሳቢ እንደሆነና የአፍሪካ ኅብረት ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ በርካታ ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም፣ አንድነታችንንና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ አዳዲስና ውስብስብ ችግሮችን እያስተናገድን እንገኛለን፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሆኖም የኅብረቱን ኮሚሽነር መልዕክት የተቃረነ በሚመስል የኢትዮጵያ ችግር የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና ይሁንና የውስጥ ጣልቃ ገብነት ፈተና እንደነበር በማውሳት፣ የአፍሪካ አገሮች ያሳዩትን አጋርነትና የሰጡትን ድጋፍ በመጥቀስ አመሥግነዋል፡፡ ሆኖም የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ጠንካራ አቋም ያላንፀባረቀ ሲሆን፣ መቀሌና አዲስ አበባ ከመመላለስ ባለፈ የሠሩት ሥራ ምን እንደሆነ በግልጽ ያልተነገረላቸውን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ የኅብረቱ ከፍተኛ ተወካይ አድርጎ ከመሾም ያለፈ ሚና አልነበረውም፡፡

በዚህም ሳቢያ ነው እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የምዕራቡ ዓለም አገሮች፣ የአፍሪካ ኅብረት ከሰላምና ፀጥታ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩት፡፡

የኅብረቱ ሊቀመንበር በመሆን መዶሻውን የተረከቡት የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በበኩላቸው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ኅብረቱ የመጣበት መንገድ ዕድገት የታየበት መሆኑን በማውሳት፣ አሁንም ግን ከሰላምና ከፀጥታ አኳያ በርካታ ሥራዎች የሚቀሩ መሆኑንና አሸባሪነትን መዋጋትም ሌላው ፈተና እንደሚሆን አልሸሸጉም፡፡

‹‹በዴሞክራሲና በአኅጉሪቱ ተቋማዊ መረጋጋት ላይ ታላቅ ጥቃት እያደረሱ ያሉ የመፈንቅለ መንግሥቶች ክስተት እየበረከተ እንደሆነ አይረሳኝም፡፡ የሰላምና የፀጥታ አንገብጋቢነት አሸባሪነትን በመዋጋት፣ በአባል አገሮች መካከል ያለን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፣ እንዲሁም ውስጣዊ ቀውሶችን በአግባቡ በመቆጣጠር ረገድ ታላቅ ኃላፊነት እንዳለብን አይዘነጋም፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን መሪዎቹ ለኅብረቱም ሆነ ለኮሚሽኑ የሰጡት ተጨማሪ ሥልጣንም ሆነ፣ ኮሚሽነሩ ባነሱት የሉዓላዊነት የተለጠጠ ትርጉም ላይ እዚህ ግባ የሚባል ያደረጉት ውይይት አልነበረም፡፡

የኅብረቱ ራስን የመቻል ጥያቄ

የአፍሪካ ኅብረት በአጀንዳ 2063 እ.ኤ.አ. በ2013 በመሪዎች ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ ግብ ሲሆን፣ አፍሪካ በ50 ዓመታት አፍሪካን የዓለም አቀፍ የኃይል ማዕከል ማድረግን ያለመ ነው፡፡ ይኼንን ቀጣይነት ያለውን ልማት በማምጣትና ፓን አፍሪካኒዝምን በተጨባጭ በማሳየት ለማሳካት የሚጥረው ይኼ ትልም፣ ሰባት ውጥኖች አሉት፡፡ እነዚህም፣ በአካታች ዕድገትና ዘላቂ ልማት ላይ በመመሥረት የበለፀገች አፍሪካን ማየት፣ በፓን አፍሪካኒዝምና በአፍሪካ ህዳሴ ላይ የተመሠረተች የተሳሰረች አኅጉርና የፖለቲካ አንድነትን ማምጣት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አፍሪካን ማረጋገጥ፣ ሰላማዊና ደኅንነቷ የተረጋገጠች አፍሪካን ማየት፣ ጠንካራ ባህላዊ ማንነትት የጋራ ቅርስ፣ እንዲሁም የጋራ እሴትና ሥነ ምግባር የሚታይበት አፍሪካን መፍጠር፣ ልማቷ በሰዎች ላይ ያተኮረ፣ በአፍሪካውያን አቅም፣ በተለይም በሴቶችና ወጣቶች ላይ የተመረኮዘ፣ እንዲሁም ልጆች እንክብካቤን የሚያገኙባትን አፍሪካ ማረጋገጥ፣ ብሎም አፍሪካን ጠንካራ፣ የተባበረች፣ አይበገሬና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፋዊ ተዋናይና አጋር ማድረግ ናቸው፡፡

እነዚህን ውጥኖች ለማሳካትም ያስችላሉ የተባሉ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ፣ እ.ኤ.አ. በ2016 የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የሚመሩት ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡ ይኼ የማሻሻያ ሥራ ይፈታቸዋል ተብለው የተቀመጡት የኅብረቱ ችግሮች፣ የአፍሪካ ኅብረት በርካታ የትኩረት ነጥቦች ስላሉት እጅግ የተለጠጠ መሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት መዋቅር ውስብስብ መሆንና አነስተኛ የአስተዳደር አቅም በመኖሩ ሳቢያ ብቃት የጎደላቸው የሥራ ዘዴዎች፣ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ተጠያቂነት አለመኖርን ማስከተሉ፣ ብሎም የአፍሪካ ኅብረት በፋይናንስ ራሱን የቻለ አለመሆኑና ራሱን ማስቀጠል የሚችል ባለመሆኑ ለበርካታ ወጪዎቹ በአጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረትና በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው ትብብር አነስተኛ መሆኑ የሚሉ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. በ2020 የአፍሪካ ኅብረት በጀት 647.3 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 157.2 ሚሊዮን ለሥራ ማስኬጃ፣ 216.9 ሚሊዮን ዶላር ለፕሮግራም ወጪዎች፣ እንዲሁም 273.1 ሚሊዮን ዶላር ለሰላም ድጋፍ ዘመቻዎች ድጋፍ የተመደበ ነው፡፡ ከጠቅላላው በጀት በአባል አገሮች የሚሸፈነው 38 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ 61 በመቶ ደግሞ ከአጋሮች ይገኛል ተብሎ የተቀመረ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ሁሉም አባላት በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ አያደርጉም፡፡

ስለዚህም የኅብረቱ በጀት በቂ፣ አስተማማኝና ተገማች ምንጭ ሊኖረው እንደሚገባና ይኼም ልማቱንና የትስስር ግቦቹን ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነ ዕሙን እንደሆነ የኅብረቱ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ኅብረቱ በፋይናንስ ረገድ ያሉበት ችግሮች የገቢዎች ኢ-ተገማችነትና ተለዋዋጭነት፣ በውጭ አጋሮች ላይ የተመረኮዘ መሆን፣ በጥቂት አባል አገሮች መዋጮ ላይ ጥገኛ መሆን፣ ለሚወጣው ገንዘብ ዋጋ መስጠትና ቁጥጥር፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚያድግ በጀት ናቸው፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ኅብረቱ 1.5 ቢሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን የሚኖሩባቸውን 55 አባል አገሮችን የሚወክል ተቋም ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተደማጭነትና ውክልና አናሳ መሆኑ ሌላው ችግር ሆኖ ይታያል፡፡

በዚህም ሳቢያ ይመስላል የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች በተናጠል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተመጣጣኝ ውክልና እናግኝ ሲሉ የሚደመጡት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ከሁለት ያላነሰ የቋሚ አባልነት ውክልና፣ እንዲሁም ከአምስት ያላነሰ የተለዋጭ አባልነት ውክልና እንዲሰጣት በኅብረቱ መድረክ ጠይቀዋል፡፡

አፍሪካ በቂ ውክልና ስለሌላት በዓለም መድረክ ያልተገባ ጫና እየደረሰባት እንደሚገኝና ለዚህም መፍትሔው ውክልና ማግኘት እንደሆነ አስረግጠዋል፡፡ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክትባት ኢፍትሐዊ ቅርምትና ሥርጭት በዚህ ሳቢያ የተባባሰ እንደሆነ በኅብረቱ ጉባዔ ተወስቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -